
ዓለማችን ሁሌም በለውጥ ውስጥ ነች። ለውጦች በየዘመኑ የሚመጣ እና የሚሄደውን ትውልድ ፍላጎትን መሠረት ያደረጉ አስገዳጅ ማኅበረሰባዊ ክስተቶች ናቸው። በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ማለፍን፤ የእያንዳንዱን ትውልድ የተነቃቃ የለውጥ መሻትን እና ስለለውጥ ዋጋ የመክፈል መነሳሳትን የሚጠይቅ ነው። ዓለማችን አሁን የደረሰችበት ሁለንተናዊ የዕድገት ደረጃም የለውጥ ክስተቶች ድምር ውጤት ነው።
ለለውጥ የተነቃቃ እና በአስገዳጅ የለውጥ ሂደት ጫና ውስጥ ያለ ትውልድ ለራሱም ሆነ ለመጪ ትውልድ የተሻሉ ነገዎችን ለመፍጠር ከሁሉም በላይ ከትናንቶች ጋር ተኳርፎ፣ መጣላት ሳይሆን ትናንቶችን ከአሁናዊ መሻቶች እና ተጨባጭ እውነታዎች ጋር አጣምሮ መመርመር እና መረዳት ይጠበቅበታል።
ትናንቶች የተገዙበትን ባህላዊ፣ መንፈሳዊ እና ማኅበረሰባዊ የአስተሳሰብ መሠረቶች ምን እንደሆኑ፤ እነዚህ አስተሳሰቦች አጠቃላይ በሆነው የማኅበረሰቡ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሕይወት ውስጥ የነበራቸው እና ያላቸውን አዎንታዊ እና አሉታዊ ተፅዕኖዎች እና የተፅዕኖዎቹን ደረጃ ለይቶ ማወቅ ይኖርበታል። ይህ የየትኛውም የለውጥ መነሳሳት የስኬት ጅማሬ ነው።
ለውጥ መሻትን ከተሸከመ ጩኸት በላይ ነው። መነቃቃቱም ፍላጎት ከፈጠረው ስሜታዊነት ያለፈ ነው። ትናንቶችን በመርገም ዛሬን የምናባክንበት/ነገዎችን በማይጨበጥ ተስፋ የምንናፍቅበትም አይደለም። ትናንትናን አውቀን የተሻለ ነገን ለመፍጠር የምንጀምረው ነገን ዛሬ ላይ የመሥራት የሕይወት ሂደት ነው።
ትናንቶችን ለሚገሩ እና ለሚያድሱ፤ አዳዲስ ተለውጦ የመለወጥ አስተሳሰቦች ሁለንተናችንን ክፍት አድርገን የምንጠብቅበት፤ በመታደስ ውስጥ ባለ መነቃቃት እና በመነቃቃቱ ለሚፈጠር መሻት ራሳችንን በእውነት እና በእውቀት ተገዥ አድርገን ለመጓዝ፤ በለውጥ እና በመለወጥ ሂደት ውስጥ ካለው ማንነታችን ጋር እርቅ የምንፈጥርበት የታሪክ ምዕራፍ ነው።
ከትናንት አሳሪ፣ ጎታች እና አደንዛዥ አስተሳሰቦች እና አስተሳሰቦቹ ከፈጠሯቸው የባሕሪ ማንነቶች/ መዛነፎች እና ድባቴዎች ወጥተን፤ ነገዎቻችንን ብሩህ ባደረጉ የለውጥ አስተሳሰቦች ራሳችንን የምንገራበት እና ለዚህ የሚሆን ሁለንተናዊ የመለወጥ ዝግጁነት የምናዳብርበት ነው።
በዓለም ላይ የተከሰቱ ስኬታማ ለውጦች የስኬታቸው ምስጢር በተለወጡ ማንነቶች መመራታቸው እና መገራታቸው፤ ዕውቀት እና እውነትን መሠረት አድርጎ መሄድ የሚያስችል የለውጥ ጉዞ ጅማሬ መፍጠር እና ማስቀጠል መቻላቸው ነው። ይህ ለሁላችንም የሚተርፍ ተሞክሯቸው ነው።
ያልተሳኩ እና የከሸፉ ለውጦችም የክሽፈታቸው ምክንያትም፤ ለውጡን በአግባቡ ተረድቶ ማስቀጠል የሚያስችል የተለወጠ ማንነት ያለው፤ ዕውቀትን እና እውነትን አጣምሮ ማስኬድ የሚያስችል የለውጥ ኃይል እና ለውጡን የሚሸከም የማኅበረሰብ ዝግጁነት አለመፈጠር ነው።
ከለውጥ ለማትረፍ የሚኮለኮል ተስፈኛ መብዛት፤ ለውጥን መሻት ከተሸከመው ጩኸት በላይ፤ መነቃቃቱንም ፍላጎት ከፈጠረው ስሜታዊነት በላይ አድርጎ የሚያስብ የነቃ የለውጥ ተስፈኛ ትውልድ አለመፈጠርም የዚህ የክሽፈቱ ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው።
እንደሀገር ትናንት የጀመርነው የለውጥ ጉዞ ዛሬ ላይ ብዙ ተስፋ ሰጪ ስኬቶች ቢኖሩት፤ ስኬቶችን በዘላቂነት ለማስቀጠልም ሆነ ለማስፋት እነዚህን እውነታዎች በአግባቡ መመርመር እና በተጨባጭ ያለንበትን እውነታ ማወቅ ተገቢ ነው።
ይህንን ማድረግ የሚያስችል ማኅበራዊ መረጋጋት እና ስክነት ያስፈልገናል፤ ትኩረታችንን ከለውጥ ወቅት ግራ አጋቢ ትርክቶች እና ክስተቶች ላይ አንስተን እንደ ሕዝብ ተስፋ ባደረግነው የለውጥ መነሳሳት እና መነሳሳቱ በፈጠረው ማኅበረሰባዊ መሻቶችና ስኬቶች ላይ ልናደርግ ይገባል።
ይህንን ማድረግ ትናንቶችን በታደሰ የለውጥ ማንነት በማሻገር፤ ነገዎቻችንን የተሻሉ እና ብሩህ እንዲሆኑ ለማድረግ ለጀመርነው አዲስ የለውጥ ምዕራፍም ሆነ ለመጪው ትውልድ የተሻለች ሀገር የመፍጠር ራዕያችን ስኬት አልፋ እና ኦሜጋ ነው!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 5 ቀን 2017 ዓ.ም