
ኢትዮጵያን እየፈተናት ከሚገኙ ማኅበራዊ ችግሮች መካከል አንዱ ዜጎች ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ከሀገራቸው ወደ ተለያዩ ሀገራት በመፍለስ የሚደረስባቸው ሞት፣ ስቃይና መከራ ተጠቃሽ ነው፡። ይህ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የሚደረግ የዜጎች ፍልሰት ጉዳቱ በእነርሱ ላይ በሚደርስ ሞትና ስቃይ የሚያበቃ ሳይሆን በቤተሰብና በሀገር ላይም ላቅ ብሎ የሚስተዋል ነው:: ይህን የሕዝብም የሀገርም ፈተና የሆነውን ኢ-መደበኛ ፍልሰት መንግሥት ሕጋዊ ለማድረግ ሲጥር ቢስተዋልም፤ ከሕጋዊው ይልቅ ሕጋዊ ያልሆነው መንገድ እየተመረጠ በስፋት ሲኬድበት ይታያል::
ለመሆኑ ይህ በገንዘብ፣ በሥነ ልቦና እና እስከ ሞት ዋጋ እያስከፈለ ያለው ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የሚደረግ ፍልሰት ምንነቱ፣ ገፊ ምክንያቱ፣ የሚኬድባቸው መስመሮችና ሌሎችንም ጉዳዮች በተመለከተ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የምርመራ ቡድን ለተከታታይ ወራት ምርመራ ሲያካሒድ ቆይቷል:: መረጃዎችንም ከምሁራን፣ የኢ-መደበኛ ፍልሰት ሰለባ ከሆኑትና ከቤተሰቦቻቸው፣ ከመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ከሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች እና ከሰነዶችም ጭምር አጠናቅሯል:: ወደተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በመንቀሳቀስም ሕጋዊ ያልሆነ ፍልሰቱ የሚካሔድበትንም አካባቢ የቃኘ ሲሆን፣ ያጠናቀረውን የምርመራ ዘገባ እነሆ ብሏል::
ክፍል አንድ
መደበኛ ያልሆነ የሰዎች ፍልሰት ምንድን ነው?
ለሥነ-ሕዝብ ዓላማዎች፣ ሁለት ዓይነት የስደት ዓይነቶች ያሉ ሲሆን፣ እነዚህም ዓለም አቀፍ እና ውስጣዊ በመባል ይገለጻሉ። ዓለምአቀፍ ፍልሰት ሰዎች የሀገራት ድንበሮችን በማቋረጥ ቢያንስ ረዘም ላለ ጊዜ በሌላ ሀገር ውስጥ ሲኖሩ ነው። የውስጥ ፍልሰት ሰዎች በሀገራቸው ውስጥ ሲንቀሳቀሱ ነው፤ ይህም ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ እንቅስቃሴን ይጠቀልላል።
ይህም እንቅስቃሴ መደበኛና መደበኛ ያልሆነ የሰዎች ፍልሰት በመባል ለሁለት ይከፈላል:: መደበኛ ፍልሰት ሰዎች ድንበር አቋርጠው በተቋቋሙ እና በተፈቀደላቸው መንገዶች መንቀሳቀስን የሚያመላክት ሲሆን፣ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት (ብዙውን ጊዜ ሕገ ወጥ ስደት በመባል የሚታወቀው) ሰው ወደ ሀገር ውስጥ ሲገባ፣ ሲቆይ ወይም ሲሠራ ያለ ሕጋዊ ፍቃድ ወይም ሰነድ ሳይኖረው መንቀሳቀስን ያመላክታል።
እንደ አይ.ኦ.ኤም፤ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት በፈቃደኝነትም ሆነ በግዳጅ፣ ያለፈቃድ ጊዚያዊ ወይም ቋሚ እና ድንበር ማቋረጥን ወይም በአንድ ሀገር ውስጥ መቆየትን የሚያካትት ሰፊ ጽንሰ-ሀሳብ ነው። መደበኛ ያልሆነ የሰዎች ፍልሰት የተለያየ ምክንያትና መዘዝ ያለው የሰው ልጅ ተግባር መሆኑን አጽንኦት ይሰጣል። መደበኛ ያልሆነ የሰዎች ፍልሰት በተለያዩ የትውልድ፣ የመተላለፊያ እና የመዳረሻ ሀገሮች ውስጥ የተለያየ አስተዳደግ ያላቸውን ሰዎች የሚያሳትፍ ተለዋዋጭ ክስተት ነው።
በሌላ አነጋገር መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት ደግሞ የሚፈጠረው ያለ ሀገራት ፍላጎት ሕጋዊ ፈቃድ ወይም ሰነድ የሌላቸው ግለሰቦች ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ፣ ሲቆዩ ወይም ሲሠሩ ነው። ይህም ያልተፈቀዱ የድንበር ማቋረጦችን፣ ቪዛዎችን ከመጠን በላይ ማቆየት፣ ወይም ያለሥራ ፈቃድ መሥራትን ያካትታል። ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት (አይ.ኦ.ኤም)፣ በዚህ መልኩ የሚጓዙት ለጉልበት ብዝበዛ እና የሰብአዊ መብት ረገጣ ተጋላጭ መሆናቸውን በአፅዕኖት ያሳያል።
ገፊ ምክንያቶች
ለዚህ ሥራ የተቋቋመው የኢፕድ የምርመራ ዘገባ ቡድን፤ በጉዳዩ ዙሪያ ጥናት ያደረጉ ምሁራንን፣ የጥናት ሰነዶችንና ተጎጂዎችን ለዚህ ውድ ዋጋ ለሚያስከፍል ድርጊት ገፊ ምክንያቶቹ ምንድን ናቸው? ሲል ጠይቋል:: ያገኘውም ምላሽ እንደሚያመላክተው ሥራ አጥነት፣ የአመለካካት መዛነፍ (በፍጥነት ለመክበር መፈለግ)፣ የጓደኛ ተጽዕኖ፣ የደላሎች ውክብያና ማታለል፣ ግጭቶች ወዘተ የሚሉ ናቸው::
ረዳት ፕሮፌሰር መሐመድ አሊ፣ የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ አመራር እና አስተዳደር ኮሌጅ ምክትል ዲን፣ በሥራ እና ክህሎት የሥራ እድል ፈጠራ አማካሪ የቦርድ አባል እና ፍልሰትና ልማት ትምህርት ክፍል መምህር ናቸው:: በእርሳቸው ገለጻ፤ ለሕገ ወጥ ስደት ገፊ ምክንያቶች የሚባሉት የእርስ በርስ ግጭት፣ ድርቅ፣ የተፈጥሮ አደጋ እና በችግር ምክንያት ሰዎች የተሻለ ሕይወት ፍለጋ፣ ድህነት፣ የመሬት እጥረት እና የኢኮኖሚ ችግር ሊጠቀሱ ይችላሉ።
