ተገኝ ብሩ
እንደ አገራችን ትልቅነት ያልተለቀው የፖለቲካ ልምዳችን ውድ ጊዜያችንን አለዝቦብን ለአገርና ለወገን የምንሰራበት ጥሩ ጊዜያችንን እንዲነጥቀን አንፈቅድምና ተማርን የምትሉ /ኤሊቶች/ ፖለቲካውን እናሾረዋለን የምትሉ የዘርፉ ተዋናዮች እባካችሁን ዘመናችንን አትቀሙን። ዘመኑን ኖሮ የሌሎችን ውድ ጊዜ የሚቀማ የምሩን ኖሮ የውሸት ለማኖር የሚተጋ ዛሬ በወጋ ወጋ ወጋችን አንስተን ችግሩን አሳይተን መታከም እንዲችል ልናስገነዝበው አሰብንና ይህን አልን።
ወጣቱ የተዋበ ጊዜው እንዲበላሽ የወደፊት ተስፋው እንዲጨልም አይፈልግምና ብሩህ ነገር ማየት የተዋበ ነገር መመልከት ይፈልጋል። የተሻለ ዘመን እንዲቀርበው መልካም ጊዜ እንዲመጣለት አጥብቆ ይመኛል። ውብ ጊዜ በጥላቻ ትርክት ማጣት በእርስ በርስ ግጭት ማበላሸትን አይፈቅድም። የሚነገረው በጎ የሚወራለት በጎ መሆን ይገባዋል። ተነስ በታሪክ የከበረችው አገርህን ለውጥ እንጂ ተነስ የነበረችውን አገርህ አፍርስ ዘመንህን አጨልም የሚል ጨለምተኛ ሀሳብ ሊቀርብለት አይገባም።
የተዋበ ውብ ጊዜውን ለመቀማት ውድ የሆነውን ዘመኑን ለመንጠቅ የሚሞክር ፖለቲከኛ የራሱን ዘመን አበላሽቶ የዚህ ዘመን ፍካት ላጠልሽ የሚል ስግብግብ ሊቆጠብ ይገባል። ወጣቱ አገሩ በልፅጋ ህዝቡ ተለውጦ ማየትን ይመኛል። ለዚህ ምኞቱ መሳካት ለመልካም ሀሳቡ ሙሉ መሆን ደግሞ አብሮነት ሊሰበክ የአንድነት ጠቀሜታው ሊነገረው ያስፈልጋል።
ዘመን ዘመንኛውን ይመስላል። በዘመኑ የሚኖሩትን ይስተካከላል። ዘመኑ የአንድነት መንፈስ የሞላበት መተባባርና ፍቅር ያየለበት ከሆነ፤ ያ ዘመን ፍስሀ የሞላበት፣ ትውልድም የሚደሰትበትና አገር የምትለወጥበት ይሆናል። በተቃራኒው ደግሞ ዘመነኞች ካበላሹት ባለ ጊዜዎች ካነተቡት ጭለማ የወረሰው፣ ሲያስቡት የሚቀፍ፣ ሲነግሩት የማይመች ሆኖ ያልፋል።
እኛ የዚህ ዘመን ትወልዶችም የዘመናችን ማማርም ሆነ መንተብ ተጣያቂዎች ነን። ስለዚህ ዘመኑን ማንፃት የተዋበም ማድረግ የእኛ ፋንታ ይሆናል። የዚህ ዘመን ዋንኛ ባለቤቱ የዘመኑ ትወልድ ባለቤቱ ደግሞ በዚህ ወቅት የተገኘ ሁሉም ነው። የዚህ ዘመን ዋንኛ ተዋናይ የሆነው ወጣት ዘመኑ እንዲኖር መፍቀድ የራሱን ብሩህ ዘመን እንዲፈጥር ማመቻቸት ተገቢ ነው።
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ዋናውን ሚና የሚጫወቱት ኤሊቶች፤ለዘመኑ ባለቤት ወጣት መልካምን ማመላከት ለጥሩ ነገር መጣራት አብሮነትን መስበክ ሲገባቸው በተቃራኒው ሊያቆሙት ሲሞክሩ ይታያል። የአገር ግንባታ ወንኛ ተዋናዩን ወጣት አስበው የእርሱን ዘመን ለራሱ በሚሆን መልኩ እንዲኖረው መፍቀድን አለመዱም።ባለፈ ታሪክ የሚጋጭ፣ ባልኖረበት ዘመን የሚጠየቅ ፣ በማያውቀው የሚሳቀቅ ለማድረግ በብርቱ ይሰራሉ።
ይህ መንገድ የተሳሳተ ዘመኑና ባለዘመኑን ትወልድ የማይመጥን ነውና የወጣቱን ዘመን መቀማቱ የተዋበ ጊዜውን መንጠቁ መቆም ይኖርበታል። ትውልዱ አብሮነት ገብቶት ተከባብሮና ተማምኖ የሚኖር ጥላቻን ንቆ ፍቅርን አንግሶ ዘመኑን በሰላም የሚያሳልፍ ውብ ጊዜውን በራሱ ቅኝት የሚያራመድ መሆኑ ሊታወቅለት ግድ ይላል።ሁሉም የራሱ የሚለው ውድ ጊዜ የኔ የሚለው ዘመን አለው። ወጣቱም ራሱና አገሩ የሚለውጥበት ትኩስ ጉልበቱ ሳይባክን ውጤታማ በሆነ ጉዳይ የሚያውልበት የእድሜው ዋንኛው ክፍል ነውና ዘመኑን ይኑረው።
