የዛሬ የስኬት ዓምድ እንግዳችን ረዥም ዓመታትን በመማር ቢያሳልፉም፤ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ንግድ ያዋጣል በሚል የንግዱን ዓለም የተቀላቀሉ ናቸው:: ነጋዴ ስለሚነግደው ዕቃ በሚገባ ማወቅ አለበት የሚል ፅኑ ዕምነት አላቸው:: አቶ ጊዜህነው ፈንታው ይባላሉ:: የፐልስ ጀነራል ቢዝነስ ካምፓኒ ባለቤት ናቸው:: ተወልደው ያደጉት ደሴ ከተማ ውስጥ ሲሆን፤ ትምህርታቸውን እዛው ደሴ ወይዘሮ ስህን የቴክኒክ እና ሙያ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል:: የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ከአዳማ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል:: በተለያዩ ኮሌጆች ለሁለት ዓመታት ካስተማሩ በኋላ፤ ማስተማራቸውን ትተው ወደ ንግድ ሥራ ገቡ::
‹‹ሕይወት በታሰበባት መንገድ እንደገመቷት አትቀጥልም::›› የሚሉት አቶ ጊዜህነው፤ ወደ ንግድ የገቡበትን አጋጣሚ ሲያስታውሱ፤ ከማስተማር ጎን ለጎን ኤክስሬ እና አልትራሳውንድ የመሳሰሉ የሕክምና መሳሪያዎችን የመጠገን ሥራ ያከናውኑ ነበር:: ጎን ለጎን የሚሠሩት ይህ ሥራ ከነጋዴዎች ጋር እንዲገናኙ ምክንያት ሆነ:: ግንኙነታቸውን ተከትሎ ወደ ንግድ ሥራ ገብተው መሥራትን መረጡ::
አቶ ጊዜህነው ለመነገድ ሲነሱ ከእሳቸው ሞያ ጋር የተገናኘውን እና ሰፊ ገበያ ይኖረዋል ብለው ያመኑበትን ቁሳቁስ ለመሸጥ አሰቡ:: በጥናት ላይ ተመርኩዘው ለትምህርት ቤት የሚሆኑ ለምሳሌ የመካኒካል ኢንጂነሪንግ ተማሪዎች የሚማሩባቸው ዕቃዎች ለማቅረብ ወሰኑ:: ይሁንና ዕቃው ከመርካቶ ተገዝቶ የሚሸጥ አይደለም:: ዕውቀት እና ጥናትን የሚጠይቅ መሣሪያ በመሆኑ ከየት እና በምን ዓይነት መንገድ ማምጣት እና መሸጥ እንደሚችሉ አጠኑ::
በጥናታቸው መሠረት ከተለያዩ የውጭ ሀገራት አምጥተው መሸጥ የጀመሩት አቶ ጊዜህነው፤ ኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ሲማሩ ይጠቀሙባቸው የነበሩ እና እሳቸው የሚያውቋቸውን መሳሪያዎች በመሸጥ የጀመሩት ሥራ፤ አሁን አድጎ ድርጅት እስከ መመስረት ዘለቀ:: በዚህ መልኩ የተመሰረተው ድርጅት ከተቋቋመ 16 ዓመታትን አስቆጥሯል::
አቶ ጊዜህነው ንግድ የጀመሩበት ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት በብዛት ዩኒቨርሲቲዎችን ሲያስፋፋ የነበረበት ጊዜ ነበር:: እሳቸው እንደሚገልጹት፤ ዩኒቨርሲቲዎቹ ደግሞ ከሕንፃ ውጪ ባዶ በመሆናቸው የገበያው ፍላጎት ሰፊ መሆኑን አወቁ:: ይህም ገበያው በጣም ጥሩ እንዲሆንላቸው ምክንያት ሆነ:: በጀመሩት ፍጥነት ለማደግ ምቹ ሁኔታ ተፈጠረላቸው::
