የአቴቴን ከሀገሬ

ሀገሬ ባሕል የወለዳት ጥበብ ናት፡፡ ሀገሬ በወግ ማዕረግ በተሸመነና በተሸሞነሞነ የጥበብ ሽንሽን አምራና ደምቃ የምትታይ የአደይ አበባ ፍካት ናት፡፡ ሀገሬ ያለ ተፈጥሮ የጥበብ እሴት ለመኖር የማይቻላት በለምለም መስክ ላይ ያረፈች እንቡጥ ፍሬ ናት፡፡ ልቧ በተፈጥሮ ፍቅር የተነደፈና በምድር ሁሉ ላይ ፍቅሯን እንደ ክረምት ዝናብ የምታረሰርስ የጥበብ ጅረት ናት። የቀስተ ደመናው መቀነቷ ከምድር እስከ ሰማይ ተዘርግቶ በቀለማት መስመር ሸንተረር እየሠራ ወደ ገነት ደጆች ያደርሳል፡፡

ሀገሬ ኢትዮጵያ የዓለምን የምስጢር ካዝና ቁልፍ ከመቀነቷ ላይ አስራ በቅኔ የተሞላች የጥበብ ፍኖት ናት፡፡ ስለ ባሕሏ፣ ስለ ወጓ፣ ስለ መልክና ስዕላዊ ውበቷ የሚነግሩን የጥንታዊ ቱውፊቶቿ ርዝራዥ ዛሬም አልፎ አልፎ ከየማህበረሰቡ ጓዳ ስር ተሸሽገው ይገኛሉ፡፡ ባሰረችው መቀነቷ፣ ባጠባችው ጡቶቿ ምልጃ ተረፉ እንጂ ገዳይ አሳዳጁማ ብዙ ነበር፡፡ የያኔው ታላቅነቷ የተገነባው ተፈጥሮን ከጥበብ፣ ጥበብን ከነብሷ ጋር አቆራኝታ ከሰማይና ምድሩ ጋር የምትገናኝበትን ያን የቀስተ ደመና መንገድና የጥበብ ድልድይ በመሥራቷ ነው፡፡ ተታለን በሞኝነት የጣልናቸው ከተፈጥሮ ግርጌና ጋራ ሲከወኑ የነበሩ ባሕላዊና ጥበባዊ ክዋኔዎቻችን የዚህ መንገድ ማሳለጫ ሰንሰለታማ መሹሊኪያዎች ነበሩ፡፡

በመንገዶቹ ላይ አሜኬላ አብቅለን ዘጋናቸውና መተላለፊያውን አሳጣናት፡፡ ያሉንን ሰምተን ከዚያ የገነት ደጃፍ ተቆራረጥን፡፡ መስሎን መቀነትን ረገጥነው፡፡ መስሎን ታላቅነታችንን ወደ ሸለቆ ወንዝ ወረወርነው፡፡ መስሎን የባዕድ አምልኮ ነው ስንል ከባዕዳን ጋር ባዕድ ሆነን ከረምን፡፡ እንደ መሰለንም… ጥበብን ፍለጋ ወደ ሰሜን ብንሄድ ደቡብ፣ ወደ ምሥራቅ ብንዞር ምዕራብ ዛሬም ርዝራዥ የጥበብ ፍሬዎችን እናገኛለን፡፡

በዛሬው የዘመን ጥበብ አምዳችን ላይ ቆመን ጥበብን ፍለጋ ጋራ ሸንተረሩን ስንማስን ከወዲህ ደግሞ ሰሞነኛ የታየን አንድ ነገር አለ፡፡ መነሻ የሆነችንን ዘንቢል አንጠልጥለን ከማሳም ከጫካም ጥንቅሽ ፍሬውን እየለቀምን በዙሪያ ገባው ለመዳከር ግድ ነው። የጥንቅሽ ፍሬው መገኛ ከዘጋቢ ፊልም ላይ ነው። ፊልሙም “አቴቴ አያና ሐዎታ” ይሰኛል። ይህንን ዘጋቢ ፊልም በተመለከተም መስከረም 4 ቀን 2017 ዓ.ም ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቶበታል፡፡