ሌላው የፍልሰት ምክንያት ደግሞ እንደባሕል የመቁጠር አይነት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል ይላሉ:: ለምሳሌ አንድ ገጠር አካባቢ የሚኖር አባት አካባቢው ላይ የሌላ ሰው ልጅ ወደውጭ ሀገር ሄዳ ቤተሰቦቿን አግዛ፣ የቤተሰብ የአኗኗር ዘይቤ ሲቀየር ሲያይ እርሱም “እንደ እነርሱ ሕይወታችንን ቀይሪልን” ብሎ ልጁን ሊልክ ይችላል። በዚህ ምክንያት አንዳንድ አካባቢዎች እንደ ባሕል የሚታይ ጉዳይ መሆኑንም ምሁሩ ይገልጻሉ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አርትስ ኤንድ ሂዩማኒቲስ መምህር እና አጥኝ የሆኑት ጉዲና በሹዳ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ስለ ፍልሰት ገፊ ምክንያቶች ሲናገሩ ‹‹እንደ እኛ ሀገር ካየነው ዋና የስደት ምክንያቱ ሥራ አጥነት፣ ድህነት እና ከዚህ ጋር የተያያዙ ምክንያች ናቸው::” ይላሉ:: ሀገርም ውስጥ ሆኖ ሰው ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ይጓጓዛል:: ለምሳሌ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ የአየር ለውጥ እና ግጭት ሲኖር ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ሰው ይሰደዳል፤ መኖሪያውንም ይቀይራል:: ከእኛ ሀገር ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ሰው የሚሰደደው በጣም ከፍተኛ አስተዋጾ የሚያደርገው ድህነት፣ ሥራ አጥነት እና በዚህ የተነሳ ሰዎች የሚኖራቸው የተሻለ ኑሮ እና ገቢ የማግኘት ፍላጎት ነው ሲሉ ረዳት ፕሮፌሰር መሐመድ አሊ የተናገሩትን ሀሳብ አጽንኦት የሚሰጥ አስተያየት ያጋራሉ::
በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሕጋዊ ያልሆነ የሰዎች ዝውውርም ሆነ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ከሀገር መውጣት ዛሬ የተጀመረ ሳይሆን ረጅም ታሪክና ሰንሰለት ያለው ብዙ አካላት የሚሳተፉበት መሆኑን ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ እና በአውሮፓ ሕብረት ፕሮጀክት ለኢትዮጵያ መንግሥት ለሚሰጡት ድጋፍ ቡድን መሪ ጉቱ ቴሶ (ዶ/ር) ይናገራሉ:: በየቀኑ የሚወጣው ሰው ቢደመር በዓመት ወደ መቶ ሺህ የሚጠጉ ዜጎች ከሀገር ወደ ውጭ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ እንደሚፈልሱ ይገመታል:: የተባበሩት መንግሥታትና ሌሎች ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ያጠኑትም የሚያሳየው መረጃ ይኼንኑ ነው::
ለዚህ ሕጋዊ ላልሆነ ጉዞ፣ ሕጋዊ ላልሆነ የሰዎች ዝውውር ወይም ደግሞ ሕገ ወጥ ፍልሰት የሚዳርጉ ብዙ አይነት ምክንያቶች አሉ:: የመጀመሪያው ከኢኮኖሚ ጋር የሚገናኝ ነገር ሊሆን ይችላል:: የሥራ አጥነት ችግር በተለይ ወጣቱ ክፍል የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን፣ የኮሌጅ ትምህርቱን እንዲሁም ከፍተኛ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ በሚታዩት ነገሮች ሊሆን ይችላል:: በሀገር ውስጥ ሠርቶ ለመኖር ሲቸገር፣ በሀገሩ ውስጥ የሥራ ዕድል የለም ብሎ ማመን ሲጀምርም ተስፋ ከመቁረጥ የተነሳ በቤተሰብ ላይ ተመልሶ ጫና ላለመሆን ሲያልም ሀገር ጥሎ ሊሰደድ ይችላል::
ሁለተኛው የአየር ንብረት ለውጥ ነው:: አብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል በተለያዩ የአየር ንብረት ለውጦች ተጽዕኖ የተጋለጡ ናቸው:: ወደ ምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል ሲኬድ አፋር፣ ሶማሌ፣ ወደ ደቡብ ሲኬድ ደቡብ ኦሮሚያ፣ ወደ ሰሜን ደግሞ አማራና ትግራይ ክልሎች በድርቅ ለረጅም ዘመናት የሚጋለጡ ናቸው:: እናም ጥናት እንደሚያመላክተው፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚከሰተው የተፈጥሮ አደጋ 70 በመቶው ከድርቅ ጋር የተገናኘ እንደሆነ ነው ይላሉ::
ሰዎች ያላቸው የእርሻ ሥራ፣ የከብት እርባታ፣ የሚተዳደሩበት ሥራ ሲበትን፤ ልጆቻቸውን ለሚስቶቸቸው ወይም ለባሎቻቸው ትተው ሀገር ጥለው የሚሰደዱበትና ወደ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ሰንሰለት ውስጥ የሚገቡበት ሁኔታ አለ:: አብዛኛዎቹ መካከለኛው ምስራቅ የምናገኛቸው ሰዎች ከተለያየ ቦታ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በመፈናቀል ቀያቸውን ለቀው የሚወጡበት ሁኔታ አለ።