‹‹አሁንም ፍላጎቱ አላቆመም:: ምክንያቱም ዩኒቨርሲቲዎቹ አሁንም ድረስ የማስተማሪያ ቁሳቁስ ጉድለት አለባቸው::›› ሲሉ የሚናገሩት አቶ ጊዜህነው፤ ይህ ሥራ አሁንም አዋጭ ሆኖላቸው እያከናወኑት ነው::
እሳቸው እንደሚገልጹት፤ የእሳቸው ሥራ የትምህርት መማሪያ መሳሪያዎችን ከውጭ አስመጥቶ መሸጥ ብቻ አይደለም:: እየቆዩ ሲሄዱ ምንም እንኳ ንግዳቸው በፈለጉት መንገድ ቢቀጥልላቸውም ጎን ለጎን ሌላ ነገር መሥራት ጀምረዋል:: በሀገሪቷ የገጠር አካባቢዎች ነዋሪዎች የመጠጥ ውሃን በቅርበት እንዲያገኙ ታስቦ የሚካሄዱ ቁፋሮዎች በሳይንሳዊ መሳሪያ የተደገፉ አለመሆናቸውን ተረዱ:: ለዚህም መፍትሄ ይሆን ዘንድ የከርሰ ምድር ውሃ መኖር አለመኖሩን መለየት የሚያስችል ማሽን ለማስመጣት ጥናት አካሄዱ:: ጥናት ላይ ተመሥርተው ከስውዲን እና ከስፔን ኤ ፒ ኤም የተሰኘ ከመሬት በታች ያለውን ውሃ ለይቶ የሚያውቅ ማሽን ማስመጣት ጀመሩ::
‹‹ከመሬት በላይ ያለው ውሃ በቀላሉ ይገኛል:: ከመሬት በታች ያለውን የውሃ ሃብት ለማግኘት ግን ቁፋሮ ከመካሄዱ በፊት መጠናት አለበት:: ይሁንና በብዛት የሚሠራው በጥናት ሳይሆን በልምድ ነው::›› የሚሉት አቶ ጊዜህነው፤ ያለ መሳሪያ እርዳታ በልምድ ብቻ በመመስረት መሥራት ወይም ትክክለኛ መረጃ ላይ ያልተመሠረተ ሥራ ሲሠራ ቁፋሮ አክሳሪ እንደሆነ ያብራራሉ::
የታዘቡትን እና የሚፈጠር ችግርን እንዲሁም እርሳቸው ይዘው የመጡትን ማሽን በተመለከተ ሲናገሩ፤ አነስተኛ ውሃ ለማግኘት በሚሊየን የሚያስወጣ ቁፋሮ ማከናወን አዋጭ አለመሆኑን በመጠቆም፤ ለሚገኘው ውስን ውሃ ምን ያህል የቁፋሮ ወጪ ማውጣት ያዋጣል? የሚለውን ለመለየት እና ለሌሎችም ለሚወሰኑ ውሳኔዎች ማረጋገጫ የሚሠጥ ማሽን መጠቀም የግድ ነው ይላሉ:: ሆኖም ግን ብዙዎች ይህንን በማድረግ በኩል ክፍተት አለባቸው::
ውሃ ማውጣት ብቻ ሳይሆን በመንገድ ግንባታ ላይ ሳይቀር የሚካሄዱ ቁፋሮዎች ከመካሔዳቸው በፊት የውሃ መስመር አስቀድሞ በመንገዱ መዘርጋት አለመዘርጋቱ የሚታወቅበት ሁኔታ ባለመኖሩ፤ ቁፋሮዎች ሲካሔዱ የውሃ መስመሮች የሚፈነዱ መሆናቸውን እና ከባድ ጉዳት እንደሚያስከትልም ገልፀዋል::
ቁፋሮ ከመካሄዱ በፊት ውሃ አለ የለም? የሚለውን ከማረጋገጥ በተጨማሪ ውሃ በምን ያህል ርቀት እና በምን ያህል መጠን እንዳለ እያስመጡት ያለው ማሽን የሚያሳይ መሆኑንም ያመለክታሉ:: ማሽኑ በኢትዮጵያ ብዙ አይታወቅም ያሉት አቶ ጊዜህነው፤ ሕብረተሰቡ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለመላመድ ጊዜ የሚፈልግ መሆኑን ጠቅሰዋል:: አሁን ማሽኑን ማስገባት ከጀመሩ አምስት ዓመት ያስቆጠሩ ሲሆን ሲጀምሩ ከነበረው ፍላጎት አንጻር ገበያው እያደገ መሆኑን እንዳስተዋሉ አመልክተዋል::