ጥበባት የሚወለዱበት የሀገራችን ባሕል የሚቀዳው በአራቱም አቅጣጫ ከሚገኙት ብሔር ብሔረሰቦች መካከል ነውና “አቴቴ”ም ወደ ኦሮሚያ ባሕልና ትውፊቶች ይመራናል። የኦሮሞን የባሕል ጥበባት አጉልቶ በማውጣት በሀገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ በማድረግ የሚታወቀው ኑቢያ ፊልም ፕሮዳክሽን አሁን ደግሞ ከኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ጋር በመተባበር ዓለም አቀፍ የእይታ አድማስ የታሰበለትን “አቴቴ አያና ሐዎታ”ን በመሥራት ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡ በትናንትናው ዕለትም በሸራተን አዲስ ተመርቆ በሀገር ውስጥ ለመጀመሪያው ጊዜ ለእይታ በቅቷል፡፡ በቀጣይም በዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫሎች ላይ የመግባት ዕድሉን በማመቻቸት ሀገርና ባሕልን ይዞ ከፍ የማለት መሻት አለው፡፡

ጥንቱን የባሕልና ጥበባት ማህቶት ሆና ለኖረች ሀገራችን ዘጋቢ ፊልሞች አቻ የሌላቸው መስታወቶች ናቸው፡፡ የሚሠሩት አስቀድሞ በታሪክና ጥናት ወደኋላም ወደፊትም ታሽተውና በእውነት ኬሻ ላይ ተንጋለው በመሆኑ ቱባውን ነገር ከነ ሙሉ ግርማ ሞገሱ ቁልጭ አድርገው የማሳየት ኃይል ስላላቸው ከሌላው የፊልም ዓይነት ለየት ይላሉ፡፡ ፊልሞች ሀገርና ወግ ባሕል፣ ጥበብና ጥንታዊነትን አውጥቶ ለዓለም የማሳየት አቅም ቢኖራቸውም እንደ ዘጋቢ ፊልሞች በቀጥታ እንደ ወረደ ስለማይቀርቡ ከግቡ አንጻር ዘጋቢ ፊልሞች ለዚህ ተመራጭ ናቸው፡፡ ዓለም አቀፍ የምርምር ተቋማትና ምሁራንም በፍለጋቸው ውስጥ ዋቢ አድርገው ከሚነሱባቸው ነገሮች መካከል ዘጋቢ ፊልሞች ከአንበሳዎቹ መካከል ናቸው፡፡ ከማንም በላይ ለኛ ወሳኝ ቢሆንም ሠርቶ ከማሳየት አኳያ ግን ገና እሳቱም አልነደደም፡፡

እኛ ስለ እኛ ከሠራናቸው በላይ እነርሱ ስለኛ የሠሩት ይልቃል፡፡ ጓዳ ጎድጓዳውን በሚያውቀው ባለቤቱ ባለመሠራታቸው ሀፍረት ከመሆኑም በላይ የእውነታ መወላገዶችና መፋለሶች ይፈጠራሉ፡፡ በኛው የፊልም ባለሙያዎች በየአጋጣሚው ተሠርተው ለእይታ የበቁ በርካታ ዘጋቢ ፊልሞች ቢኖሩም ትኩረት ሰጥቶ በባለቤትነት የሚመራው አካል ግን የለም፡፡ በፊልም ኢንዱስትሪው ውስጥ አንድ አካል አድርጎ ለመሥራት ጥረት ቢደረግበት ኖሮ ልንመለከት የምንችላቸው ታላላቅ ነጥቦች ቢኖሩን ነበር፡፡ ፊቱን ወደ ተደበቁትና ወደ ተሰወሩት የባሕል ምሽጎች አዙሮ ቢገባበት አይቶ የሚያሳየን ተአምር አይጠፋም ነበር፡፡ አሁን አሁን ግን ግድ ሊለው የሚገባ ይመስለኛል፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ ከተሠሩት መካከል እንኳን ወድቆ የወደቅ አንድም የለም፡፡ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ተፈላጊነታቸው ከፍ ያለ ነው፡፡