በሶስተኛ ደረጃ ገፊ ምክንያቱ ከግጭት ጋር የተገናኘ ነው:: በሚከሰት ግጭት ቀያቸውንና ሀብት ንብረታቸው ጥለው የተፈናቀሉ ሰዎች ኑሮን ለማሸነፍና ከጦርነት ለመሸሽ ሲባል እና ሰላም ፍለጋ ከሀገር የሚሰደዱበት ሁኔታ ይከሰታል:: ለምሳሌ ከትግራይና አማራ አዋሳኝ፤ ከቤኒሻንጉል እና ከኦሮሚያ አዋሳኝ፤ ኦሮሚያና ከሱማሌ አዋሳኝ፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ በሚደረጉ ግጭቶች ምክንያት ወደ ጎረቤት ሀገር ብሎም አካባቢውን ለቅቀው የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ወደ አውሮፓ፣ አሜሪካ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ መካከለኛው ምስራቅ እና ሌሎች ሀገራት የሚሰደዱበት ሁኔታ አለ:: ስለሆነም ግጭትና ጦርትነትም ቀላል የማይባል ድርሻ የያዘ ለሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እና የሰዎች ፍልሰት ምክንያት የሚሆን እንደሆነ ጉቱ (ዶ/ር) ይናገራሉ::
ጸደቀ ላምበሬ (ዶ/ር)፣ በዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ መምህርና በፍልሰት ጉዳዮች ላይ ለረዥም ዓመታት ምርምር ያካሄዱ መጽሐፍም ያዘጋጁ ናቸው:: በዩኒቨርሲቲው የምርምር ሥራዎቹ የተካሔዱት በዋናነት ሶስት አካባቢዎች ላይ ነው ይላሉ:: እነርሱም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሀድያ፣ ከምባታ ጠንባሮ ልዩ ወረዳ እና በከፊል ሀላባን የሚያካትት እንደሆነም ያስረዳሉ።
በጥናታቸው በተገኘው ውጤትም፤ በአካባቢው ካለው ማኅበረሰብ 40 በመቶ የሚሆኑት ቤተሰባቸውን ወደውጪ ልከዋል። ይህ ከፍተኛ ፍልሰት በአካባበቢው መኖሩን የሚያመላክት ነው። ከዚሁ ጋር በተያየዘ አብዛኛው ስደተኛ ለመሄዱ እንደ ምክንያት የሚያነሳው የኢኮኖሚ ጉዳይን ነው።
ወጣቱ እንዴት በቀላሉ ገንዘብ አገኛለሁ? የሚለው አመለካከት በውስጡ ሰርጿል። ይህንንም ተከትሎ ፍልሰትን ባሕል የማድረግ ነገር በአካባቢው በስፋት የሚስተዋል ሆኗል። ይህም ሆኖ በሥራ እድል ፈጠራ ወጣቶችን በበቂ ሁኔታ መቀበል የሚችሉ ፋብሪካዎች በአካባቢው አለመኖርም አንዱ ነው። ይህ ማለት ግን ዜጎች ይሰደዱ ማለት አይደለም ይላሉ። መንግሥት አማራጭ ባያዘጋጅ፤ ፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎችም ባይኖሩ እንኳን ሀገር ለቆ መሰደድ ተገቢ አይሆንም። ሀገሬ ላይ ላተርፍ አልችልም የሚል ግምት መኖርና በሀገር ሰርቶ ለመለወጥ እራስን አለማዘጋጀት ነገር ይስተዋላል ሲሉ ይናገራሉ::
ለዚህ ደግሞ አንዱ የአመለካካት ችግር ነው፤ ፍልሰትን ባሕል ወደማድረግ ተመጥቷል ብለን የገለጽንበት ምክንያት አስራ ስምንት ዓመት ያልሞላቸውም ልጆች እየሄዱ መሆኑን በማየታችን ነው። አስራ ስምንት ዓመት ያልሞላው ልጅ ሄዶ ምን ሊሠራና ገቢ ሊያገኝ ይችላል? ተብሎ ሲታሰብ ባሕል እየሆነ መምጣቱን አመላካች ነው። እነዚህ ወጣቶች እንኳን ሀገር አቋርጠው ገንዘብ እንዲያመጡ መጠበቅ ይቅርና በሀገር ውስጥ ሥራ ሠርተው ገቢ እንዲያመጡ ማድረግም አስቸጋሪ በመሆኑ ነው። በሁለተኛ ደረጃ የሚሄደው ወጣት በሙሉ በጉልበት ሥራ የሚሳተፍ ነው። ይህ ልምምድ ወደ ክህሎት ሥራ መቀየር ያለበት ነው። ለዚህ ደግሞ እዚህ ሀገር እያሉ ክህሎት እንዲቀስሙና እንዲሄዱ በመንግሥት በኩል ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል።
ለምሳሌ በቀላሉ በሙያ ማሰልጠኛዎች በኩል ወደ አረብ ሀገራት የሚሄዱትን ከአልጋ ማንጠፍ ጀምሮ ልብስ እንዴት እንደሚታጠብ እና ቀላል ማሽኖችን እንዴት ማንቀሳቀስና መቆጣጠር እንደሚችሉ የማሳወቅ ሥራ ይሠራል። ይህ ከሆነ የተሻለ ከፍያ የማግኘት እድል ይኖራቸዋል። ለእራሳቸውም ለቤተሰቦቻቸውም ብሎም ለሀገር ጠቀሜታ የሚኖረው ይሆናል። ካልሆነ ግን ካለእውቀት እንዲያው በልምድ ብቻ የሚኬድ ከሆነ የሚከፈለው ገንዘብ ዝቅትኛ ይሆናል። በመሆኑም በተመሳሳይ በደቡብ በኩል የሚሄዱትም ቢያንስ መንጃ ፈቃድ ቢይዙ፣ ሱቅ ውስጥ እንዴት መሥራት እንደሚችሉ መሰረታዊ እውቀት ቢኖራቸው፣ ከንግድ ሥራ ጋር በተያያዘ አጫጫር ስልጠናዎችን ወስደው እንዲንቀሳቀሱ ቢደረግ በምንም መንገድ ቢጓዙ እንኳ ውጤታማ መሆን ይችላሉ ማለት ያስደፍራል ሲሉ ያብራራሉ።
ለዚህ ጽሁፍ ግብዓት ይሆን ዘንድ ያነጋገርነው ከስደት ተመላሹ (ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ) ወጣት እንደሚናገረው፤ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ከፋ ዞን ጊምቦ ወረዳ ዲሊ ቀበሌ የሚባል አካባቢ ተወላጅ ነው። ቦንጋ የአትክልት ሀገር እንደመሆኑ ለውጭ ገበያ ጭምር ለማቅረብ የሚያስችል አቅም ያለበት ቦታ ነው። ባለትዳር እና የሁለት ልጆች አባት የሆነው ወጣቱ አርሶ አደር፣ ወደ ስደት ከመውጣቱ በፊት በአባቱ ውስን ማሳ እና ከሌላ ሰው ማሳ ተኮናትሮ ሲሠራ ቆይቷል።
ለስደት ያነሳሳው ምክንያት መሬቱን ኮንትራት ሰጥቶት የነበረው ግለሰብ መሬቱን ስለወሰደበት ነው:: በአካባቢውም ሌላ ሊሠራው የሚችለው ሥራ ባለመኖሩ እና በኮንትራት የሰው መሬት ይዞ መሥራት ኪሳራ ስለሆነ ወደ ሳዑዲ በኢ-መደበኛ መንገድ መሰደድን ምርጫው እንዳደረገ ይናገራል።