አስቀድሞ ትክክለኛ መረጃ ይዞ ወደ ሥራ ለመግባት የሚፈልግ የመንግሥትም ሆነ የሕዝብ ሃብት እንዳይባክን የሚሻ አካል፤ ማሽኑን እንደሚገዛ በመጠቆም፤ ካምፓኒያቸው የከርሰ ምድር የውሃ መመርመሪያ ማሽኖችን የሚያቀርበው ውሃ ለሚያወጡ ብቻ ሳይሆን የፎቅ ግንባታ ለሚያከናውኑና መሬትን በጥልቀት ለሚቆፍሩ አካላት ጭምር መሆኑን ጠቅሰው፤ ተቋራጮች የሕንፃ መሠረት ከማውጣታቸው በፊት መሬቱ መጠናት አለበት:: መሬቱ ውሃ አለው የለውም? የሚሉትን ጥያቄዎች ብቻ ሳይሆን በማሽኑ የመሬት መንቀጥቀጥ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት ለመቋቋም በሚያስችል መልኩ ሕንፃዎችን ለመገንባት ማሽኑ መረጃ እንደሚሰጥ አመላክተዋል::
የውሃ ቢሮዎች እና የመንግሥት ተቋማት ቢገዙም፤ ማሽኖቹ እጅግ በጣም ውድ ገበያው ደግሞ ከብዙ ጊዜ አንድ ጊዜ የሚገኝ በመሆኑ ሙሉ ለሙሉ በዚህ ሥራ ላይ ብቻ እንደማይገደቡ እና አሁንም ለማስተማሪያ የሚሆኑ ማሽኖችን በማምጣት ሽያጫቸውን እንደሚቀጥሉ ይናገራሉ::
ጂኦፊዚክስ ሰፊ ጉዳይ መሆኑን እንዲሁም ማሽኑ የጂኦፊዚክስ ሥራዎችን እንደሚያከናውን አስታውሰው፤ ይሁንና ከጂኦ ፊዚክስ ሳይንስ አንፃር ኢትዮጵያ ውስጥ ገና ምንም አልተሠራም ብለዋል:: ሆኖም ጅምሮች መኖራቸውን መካድ አይቻልም ሲሉ ተናግረዋል::
ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር ተያይዞ አቶ ጊዜህነው እንደሚገልፁት፤ መጀመሪያ ማሽኑን በሚጠቀሙ ሰዎች ዙሪያ ግራ መጋባት እንዳይኖር የሚመጣው ዕቃ ምንድን ነው? የሚለውን ማወቅ ብቻ ሳይሆን ስድስት ሠው ቀጥረው በማሰልጠን የዕውቀት ሽግግር አድርገዋል:: እያንዳንዱ ፕሮጀክት ላይ ከአሥር እስከ አስራ አምስት ሰው ጊዜያዊ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ሲሆን፤ ከእሳቸው ጋር ከሚሠሩ ሠራተኞች በተጨማሪ ሌሎችን በማሠልጠን የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ላይ ናቸው::
ለአብነት አንድ ዕቃ ዩኒቨርሲቲ ሲገባ፤ ስልጠና ይሠጣሉ:: የሠለጠኑ ሰዎች ማሽኑን ከመጠቀም በተጨማሪ ሌሎችን ያሠለጥናሉ:: ከዛ አንፃር ብዙዎች የራሳቸውን ገቢ የሚያገኙበት ዕድልም ይፈጠራል:: ከኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን አንዳንዴ ከሌሎች ሀገሮች ለአብነት ከኬኒያም ሠው በመቅጠር እያሠሩ መሆኑን በመጠቆም፤ መሳሪያውን ማስመጣት ብክነትን ከመቀነስ በተጨማሪ ለቴክኖሎጂ ዕውቀት ሽግግርም የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ነው:: የዕውቀት ሽግግሩም ሰፊ ነው ሲሉ ተናግረዋል::
ይሁንና ውስን አዳዲስ ማሽኖች ሲመጡ ብቻ የውጪ ዜጎችን እንደሚቀጥሩ በመጠቆም፤ ኬኒያዊ የጂኦፊዚክስ ሰው ለማምጣት የተገደዱት፤ አዲስ ዕቃ በማምጣታቸው መሆኑን አመልክተዋል::