ተሠርተው ከቴሌቪዥን መስኮቶች ውስጥ ብቅ ባሉ ቁጥር ከህጻን እስከ አዋቂ በተመስጦ እንደሚመለከታቸው ከዚህ ቀደም በይፋ የቀረቡ ዘጋቢ ፊልሞች ማሳያ ናቸው፡፡ ዘጋቢ ፊልሞች የሚሠሩት ከፍ ባለ ጥናትና ምርምር እንደመሆኑ በታሪክ ውስጥ እንደ አንድ ሰነድ ይጠቀሳሉ፡፡ ስለ ጉዳዩ ጠለቅ ያለ ዕውቀት ያላቸው ግለሰቦች ደግሞ በማኅበረሰቡ ውስጥ ይገኛሉ። ያለውን ነገር ለማውጣት ይፈልጋሉ ግን ደግሞ አቅም ያጣሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የሀገራቸውን ባሕል ተኮር ጥበባትን አውጥቶ የማሳየት ፍላጎት ያላቸው ባለሙያዎችም ሆኑ ባለሀብቶች በውጭና በአራቱም ማዕዘናት ይገኛሉ፡፡ ችግሩ ግን ያ ነገር ደጃቸው ድረስ ካልመጣ በስተቀር አስሶ ማግኘቱን አይታትሩበትም። እንግዲህ ሻጭና ገዢ ሳይገናኙ…የሚባለው ለዚህ ዓይነቱ ነው፡፡

አሁን ለእይታ የደረሰው “አቴቴ” ዘጋቢ ፊልም ታሪክና መነሻውን መሠረት አድርጎ የተነሳው በኦሮሚያ የገዳ ሥርዓት ውስጥ በሚገኘው የስንቄ ባሕል ቢሆንም ቅሉ የመላው ኢትዮጵያ አንደኛው ትውፊት ነው፡፡ እንደ ኦሮሞ ማኅበረሰብ ቢሠራም ዓለም የሚመለከተው ግን እንደ ኢትዮጵያ ነው፡፡ አቴቴ ማለት በኦሮሞ አልፎም በኢትዮጵያ የባሕል ጥበብ የተወለደችና የወለደች እናት ናት፡፡ ስንቄ ከገዳ ባሕልና ወግ ለእናት የተበረከተና የትውልድ ስንቅ የሆነ ዘንግ ነው፡፡ ስንቄ የሰላም ጦር ነው፡፡ ስንቄን የያዘች እናትም እውነተኛ የሰላም አምባሳደር ናት፡፡

መቼቱን በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በሚገኝ የተፈጥሮና ጥንታዊ የባሕል ክዋኔ ላይ በማድረግ በዋናነትም የአቴቴን ወይንም የስንቄን ሥርዓት ያንጸባርቃል፡፡ በገዳ ውስጥ አቴቴ፣ በአቴቴ እጅ ደግሞ ስንቄ አለ፡፡ አቴቴ የመጀመሪያው ባለ ስንቄ ለመሆን የበቃች እናት ናት፡፡ ይህቺ እናትም ያንን ዘንግ ከትውልድ ትውልድ ለሴት ልጇ ስታወርስ ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡ “ስንቄ” ልዩ በሆነ ማንነት ባሕልን ከሥነ ጥበባዊ ትውፊት ጋር አቆራኝቶ የያዘ በትር ነው፡፡

