መንግሥት በአሁኑ ወቅት በሀገራችን የተከሰተው የኑሮ ውድነት ምክንያት ምን እንደሆነ በማጥናት ለመፍትሄው እየሰራ ይገኛል፡፡ በአንድ በኩል ህዝቡ በኑሮ ውድነቱ ሳቢያ ዜቶች እንዳይጎዱ ለማድረግ አቅሙ በሚፈቅደው ልክ ድጎማ እያደረገ ስኳርና የምግብ ዘይት የመሳሰሉትን የፍጆታ ሸቀጦች እያቀረበ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ አለአግባብ የሚደረግ የዋጋ ጭማሪን ለመቆጣጠር በትኩረት እየሰራ ነው፡፡
መንግሥት በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለው ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ጭማሪ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የለውም ፤ዋጋ እየጨመራችሁ ያላችሁ አካላት ከድርጊታችሁ ታቀቡ፤ አለበለዚያ እርምጃ እወስዳለሁ እያለ የንግዱን ማህበረሰብ እያሳሰበ ይገኛል፡፡ የዋጋ ጭማሪው ግን ከመቀነስ ይልቅ እየጨመረ ነው፡፡ ይህም ችግሩን ለመፍታት ከእስከ አሁኑም የላቀ ጠንካራ እርምጃ መውሰዱን ይጠይቃል፡፡
ለኑሮ ውድነት ምክንያቱ ምን እንደሆነ ለመመልከት መንግሥት ጥናት ማካሄዱንና እርምጃዎችን መውሰዱንም የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሰሞኑን አስታውቋል፡፡ በጥናት ከተለዩት መካከልም በዓለም የተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝና ተያያዥ ሁኔታዎች በኢትዮጵያም ላይ ተጽእኖ ማሳደረቸው፣ በነዳጅ ገበያ ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ መታየቱ ይህን ተከትሎም ምርቶች በቀጣይ የዋጋ ጭማሪ ሊያሳዩ ይችላሉ በሚል ነጋዴዎች መደበቃቸው የሚሉት ይገኙበታል፡፡
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሰሞኑንም ያለፉትን ዓመታት አይነት እርምጃዎች ወስዷል፡፡ ሚኒስቴሩ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳስታወቀው፤ ምርትን አለአግባብ በሚይዙና በገበያ ላይ ዋጋ በሚጨመሩ አካላት ላይ እርምጃ ተወስዷል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ 69 ሺ 553 ነጋዴዎች የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፤ 42 ሺ 555 ነጋዴዎች ደግሞ ድርጅቶቻቸው ታሽጓል፤ 90 ነጋዴዎች ንግድ ፈቃዳቸው የታገደ ሲሆን፣303 ነጋዴዎች ደግሞ ንግድ ፈቃዳቸው ተሰርዟል፡፡ አንድ ሺ 220 ሰዎች ደግሞ በፍርድ ቤት ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው እየታየ ነው፡፡
ንግድ ፈቃድ ሳይኖራቸው በህገ ወጥ መንገድ የንግድ እቃዎችን ሲያዘዋውሩ ከተገኙ 95 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው ንብረቶች ተይዘው ለገበያ እንዲቀርቡ እየተደረገ ይገኛል፡፡ በፍርድ ቤት ከተከሰሱትም 12 ነጥብ
ስምንት ሚሊዮን ብር ገቢ ተገኝቷል፡፡ እርምጃዎቹ ሊያርሙ ሊያስተካክሉ ሊያስተምሩ እንደሚችሉም ሚኒስቴሩ አመልክቷል፡፡
