
የአካል ጉዳተኞች ናቸው። በተለያዩ የሙያ መስኮች የሠለጠኑ። የአለባበስ ሁኔታቸው ይማርካል። የአዳራሹ ድባቡ ደግሞ ድግስ ቤት ይመስላል። የአብዛኞቹ የአካል ጉዳት መመሳሰል ለአቀማመጥ ምቹ የሆነ ምርጫ እንዲኖራቸው አድርጓል። ወንበሮቹን ሳብ አድርገው ለእግራቸው በሚስማማ መልኩ ተጠቅመዋቸዋል። ወጥነቱ ደግሞ ለእይታ ሳቢ ነው። ከሁሉም ግን ከመሐል የተቀመጡት አባት የተመልካችን ቀልብ ይገዛሉ። በአለባበሳቸው ‹‹ኑ ከእኔ ስር ተቀመጡ›› የሚሉ ይመስላሉ።
ወደ አዳራሹ ዘለቅሁ። በጣም ጥሩ ተሞክሮ ይኖራቸዋል ብዬ አስቤያለሁ። ከጎናቸው ለመቀመጥ ግን ብዙዎች ከበዋቸዋልና አልተቻለኝም። መርሐግብሩ እስኪጀመር ድረስ ለእርሳቸው ቀረብ በሚል ቦታ ተቀመጥኩ። ንግግራቸውንም እያዳመጥኩ ነው። ወጋቸውን ስስማ ‹‹እውነትም ምርጫዬ ትክክል ነበር›› አልኩ። ምክንያቱም ላናግራቸው የወደድኩት አባት ከመሰሎቻቸው ጋር ስለ ነገ ተስፋ ይነጋገራሉ። አካል ጉዳተኛ መሆን ምንም ማለት እንዳልሆነም ይመክራሉ።
የተገኘሁበት አጋጣሚ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ አካል ጉዳተኞችን በተለያየ ዘርፍ አሠልጥኖ ለሥራ ማስጀመሪያ የሚሆን ግብዓት ድጋፍ እንደሚሰጣቸው ሰምቼ ነው። እኝህ አባትም ከሠለጠኑትና ከተመረጡት መካከል ናቸው። በሁኔታቸውና በንግግራቸው ስገረም ከቆየሁ በኋላ እውነትም ቢሮው እየሠራ ያለው ትልቅ ሥራ እንደሆነ ተረዳሁ። ምክንያቱም እንዲህ ያሉ ሰዎችን ሲመርጣቸው ለሌሎች አካል ጉዳተኞች ተስፋ እንደሚሆኑ አስቦ ነው።
እርሳቸው ሰው በገባ ቁጥር ይነሱና የአክብሮት ሰላምታ ይሰጣሉ። ትሕትናቸው ይበልጡን ገዛኝ። ‹‹ከሥራቸው አትራቁ›› ያሰኛልና መርሐግብሩ የሚቆይ ሲመስለኝ ከእርሳቸው ዘንድ ለመሄድ ወሰንኩ። በየትኛው ዘርፍ እንደሠለጠኑ ለመጠየቅ ጓጓሁና ከተቀመጡበት ስፍራ ጠጋ አልኩ። ለመግቢያ ይሆነኝ ዘንድም ‹‹አባ እንዴት ዋሉ›› ስል ሰላምታዬን አቀረብኩ።
እርሳቸውም ፈገግታ በተሞላው ገጽታቸው ለሰላምታዬ ምላሽ ሰጡኝና ‹‹ምን ልታዘዝ የእኔ ልጄ›› አሉኝ። ገና ሃሳቤን ሳላወጣ ትሕትናቸውን፤ ቃላት አጣጣላቸውን ስመለከት ስለ እርሳቸው ማሰብ ጀመርኩ። ለጥቂት ሰከንዶች ዝም ብዬ እየተመለከትኳቸው ይህንን ልዩ የሆነ ባሕሪ እንዴት ተላበሱት ስል ራሴን ጠየቅሁ። ዝምታዬ ሳያሳስባቸው አልቀረም። ‹‹ልጄ ከየት ነሽ፣ ምንስ ልጠይቂኝ ነው›› ሲሉኝ ከገባሁበት የግርምታ ቆይታዬ ነ ቃሁ።