ስንቄ ሁልጊዜም ቀጥ ያለና ቀጭን ነው፡፡ እንዲህ ለመሆኑ የራሱ የሆነ ምክንያትም አለው፡፡ ቀጥ ማለቱ ቀጥተኛዋን እውነትን የሚያመለክት ሥነ ጥበባዊ ውበት ነው፡፡ እውነት ብትቀጥንም አትበጠስምና መቅጠኑም ለዚሁ ነው፡፡ ስንቄ ከእንጨት የተሠራ ቀጭን በትር ብቻ አይደለም፡፡ በባሕልና ሥነ ጥበብ፣ በእደ ጥበብና የታሪክ ቀለማት አሸብርቆ ውበት የፈሰሰበትም ነው፡፡ “አቴቴ አያና ሐዎታ” መሠረት ያደረገው በገዳ ሥርዓት ውስጥ ያለውን የእናቶችን ብሎም የሴቶችን ሚናና ከፍተኛ የሆነ ተፈጥሯዊ የስልጣን ኃይል እንዳላቸው የሚያሳይም ጭምር ነው፡፡ ፊልሙን ሠርቶ ለማጠናቀቅ ሁለት ዓመታትን የፈጀ ሲሆን 4 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበታል። በሮብሰን ዋቤ ዳይሬክት ተደርጎ በተሰናዳው በዚህ ዘጋቢ ፊልም ሌሎች እውቅ የፊልም ባለሙያዎችም ዐሻራቸውን አኑረውበታል፡፡ ከመቶ በላይ የሆኑ ሰዎች ተሳትፈውበታል፡፡ በቅድመ ዝግጅቱም ሆነ በፊልሙ ውስጥ በዋናነት የታሪክ ባለቤት የሆኑትን የስንቄ እናቶችን አስቀድሟል፡፡ ዘጋቢ ፊልም እንደመሆኑ ታሪካዊው ታሪክ እንዳይፋለስ እውቅ የታሪክና ጥናት ተመራማሪዎች፣ የአባገዳ አባቶችንና ሌሎችንም ያሳተፈ ቅድመ ጥናታዊ ምርምሮች ተካሂዶበታል፡፡

የራስን ጥሎ የሰው አንጠልጥሎ… ለምን? እኛ የማይነጥፍ ባሕል አለን፡፡ ጥበብ አለን፡፡ ግን ከምናውቀው የማናውቀው፣ ከምንጠቅምበት የማንጠቀምበት ልቆ ይገኛል፡፡ እንደ ሀገራችን የኪነ ጥበብም ሆነ ሥነ ጥበብ ታሪክ ማሽቆልቆል የፈጠነው ባሕላዊ ትውፊቶቻችንን ቸል ማለት ስናበዛ ነው፡፡ የኛ ጥበባት ያለ ባሕላዊ ትውፊቶቻችን ህልውና የሌላቸው ባዶ ጣሳ ናቸው፡፡ አንዳችም ሳይዝ በነኩት ቁጥር ሁሉ ሲንቋቋ ይኖራል፡፡ የረገጠው ሁሉ ያጨማድደዋል። የመጣ ንፋስ ሁሉ እየገፋ ይወስደዋል፡፡ ከጥበባት ውድቀት በፊት የቀደመው የባሕል ውድቀት ነው። ባሕል በወደቀበት ቅጽበት ጥበባት ይሰበራሉ፡፡ ዛሬም ድረስ በውል ያላጤነው ነገር ይኼው ነው። ለምንድነው ኪነ ጥበባት የቀዘቀዙት? … ሥነ ጥበባትስ ለምን ተዳከሙ? የምንል አብዛኛዎቻችን ስለ ባሕልና ወጎቻችን አናነሳም፡፡ የችግሩን ህብለ ሠረሰር ስላልጨበጥነው ምላሽና መፍትሔውም እንቆቅልሽ ሆኖ ይቀጥላል፡፡