እንደእሳቸው ገለፃ፤ ሠራተኛው ሶስት እና አራት ሰዎችን ያሰለጥናል:: ሰልጣኞቹ ደግሞ ሌሎችን ያሠለጥናሉ:: ዕቃው በተሸጠ ቁጥር የሥራ ዕድል የመፈጠር ሁኔታውም ሆነ የእውቀት ሽግግሩ እየቀጠለ ይሔዳል::
‹‹ እኛ በዋናነት ፕሮጀክቱ ምን ይፈልጋል? የሚለውን እናያለን:: የጂኦሎጂ ዕቃ ከሆነ የጂኦሎጂ ዕቃ እናቀርባለን:: ጥናት አናደርግም:: ስለዚህ እቃውን የገዛው አካል ወስዶ ለወደፊት ለመጠቀም ገዢው ራሱ የሚሠራለትን ይቀጥራል:: እኛ ደግሞ እናሠለጥናለን::›› ሲሉ ተናግረዋል:: አሠልጣኞቻቸው ቋሚ ተቀጣሪዎች ሳይሆኑ ዕቃው ሲሸጥ ብቻ የሚያሠለጥኑ መሆናቸውን አስታውሰው፤ በእነሱ አማካኝነት ውጭ ሔደው የሠለጠኑም ብዙ መሆናቸውን አመላክተዋል::
አቶ ጊዜህነው ማኅበረሰቡን ከመርዳት አንፃር አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እና ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ መሳሪያውን የገዙ መሆናቸውን አስታውሰው፤ ዩኒቨርሲቲዎቹ የአካባቢያቸው ማኅበረሰብ ቁፋሮ ከማካሔዱ በፊት በማሽኑ እንዲጠቀሙ እያመቻቹ እንደሚገኙም አመላክተዋል::
ሥራውን ሲጀመሩ የዓመት ሽያጫቸው 500 ሺ ብር አካባቢ መሆኑን አስታውሰው፤ አሁን ላይ በአማካኝ ከ60 እስከ 100 ሚሊየን ብር አካባቢ ሽያጭ ያላቸው መሆኑን ይናገራሉ:: ሲጀምሩ በ100 ሺ ብር የተጀመረ መሆኑን ጠቅሰው፤ አሁን ላይ ካፒታላቸው 25 ሚሊየን ብር አካባቢ የደረሰ መሆኑን የገለፁት አቶ ጊዜህነው፤ ይህ ትልቅ ስኬት ባይባልም መልካም መሆኑን ግን መካድ አይቻልም ይላሉ::
የወደፊት ዕቅዳቸውን አስመልክቶ ሲናገሩ፤ የትም ሀገር ቢሆን ለማምረት ሲታሠብ በቅድሚያ ገበያው ይታያል:: ውስን ማሽን ለመሸጥ ፋብሪካ መክፈት አዋጭ አይደለም:: በተጨማሪ እርሳቸው ማሽኖቹን የሚገዙባቸው አምራች ድርጅቶች ያካበቱት ልምድ በቀላሉ የሚገመት አይደለም:: ብዙ ዓመታትን የፈጀ ልምድ አካብተዋል:: በዚህም ከራሳቸው አልፈው የዓለምን ገበያ ተቆጣጥረዋል:: ስለዚህ ትልልቆቹን ማሽኖች ሀገር ውስጥ ማምረት አዋጭ አይደለም:: እጅግ ከባድ ነው:: አጠቃቀሙን ሰዎች እንዲያውቁት ማድረግ ሰዎችን ማብቃት እንጂ እዚህ ተመርተው እዚህ እንዲሸጡ መሰብ አያዋጣም ብለዋል::
ሆኖም አቶ ጊዜህነው፤ ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ ለትምህርት ግብዓት የሚያስፈልጉ የቴክኖሎጂ መማሪያ ቁሳቁሶችን ማምረት እንደሚቻል አመልክተው፤ እርሳቸው የሚያስመጧቸውን የትምህርት መሳሪያዎች በሀገር ውስጥ መገጣጠም ወይም ማምረት የሚቻል በመሆኑ ወደፊት ዕቅዳቸው የመማሪያ ዕቃዎችን መገጣጠም ማምረት እና መሸጥ መሆኑን ያመለክታሉ::
