የቦክስ ክለቦች ውድድር በታሪካዊቷ ከተማ እየተካሄደ ነው

አራተኛው ዙር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቦክስ ክለቦች ማጠቃለያ ውድድር በጎንደር ከተማ እየተካሄደ ነው። አራተኛ ቀኑን በያዘው የቦክስ ውድድር በተለያዩ ኪሎ ግራሞች የተለያዩ የቡጢ ፍልሚያዎች እየተካሄዱ ሲሆን ውድድሩ እስከ ሐምሌ 10/2017 ዓ.ም እንደሚቀጥል ታውቋል።

በውድድሩ ሰባት ክለቦች በዋናነት የሚሳተፉ ሲሆን፣ አንድ ተጋባዥ ቡድንን ጨምሮ በድምሩ ስምንት ቡድኖች እየተሳተፉበት ነው።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ከኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር ያዘጋጁት 4ኛው ዙር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቦክስ ክለቦች ማጠናቀቂያ ውድድርን በተመለከተ ከቀናት በፊት አዘጋጆቹ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ማሩ መሐመድ እንደገለፁት፣ የቀድሞውን የከተማዋ ቦክስ ስፖርት በማጠናከር ውጤታማ ስፖርተኞችን ለማፍራትና የከተማዋን የልማት እንቅስቃሴ ለማስተዋወቅ በሚካሄደው ውድድር የስፖርት ወዳዱ ማኅበረሰብ በመገኘት የቦክስ ስፖርተኞቻችን እንዲያበረታታ ጠይቀዋል። የቦክስ ስፖርት በታሪካዊቷ ከተማ ተጠናክሮ መካሄድ እንዲችል አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉም ተጠቁሟል።

የብሔራዊ ቦክስ ክለቦች ውድድር በውድድር ዓመቱ በተለያዩ አራት ዙሮች የሚካሄድ ሲሆን፣ ሦስተኛው ዙር ውድድር የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ከ ቃና ቴሌቪዥን ጋር በጋራ በመሆን ከግንቦት 12 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ መካሄዱ ይታወሳል።

ለአራት ተከታታይ ቀናት በተካሄደው ሦስተኛው ዙር ውድድር በዚህ ዓመት የተቋቋመው ዩናይትድ ስዊት ቦክስ ክለብን ጨምሮ በርካታ ክለቦች ተፎካካሪ ነበሩ። አዲስ አበባ ፖሊስ ቦክስ ስፖርት ክለብ፣ ኦሜድላ ቦክስ ስፖርት ክለብ፣ ፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ቦክስ ስፖርት ክለብ፣ ድሬዳዋ ከነማ ቦክስ ስፖርት ክለብ፣ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ቦክስ ቡድን፤ ፋሲል ከነማ ስፖርት ክለብ፣ ደሴ ቦክስ ቡድን፣ ሀዲያ ቦክስ ቡድን፣ ደቡብ ኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ጋሞታ ቦክስ ስፖርት ክለብ ተሳታፊ በነበሩበት የሦስተኛው ዙር ውድድር በተለያዩ ኪሎ ግራሞች የተካሄዱ የቡጢ ፍልሚያዎች በ “ኤ” እና በ “ቢ” ተከፍለው ተከናውነዋል።

በርካታ ጠንካራ ተወዳዳሪ ክለቦች በተሳተፉበት ውድድር የአዲስ አበባ ፖሊስ ቦክስ ክለብ በ “ኤ” ምድብ በተደረጉት የቡጢ ፍልሚያዎች በበላይነት በማጠናቀቅ የተዘጋጀውን ዋንጫ ማሸነፍ ችሏል። በ “ቢ” ምድብ የተዘጋጀውን ዋንጫ ደግሞ አዲስ የተቋቋመው ዩናይትድ ስዊት ቦክስ ክለብ በመጀመሪያ ውድድሩ ዋንጫውን ከፍ ማድረግ ችሏል። በሴቶች የተዘጋጀውን ዋንጫ ደግሞ የድሬዳዋ ከተማ ቦክስ ክለብ አሸናፊ መሆን እንደቻለ ይታወሳል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You