እኔም ምንም እንዳልተፈጠረ በማስመሰል ‹‹ይቅርታ አባቴ የእርሶ ትሕትና በጣሙን አስገርሞኝ ነው ዝም ያልኩዎት። የመጣሁበት ምክንያት በምን ዘርፍ ሠለጠኑ፣ እንዴት ሙያውን መረጡትና መሰል የሕይወት ተሞክሮዎን እንዲያጋሩኝ ፈልጌ ነው›› አልኳቸው። እርሳቸውም ቀጠል አደረጉና ‹‹ምን የሚያስተምር ሕይወት አለን ብለሽ ነው። ይሆናል ካልሽ መልካም ጥያቄዎችሽን ቀጥይ›› አሉኝ። እኔም የመጀመሪያ ያልኩትን ጥያቄ ሰነዘርኩ ‹‹እንዴት ይህንን ዘርፍ መረጡት›› ስል። ምክንያቱም በብዙዎቻችን ዘንድ እንደሚታሰበው የልብስ ስፌት ሙያ ከእጅና እግር ውጪ አይታሰብም። የእርሳቸው ጉዳት ደግሞ እግራቸው ላይ ነው። ችግሩ እስከ ወገባቸው የዘለቀ ይመስላል። በአግባቡ ተቀምጦ ለመሥራት የሚያስቸግራቸው እንደሚሆን ገመትኩ።
ነገሮችን በጥልቀትና ማስተዋልን የሚያዩት አባ ገብረሰንበት ግን እንዲህ ሲሉ መለሱልኝ። ‹‹እኔ ሁሌም ያየሁትን በሥራ መተርጎም እሻለሁ። በተለይም ከአካል ጉዳቴ ጋር ተያይዞ የሚገጥመኝን ፈተና ለመቋቋም የሚያስችል ዕድል ካገኘሁ ከመጠቀም ወደ ኋላ ማለትን አልፈልግም። እውቀት እስከሆነኝ ድረስ እዘልቅበታለሁ። የሚለውጠኝም ሆኖ ካገኘሁት ነገዬን አበራበታለሁ። መጀመሪያ በፍራቻ አልችለውም ብዬ ራሴን መጎተት አልሻም። ገብቼበት፣ ሞክሬው ከጣለኝም እወድቅለታለሁ። ነገር ግን እጅ አልሰጠውም፣ ተስፋ እንዲያስቆርጠኝም አልፈቅድለትም። እናም ወደ ልብስ ስፌት ሙያ ሥልጠና የገባሁትም የሚፈትን እንጂ የሚጥል ሥራ እንደማይገጥመኝ ስላመንኩ ነው›› አሉኝ።
ከዚህ ንግግራቸው አንድ ነገር ተረዳሁ። አባ ገብረሰንበት ይህንን የተለየ ባሕሪያቸውን ያዳበሩት ለራሳቸው የሚሰጡት ግምት ከፍ ያለ በመሆኑ ነው። ማንም በምንም መልኩ ‹‹አትችልም›› እንዲላቸው አይፈቅዱም። በአካል ጉዳታቸውም እንዲሳለቅ ዕድል አይሰጡም። ‹‹የፈጣሪ ምርጥ የእጁ ውጤት ነኝና ለእኔ የተሻለውን ሁሉ ያመላክተኛል›› ብለው የሚያምኑ ዓይነት ናቸው። በሥራቸው ውጤታማ ሆነው ሌሎችን ማስከተልም የሚያስቡ ስለመሆናቸው ከንግግራቸው ተገነዘብኩ።
ሁሌም በጉዟቸው ውስጥ ‹‹በእኔ ላይ የሆነው ሁሉ ለመልካም ነው›› ብለው ያምናሉ። በተሰጣቸውም ባልተሰጣቸውም ያመሰግናሉ። ሠርቶ መለወጥን በማንም ጫንቃ ላይ አለመታዘልን ባሕሪያቸው አድርገው ይጓዛሉ። በዚህም በአስኳላው ትምህርት ብዙ ባይገፉም በጥልቀትና በእውቀት የዘለቁበት ለእንጀራቸውም ለመንፈሳቸውም ያሉትን ትምህርት ተምረዋል። ይህም የአብነት ትምህርት ነው።