በሥራው ላይ የሚያጋጥማቸውን ፈተና አስመልክቶ ሲናገሩ፤ ብዙ ነጋዴ የሚያጋጥመው እና እርሳቸውንም ፈትኗቸው የነበረውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ችግርን አንስተዋል:: ሌላኛው እና ዋነኛው ችግር ብለው የጠቀሱት ደግሞ የጉምሩክ ሠራተኞች የዕውቀት ክፍተት እና የቢሮክራሲው ውጣ ውረድ ነው ይላሉ:: ከእነዚህ ውጪ ሥራው ላይ ብዙ ፈታኝ ሊባል የሚችል ነገር እንዳላጋጠማቸው ይናገራሉ::
‹‹ የምሸጠው የተማርንባቸው እና የምናውቃቸውን ቁሳቁሶች በመሆኑ መቼ በምን ያህል መጠን የትኛው ገበያ ላይ መሸጥ እንደምችል አውቅ ነበር::›› የሚሉት አቶ ጊዜህነው፤ ሰዎች የሚነግዱትን ዕቃ በደንብ ማወቅ አለባቸው የሚል ፅኑ አቋም እንዳላቸው ያስረዳሉ:: ሰዎች የሚሠሩትን ጉዳይ በቅጡ የሚያውቁ ከሆነ ወደ ሥራ መግባት እና ስኬታማ ለመሆን ብዙ አይቸገሩም ይላሉ::
በብዙ ነጋዴዎች ዘንድ ያለውን ዝንባሌ ሲጠቁሙ፤ ‹‹ ሰው ስላስመጣው የማያውቁትን ዕቃ ማስመጣት ይስተዋላል:: ይህ ደግሞ ግራ መጋባት ያመጣል:: የማያውቁትን ዕቃ ከማስመጣት በፊት በቅድሚያ የሚመጣውን ዕቃ በደንብ ማወቅ እንዲሁም አምራቹ ሲያመርት ተጠቃሚው ወይም ሸማቹ የሚፈለገውን ዕቃ በብቃት ማምረት እንደሚችል ማረጋገጥ ያስፈልጋል::›› ሲሉ ተናግረዋል::
ጨምረውም ሰው መሥራት ለሚፈልገው ነገር ቁርጠኛ ሆኖ በፍፁም ትጋት መሥራት እንዳለበት የሚናገሩት አቶ ጊዜህነው፤ እንደውም አስፈላጊ ከሆነ ዕቃው ከመጫኑ በፊት የሚመረትበት ቦታ ድረስ መሔድ፤ በደንብ ማየት እና ቁሱ የተሠራው ከምንድን ነው? ኢትዮጵያ ቢመጣ ምን ያህል ያዋጣል? የሚፈለገውን ነገር ለማከናወን ይችላል? የሚሉትን ጥያቄዎች በተገቢው መልኩ ለመመለስ በደንብ ማጥናት እና ለዛም የሚያስፈልገውን መስፈርት ማሟላት አለማሟላቱን ማረጋገጥ የግድ መሆኑን ይናገራሉ::
አቶ ጊዜህነው እንደሚያስረዱት፤ እሳቸው ወደሀገር ውስጥ ሊያስገቡ የሚያስቡትን እቃ ማጥናት የሚጀምሩት የሚያመጡትን ዕቃ መስፈርት ከመለየት ነው:: እያንዳንዱ ማሽን ምን አይነት አገልግሎት እንደሚሰጥና ከምን እንደተሠራ ለማወቅ ጊዜው ምቹ በመሆኑ መስፈርቶችን ለማረጋገጥ በቅድሚያ ኢንተርኔት ይጠቀማሉ:: በአካል ሔደው ያረጋግጣሉ:: ይህ ቀድሞ የሚሠራ ከሆነ ንግድን ማከናወን ቀላል እና ስኬታማነትም አደጋች እንደማይሆን ይገልፃሉ::
በእርሳቸው በኩል የሚያመጧቸው የትምህርት መሣሪያዎችን አጥንተው የሚያመጧቸው በመሆኑና ገበያው ገና ምንም ያልተነካ መሆኑን ተከትሎ ሥራቸው ላይ ብዙ ችግር እንዳላጋጠማቸው ያስረዳሉ::
የግድ ዕውቀት ያለው ብቻ ሳይሆን ያልተማረ ነጋዴ መሆን እንደሚቻል አይካድም ያሉት አቶ ጊዜህነው፤ ሆኖም ነጋዴው ስለሚያስመጣው ዕቃ ቀጥርም ቢሆን ማስጠናት እንደሚኖርበት መዘንጋት እንደማይገባም መክረዋል::
በምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 5 ቀን 2017 ዓ.ም