ሌላኛው ወጣት እድሜው 22 ነው። በኢ-መደበኛ መንገድ ወደ ሳዑዲ ተሰድዶ የተመለሰ ነው:: እስከ ስምንተኛ ክፍል ተምሯል። ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ስደት የወጣው በ2010 ዓ.ም ነው:: በወቅቱ መማር ቢፈልግም የቤተሰቦቹ አቅም እሱን ለማስተማር የሚያበቃ አልነበረም። “ሀገር ውስጥ ተቀምጬ ቤተሰቦቼ ላይ ጫና ከምፈጥር ብዬ ስደትን አማራጭ አደረግሁኝ።›› ይላል::
ሌላው ከስደት ተመላሽ ወጣት እንድሪስ ፈንታው ሲሆን፣ በቶጎ ውጫሌ አድርጎ ከሀገር እንደወጣም ይናገራል:: ለስደት ያነሳሳውን ምክንያት በ2010 ዓ.ም የ10ኛ ክፍል ትምህርቱን ጨርሶ ሥራ በማጣቱ መቸገሩን ያስረዳል:: ስለዚህም ሥራ አጣሁ በሚል ምክንያት ለስደት እንደበቃ ያመለክታል:: “ለጀልባ 15 ሺህ ብር ከፍዬ ነው የሄድኩት፤ በጥቅሉ ሳዑዲ ለመድረስ እስከ 100 ሺህ ብር ከፍያለሁ።›› ሲል ያወጣውን ወጪ አስልቶ ይገልጻል::
ወጣቱ፣ የስደትን መከራ የቀመሰው ሁለቴ ነው:: ምክንያቱም ለሁለተኛ ዙርም ተሰድዷል:: ከ2011 ዓ.ም ስደቱ መልስ በ2014 ዓ.ም መንቀሳቀሻ ገንዘብ ሲያጣ፤ በድጋሚ በ-ኢመደበኛ መንገድ ተሰደደ:: ከመጀመሪያ ስደቱ ከተመለሰ ከስምንት ወር በኋላ ተመልሶ ሄደ:: ለስምንት ወራትም ቋሚ ሥራ ሳይገባ የተለያዩ ሥራዎችን መሥራቱን ይናገራል። ፍተሻ ሲደረግ ተይዞ አምስት ወር ታስሮ ወደ ሀገሩም ተመልሷል::
ሌላኛው ከስደት ተመላሽ ወጣት ክንዴ (ስም የተቀየረ)፣ ከሀገር የወጣበትን ምክንያት ሲያስታውስ፤ “ሳዑዲ የገባሁት ገንዘብ እስከ 260 ሺህ ብር ከፍዬ ነው። ይህን ብር ትንሽ ጨምሬበት አንድ ባጃጅ ብገዛበት ይሻለኝ ነበር:: ለችግር ጊዜ የሚክፍል ቤተሰብ ሀገር ወስጥ ሆኜ ልሥራ ብል አይሰጥም” የሚለው ክንዴ፣ “እህቴ ባጃጅ መግዣ ብዬ ብር ብጠይቃት አትሰጠኝም:: ነገር ግን ተይዤ ስደበደብ ብር ልካልኛለች። ይህ በመሆኑ ነው ስደትን አማራጭ አድርጌ ለመሄድ የተገደድሁት።›› ይላል::
“ለስደት ከባከነው ገንዘብ ግማሹን ለምሠራበት ማቋቋሚያ የሚሰጠኝ ባገኝ ኖሮ በደንብ በሀገሬ ሠርቼ ማትረፍ እችል ነበር። አሁን ያባከንኩትን ያህል 260 ሺህ ብር ቀርቶ 100 ሺህ ብር ባገኝ እንዴት እንደምሠራበት አውቅ ነበር” ሲል ይቆጫል:: “አሁን ወደ ቀዬ አቀናለሁ:: ባገኘሁት አማራጭ ሁሉ ሥራ ሠርቼ መኖር እሻለሁ:: ከዚህ በኋላ የማስበው ነገር ቢኖር የቀን ሥራም ቢሆን ሰርቼ መለወጥን ነው:: ከዚህ በኋላ ስደትን የሚባለውን ነገር በፍጹም አላስበውም:: ዋሽቶ ለመከራ የዳረገኝን ደላላ፣ ተረኞችን እንዳይዋሽ የተቻለኝን አደርጋለሁ:: ስለደላላ የምሰማው ወይም የማየው ነገር ካለም ለጸጥታ ኃይሎች እጠቁማለሁ::” በማለት ይናገራል::
ሌላኛዋ ከስደት ተመላሽ የ23 ዓመት ወጣት ናት፤ አላማጣ ላይ ቁርስ ቤት እንደነበራት ትናገራለች:: ነገር ግን በነበረው ጦርነት ንብረቷ ሁሉ ሲወድም ስደትን ምርጫዋ አድርጋለች፤ እዚያ ሄዳ ግን እድል አልቀናቻትም፤ ምንም ነገር ሳትሠራ ታስራ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሳለች::
‹‹የነበርኩበት አካባቢ ብዙ ደላሎች አሉ፤ ደላሎቹ ወጣት ሴቶችን እየመረጡ በነጻ አረብ ሀገር እንደሚልኩ እና እዚያ ሰርቶ መክፈል እንደሚቻል ይናገራሉ:: ነገር ግን ልክ ሳዑዲ ስንደርስ ሁላችንም እየተደበደብን ቤተሰብ ዘንድ እንድንደውል ይደረግና ከ240 ሺህ እስከ 250 ሺህ ብር ድረስ ቤተሰብ እንዲልክ ይደረጋል” ትላለች::
የት እንደሔድኩ ምንም መረጃው ወደሌለው አባቴ ተደውሎ 240 ሺህ ብር ክፈል በመባሉ ከፍሎልኛል:: ይሄንን ብር አባቴ እንዴት እና ከማን እንኳን እንደተበደረ አላውቅም:: እንዴት ዐይኑን አየዋለሁ የሚል ፍርሃት ይዞኛል ስትል ታስረዳለች::
ሕጋዊ ያልሆኑ የፍልሰት መስመሮችና መዳረሻዎች – የሞት በሮች
ሕጋዊ በሆነ መልኩ ከቦታ ወደ ቦታ መዘዋወር የቀጠለ ተግባር ነው። የየሀገራቱ ሰዎች በሥራ፣ በትምህርት፣ በሕክምና እና በመሳሰሉት ጉዳዮች ከሀገራቸው ሲወጡ የሚጠብቅባቸው መስፈርቶች አሉ። በተለይም ለሥራ የሚሄዱ ዜጎች ለአካለ መጠን የደረሱ፣ በቂ ወይም የተሟላ ጤንነት ያላቸው፣ የጉዞ ሰነዳቸው የተሟላ፣ ወደ ሚሄዱባት ሀገር የሕይወት እና የሥራ ዋስትና (ኢንሹራንስ) መግባት፣ ጊዜው ያላለፈበት ፓስፖርት መያዝ እና የመሳሰሉትን ሟሟላት አስፈላጊ እና ቅድመ ሁኔታዎች ናቸው።
ይሁንና ሰዎች የተጠቀሱትን ቅድመ ሁኔታዎች/መስፈርቶች መካከል በሙሉም ወይም በከፊል ማሟላት ሲያቅታቸው በሕገ ወጥ ደላሎች ወይም በራስ ተነሳሽነት ሕገ ወጥነትን ይመርጣሉ። በተለይም ሕገወጥ ደላሎች እና አዘዋዋሪዎች ይህን ክፍተት ተጠቅመው ሰዎችን ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ እንዲሰደዱ በማግባባት ለከፋ ስቃይ፣ እንግልት እና መከራ እንዲዳረጉ ያደርጋሉ።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ከፍተኛ የወጣቶች ፍልሰት እና ሕጋዊ ያልሆነ የሰዎች ዝውውር ከሚታይባቸው ሀገራት መካከል አንዷ ናት። ዜጎች በሕገ ወጥ መልኩ ሥራ ለማግኘት ወደ ደቡብ አፍሪካ፣ አረብ ሀገራት፣ ሱዳንና አውሮፓ መዳረሻቸውን በማድረግ በየብስ ትራንስፖርት፣ በእግርና በባሕር ጀልባ ላይ በየቀኑ ወደ ውጭ ይፈልሳሉ። ስደተኞቹ ሕጋዊ ያልሆነ መንገድ ስለሚጠቀሙ የተለያዩ እንግልቶች ያጋጥማቸዋል። ለመሆኑ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያውያን በሕገ ወጥ መልኩ ለመሰደድ የሚጠቀሙባቸው መንገዶች ወይም መስመሮች የትኞቹ ናቸው? የሚለው ጥያቄ ደግሞ የዚህ ንዑስ ርዕስ ጽሁፍ ማጠንጠኛ ይሆናል።