መንግሥት የኑሮ ውድነት ምክንያቱን በጥናት ለመለየት ያከናወነው ተግባር በጥንካሬ ሊታይ ይገባል፤ እርምጃዎቹም ጥሩ የሚባሉ ናቸው ፤ ሊያርሙ ሊያስተካክሉ ሊያስተምሩ እንደሚችሉ የታመነባቸው ቢሆንም ፣ ምን ያህል ያስ ተካክላሉ ፣ያርማሉ ፣ያስ ተምራሉ የሚለው ግን መ ታየት ይኖርበታል፡፡
ባለፉት ዓመታትም ተመሳሳይ እርምጃዎች ተወስድዋል፡፡ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የንግድ ድርጅቶች የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ሲሰጣቸው፣ በብዙ ሺዎች ድርጅታቸው ሲታሸጉ ፣ ጥቂት የማይባሉ ፈቃዳቸው ሲታገድና ሲሰረዝ የመጣው ለውጥ ምን ነበር ብሎ መለስ ብሎ መመልከትም ይገባል፡፡ ይህ ሁሉ ተደርጎም ነው ዛሬ ላለንበት ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ውስጥ ለከተተን የዋጋ ጭማሪ የተዳረግነው ፡፡
ዓለም አቀፍ እና ሀገራዊ ችግሮችን ማንም የሚያውቃቸውና የሚታገሳቸው ናቸው፡፡ ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች ተብለው የሚታወቁም ስለሆኑ ብዙም አነጋገሪ አይሆኑም፡፡ ሀገራችንን እያሳሰበ ያለው ግን በዚህ ክፉ ቀን በአንዳንድ የንግዱ ማህበረሰብ አካላት ዘንድ የሚታየው ስግብግብነት ህዝብን ለከፍተኛ የኑሮ ውድነት መዳረጉ ነው፡፡ የንግዱ ማህበረሰብ ስግብግብነት ስር የሰደደና የመንግሥትን ጠንካራ እርምጃ የሚፈልግ ህገ ወጥ ድርጊት እየሆነ ይገኛል፡፡
ህገወጥ ነጋዴዎች እንኳንም እናቴ ሞታ እንዳውም አልቅስ አልቅስ ይለኛል እንደሚባለው እንኳንስ ዋጋ ለመጨመር የሚያስችሉ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ተፈጥረው፣ ምክንያት በመፍጠር ምርት የሚደብቁና ዋጋ የሚጨምሩ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ይህም ስር የሰደደ የሀገራችን የንግዱ ዘርፍ ችግር ነው፡፡ ችግሩ በአንድ ሰሞን ማስፈራሪያና እርምጃ እንዲሁም በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የእለት ተእለት ሥራ ብቻ መፍትሄ ሊያገኝም አይችልም፤ ባለፉት ዓመታት የኑሮ ውድነት በተከሰተ ቁጥር ተወሰዱ በተባሉ እርምጃዎች አለመፈታቱም ይህንኑ ያስገነዝባል፡፡
እርምጃዎች አለአግባብ ዋጋ የመጨመር አባዜን በዘላቂነት መፍታት የሚያስችሉ ሊሆኑ ይገባል፡፡ እስከ አሁን የተወሰዱት እርምጃዎች ማስታገሻ ነው የሆኑት፡፡ ማስታገሻ ደግሞ መድሃኒት አይደለምና ከርሞም ወደ ተመሳሳይ እርምጃ ከመግባት አያስቀርም፡፡
ከዚህ በኋላ የሚወሰዱ እርምጃዎች በወሳኝ መልኩ በየዓመቱ ከመመላለስ የሚያድኑ እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለእዚህ ደግሞ የዋጋ ጭማሪ በአናት በአናቱ በማድረግ የኑሮ ውድነቱ እንዲባባስ ዋና ምክንያት እየሆኑ የሚገኙት የንግዱ ማህበረሰብ አካላት የጥፋት እጃቸውን እንዲሰበስቡ፣ ታችኛው መደብር ድረስ የዘረጉትን ሰንሰለት መበጣጠስ የሚያስችል ሊሆን ይገባል፡፡ የማያመላለስ ዘላቂ መፍትሄ ማስቀመጥ የሚቻለው በእነዚህ ህገወጥ ነጋዴዎች ላይ ጠንካራና አስተማሪ እርምጃ ሲወሰድ ነው !!