
ዜና ሐተታ
ሌሊቱን ሲዘንብ ያደረው ከባድ ዝናብ ንጋቱንም ሳያባራ ቀጥሏል። ጭጋጋማው የሐምሌ ማለዳ ለቅዝቃዜ እጁን እንደሰጠ ነው። ሰዓቱ ነጉዷል። ፀሐይም እንዳኮረፈች አርፍዳለች። ከጥቂቶች በቀር የአብዛኛው ነዋሪ በርና መስኮት ዝግ ነው። ብርዱ የሚቻል አልሆነም። ጊዜው ጥቂት ሳብ እንዳለ ሕይወት እንደትናንቱ ሊቀጥል ግድ ማለት ያዘ። ሳይወዱ በግድ ከሞቀ መኝታቸው የሚነሱ፣ ለውሎ ግዴታቸው የሚተጉ ሁሉ በር መስኮታቸውን ከፈቱ።
ከነዋሪዎች መሐል የአንደኛው ቤት በር እንደወትሮው ሳይከፈት፣ ድምፅ ሳይሰማበት ቆየ። በቤቱ ሦስት እህትማማቾች ተከራይተው ይኖራሉ። ሁሉም ወደ ውጭ ሀገር ለመሄድ ቀነ-ቀጠሮ እየጠበቁ ነው። እስከዛሬ እንዲህ ተኝቶ ማርፈድ ልምዳቸው አይደለምና የሚያውቋቸው ጥርጣሬ ገብቷቸዋል።
ለእነሱ የቀረቡ አንዳንዶች ጉዳዩን ከዕለቱ ብርድ ጋር አዛምደው ዝምታን መርጠዋል። ሰዓቱ አንድ ሁለት ሲል እየቆጠረ ነው። አሁንም በቤቱ ዙሪያ አንዳች ድምፅ አይሰማም። ከውስጥ በኩል የተዘጋው በር እስካሁን አልተከፈተም። በሁኔታው የሰጉ ጎረቤቶች ጠጋ ብለው በሩን በዝግታና በኃይል ደጋግመው አንኳኩ። ምላሹ የቀደመው ዓይነት ዝምታ ሆነ።
ጥቂት ቆይቶ የሰዎች ቁጥር ጨመረ። በር መስኮት የሚያንኳኩ፣ በስም የሚጣሩ በረከቱ። አሁንም ከዝምታ በቀር ምላሽ አልተገኘም። በሁኔታው የሰጉ፣ ባልተለመደው አጋጣሚ የደነገጡ ጎረቤቶች ፖሊስ ጠርተው ሁኔታውን አስረዱ። በስፍራው የተገኘው የፖሊስ ኃይል የተዘጋውን በር ሰብሮ ወደ ውስጥ ዘለቀ። በቤቱ የነበሩት ሦስት እህትማማቾች እርስ በርስ እንደተደጋገፉ ወድቀዋል።
ሕይወት ለማዳን የፈጠኑ ከወደቁበት አንስተው ትንፋሻቸውን አዳመጡ። በአሳዛኝ ሁኔታ ሁሉም ነገር የዘገየ ሆኗል። እህትማማቾቹ በሕይወት አልነበሩም። ፖሊስ አስከሬኑን በተገቢው መንገድ መርምሮ ስፍራውን በጥንቃቄ ቃኘ። ቤቱ ጠባብና በቀላሉ አየር የማያስገባ ነው። ይህ ብቻ አይደለም። ከሟቾቹ አጠገብ ያለው ትልቅ የከሰል ምድጃ አመድ እንደሞላ ተቀምጧል። በውስጡ ተጠብሰው ያለቁ እሸት በቆሎዎች ቆሮቆንዳ ይታያል። ሁኔታው አስደንጋጭና ከባድ ይሉት ነበር። ከቀናት በኋላ በተሰማው የምርመራ ውጤት የእህትማማቾቹ ሞት መንስኤ በከሰል ጭስ መታፈን ስለመሆኑ ተረጋገጠ።
‹‹ካርቦን ሞኖክሳይድ›› በከሰል ጭስ ውስጥ የሚገኝ መርዛማ ንጥረነገር ነው። ይህን ጭስ ሰዎች ወደውስጣቸው በሚስቡ ጊዜ ለጤናቸው አስጊ የሆነ አደጋን ያስተናግዳሉ። በዚህ ጭስ ምክንያት ሕይወት ሊጠፋ አካል ሊጎዳ ይችላል። በአብዛኛው ከጥንቃቄ ጉድለት በሚከሰተው አደጋ በርካታ ሰዎች ሕይወታቸውን ያጣሉ። ጥቂት የማይባሉትም በከፍተኛ ሕመም ይሰቃያሉ። ይህ አደጋ በሰዎች ሕይወት ውስጥ ዝምተኛው ገዳይ እንደሆነ ቀጥሏል።
ክረምት በመጣ ጊዜ ሰዎች ውስጣቸውን የሚያሞቅ፣ አካላቸውን የሚያነቃቃ ነገር ይሻሉ። ሙቀትን ፍለጋ በሚኖር ፍላጎትም ከብዙ አማራጮች ያደርሳል። አብዛኞች አለባበሳቸውን ከበጋው ጊዜ ለውጠው ወፍራም ልብሶችን ይመርጣሉ። ገሚሶቹ ውስጣቸውን የሚጠግን፣ አካላቸውን የሚያበረታ ምግብ መጠጥ ይሻሉ። ከሰልን የሚሞቁ፣ ለማብሰያነት የሚመርጡም ብዙ ናቸው። ይህ የክረምቱን ተፅዕኖ ለማሸነፍ የሚደረግ ተለምዷዊ ትግል ነው።
