የግብርና ኢንሹራንስን ፖሊሲ ለማውጣት እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፡- እንደ ሀገር የግብርና ኢንሹራንስን በፖሊሲ የተደገፈ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የገጠር አገልግሎት ዘርፍ ቡድን መሪ ጌታቸው መኮንን ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ እስከ አሁን ድረስ በኢትዮጵያ የግብርና ኢንሹራንስ ፖሊሲ የለም፡፡ በግብርናው ዘርፍ የመንግሥትን የሥራ ድርሻ፣ የዋጋ ተመኑን እና ማን የኢንሹራንስ አቅርቦት መስጠት እንዳለበት በዝርዝር የሚገልጽ ምንም አይነት ፖሊሲ አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡

በብሔራዊ ባንክ ባሉ ፖሊሲዎች ከዚህ ቀደም የተወሰኑ የሙከራ ጥናቶች ሲደረጉ መቆየታቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

ላለፉት 10 እና 15 ዓመታት በርካታ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የግብርና መድኅን ሞዴሎች ሞክረው ሙከራቸው እንዳልተሳካ ገልጸው፤ ለዚህም ምክንያቱ አብዛኞቹ የሙከራ ጥናቶች (Pilot Studies) የሚደረጉት ከድጋፍ ሰጪዎች በመጣ ገንዘብ በመሆኑና መንግሥት እምብዛም ሚና ስላልነበረው ነው ብለዋል፡፡

መንግሥታዊ ያልሆኑት ድርጅቶች ለአምስት ዓመታት ሲሞክሩ ቆይተው ሙከራቸውን ሲያጠናቅቁ ተረክቦ የሚያስቀጥል አካል እንዳልነበርም አውስተዋል፡፡

ርዳታ ሰጪዎቹ ከሀገር ሲወጡ ሃሳቡ አይቀጥልም ነበር የሚሉት ቡድን መሪው፤ አሁን መንግሥት የግብርና ምርት መድኅን እንደሚያስፈልገው በመገንዘብ ግብርና ሚኒስቴር፣ የገንዘብ ሚኒስቴር እና በብሔራዊ ባንክ የተለያዩ ጥረቶች እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

መንግሥት የግብርና መድኅን ሥራንም ተቋማዊ ይዘት እንዲኖረው ማገዝ እንዳለበት ጠቅሰው፤ በሀገር ውስጥ በቂ አቅም ተገንብቶ የመድኅን (ኢንሹራንሱ) አገልግሎቱ ለገበሬ እንዲደርስ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የመድኅን ሥራ በኢትዮጵያ አምስት በመቶ ብቻ ድርሻ እንዳለው የተናገሩት አቶ ጌታቸው፤ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

ገበሬ ምርት ለማምረት ሲጀምር እንደ ድርቅ እና የዝናብ እጥረት ያሉ የተለያዩ ተፈጥሯዊ አደጋዎች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ጠቅሰው፤ ማሳው ላይ ኢንቨስት ያደረገውን ምርት ሲያጣ የሚተካለት ባለመኖሩ ለማምረት ተነሳሽነቱ ይቀንሳል ነው ያሉት፡፡ ገበሬው ያለውን ካፒታል ሙሉ በሙሉ አሟጦ እና ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ መሬቱ ላይ ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎቱ የሚጨምረው የመድኅን ሽፋን ሲኖረው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የመድኅን ዋስትና ያለው ገበሬ ኃላፊነት ወስዶ የእርሻ ሥራን እንደሚከውን ገልጸው፤ ብድር የሚሰጡ አካላትም ደፍረው ብድር መስጠት ይችላሉ ብለዋል፡፡

ለሌሎች ቋሚ እና ተንቀሳቃሽ ንብረቶች ዋስትና እንደሚሰጥ እና ባለንብረቱም በቀላሉ ብድር ማግኘት እንደሚችል ሁሉ አርሶ አደሮች ለምርታቸው ዋስትና ሲኖራቸው በቀላሉ ብድር በማግኘት በሌሎች የልማት ሥራዎች ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ ያስችላል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የገጠር አገልግሎት ዩኒት ቡድን በማቋቋም የፋይናንስ እና የኢንሹራንስ ሥራዎችን በማዕከላዊነት የሚያስተሳስር ዘርፍ መመሥረቱን ተናግረዋል፡፡ ዘርፉ በብዛት ተበጣጥሰው የሚሠሩ ሥራዎችን በአንድ በማምጣት ውጤታማ ሥራ እንደሚሠራም ጠቁመዋል፡፡ የተለያዩ ፖሊሲ እና መመሪያዎች እንዲወጡም ቡድኑ የበኩሉን ሚና ይወጣል ብለዋል፡፡

ድጋፍ ሰጭ አካላት የሙከራ ሥራዎችን ሲሠሩ ሃሳቡ መተግበር የሚችልበትን ሥርዓት ቢተገብሩ የተሻለ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ጠቅሰው፤ ሀገር ውስጥ ያሉ መድኅን ሰጪዎችም በሀገር ውስጥ ጥረት እና እውቀት ሥራዎችን ቢሠሩና መንግሥትም ድጋፍ ቢያደርግ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል አቶ ጌታቸው አስረድተዋል፡፡

መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You