ሀገር የሚሠራው ለማን ነው?

እንኳንስ ሀገር ይቅርና በጣም ቢበዛ ከ100 ዓመት በላይ መቆየት የማይችል መኖሪያ ቤት የሚሠራው ለልጆች በሚል ነው:: አንድ ከ50 ዓመት በላይ የሆነው ጎልማሳ ሰው ደፋ ቀና ብሎ የሚሠራው ለአንድ ሆዱ አይደለም:: ለልጆቹ እና ለልጅ ልጆቹ በሚል ነው::

በግለሰቦች ደረጃ እንዲህ ለልጅ እና ለልጅ ልጆች ከተሠራ፤ በሀገር ደረጃ ሲሆን ደግሞ ምን ያህል ከባድ እና ጥልቅ እንደሚሆን ግልጽ ነው:: የዓድዋ ዘማቾች ጣሊያንን ሊዋጉ የሄዱት ዘለዓለም እንኖራለን ብለው አይደለም፤ እንዲያውም እኮ የሄዱት ሊሞቱ ነው::

ሊሞቱ የሄዱት ግን ለሀገራቸው ነው፤ ለሀገራቸው ማለት ለልጅ ልጆቻቸው፣ ለቀጣዩ ትውልድ (እነሆ ለእኛ) ማለት ነው:: እነርሱ ሞተው ሀገር አዳኑ ማለት ነው:: የሥልጣኔ ማማ ላይ የወጡ የዓለም ሀገራት ነባራዊ ሁኔታም ቢሆን ይሄው ነው::

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ደጋግመው የሚናገሩት ነገር ይሄው ነው:: ሀገር እየሠራን ያለነው ለቀጣዩ ትውልድ እንጂ ለእኛ ብቻ አይደለም የሚል ነው:: ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰው ናቸው የማንኛውም ሰው ዕድሜ ነው የሚኖራቸው፤ ዳሩ ግን ገናና የሆኑ ሀገራትን የሠሩ ሰዎችም ዓላማቸው የወደፊት የሀገራቸው ኃያልነት ነበር::

ከ170 ዓመታት በፊት የጃፓኑ ንጉሥ እነዚያን ርምጃዎች ሲወስድ፣ እነዚያን ቆራጥ ውሳኔዎች ሲያሳልፍ… ዘለዓለማዊ ሕይወት ይኖረኛል ብሎ አይደለም:: ጃፓን በእሱ ዕድሜ የሚፈለገው የሥልጣኔ ደረጃ ላይ እንደማትደርስ ያውቃል:: እነሆ ግን ከ150 ዓመታት በኋላ የዓለም የሥልጣኔ ተምሳሌት የሆነች ሀገር አደረጋት::

ጃፓን ከሠለጠነች ቆየች::

መሪዎች ሀገራቸውን በተለያየ ሁኔታ ለነገዋ ብለው ይሠራሉ:: ሀገራቸውን ይሠራሉ ሲባል ገናና የምትሆንበትን ተቋማዊና ሥነ ልቦናዊ ሁኔታ ይፈጥራሉ ማለት ነው:: የእሥራኤል አባት የሚባለው ዴቪድ ቢንጎሪዮን የእሥራኤልን ሰማይና ምድር አልፈጠረም::

ዳሩ ግን እሥራኤል አሁን ያለችበትን ቅርጽ፣ የሕዝብ ሥነ ልቦና እና ተቋማዊ ባሕሪ እንዲኖራት አደረገ:: የጣሊያኑ ጋሪ ባልዲ ከ200 ዓመታት በፊት የወሰደው ሀገርን የመመሥረት ቆራጥ ውሳኔ እነሆ የዛሬዋን ጣሊያን ፈጥሯል:: የአውሮፓም ሆኑ የእስያ ሀገራት፣ የምዕራቡም ሆነ የምሥራቁ ዓለም ጠንካራ ሀገራት የተፈጠሩት በመሪዎች ወይም በጥቂት ሀገር ወዳድ ሰዎች ነው::