በባዕድ አምልኮ ስም መርገው እንዲያስጠላን ካደረጉን በኋላ ባዕዳን ለራሳቸው ወስደው ዛሬ የሚዘንጡባቸው በርካታ ትውፊታዊ ጥበባት እነርሱ ጋር አለን፡፡ ነገሩ “ሊበሏት የፈለጓትን አሞራ ጅግራ ናት ይሏታል” እንደሚባለው ነው፡፡ ምራቅ የዋጡባቸውን ነገሮች በሙሉ እንዴት አስቀያሚና ጸያፍ እንደሆኑ ነግረውናል፡፡ አምነን በራቅናቸው ቁጥር አብደን እንደ ጨርቅ ጥለናቸዋል፡፡ የተቀሩትም በጥቂቶች እምቢታ ተርፈው ለዚህ በቁ እንጂ ዛሬ ላይ የምናወራለት ምንም ባሕል፣ ምንም ጥበብ አይኖረንም ነበር፡፡ “አፍንጫ ሲመታ ዓይን ያለቅሳል” ነውና ባሕል ሲነካ ጥበብ መጮህ አለባት፡፡ አለበለዚያ ለአንደኛው የመጣው ደራሽ ጎርፍ ሁሉንም ጠራርጎ ይሄዳል፡፡ ባሕልና ጥበብ ሥጋና ደም አንድ ናቸው፡፡ የሰው ልጅ ሰው ሆኖ የሚቆመው በሥጋና ደሙ ነው፡፡ ሀገር ለመቆም የምትችለው በባሕልና ጥበብ ነው፡፡ ባሕል ሲነካ ጥበብ ትደማለች፡፡ ጥበብ ስትደማ ባሕል ትቆስላለች። በመጨረሻም በሁለቱ የቆመች ሀገር ወደፊት በግንባር ተላትማ ትዘረራለች፡፡

አቴቴ አምልኮ ወይንስ የባሕል ጥበብ? የአንዳንዱ አንዳንድ ነገር… የተሳሳተ ሀዲድ፣ የተሳሳተ ባቡር ነው። በዚህ መስመሩን ጥሶ ባለፈ ባቡር እየተሳፈሩ፤ የአቴቴ ባሕልና ሥርዓት ሃይማኖታዊ የባዕድ አምልኮት ነው ሲሉ በእሾህ ላይ ተደግፈው ሽንጥ ይገትራሉ፡፡ ይህን ለማስረዳት ሌላ የተለየ ምንም ሳያስፈልግ ይህን ማየት ብቻ በቂ ነው…በገዳ ሥርዓትም ሆነ በስንቄ ውስጥ የሚገኙት ሁሉ የየራሳቸው ሃይማኖት ያላቸው ናቸው። ሙስሊም፣ ክርስቲያን እንዲሁም ዋቄዎችም አሉበት። ወደኋላ መለስ ለማለት ከቻልን አሉባልታው የኛ አይደለም፡፡

ስንቱን በእጅ የያዝነውን ወርቅ እንደ ህጻን እያሞኙ አስጥለውን ዛሬ እዬዬ! ከምንልላቸው ስለምንስ አንማርም? ትናንት ለዛሬ መማሪያ ካልሆነ የትናንት መኖርስ ጥቅሙ ከምኑ ላይ ነው? ይሁንና በአቴቴ የባሕል ሥርዓት ውስጥ ያለው በእናት ወግ የተከሸነ ተፈጥሮ አዘል የባሕል ጥበብ ነው፡፡ ከክረምት ወራት የተፈጥሮ መስተጋብር ጋር የተቆራኘም ነው። እናትነትና የክረምት ተፈጥሮ ሁለቱም አንድ የሚያደርጋቸው ልዩ መስተጋብር አላቸው፡፡ ይሄ ዝናባማ ወቅት ከእናትነት ብሎም ከሴትነት ጋር ያለው ልዩ መስተጋብር በጥበብ አዘል ሴትነት በክረምቱ ወራት ሲገለጥ ያስተዋልን ስንቶች እንሆን…