የአብነት ትምህርቱ ላይ በመግፋታቸው ዛሬ በሐያት ጨፌ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን እያገለገሉ ለመኖር የሚያስችላቸውን ገቢ ያገኛሉ። ኑሯቸው ከእጅ ወደ አፍ ቢሆንም ቤታቸውን የሚደጉሙበት ዕድል አልነፈጋቸውም። በእርሱ ትምህርት ባይገፉ ኖሮ በሰዎች ጫንቃ ላይ መቀመጣቸው አይቀርም ነበር። ግን ሳይደግስ አይጣላም እንዲሉ ሆኖ ትምህርቱን በሚገባ ወስደው ስለነበር ሁሌም የተሻለውን የሚመለከቱ አድርጓቸዋል።
አባ ገብረሰንበት ከቤተክርስቲያኑ አገልግሎት ባሻገር ራሳቸውንም ሆነ ቤተሰባቸውን ከተረጅነት ለማውጣት የተለያዩ ሥራዎችን ያከናውናሉ። በዚህ ጉዟቸው ውስጥ ደግሞ በምንም መልኩ አካል ጉዳተኝነታቸውን ካለመሥራት ጋር አያገናኙትም። አካል ጉዳተኝነት ያለመሥራት ምንጭ ሳይሆን የፈጠራና የአዳዲስ ልምዶች መሠረት ነው። አለመሥራት የሚመነጨው ከእርሱ መነሻነት ሳይሆን አዕምሮ ሲዝልና ልባችን ደካማ ሲሆን ነው ብለው ያምናሉ።
አካል ጉዳተኝነት እንደሁኔታው የሚገድቡት የሥራ ዓይነት ሊኖርበት ይችላል እንጂ እንዳይሠራ የሚያደርገው አንዳችም ምክንያት የለም ባይ ናቸው። ለእርሱ በሚሆን መልኩ የተፈጠሩ በርካታ የሥራ ዓይነቶች እንዳሉም ያምናሉ። አካል ጉዳተኛው የውስጥ ተነሳሽነት እስካለው ድረስ ምንም አይነት የአካል ጉዳት ቢያጋጥመው ለሥራ የሚሆነውን አማራጭ ማግኘት እንደማያዳግተው ያስባሉ። እናም እርሳቸውም ዛሬ የተሰጣቸውን ዕድል ለመጠቀም የወሰኑት ከዚህ የተነሳ እንደሆነ ይናገራሉ።
‹‹እኔ አካል ጉዳተኛ ስለሆንኩ ይህንን ማድረግ አልችልም›› ማለት ስንፍናን መጥራት ነው›› የሚሉት አባ ገብረሰንበት፣ ‹‹ልብ ከደከመ አዕምሮ ከዛለ አይደለም አካል ጉዳተኛ ጉዳት አልባ የሆነ ሰው መሥራት አይፈልግም›› ባይ ናቸው። በዚህ ምክንያት ኑሯቸውን አዲስ አበባ ‹‹ለሚ ኩራ›› አካባቢ ሲያደርጉ ልባቸውንም ሆነ አዕምሯቸውን ሁሌም ለሥራ አጎብዘው ነው። ሥራ ወዳድነታቸው በእርሳቸው ፍላጎት መሳካት ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም አርዓያ ሆነው በመታየት እንዲገለጥ ይሻሉ። ለዚህም ስኬት ዘወትር ይተጋሉ።
በአብነቱ ትምህርት ብቻ የኑሮ ደረጃቸውን ማሻሻል እንደማይችሉ የሚያምኑት አባ ገብረሰንበት፣ በተለያዩ ሙያዎች ቢሠለጥኑና መሥራት ቢችሉ ደስ ይላቸዋል። ነገር ግን በራሳቸው አቅም ይህንን ማድረግ በእጅጉ ይከብዳቸዋል። እናም ለዓመታት እንዲህ አይነት ዕድሎችን ለማግኘት ሲመኙ ቆይተዋል።