ሰዎች ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የሚሔዱባቸውን መስመሮች አስመልክቶ የጠየቅናቸው ጸደቀ (ዶ/ር)፣ ናቸው:: እርሳቸው እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያውያን መደበኛ ባልሆነ መንገድ ከሀገር የሚወጡባቸው የፍልሰት መንገዶች ወይም በሮች የሚባሉት አብዛኛዎቹን ጥናቶች በሶስት ዋና ዋና መስመሮች ይመድቧቸዋል:: እነዚህም የምስራቁ፣ የሰሜኑ እና የደቡብ በር ይባላሉ:: የምስራቁ በር የሚባለው ኢትዮጵያውያን በዋናነት የአፋሩ ጋላፊን እንደ ዋና መውጫ በር የሚጠቀሙ ሲሆን፣ በጅቡቲ – ሶማሌ ላንድ – የመንን እንደ መተላለፊያ መስመር በመጠቀም ወደ ሳዑዲ አረቢያና ሌሎች የመካከለኛው ባህረ ሰላጤ ሀገራት ለመድረስ የሚሄዱበት መስመር ነው:: መስመሩም ምልልስ ሲደረግበት ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ ነው::
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ በምስራቁ በር አልፎ አልፎ በሶማሌ ላንድ በኩል አድርገው ወደ ጅቡቲ የሚገቡ ሲሆን፣ የመንን እንደ መተላለፊያ መስመር የሚጠቀሙ ናቸው:: በዚህ መስመር በሱማሌ ክልል አድርገው መቋድሾ – ከዚያም ወደሚፈልጓቸው ሀገራት በአውሮፕላን የሚበሩበት ሁኔታ አለ::
ሰሜን በር በሚባለው ጉዞ እንደ መውጫ የሚጠቀሙት የመተማን በር ነው:: የመተማን በር በመምረጥ ሱዳዳ – ግብጽ – ሊቢያን እንደ መዳረሻ ወይም መተላለፊያ መስመር ይጠቀሙና ወደ አውሮፓ እና መካከለኛው ምስራቅ ለመድረስ የሚጓዙበት መስመር ነው:: ይህ መስመር በጣም ከፍተኛ በረሃን የሚያቋርጡበትና ሰቅጣጭ አደጋ የሚከሰትበትም ጭምር ነው ይላሉ::
እንደ ጸደቀ (ዶ/ር) ገለጻ፤ ሌላኛውና ሶተኛው የደቡባዊ በር የሚባለው ሲሆን፣ ሞያሌን እንደ መውጫ መንገድ ኢ-መደበኛ ፍልሰተኞች በዋናነት ይጠቀማሉ:: ይህ በር በኬንያ – ታንዛኒያ – ማላዊ – በተወሰነ መልኩ ሞዛምቢክ – ዝምባብዌን ጭምር በመንካት – ደቡብ አፍሪካ ለመድረስ የሚደረግበት መስመር ነው::
ቁጥሩ የሚለያይ ቢሆንም ኢ-መደበኛ ባልሆነ መንገድ ከሁሉም የሀገሪቱ አካባቢ ተነስተው በሁሉም መስሮች ይወጣሉ:: ነገር ግን ካሉት መስመሮች የሰሜኑና የደቡባዊው በር የበለጠ መሆኑን ጸደቀ (ዶ/ር) ያብራራሉ::
በፍትህ ሚኒስቴር የብሄራዊ ፍልሰት ትብብር ጥምረት ሴክሬቴሪያት ኃላፊ አቶ አብርሃም አያሌው፣ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ መውጫ ናቸው የሚባሉትን መስመሮች ሲጠቅሱ፤ አንዱ የምስራቃዊ መስመር ሲሆን፣ በጋላፊ፣ በቶጎ ውጫሌ እና በደወሌ፣ ጅቡቲ፣ ቀይ ባሕር አድርጎ የመን እና በመጨረሻም ወደ ሳዑዲ አረቢያ የሚደረግበት መስመር ነው:: ደቡባዊ መስመር የሚባለው ደግሞ በሞያሌ በኩል ኬንያን፣ ታንዛኒያ፣ ማላዊ፣ ሞዛምቢክ፣ ቀጥሎም በዚምባብዌ በማድረግ መዳረሻን ደቡብ አፍሪካ የሚያደርግ ነው:: የሰሜን ምዕራብ መንገድ የሚባለው ደግሞ በመተማ በኩል ሱዳን፣ ሊቢያ፣ ሜዲትራኒያን ባሕርን ከዚያም አውሮፓን መዳረሻ የሚያደርግ መስመር ነው ይላሉ::
በመስከረም 30 ቀን 2017 ዓ.ም. ለኢዜአ እንደገለጹት፤ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገራት ሕጋዊ ያልሆነ የሰዎች ዝውውር ከሌሎች ችግሮች በተለየ ሁኔታ ስር የሰደደ ችግር ሆኖ አምራቹን የወጣት ክፍል ለሰብዓዊ ችግር እየዳረገው ይገኛል። ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 30 ያሉት ወጣቶችም “የተሻለ ኑሮ፣ ገቢና እና ሕይወት ይገኛል” በሚል ተስፋ፤ ለተለያዩ ጉዳቶች ተጋላጭ እየሆኑ መምጣቱ ውሎ ያደረ ጉዳይ ሆኗል። በርካታ ወጣቶች በበርሃ ጉዞ ላይ በረሃብና በአሰቃቂ ችግር ውስጥ ለህልፈት እየተዳረጉና በጀልባ ሀገር አቋርጠው ሲጓዙ በውሃ እየተወሰዱ ሲሞቱ ይታያል።
በዋናነትም በኢትዮጵያ 29 ፍልሰት የሚበዛባቸው ዞኖች፣ 14 የድንበር መውጫ በሮች፣ 135 መተላለፊያ ሥፍራዎች መኖራቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ ብለዋል። በዚህም ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ትግራይ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና ሲዳማ ክልሎች ከፍተኛ ኢ-መደበኛ ፍልሰት የሚከናወንባቸው አካባቢዎች መሆናቸው ጠቅሰዋል::
