ገበያው የመንግሥት የግምጃ ቤት ሰነዶችንና ሌሎች የሰነደ ሙዓለ ንዋዮችን ማገበያየት ጀመረ

አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ የመንግሥት የግምጃ ቤት ሰነዶችን እና ሌሎች የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ግብይትን በይፋ አስጀመረ፡፡

ግብይቱን ትናንት ሐምሌ 4 ቀን 2017 ዓ.ም በሸራተን አዲስ ሆቴል በይፋ ያስጀመሩት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን፣ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ማዕከላዊ ግምጃ ቤት እና የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በጋራ በመሆን ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ እስማዔል ጥላሁን (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ለመጀመሪያ ጊዜ የመንግሥት የግምጃ ቤት ሰነዶችን ማገበያየት ጀምሯል። የመንግሥት የግምጃ ቤት ሰነድን ግብይት በገበያው በቀዳሚነት ተመዝጋቢ ሆነው መገበያየት የጀመሩት የወጋገን ባንክና የገዳ ባንክ ናቸው። ባንኮቹ በዕለቱ አክሲዮኖቹን በይፋ ማገበያየት ጀምረዋል ብለዋል።

እስማኤል ጥላሁን (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ገበያው ዛሬ ላይ ለመድረሱ ከተለያዩ ተቋማት የብዙ ዓመታት ጥረትን ጠይቋል። ለአብነትም የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም፣ የተቋማት ግንባታ፣ የሕግ ዝግጅት፣ የሰው ኃይል ሥልጠናና የተሳታፊዎች በአንድ ላይ መተባበር ነው ብለዋል።

ከተመዘገቡት ኩባንያዎች ጎን ለጎን የሲቢኢ ካፒታልና የወጋገን ካፒታል ሁለት ኢንቨስትመንት ባንኮች በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ፈቃድ ተሰጥቷቸው ወደ ሥራ መግባታቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይ ግለሰቦች፣ ኢትዮጵያውያንና የተለያዩ ድርጅቶች የግምጃ ቤት ሰነዶችንና አክሲዮኖችን በቀላሉ አገናኝ አባላቶችና ኢንቨስትመንት ባንኮች ጋር የፋይዳ መታወቂያቸውን ይዘው በመሄድና በመደወል ኢንቨስት ማድረግ እንደሚችሉ ገልጸዋል።

እንዲሁም ባሉበት ቦታ ሆነው በቀላሉ ኢንቨስት ማድረግ የሚችሉባቸውን የሞባይል መተግበሪያዎችንና ሌሎች የትምህርትና የሥልጠና ዝግጅቶችን የሚከታተሉ ይሆናል ብለዋል።

ግለሰቦችና ድርጅቶች የግምጃ ቤት ሰነድ መግዛት ሲፈልጉ በቀላሉ የፋይዳ መታወቂያቸውን በመስጠት ኢንቨስትመንት ባንኮቹ ጋር ይመዘገባሉ ያሉት እስማኤል ጥላሁን (ዶ/ር)፤ ገንዘብ አስገቡ በሚባሉበት አካውንት በማስገባት ይግዙልኝ ወይም ይሽጡልኝ በሚለው መስፈርት መገበያየት እንደሚችሉ አስረድተዋል።

ከዚህ ውጭ ለአተገባበር አስቸጋሪ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን እንዲረዱና እንዲጠቀሙ እንደማይገደዱ ጠቁመው፤ በቀጣይ ግን ለመተግበር ቀላል የሆነና ገበያው ላይ መሳተፍ የሚያስችሉ ቀላል የሞባይል መተግበሪያዎች እንደሚኖሩ ገልጸዋል።

የአክሲዮን ግብይት ጅማሮ ዘመናዊ የግብይት መሠረተ ልማት ለመገንባት የተሠሩ ሥራዎች ውጤታማነት ማረጋገጫ ነው ያሉት እስማኤል ጥላሁን (ዶ/ር)፤ ገበያው በዚህ የለውጥ ሂደት ውስጥ የመሪነት ሚና መጫወት እንደቻለ ጠቅሰዋል። አያይዘውም ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ማበርከት የሚያስችል የግብይት መድረክ እንደሆነ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ጅማሮን ለማብሰር የተገኙት የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምሕረቱ እንዳሉት፤ ብሔራዊ ባንክ ከዛሬ አምስት ዓመታት በፊት ካፒታል ገበያን ወደ ሥራ ለማስገባት የካፒታል ገበያ አዋጅና የካፒታል ገበያ ባለሥልጣንን በማቋቋም ሂደት ፈር ቀዳጅ ሚና ሲጫወት ቆይቷል። የካፒታል ገበያ ሥርዓት እንዲያድግና ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አማራጭ ፋይናንስ ምንጭ ሆኖ እንዲያገለግል በማሰብ እንደሆነ ተናግረዋል።

የካፒታል ገበያ በዘመናዊ መንገድ መደራጀት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ላስቀመጣቸው ዋና ዋና ስትራቴጂካዊ ዕቅድ መሳካት ወሳኝ ሚና ይጫወታል ያሉት ማሞ ምሕረቱ፤ በዋናነት የዋጋ መረጋጋትን ለማምጣት፣ የገንዘብ ፖሊሲ መሣሪያውን ውጤታማነት ለማሳደግና አሠራሮችን ለማዘመን ለሚደረገው ጥረት አጋዥ መሣሪያ ነው ብለዋል።

በተለይም መንግሥት የተለያዩ ሀገራዊ የልማት ዕቅዶችን ለማሳካት በሚያደርገው ጥረት መሠረት የሚገጥሙ የበጀት ጉድለት ገበያ መር በሆነና የዋጋ ግሽበትን የማያስከትሉ ዘዴዎችን ለመጠቀም ዕድል የሚሰጥ እንደሆነም አመላክተዋል።

በቀጣይም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቀጣይነት ባለው የፈጠራ ሥራዎች እና ትብብር የካፒታል ገበያውን ሥነ-ምኅዳር እና ደጋፊ የሆኑ መሠረተ ልማቶችን በመደገፍ የሀገሪቱን የረጅም ጊዜ የፋይናንስ ብልፅግና ለማሳደግ ቁርጠኛ ነው ብለዋል።

በ ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You