አካል ጉዳተኛ ስለሆኑ በምን ዘርፍ ሠልጥነው መሥራት እንደሚችሉ ዕውቀቱ አልነበራቸውም። አንድ ቀን ግን ለዚህ ችግራቸው መፍትሔ የሚሰጥ ዕድል ከደጃፋቸው ከተፍ አለ። ቀበሌ የሚሠሩ ሰዎች መጡና ‹‹እንዲህ አይነት ሥልጠና ለመስጠት ታስቧል መሳተፍ ይፈልጋሉ›› ሲሉ ጠየቋቸው። የዓመታት ጉጉታቸው ነበርና ምንም ሳያሰላስሉ ፈጥነው ፍላጎታቸውን ገለጹ። መዝግበዋቸው ከሄዱ በኋላ ብዙ ሳይቆዩ ሥልጠናውን ጀመሩ። ይህ ዕድላቸው ደግሞ ከሥልጠናው ባሻገር ሌላ ትምህርት አስተማራቸው። የመረጡት የሥልጠና ሙያ ለእርሳቸው ጉዳት የሚመጥን እንደሆነ አሳመናቸው።
አባ ገብረመድኅን ሥልጠናቸውን እየወሰዱ ጎን ለጎን ከውጪ ያለውን ለልብስ ስፌት ሙያ ምን ያህል ምቹ እንደሆነ አጠኑ። ከአካል ጉዳታቸው ጋር ምን ያህል ተስማሚ እንደሆነም የዳሰሳ ጥናት አደረጉ። በዚህ ምልከታቸው የተረዱት የእግር ጉዳት የገጠማቸው ብዙዎች ዘርፉን እንደተቀላቀሉ ነው። እናም በዚህ ሙያ ሥልጠና የማግኘታቸውን ዕድል አመሰገኑት። የበለጠ ለመሥራትም ተመኙ። ከመንከራተት ይታደገኛል ብለው ለትምህርቱ ልዩ ትኩረት ሰጡ። ፍላጎታቸው የላቀ በመሆኑ ‹‹ሲኦሲ›› ሲወስዱ ጥሩ ውጤት በማስመዝገብ ትምህርታቸውን አጠናቀቁ።
ከሰዎች ጋር የመግባባት ባሕሪያቸው እንደአባትነታቸው ልዩ የሆነው አባ ገብረሰንበት፣ ንግግራቸው ከፈገግታቸው ጋር ተዳምሮ ሳይናገሩ የውስጥን ሐሴት ይሞላሉ። በተለይ ስለ ሌሎች በጎ ተግባርና አርዓያነት ሲያወሱ በእውነትም የሃይማኖት መምህርነታቸው ልዩ ተሰጥዖን እንደቸራቸው ያሳስባል። እርሳቸው ‹‹እኔ አደረኩ›› ከሚለው በላይ ‹‹ሰዎች አስተማሩኝ›› ማለትን ያስቀድማሉ። በመምህርነታቸው ውስጥም ተማሪነታቸውን ማጉላት ይሻሉ። ለዚህም አብነት አድርገው ያወጉኝን ታሪክ ላንሳ።
ባለታሪኩ እርሳቸው የአካል ጉዳታቸውን ሳያስቡ ሠልጥነው እንዲሠሩ ግፊት ያደረገባቸው ነው። ይበልጥ በሙያው እንዲገፉበት ጥንካሬን ሰጥቷቸዋል። በምክሩ ብቻ ሳይሆን በተግባሩም ወደ ሥራ፣ ወደ ትምህርት እንዲያተኩሩ ገፊ ምክንያት ሆኗል። እንዴት ከተባለ ደግሞ ነገሩ እንዲህ ነው። ሰውዬው እንደእርሳቸው የእግር አካል ጉዳት ሳይሆን የእጅ አካል ጉዳት የገጠመው ነው። በዚህም ወሳኝ የሆነውን ለልብስ መስፊያ የሚሆነውን ክር ለማስገባት በጣሙን ይቸገራል። ነገር ግን በልምምዶቹ ይህንን ችግሩን ፈትቶ ውጤታማ ልብስ ሰፊ ሆኗል። ክር በማስገባትም ማንም አይቀድመውም። ዲዛይን ማውጣትና ልብስ መቆራረጥንም እንዲሁ አንድ እጁን ከእግሮቹ ጋር በማዋሓድ ያደርገዋል።