የሀገሬ የጥበብ ወገብ በለምለም ሳርና ቅጠል መቀነቱን አስራ በአሸንዳና ሻደይ እሽክም! የምትለው ክረምት ላይ ነው፡፡ ክረምቱ ሊያልፍ ምድር በአደይ አበባ ስትንቆጠቆጥ ለመሰነባበቻው በእንቁጣጣሽ አበባየሆሽ ቀጠሮ ይዘው ይገናኛሉ፡፡ እኚህም ሌሎችም ሁሉ ከተፈጥሮ ጋር የተጋመደ የራሳቸው የሆነ ሚስጥራዊ ጥበብ አላቸው፡፡ አቴቴም ከሴትነት ተፈጥሮ ጋር በክረምት መቀነት ከታሰሩ ከእነዚህ ጥበባዊ ትውፊቶች መካከል አንደኛው ነው፡፡ የአቴቴ ሥርዓት በተፈጥሮ ውስጥ የእናትነትንና የሴትነትን ጥበብ መከወኛ እንጂ እንደ አንዳንዶች አሉባልታ ሃይማኖታዊ የባዕድ አምልኮ አለመሆኑን ራሳቸው ስንቄዎቹ ይናገራሉ፡፡ “ከባለቤቱ በላይ ያወቀ ቡዳ ነው” የሚለውን አባባል በማሰብ እውነታውን ለባለቤቱ ብቻ እንስጠው፡፡ “…ኢትዮጵያ ወደ ራሷ ባሕል ስትመለስ ሰላሟም ይመለሳልና ጥሩ ባሕል ብቅ ሲል ጭንቅላት የሚመቱትን እንቃወማለን!” ያሉትም የስንቄ እናቶችን በመወከል በፊልሙ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተሳተፉ አንድ እናት ነበሩ፡፡

በገዳ ሥርዓት ውስጥ የሚገኘው የአቴቴ ስንቄ ትውፊታዊ ባሕልና ተፈጥሮ መራሽ ጥበብ ነው፡፡ በተፈጥሮ መስተጋብር በሚካሄደው ባሕላዊ ሥርዓት ውስጥ አብዛኛዎቹ የሚገለጹት በትውፊታዊ ክዋኔዎች ነው፡፡ በክዋኔዎቹ ውስጥ ደግሞ ኪነ ጥበብና ሥነ ጥበብ ነብስ ዘሪ ናቸው፡፡ በእያንዳንዱ ሥርዓት ውስጥ እነዚህን ነገሮች እንደ ማጣፈጫ ቅመም ተነስንሰው እናገኛቸዋለን፡፡ በገዳ ውስጥ ያለው የስንቄ ባሕል ለመለመ ማለት በተዘዋዋሪ ጥበባት አደጉ ማለት ነው፡፡ ጥቂት ለማሰላሰል ከዳዳን ሀገራችን ወደ አዘቀጡ መንደርደር የጀመረችው ስንቄን የመሳሰሉትን ከተውንበት ጊዜ አንስቶ ነው፡፡ እርስ በርስ ለመበላላት ጥርስ ያበቀልነው ተፈጥሮንና ጥበብን ከባሕል ጋር አዋህደን መብላት ካቆምንበት ጊዜ ይነሳል፡፡

ምን ሁከት ተነስቶ ለያዥ ለገናዡ፣ ለአዋቂ አዛውንቱ እዝጎ! አሻፈረኝ ቢል፤ አንዲት ስንቄን በእጇ የጨበጠች እናት ወጥታ ድምጽዋን ያሰማች እንደሆን ግን እየተርበደበደ እግሯ ስር ይደፋል፡፡ ጥበባዊ የሰላም ኃይል ያላትና ያለው ሥርዓት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ስንቄ የሴቶች የፍትህና የነፃነት አርማ ነው፡፡ ከየትም ትምጣ፣ የትም ተወልዳ የትም ትደግ አንዲት በማኅበረሰቡ ውስጥ የምትገኝ ሴት መብቷ ተጥሶ በደል የደረሰባት እንደሆን አቴቴ ስንቄዋን ይዛ ትቆምላታለች፡፡ ዘንጓን ከፍ አድርጋ ስለ ነፃነቷ ትሟገትላታለች፡፡ “ሰላም ለሀገሬ! ሰላም ለሕዝቤ! ሰላም ለቤቴ!” ሰላም…ሰላም….ሰላም! ይሄ የስንቄዎቹ የአቴቴ ህብረ ዜማ ነው፡፡ ዘጋቢውን ተመልክተን የተዘጋውን ሌላም እንክፈት፡፡ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ባሕሏን በጥበብ ይዘን አምሯል ሸገኑ! እንበል፡፡

እቴ ሜቴ! እቴ ሜቴ!

ሆኗል ይሁን ከአቴቴ፤

በሀገሬ …

ጥበብ ሞልቷል ከእናቴ፡፡

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን መስከረም 9/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You