መስመሩ ከኢትዮጵያ ደቡብ ክልል – ታንዛኒያ- ደቡብ አፍሪካ፤ በመተማ – ሱዳን – ሊቢያ – ጣሊያን – አውሮፓ ነው ሲሉ የጸደቀን (ዶ/ር) ሐሳብ የሚያጠናክሩት ደግሞ ረዳት ፕሮፌሰር መሐመድ ናቸው:: እነዚህ መስመሮች በአፋር – ጅቡቲ- የመን – ሳዑዲ አረቢያ፤ ሲሆን፣ የከፋ ጉዳት የሚመዘገበው በመተማ – ሱዳን – ሊቢያ – ጣሊያን- አውሮፓ ነው ይላሉ:: ለሚያጋጥመው ዋና ጉዳት ምክንያቱ የሚታለፉባቸው ቦታዎች የጦርነት ቀጣና የሆኑ እና የባሕር ላይ ጉዞ ያለው በመሆኑ እንደሆነ ያስረዳሉ::
ጸደቀ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ መደበኛ ባልሆነ መልኩ የሚካሄድ ፍልሰት በቀዳሚነት ለጉልበት ብዝበዛ የሚዳርግ እንደሆነ ይገልጻሉ። እንደምሳሌ የሚጠቅሱት ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የሚሔዱ ተጓዦች ታንዛንያ ላይ የሚያጋጥማቸውን ችግር ነው። የታንዛንያን ድንበር ረግጦ የተያዘ ወጣት ለሶስት ዓመታት እስር ቤት የሚቆይ ይሆናል ይላሉ።
በዚያ አካባቢ እስር ቤት መግባት ማለት እንዲያው ለመቆያነት ብቻ ሳይሆን የሚፈለገው፤ ጊዜውን በጉልበት ሥራ እንዲያሳልፍም ጭምር እንደሆነ ያመለክታሉ:: እስረኞቹ በግንባታና በእርሻ ሥራ እንዲሰማሩ ይደረጋል። የሚሠሩበትም ሥራ በአብዛኛው ከአቅማቸው በላይ የሆነ ነው።
ሌላው ፍቃዱ አዱኛ (ዶ/ር) እና ተካልኝ አያሌው (ዶ/ር) የተባሉ ተመራማሪዎች “የስደት ኢንዱስትሪን በኢትዮጵያ መረዳት” በሚል ርዕስ ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ የዓለም አቀፍ ፍልሰት ማዕከል ነች። ሀገሪቱ የዓለም አቀፍ ስደተኞች ምንጭ፣ መሸጋገሪያ እና መድረሻ በመሆኗ በጣም አስፈላጊ ነች። በተለይም እ.ኤ.አ. በ2017 የጥናት መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ከኢትዮጵያ በየዓመቱ የሚሰደዱ ከ500 ሺህ እስከ 600 ሺህ የሚገመት ሲሆን፣ ከነዚህም ውስጥ ከ60 እስከ 70 በመቶ የሚሆኑት መደበኛ ያልሆኑ የባሕር መንገዶችን እና ኔትወርክን የሚጠቀሙ ስደተኞች ናቸው።
በእዚህም በኢትዮጵያ መደበኛ ያልሆነ ስደትን የሚጠቀሙ ሰዎች የሚሄዱባቸው ሶስት ዋና ዋና የምድር ላይ መስመሮች ወይም መንገዶች አሉ። እነዚህም አንደኛ የምስራቁ መስመር ሲሆን፣ ይህም ወደ መካከለኛው ምስራቅ እና ወደ ባሕረ ሰላጤው ሀገራት ለመሄድ የሚጠቀሙበት መስመር ነው ይላሉ። ሁለተኛው በተለምዶ የደቡባዊ መስመር የሚባል ሲሆን፣ ይህም ሕገ ወጥ ስደተኞች ወደ ደቡብ አፍሪካ ሪፐብሊክ ለመሄድ የሚከተሉት መንገድ ነው። የመጨረሻ ባይሆንም ሶስተኛው የሰሜን – ምዕራብ መስመር በመባል ይታወቃል። ይህ መንገድ ወይም መስመር ሕገ ወጥ ስደተኞቹ ወደ ሱዳን – ሊቢያ/ግብፅ – አውሮፓ ለመግባት የሚጠቀሙበት መስመር ነው።
በሕገ ወጥ መልኩ የምስራቁን መስመር ተጠቅመው ወደ መካከለኛው ምስራቅ እና የባሕረ ሰላጤው ሀገራት የሚሰደዱ ፍልሰተኞች አብዛኞቹ ወጣት ሴቶች ናቸው። እ.ኤ.አ. በ2009 እና 2012 መካከል 387 ሺህ 061 ወደ ባሕረ ሰላጤው የተመዘገቡ መደበኛ የጉልበት ስደተኞች ነበሩ። አብዛኛዎች ደግሞ ዝቅተኛ የትምህርት ደረጃ ያላቸው ሴቶች ናቸው።
በተቃራኒው የደቡባዊ መስመርን ይዘው ወደ ደቡብ አፍሪካ በሕገ ወጥ መልኩ የሚሰደዱ ሰዎች በዋናነት የሚፈልሱት ከሀዲያ እና ከከምባታ ዞኖች ነው። ከእነዚህ ሕገ ወጥ ስደተኞች መካከል አብዛኛው ወጣቶች ናቸው። ዓለም አቀፉ የስደተኞች ተቋም (አይ.ኦ.ኤም) እ.ኤ.አ. በ2009 ባደረገው ጥናት ባስቀመጠው ግምት ከ17 ሺህ እስከ 20 ሺህ የሚሆኑ የአፍሪካ ቀንድ ስደተኞች በየዓመቱ ወደ ደቡብ አፍሪካ ይሰደዳሉ ብሏል::
እንደ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (ዩ.ኤን.ኤች.ሲ.አር) ገለፃ ደግሞ፤ ከ50 እስከ 100 ኢትዮጵያውያን ሕጋዊ ያልሆኑ ሰዎች በየቀኑ ወደ ሱዳን ይሻገራሉ። ይህ የሚያመለክተው ከ18 ሺህ እስከ 37 ሺህ ኢትዮጵያውያን በየዓመቱ በመተማ በኩል ወደ ሱዳን እንደሚሰደዱ ነው። እ.ኤ.አ. በ2015 በግምት 154 ሺህ ስደተኞች በማዕከላዊ ሜዲትራኒያን ባሕር አቋርጠው ወደ አውሮፓ የገቡ ሲሆን፣ አብዛኞቹ ከኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ እና ኤርትራ በሕገ ወጥ መልኩ የሄዱ ናቸው።
ዜጎች ከላይ የተጠቀሱትን መንገዶች ወይም መስመሮች ይዘው ሲሄዱ በውስጣቸው በተለያየ ስም የሚጠሩ ብዙ ሕገ ወጥ ሰዎች አሉ። እነዚህም በውስጡ የሚሳተፉ ባለስልጣናት እና ባለሃብትን ሳይጨምር በመደበኛነት ሥራውን የሚሠሩ ሰዎች ለቃሚ (ቀጣሪ)፣ ደላላ ፣ ድንበር አሻጋሪ፣ እና ሃዋላ ሰሪ ይባላሉ። ለቃሚ ወይም ቀጣሪ ከመነሻ የሚያስተባብር እና ሰዎች እንዲሰደዱ የሚያነሳሳ ነው። ሕገ ወጥ መንገዶቹ “ጥሩ” መሆናቸውን፣ ለውጥ በአጭር ጊዜ ማምጣት እንደሚችሉ የሚያግባባ ነው። ደላላ ደግሞ ከቀጣሪ የተቀበላቸውን ሕገ ወጥ ስደተኞች ይዞ ድንበር ድረስ የሚያሻግር ነው። ደላላው ድንበር ከደረሰ በኋላ ለድንበር አሻጋሪ ደላላ ወይም አሻጋሪ ለሚባል ያስረክባል። አሻጋሪም ሕገ ወጥ ስደተኞችን ተቀብሎ በመውሰድ ኢ-መደበኛ የገንዘብ ማስተላለፊያ ወኪሎች በጋራ በመሆን ይሠራል። እነዚህ ተዋናዮች የተለያዩ የስደት አገልግሎቶችን ይሰጣሉ::