በአንድ እጁ አጀብ የሚያሰኙ ተግባራትን ሲፈጽም ለተመለከተው በዓይን የሚታይ ባይሆን ኖሮ አካል ጉዳተኝነቱን ጥርጣሬ ውስጥ ይከታል። በዚህ ተግባሩ ደግሞ እንደእርሱ አካል ጉዳት ያጋጠማቸው ብቻ ሳይሆኑ አሠልጣኞቹ መምህራን ጭምር ይደመሙበታል። ተስፋ የቆረጡ አካል ጉዳተኞችንም እንደሚችሉ፣ ምንም የሚገድባቸው ነገር እንደሌለ አርዓያ ያደርጉታል። ብዙዎች ‹‹ባንዘልቅበትም›› ስጋት ሥልጠናውን ቢጀምሩም በእርሱ ግፊት ውጤታማ ሆነው አጠናቀዋል። እርሱ እግሩን ከአንድ እጁ ጋር እያጣመረ በመሥራቱ ቤተሰብ ጭምር መምራት እንደቻለ ሲነግራቸው ግን የነገ ተስፋቸው ይለመልማል።
አባ ገብረሰንበትን ጨምሮ በሥልጠናው ላይ የሚሳተፉ ሁሉ በእርሱ ጥንካሬና ሁሌም ባላቸው ነገር እንዲኮሩ ዕድል ሰጥቷቸዋል። ‹‹አካል ጉዳት አለብኝ ብለህ እጅህን አጣጥፈህ አትቀመጥ። ይህንን ካደረግህ ሰዎች ሁሉ ይረማመዱብሃል እንጂ ሊያሳልፉልህ አይፈቅዱም። ተጣጥረህ እነርሱን መብለጥ ከቻልክ ግን አጨብጫቢዎችህን ታበዛለህ›› የሚለውን የእርሱን መርሕን እንዲከተሉ አግዟቸዋል።
አባ ገብረሰንበት ከእርሱ ሃሳብ ብዙ ነገር ተምረዋል። ዛሬም ድረስ ለራሳቸው የሕይወት ስንቅ ያደረጉት ትምህርትን አግኝተዋል። በተለይም ‹‹አካል ጉዳት ሲያጋጥም ያልተጐዱትን አካላት ለማንቃት ያስችላል። የማንጠቀምባቸውን የአካል ክፍሎቻችንን ሥራ እንዲጀምሩ ያደርጋል። ከሌሎች የምንለይባቸውን ስኬታማ የሆኑ ተግባራትም እንድናከናውን ዕድል ይሰጠናል›› የሚለው መርሕ ብዙ የተማሩበት እንደሆነ አጫውተውናል።
‹‹የአካል ጉዳት በማንኛውም ሰው ላይ የሚደርስ ክስተት ነው። በዚህም ዘወትር እንደ ችግር ከማየት ይልቅ የችግር መፍቻ ቁልፍ አድርጎ መውሰድ ይገባል። በአካል ጉዳት ውስጥ በርካታ በረከቶችም እንዳሉ ማመንም ያስፈልጋል። ነፃና የተሻሉ ነገሮችን መፍጠር የምንችል መሆናችንን ጭምር ለራሳችን መንገር ይኖርብናል። ምክንያቱም አሸናፊ የምንሆነው አማራጭ በማጣታችን ውስጥ በምንፈጥራቸው ዕድሎች ነው። እናም ዘወትር ባለን ተደስተን፣ ያለንን ማሠራትና መለወጥን ገንዘብ ማድረግ አለብን›› ሲሉ ለመሰሎቻቸው ሃሳብን ይቸራሉ። እኛም መልዕክታቸውን ለኑሯችን መሠረት፣ ለነጋችን መብራት እናድርገው በማለት ለዛሬ የያዝነውን አበቃን።
በጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 5 ቀን 2017 ዓ.ም