ሀገራት በተመሳሳይ መንገድ ይገነባሉ ማለት አይደለም:: መሪዎች በሀገራቸው ዓውድ፣ በሚያስፈልጋቸው ዓይነትና መጠን ሀገርን ወደ ሥልጣኔ እና ዘላለማዊ ምቾት ይወስዳል የሚሉትን ነገር ያደርጋሉ:: ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዘላቂ ሀገር የመሥራት ውሳኔዎች ችግኝ ተከላን ብቻ እንውሰድ::

ችግኝ ተከላ ሲባል ‹‹አሁን ይሄ ቁም ነገር ሆኖ ነው እንደ ሀገራዊ ጉዳይ የሚታይ?›› በሚል ብዙ ሰው ሊገርመው ይችላል:: ሀገር መሥራት ማለት ግን አየሯ እና ተፈጥሮዋ የተስተካከለ ሀገር ማለት ነው::

የሰሞኑን ነባራዊ ሁኔታ እንኳን ብናይ ብዙ የአውሮፓ ሀገራት በከፍተኛ ሙቀት እየተሰቃዩ ነው፤ በአሜሪካ የጎርፍ አደጋ እያስከተለ ነው:: እነዚህ የሥልጣኔ ማማ ላይ ናቸው የሚባሉ ሀገራት ብዙ የቴክኖሎጂ መቆጣጠሪያ ዘዴ እያላቸው አሁንም ተፈጥሮ ከቁጥጥራቸው ውጭ እየሆነች ነው፤ በሙቀት እና በጎርፍ የሰው ሕይወት እያጡ ነው፤ በጎርፍ ንብረታቸው እየወደመ ነው:: በብዙ ሀገራት በሙቀት ሰው ሲሞት ሰምተናል::

ታዲያ ይህን ዓለም አቀፍ አደጋ የሚከላከል ተፈጥሮን የሚያስተካክል ሥራ መሥራት ተራ ጉዳይ ነው ወይ? ሀገር መሥራት ማለት ይሄው ነው:: ችግኝ ተከላ የዕለት ከዕለት ሥራ መሆን ቢገባውም አላደረግነውም:: ብዙ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ደን ተመናምኖባቸው በረሃማ እየሆኑ ነበር::

ሀገርን ወደ ጥፋት የሚወስዱት እንዲህ አይነት ትንንሽ የሚመስሉ ግዴለሽነቶች ናቸው:: ከቁስ ሥልጣኔ በላይ የአየር ንብረትን ማስተካከል ትልቅ ሥልጣኔ ነው:: ምክንያቱም የአየር ንብረትን ማስተካከል የረጅም ዘመን ትዕግስት እና ብልህነት የሚጠይቅ ነው::

ከአስፋልት መንገድ ፕሮጀክት በላይ ነው፤ የአስፋልት መንገድ መሥራት ቀላል ነገር ነው እያልኩ አይደለም፤ ዳሩ ግን የአየር ንብረትን ያህል ነገር መሥራት፣ ተፈጥሮን ያህል ነገር መቆጣጠር መቻል ግን የሥልጣኔዎች ሁሉ ቁንጮ ሊባል የሚገባው ነው::

ነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ ‹‹መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር›› በሚለው መጽሐፋቸው ስለሥልጣኔ አንድ ነገር ደጋግመው ይናገራሉ:: ይሄውም፤ የሰው ልጅ ሥልጣኔ ማለት ተፈጥሮ ትቆጣጠረው የነበረውን ነገር ቀይሮ ተፈጥሮን ሲቆጣጠራት ማለት ነው::

ተፈጥሮን ከተቆጣጠርንባቸው ሥራዎቻችን አንዱ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ነው:: እነሆ ይሄን ግዙፍ ፕሮጀክት ከደለል ለመከላከል ደግሞ ዛፍ እንተክላለን ማለት ነው:: ኢትዮጵያ በረሃማ እንዳትሆን እና የአየር ንብረቷ ተጠብቆ እንዲቆይ ዛፍ እንተክላለን፤ እንንከባከባለን ማለት ነው::