ጉዲና (ዶ/ር)፣ እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ድንበሮች ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የሰዎች መፍለስ፣ ከሀገር መውጣትና ዝውውሮች ይካሄዳሉ:: ለምሳሌ በሞያሌ በኩል ኬንያ- አድርጎ ወደ ታንዛኒያና ደቡብ አፍሪካ የሚወስድ በር አለ:: በሐረር በኩል አድርጎ ወደ ሱማሌ ላንድ የሚወስድ በር ያለ ሲሆን፣ በተጨማሪም በሱማሌ ክልል በደወሌ- ጊርሌ – ጅቡቲ የሚወስድ መስመርም የሚጠቀስ ነው:: እንዲሁም በምዕራብ በኩል በሁመራ – በጋምቤላ – ሱዳን በኩል አድርጎ የሚሄዱበት ሌላኛው በር ነው:: በደቡብ ሱዳንም በተመሳሳይ የሚሄዱ እንዳሉ ተጠቃሽ ነው::
በብዙ አቅጣጫዎች መደበኛ ባልሆነ መንገድ ሰዎች እንደሚፈልሱ ጠቅሰው፤ ለአብነትም ከሰሜን ተነስቶ በአዲስ አበባ በኩል አድርጎ በሞያሌ – በኬንያ – ታዛኒያ እስከ ደቡብ አፍሪካ ድረስ የሚሄዱ ረጅም ሰንሰለቶች ያሏቸው መስመሮች እንዳሉ ያስረዳሉ::
በሱዳን በኩልም ከደቡብ ኢትዮጵያ በመነሳት መሀል ሀገርን በማቋረጥ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ በመጓዝ ወደ ሱዳን – ሊቢያ – ከዚያም የሊቢያን በረሃ የሚሻገሩ ዜጎች አሉ ሲሉ ይናገራሉ:: እናም በምስራቅ በኩል ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ወጥተው በምስራቁ የኢትዮጵያ ክፍል አድርገው በጅቡቲ አድርገው ወደ አረብ ሀገራት የሚሄዱ ዜጎች በርካታ እንደሆኑ ምሁራኑ ያስረዳሉ::
ስለሆነም ጉዳዩ ሲታይ ረጅም የሆነ ሰንሰለት ያለው ሕጋዊ ያልሆነ የሰዎች ዝውውር መኖሩን በግል የሚያመላክት ነው:: ሲዘዋወሩም አንድ ሁለት ሰው ሆነው ሳይሆን በቡድን ተደራጅተው 10 እና ከዚያ በላይ ሆነው ነው:: በሌላ በኩል ድንበር ላይ ተከማችተው በአንድ ላይ ሆነው በጋራ የሚወጡበት ሁኔታ አለ:: በየቀኑ የሚወጣው ሰው ቢደመር በብዙ ሺህ ማለትም ወደ መቶ ሺህ የሚጠጉ ዜጎች በዓመታት ከሀገር ወደ ውጭ በሕገ ወጥ መንገድ የሚፈልሱ እንደሚኖሩ ይገመታል ብለዋል::
በከንባታና ሀዲያ በኩል ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚሄዱበት አጋጣሚ አለ ይላሉ:: በሱዳን በሊቢያ በኩል እንዲሁ ብዙዎች መዳረሻቸውን አውሮፓ ለማድረግ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በየዓመቱ ይሰደዳሉ:: በቅርብ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው፤ አምና (እንደ አ.ኤ.አ 2024) ከጥር ወር እስከ ነሐሴ ወር ብቻ 160 ሺህ 685 ኢትዮጵያውያን በተለያየ አቅጣጫ እንደተሰደዱ ያሳያል:: ሌሎችም በግምት ይህ ቁጥር እስከ 200 ሺህ እንደሚሻገርም ይጠቅሳሉ::
የምርመራ ቡድኑ፣ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የተሰደደን ወጣት አሕመድ ሙሐመድን ባነጋገረበት ወቅት ወጣቱ እንደጠቀሰው፤ ነዋሪነቱ ደቡብ ወሎ ሀይቅ አካባቢ ነው:: ስደትን አሀዱ ብሎ የጀመረው በ2004 ዓ.ም ሲሆን፣ ለስደት የዳረገው ሥራ አጥነት ነው:: ስደትን መርጦ ይሒድ እንጂ እንዳሰበው አልተሳካለትም:: እንዲያውም እንግልቱና ስቃዩ የበረታ በመሆኑ ከፍተኛ የሆነ የጨጓራ እና የኩላሊት ሕመም አጋጥሞታል::
ወጣት አሕመድ ከሀገር የወጣው ለመጀመሪያ ጊዜ በሱማሌ ክልል ባለው መስመር ነው:: ሰባት ጊዜ ከሀገር ወጥቶ ሕገ ወጥ በሚል በሳዑዲ አረቢያ እስር ቤት አንድ ዓመት ከአምስት ወር እንደቆየ በኢትዮጵያ መንግሥት ጥረት ወደ ሀገሩ ተመልሷል:: ሰባት ጊዜ የተመላለሰው መንግሥት ከስቃዩ ሊያሳርፈው ሲመልሰው፤ እርሱ እንደገና ተመልሶ ከሀገር ሲወጣ በተደረገ ምልልስ ነው:: ከዓረብ ሀገር ወደ እናት ሀገሩ የተመለሰው በኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው:: ሀገር ጥሎ ሲወጣ ግን በበረሀ በእግር አቆራርጦ በደላሎች እየተመራ ነው:: በኢ-መደበኛ ፍልሰት ከሀገራቸው ወጥተው ካለፈላቸው ይልቅ፤ ያለፈባቸው ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ ነው::
ስደትን መቀነስ ይቻላል ወይ? ከተባለ ይከብዳል፤ ምክንያቱም መቀመጫውን ኢትዮጵያ ውስጥ ያደረገ ሰብሳቢ ያለ ሲሆን፣ የመን፣ ጅቡቲና ሳዑዲ አረቢያ ላይ ተቀባይ ደላሎች አሉ:: ለምሳሌ በመቶ ሺህ ብር እስከ ድንበር ያሳልፏቸውና ድንበር ላይ ሲደርሱ 50 ሺህ ብር ይጨምራሉ:: ከተከፈለም በኋላ ሌላ ተጨማሪ ብር ይጠይቃሉ፤ መክፈል ካልተቻለ ሩህሩህ ናቸው የተባሉት አካለ ጎደሎ ሲያደርጉ፤ ጨካኞች ደግሞ ሕይወትን እስከማጥፋት ይደርሳሉ ሲል ይናገራል::