አገር የምትገነባበት ህዘብ የሚለወጥበት መንገድ ማመላከት የወደፊቱ ዘመን ብሩህ እንዲሆን መስራት ሲገባቸው የወጣቱን ዘመን የሚያጨልሙ መልካም ጊዜውን የሚነጥቁት ማነሳሻዎች በርክተዋል። የተሻለች አገር መስርቶ የእራሱ የሆነው ምጩ ሁኔታ የሚፈጥር ትወልድ ለእነሱ ጉዳይ ሳይሆን መሰላል የፍላጎታቸው ማሟያ ለማድረግ ይጥራሉ። ለወጣቱ የሚሆን ብሩህ ጊዜውን በሰላም የሚኖርበት እድሉን የሚነጥቁት ሀሳቦች እንዲላበስ አጉል እኔ ላንተ ተቆርቋሪ ነኝ፤ስላንተ እኔ ተሟጋች ነኝ የሚል ማታለያ ያቀርቡለታል።
ወጣቱ እኔ በዘመኔ በፍቅር ማደር፣ በወቅቴ ተስማምቶ መኖር እሻለሁና አስማሙኝ፣ ጥንት አባቶች የነበሩበት አንድነት አብረው ያደሩበትን መቻቻል አስተምሩኝ ቢልም እነሱ በተቃራኒው የሚነግሩት አሉታዊ ነገር የሚያስረዱት የተዛባ ሆኗል። ወጣት ሆይ ከዛሬ ምናምን አመት በፊት እነ እነትና አባቶችህ በድለዋልና ተነስ ተዋጋ፤ ወገኔ ሆይ እነ እንትና ሊያጠቁህ ከጫፍ ደርሰዋልና ጠላት ሁናቸው የሚሉ ማታለያዎች አይፈልግም።
ይህ ዘመን መልካም አስተሳሰብ የሚያሸንፍበት የማያሻግር አመለካከት የሚከስምበት መሆን ይኖርበታል። አዎን ይህ ዘመን ዋንኛ ባለቤቱ የዘመኑ ትወልድ ዋንኛ ተዋናዩም የዛሬው በፍቅር ያመነ ዜጋ ነው። ይህ ፈፅሞ ሊቀማ አይገባውም። ወጣቱ ስለ አገሩ መልካም መሆን በርትቶ የሚሰራበት ቀድማ ጀምራ ኋላ የቀረችው አገሩ ወደፊት እንድትራመድ ትኩስ ጉልበቱ ሳይሰስት የሚሰዋበት ዘመኑ ነውና ይህ ዘመን ሊቀማ አይገባም።
የዚህ ዘመን ትውልድ የራሱ የሆነ ጊዜው በፍቅር ያመነ በአንድነት የፀና ሆኖ እንዲያሳልፈው የምትሰብኩት ፍቅር የምትነግሩት ደግሞ አብሮነት ይሁን። ድንቅ የሆነ ዘመኑን ተቀምቶ ባልኖረበት ዘመን ታሪክ የሚጋደል ባላየው ሁነት የሚጋጭ መሆን ከቶም የለበትም። ለዚህ ትውልድ ይህ ዘመን ምትክ የሌለው የተዋበ መልካም ነገሮችን የሚያልምበት ተስፋው እንዲሳካ የሚታትርበት ነውና ዘመኑን ለራሱ ለባለቤቱ ይተውለት። የተሳሳተ ትርክት በማንሳት አትለዩት።
የራሳቸውን አበላሽተው ሲያበቁ የወጣቱን ዘመን ቀምተው መጠለያ ለመስራት የሚያስቡት ፖለቲከኞቻችን ሊያውቁት የሚገባው ትልቁ ቁም ነገር አለ። ዘመኑን የዋጀ የፖለቲካ እሳቤና በአንድነት ቆሞ ጠንካራ ማድረግ የሚችል ሀሳብ እንጂ ወጣቱን ነጣጥሎ በተለያየ ጎራ ሆኖ የሚናቆርበት ሊሆን አይገባም። ከዚህ በተለየ መልኩ የእርስ በርስ ወዳጅነቱ እንዲጠናክር አብሮነቱ እንጂጎለብት ሊነግሩት ሊያስተምሩትም ቢጥሩ ለእነሱም እረፍት ለአገሪቱም ብስራት ይሆናል።
የወጣትነት ውብ ጊዜን የሚያጨልሙ ትርክቶችን ማጥፋት የእርስ በርስ ግጭቶችን የሚፈጥሩ ንግግሮችን ማስቆም ይገባል። የወጣቱን ዘመን ለመቀማት የምትፈልጉ የእናንተን በመንገር የእሱን ለመውሰድ ያቀዳችሁ ተግባራችሁ ሊገራ ሀሳባችሁ ሊታደስ ይገባዋል። ወጣቱን ገርታችሁ በአንድነት እንዲቆም፤ አስተካክላችሁ አብሮነቱ እንዲያጠናክር መንገር ከእናንተ ይጠበቃል። አገሩን የሚለውጥበት ትኩስ ጉልበቱ በአግባቡ እንዲጠቀምበት፤ይህች ከእርሱ ብዙ የምትጠብቀው እናት ምድሩን እንዲያፀናት ደግፉት! እንዲወድ አድርጊት! መልካምን በመንገር መልካም ዘመኑን ከመቀማት ታቀቡ። አበቃሁ፤ ቸር ይግጠመን።
አዲስ ዘመን መጋቢት 19 ቀን 2012 ዓ.ም