‹‹ያለችን አንድ ኢትዮጵያ ነች፡፡ ከየትኛውም የፖለቲካ አመለካከት በላይ ሀገራዊ አንድነት ይበልጣል፡፡ አንድነት ማለት ግን አንድ አይነትነት ማለት እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ አንድነታችን ልዩነታችንን ያቀፈ፣ ብዝሃነታችንን በህብረ ብሔራዊነታችን ያደመቀ መሆን አለበት››
‹‹በዋናነት ፉክክራችን ከዓለም ጋር እንጂ ዕርስ በዕርሳችን ሊሆን አይገባም፡፡ ከዓለም ጋር ስንፎካከር በመጠፋፋት መንፈስ ሳይሆን ለሁላችንም የምትሆን የተሻለች ዓለምን በመገንባት በቀና መንፈስ ላይ መሆን ይኖርበታል፡፡ ዕርስ በዕርስ ግን ከመደመር ውጭ የተሻለ አማራጭ የለም፡፡ መደመር ሁሉም የየራሱን ጥንካሬ ይዞ ከሌሎች ጥንካሬዎች ጋር በማዋሐድ የበለጠ ጠንካራ ህዝብና አገር የመፍጠር ሁነኛ አቅጣጫና መንገድም ነው››
‹‹በምሥራቅ አፍሪካ ያለውን የተበጣጠሰ ሀብት በመደመር ከፍተኛ ህዝብ ያለው ትልቅ ቀጣና መፍጠር ይቻላል፡፡ በአፍሪካ ቀንድ ያሉ አገራት አንድ ጠንካራ የተባበረ አገር መሆን ከቻሉ በዓለም ላይ የመገዳደር አቅምን ያሳድጋል››
እነዚህ ትልልቅ ሐሳቦችን ያዘሉ መልዕክቶች ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ በተለያየ ወቅት ያስተላለፏቸው ናቸው፡፡ ሕብረ ብሔራዊነትን ስላከበረ አገራዊ አንድነት፣ ስለ ኢትዮጵያዊነትና ኢትዮጵያ ታላቅነት፤ መደመር ስለሚፈጥረው ሕብረት፣ በራስ ክልል ከመወሰን አልፎ በቀጣናዊ እና አህጉራዊ ደረጃ መተሳሰር ስለሚያስገኘው ትሩፋትና ድምቀት እንዲሁም በሌሎችም በርካታ ጉዳዮችም በርቱዕ አንደበታቸው የብዙውን የሻከረ ልብ አለስልሰዋል፤ በተከታታይ በወሰዷቸው አዎንታዊ እርምጃዎችም በመንታ መንገድ ላይ የቆመችውን አገር ወደ ቀናው ጎዳና እያመሯት ይገኛሉ፡፡
አገራችን ትልልቅ ሐሳብ በሚያመነጩት መሪዋ እና ሌሎች የሥራ ባልደረቦቻቸው እንዲሁም በመላው አገር ወዳድ ዜጋ ወደ ብሩህ ተስፋ እንደምታመራ በእርግጠኝነት መናገር ቢቻልም፤ አሁንም የዜጎች እና የአገርን ህልውና ከማስጠበቅ አንፃር ከባድ ነገር ግን ያለምንበት ለመድረስ ከያዝነው ግብ አንፃር ትናንሽ የሚባሉ እክሎች አልጠፉም፡፡
ሥርዓት አልበኝነት፣ የዜጎች ሞት፣ መፈናቀልና እንግልት በዋናነት እያጋጠሙን ያሉ ችግሮች ናቸው፡፡ ችግሮቹ በተለይ ሰለባ ከሆኑት ቤተሰቦች በኩል ሆኖ ለተመለከታቸው ልብ ይሰብራሉ፡፡ በየስፍራው በሚፈጡት ሳንካዎችም ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች መስተጓጎላቸው፤ የህዝቦችን አንድነት መሸርሸር ባይቻልም፣ ጊዜያዊ መሻከር መፈጠሩ አልቀረም፡፡ ይሁንና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ የኖረውን የህዝቦች እሴት በጥልቀት በሚያንፀባርቅ መልኩ የለገሷቸው ሐሳቦች ይዋል ይደር እንጂ አሸናፊ ስለመሆናቸው መጠራጠር አይገባም፡፡
ኢትዮጵያ አንድነቷ እንደተጠበቀ በሕብረ ብሔራዊነቷ እንደ ደመቀች፤ ብሔራዊ ማንነት ሳይደፈጠጥ ኢትዮጵያዊነት ሳይደበዝዝ ለዘላለም የምትኖር አገር ነች፡፡ ህዝቦቿን ያስተሳሰረው የማይበጠስ ጠንካራ ገመድ እንደ አገር እንድትቀጥል ያደርጋታል፡፡ ይሁንና ይህንን ለመሸርሸር የሚደረግ ከፍተኛ ጥረት እዚህም እዚያም አለ፡፡ በተለይ በማህበራዊ ድረ ገፆች ብሔር ተኮር ዘመቻ በመክፈት ለዕኩይ አላማ የተሰለፉ ጥቂት ግለሰቦችን አልያም ከመበተን ፍርፋሪ ጥቅም ይገኛል ብለው የሚያስቡትን አካላት ለመጥቀም የሚደረግ ሩጫ ይታያል፡፡ ስለዚህ ይህን በመገንዘብ ትልቁ የአንድነት ሀሳብ በትንሹ የመከፋፈል እክል እንዳይረታ ሁሉም ዜጋ በንቁ ዓይን ሊከታተለው ይገባል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት መደመር ሁሉም የየራሱን ጥንካሬ ይዞ ከሌሎች ጥንካሬዎች ጋር በማዋሐድ የበለጠ ጠንካራ ህዝብና አገር የመፍጠር ሁነኛ አቅጣጫ ነው፡፡ በዚህ መሰረት ሁሉም የአገራችን ብሔር ብሔረሰቦች በኢኮኖሚው፣ በማህበራዊውና በፖለቲካው መስክ ለዓመታት ያዳበሩት ልምድ አላቸው፡፡ ይህን በማዋሐድ ጠንካራ አገር መፍጠር የአገሪቱ ቁልፍ ግብ ሊሆን ይገባል፡፡ በየቦታው ግጭት እየጫሩ የብሔር ግጭት እንዳለ በማስመሰል ለመከፋፈል መሞከሩ ለጊዜው ትልቁን የመደመር እሴት የሚያደበዝዝ ቢመስልም፤ ለዘለቄታው አይሳካም፡፡
እኛ ኢትዮጵውያን ከራሳችን ሠላም፣ ልማትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ያለፈ ራዕይ ያለን ህዝቦች ነን፡፡ ባለፈው ታሪካችንም ከባህር ማዶ እስከ ጎረቤት አገራት የተመሰከረለት የሠላም ዘብነታችን ለዚህ ሁነኛ ዋቢ ነው፡፡ የአፍሪካ የነፃነት ቀንዲልና የሥልጣኔ አብነት እንደሆንን ሁሉ ዛሬም ታሪካችንን በማደስ ትልልቅ ህልሞች እናልማለን፤ እውንም እናደርጋለን፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ የመደመር እሳቤ ከቀጣናችን ባሻገር ስለ አህጉራዊ ብልፅግና እንሞግታለን፤ እንታትራለን፡፡ በትንንሽ ሐሳቦች የሚሞግቱንን በሩቅ አላማችንና በሐሳብ ልዕልና እያሸነፍን ወደ ፊት እንጓዛለን፡፡