እርሱ፣ በሰባተኛው ዙር ከሀገሩ ሲወጣ 700 ሺህ ብር ጨርሷል:: የመጀመሪያ ስደት ስድስት ሺህ የሳዑዲ ሪያል ሲሆን፣ አሁን ላይ 15 ሺህ ሪያል ድረስ ይጠየቃል:: ሕይወትን ለመቀየር ሲባል ክቡር የሆነው ሕይወት እየጠፋ ነው:: ወጣቱ እየተጓዘ ማለቁ ነው:: እርሱም አካሉ አልጎደለም እንጂ ውስጡ ጎደሎ ሆኗል::
በቅርቡ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሀገራቸው ከተመለሱት ዜጎች መካከል ወጣት ሰይድ ጌታሁን አንዱ ነው፤ ወጣቱ፣ አማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን፣ መርሳ ከተማ መሀል አምባ ወይም ሊሊበር አካባቢ ነዋሪ ነው:: ቤተሰቡ ላሏቸው ስድስት ልጆች ያላቸውን እርሻ አከፋፈሉ። ይሁንና እርሱ የደረሰው አነስተኛ በመሆኑ መሬት በኮንትራት እየወሰደ ቢያርስም ውጤታማ መሆን አልቻለም:: ከግብርና ውጭ ሌላ የሥራ እድል አማራጭ ስለማይኖረውም ከሀገር ወጥቶ መሞከርን አሰበ:: ስለዚህም ስደትን ምርጫው በማድረጉ ጉዞውን በኢ-መደበኛ መንገድ አደረገ::
የመረጠውም መስመር አፋር ነው:: በዚያ በአፋር ክልል ያለው መስመር በውሃ ልማት አድርጎ ዴችአቶን ተከትሎ በጋላፊ በኩል መጀመሪያ ጂቡቲ የሚገባበት ነው::
ወጣቱ፣ ውሃ ልማት የሚባል ቦታ ከሰመራ በግምት 70 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኘው ስፍራ በደላላ አማካይነት ማቅናቱን ይናገራል:: በዚህ ስፍራ ፖሊስ ጣቢያ መኖሩን የተመለከተ ሲሆን፣ ፖሊሶችም በኢ- መደበኛ መንገድ ዜጎች እንደሚወጡ ያውቃሉ ይላል:: በዚያ መስመር ፖሊሶችም ጭምር የደላሎች ተባባሪ ናቸው ሲል ያየውን ይናገራል:: ፖሊሶቹን በማየቱም ጉዞው ሕጋዊ እንደሆነ መረዳቱን ያመለክታል:: ይህ በመሆኑም የልብ ልብ እንደተሰማውም ይገልጻል::
የኢ-መደበኛ ፍልሰት እንግልትና ስቃዩ የሚጀምረው በሀገር ውስጥ ነው የሚለው ወጣቱ፤ ከሰመራ ወደ ውሃ ልማት ጉዞ ሲጀመር በአንድ ባጃጅ ላይ እርሱን ጨምሮ 14 ሰዎች መጫናቸውን ያስታውሳል:: ከ14ቱ መካከልም ብዙዎቹ ሴቶች መሆናቸውን ያስረዳል:: ከውሃ ልማት እልፍ ሲባል ደግሞ ዲችኤቶ የሚባለውን ስፍራ እንዳዩ የሚገልጸው ወጣቱ፤ ብዙ ኪሎ ሜትሮችን እንደተጓዙ የጅቡቲና የኢትዮጵያ ድንበር መድረሳቸውንና ከዚያም ጅቡቲ መግባቱን ይናገራል::
እርሱ እንደሚለው፤ በወቅቱ ቁጥራቸው 835 ነው፤ የተወሰነ መንገድ በእግር ተጉዘዋል:: ጉዟቸው ደግሞ ቀንም ሌሊትም ጭምር ነው:: በእግር ጉዞው ብዙ ሰው ስለሚደክም መጓዝ ያቅተዋል:: መንገድ የሚመሩ ደላሎች ደግሞ በየተወሰነ ጊዜ ውስጥ “ሰው ወደ ኋላ ቀርቷል፤ ቁሙ” ይላሉ። ለአፍታ በሚቆምበት ጊዜ ደግሞ ሰው ከድካሙ የተነሳ ባረፈበት ቦታ ይተኛል። እንቅልፍ ሰለሚጥላቸው ካሉበት ሳይነሱ እዚያ ይቀራሉ:: ጨለማ ስለሚሆን እንቅልፍ አሸንፎት የቀረውን ለማየት ይከብዳል:: የቀረው ሰው ደግሞ በዚያው እስከወዲያኛው ያሸልባል እንጂ በሕይወት የመኖር እድል አይኖረውም::
በዚያ መስመር ጉዞ ከጀመሩት ከ835ቱ ውስጥ ሲቆጠር 16 ሰው መቅረቱን የሚናገረው ወጣቱ፣ እነርሱ የት እንደገቡ አይታወቅም ይላል። ምክንያቱም የሚጓዙበት መስመር ከበረሃማነቱ የተነሳ ጉዞው ከባድ ነው፤ ውሃ ጥሙም አይጣል ነው ሲል ያስረዳል:: ከአፋር ክልል፤ ውሃ ልማት ተብላ ከምትጠራው ስፍራ ጅቡቲ ወደብ ለመድረስ 13 ቀን እንደፈጀባቸው የሚናገረው ወጣት ሰይድ፤ ወደ ጅቡቲ ድንበር ሲገባ ስቃዩ ይጨምራል። የተያዘው ብር ያልቃል። የሚበላና የሚጠጣ ነገር ይጠፋል ይላል።
ታጁራ የምትባል የጅቡቲ ከተማ ሲደርሱ አንድ ተራራ ሥር ይሰበሰባሉ:: በስፍራው ምግብ የለም፤ ውሃ የለም፤ ብቻ የሚቀመስ የሚላስ ይሉት ነገር አይገኝም በማለት ይናገራል:: በተለያየ ምክንያት የተበታተነውና ችግር ያጋጠመው ስደተኛ የት እንደደረሰ ስላልታወቀ ደላላው የቀሩትን ሰብስቦ ‘ሀዩ’ የሚባል የወደብ ከተማ እንደወሰዳቸው የሚገልጸው ሰይድ፣ እዚያም ሁለት ቀን ካደሩ በኋላ፤ በጀልባ ተጭነው በ45 ደቂቃ ውስጥ የመን ድንበር መድረሳቸውን ያብራራል::
የመን ከገቡ በኋላ የየመን ፖሊሶች ተቀብለው ወደ ጫካ ገለል እንዳደረጓቸውና የማለፊያ ክፈሉ እንደተባሉ ይናገራል። እህቱ ሳዑዲ ስለምትኖር 80 ሺህ ብሩን ከፍሎ የመንና ሳዑዲ ድንበር ወደሆነው ‘ራጎ’ ወደተባለ ቦታ በሚኒባስ እስከ 45 ሰው ተጭነው መድረሳቸውን ያስረዳል:: ስፍራው ልክ የተለያየ ሸቀጣሸቀጥ የሚሸጥበትን መርካቶ ገበያን ይመስላል የሚለው ወጣቱ፤ እዚያ የሚሸጠው ግን እንደመርካቶ ሸቀጥ ሳይሆን የሰው ልጅ ነው ሲል ይናገራል:: ሰው እንደ እንስሳ የሚሸጥበት ስፍራ ‘አውሽ’ የሚባል እንደሆነም ጠቅሶ፤ ቦታውም የደላሎች ሰፈር እንደሚባልና ደላሎች እያንዳንዱን ሰው ገንዘብ እያስላኩ፤ ለድንበር መቁረጫ ሁለት ሺህ ሪያል (በወቅቱ ምንዛሬ ወደ60 ሺህ ብር) እንደሚያስከፍሉ ያለፈበትን ስቃይና መከራ ያስረዳል፤ እርሱም የተቆረጠውን የብር መጠን መክፈሉን እንደከፈለ ያመለክታል::
ወድ አንባቢያን በነገው ዕለትም ክፍል ሁለት የሚቀጥል ይሆናል::
በኢፕድ የምርመራ ቡድን
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 5 ቀን 2017 ዓ.ም