ከሰል በባሕርይው ቤት ያሞቃል፣ አካል ያነቃቃል። ከዝናቡ ማየል ጋር በሚኖር የመብራት መቆራረጥም ኤሌክትሪክን ተክቶ ከጥቅም ይውላል። በክረምት ቅዝቃዜን ለመከላከል በሚኖር አጋጣሚ አብዛኞች ከሰልን እንደአማራጭ ይጠቀማሉ። በከሰል ጥሩ ቡና፣ ትኩስ ወጥና ፈጥኖ የሚደርስ ምግብ ሁሉ ተመራጭ ነው። ይህ ደግሞ ክረምት በሆነ ጊዜ ብዙዎችን ያስደስታል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳትና አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ እንደሚሉትም ክረምት በመጣ ቁጥር ስጋት ከሚባሉት መሐል የከሰል ጭስ አንዱና ዋነኛው ነው። አብዛኞች በክረምት ከሰልን ምርጫ ከማድረጋቸው ጋር ተያይዞ ጭሱ በሚያደርስባቸው ጉዳት ለሞትና ሕመም ይዳረጋሉ። በከሰል የመጠቀም ምርጫ ጠቀሜታው እንዳለ ሆኖ ጉዳቱ ከፍተኛ ነው የሚሉት አቶ ንጋቱ፤ በተለይ ክረምት ላይ ይህ ችግር ጎልቶ እንደሚስተዋል ይናገራሉ።
በክረምት ወቅት በከሰል ጭስ ታፍነው የሚሞቱ ሰዎች ይበረክታሉ። ከሰል በዓውደ ዓመት ሥራ በር ዘግተው የሚጠቀሙትን ጭምር ሰለባ ያደርጋል። አብዛኛው ሰው ጭሱ በሕይወት ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት ቢያውቅም በቸልተኝነት መዘናጋቱ ዋጋ እንደሚያስከፍለው አቶ ንጋቱ ይናገራሉ።
ብዙ ጊዜ በርካቶች የክረምት ቅዝቃዜን ለማምለጥ በቤታቸው ንፍሮ በቆሎ፣ ድንችና መሰል ምግቦችን ይቀቅላሉ። ይህ ልማድ በተለይ ምሽት ላይ በር ተዘግቶ የሚከወን ከሆነ የከሰሉ ጭስ ሕይወትን እስከመንጠቅ ይደርሳል።
አቶ ንጋቱ እንደሚሉት፤ የከሰል ጭስ አደጋን ለመከላከል መፍትሔው ከባድ የሚባል አይደለም። ከሰልን አቀጣጥሎ ወደ ቤት ከማስገባት በፊት ጭሱ ወጥቶ ፍም እስኪሆን መጠበቅ ያስፈልጋል። እንዲያም ሆኖ በርና መስኮትን መክፈትና አየር እንዲገባ ማድረግ የግድ ይላል። ከሰሉን አቀጣጥሎ ለዕንቅልፍ ወደ መኝታ ከመሄድ በፊት በውሃ አጥፍቶ ከአጠገብ ማራቅና ስፍራውን ማናፈስም ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ይናገራሉ።
እንደ አቶ ንጋቱ አገላለጽ፤ አብዛኞች ከሕይወታቸው ማለፍ በኋላ በቤታቸው የሚገኘው በከሰሉ ተጥዶ የቆየ ምግብ አልያም ጥራጥሬ ነው። ይህ እውነት ደግሞ መርዛማው ጭስ በቤቱ መታፈን ምክንያት መውጫ በማጣቱ አፍኖ እንደገደላቸው አመላካች ይሆናል።
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት እስካሁን በከሰል ጭስ ምክንያት ሕይወታቸውን ከሚያጡት መሐል አብዛኞቹ ከገጠር አካባቢ የሚመጡ ናቸው። አቶ ንጋቱ እንደሚሉት፤ አደጋው ከከተሜው ይልቅ በእነሱ ላይ የመከሰቱ ምክንያት የግንዛቤና የመረጃ እጦት ችግር በመኖሩ ነው።
ወቅቱ የክረምት ጊዜ ከመሆኑ ጋር የከሰል ጭስ አደጋን ለመከላከል ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል የሚሉት አቶ ንጋቱ፤ በክረምት ከከሰል ይልቅ ሌሎች አማራጮችን መጠቀም ሕይወትን ከችግር ለመታደግ እንደሚያግዝ ይናገራሉ። በከሰል የመጠቀም አጋጣሚ ሲኖር ከፍ ያለ ጥንቃቄ በማድረግም ራስን ከሞትና ጉዳት መጠበቅ አስፈላጊ ነው ሲሉ መልዕክት ያስተላልፋሉ።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 5 ቀን 2017 ዓ.ም