ኢትዮጵያ ከምትታወቅባቸው ውብ ተፈጥሮዎች አንዱ ምቹ የሆነው የአየር ንብረቷ ነው:: ይህ የአየር ንብረቷ ሰው ሠራሽ በሆኑ ችግሮች ሲሸረሸር እና ብዙ ጥፋት ሲደርስ አይተናል:: በአንዳንድ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ድርቅ በተደጋጋሚ እያጠቃን ነው::

በአንዳንድ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ደግሞ ጎርፍ ጉዳት እያደረሰ ነው::

እነዚህ የተፈጥሮ ክስተቶች የበጋ እና የክረምትን መግባት ተከትሎ የሚመጡ ቢሆኑም፤ ዛፍ በመትከል ግን ማስተካከል እና ሚዛናዊ ማድረግ ይቻላል:: ተፈጥሮን በቁጥጥር ሥር ከማዋል በላይ ሥልጣኔ የለም::

ችግሩ ግን እንዲህ ዓይነት ሀገርን የመሥራት ሥራዎች ሲሠሩ የሠለጠነ ዜጋም ያስፈልጋል:: ሀገር መሥራት ማለት እንደ ቁስ አካል ጠፍጥፎ መሥራት ወይም በማሽን ማምረት ማለት አይደለም፤ ሀገር መሥራት ማለት ተፈጥሮን መቆጣጠር፣ መልካም አስተዳደራዊ ሥርዓት መገንባት፣ የሠለጠነ ዜጋ መፍጠር፣ ሀገሩን የሚወድ ሥነ ልቦና ያለው ዜጋ መፍጠር ማለት ነው::

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ የአረንጓዴ ዐሻራ ፕሮጀክት፣ ኢትዮጵያን የወደብ ባለቤት ማድረግ… የመሳሰሉት ትልልቅ ፕሮጀክቶች እና አጀንዳዎች የሀገር ግንባታ ፕሮጀክቶች ናቸው:: በተለይም አረንጓዴ ዐሻራ የመቶ እና የሺህ ዘመናት ፕሮጀክት ነው:: ምክንያቱም የአየር ንብረት አንድ ጊዜ ከተስተካከለ ራሱን በራሱ በማራባት የተፈጥሮን ሚዛን ያስተካክላል::

በደን የተሸፈነ አካባቢ ዝናብ እንዲኖር ያደርጋል:: ዝናብ እንዲኖር አደረገ ማለት በቂ ምርት ይመረታል ማለት ነው:: ዝናብ እንዲኖር አደረገ ማለት ብዙ የብዝኃ ሕይወት ዓይነቶች እንዲኖሩ ያደርጋል ማለት ነው::

የዕፅዋትና የእንስሳት ዝርያ ዓይነቶች ዓይነትና መጠናቸውን እየጨመሩ ይኖራሉ ማለት ነው:: ተፈጥሮ ሲመቻቸው የዝግመተ ለውጥ ዓይነታቸውን እየቀያየሩ ለሺህ ዘመናት የሚኖሩ ይሆናሉ ማለት ነው::

አካባቢ ከተራቆተ እና ወደ ምድረበዳነት ከተቀየረ ግን የጠፉ ዝርያዎችን ለመተካት ብዙ ዘመን ይወስዳል፤ ለዚያውም የሚቻል ከሆነ ነው:: ስለዚህ የአረንጓዴ ዐሻራ ማልበስ ማለት የሺህ ዘመናት ተፈጥሮ ማስተካከል ማለት ነው::

የእንስሳትና ዕፅዋት ዝርያን ማስቀጠል ማለት ነው፤ ማስቀጠል ብቻ ሳይሆን አዳዲስ ዝርያዎች እንዲፈጠሩም ማድረግ ነው:: ስለዚህ እየተሠራ ያለው የሀገር ግንባታ ሥራ ብቻ ሳይሆን የተፈጥሮ ግንባታ ሥራ ነው:: ሀገርና ተፈጥሮ የምንገነባው አሁን ላለነው ብቻ ሳይሆን ለቀጣዩ ትውልድ ነውና በሀገርና ተፈጥሮ ግንባታ ውስጥ ሁላችንም እንሳተፍ!

 ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው።በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።

በሚሊዮን ሺበሺ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You