ጊፋታ- አብሮነት የሚደምቅበት የዘመን መለወጫ

ኢትዮጵያውያን በመስከረም ወር ከጫፍ እስከጫፍ ይደምቃሉ። ወሩ አዲሱን ዓመት በተስፋ ለመቀበል የሚያስችላቸው ብሩህ ተስፋ የሚሰንቁበት ነው። የዓመቱ የመጀመሪያ ወር በሆነው መስከረም የእያንዳንዱን ማሕበረሰብ እሴት አጉልተው የሚያሳዩ በርካታ በዓላት በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች ይከበራሉ። እነዚህ በዓላት ኢትዮጵያ በማሕበረሰብ እሴቶች የደመቀች፤ በአገር በቀል አውቀቶችና ልምዶች የካበተች መሆኗን ያመላክታሉ።

የዛሬው የቱሪዝም ገፅ አምዳችን ከእነዚህ የማሕበረሰብ እሴቶች ውስጥ አንዱ የሆነውን የወላይታ ብሔረሰብ የአዲስ ዘመን መለወጫ የጊፋታ ክብረ በዓልን ያስቃኘናል። የአዲሱ የደቡብ ክልል የወላይታ ዞን የባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ገዛኸኝ ተሾመ ክብረ በዓሉንና እያንዳንዱን ባሕላዊ ክንውን አስመልክተው እንደገለጹልን፤ የወላይታ ማሕበረሰብ የአዲስ ዘመን መለወጫ ጊፋታ በዓል ከአሮጌው ዓመት ወደ አዲሱ ዓመት ሽግግር የሚደረግበት ነው፡፡

ጊፋታ የሚለው ቃል ታላቅ ወይም የመጀመሪያ የሚል ትርጉም እንዳለው ኃላፊው ጠቅሰው፣ የመስከረም ወርም (ጊፋታ አግና) የሚል ስያሜ እንዳለው ያስረዳሉ። ‹‹ጊፋታ በወላይታ ሕዝብ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ከዘመን ዘመን የምንሸጋገርበት ክብረ በዓል ነው›› የሚሉት የመምሪያ ኃላፊው፤ ከሌሎች መሰል በዓላት የሚለየው አከባበሩ በሚጀመርበት ቀን መሆኑን ይገልፃሉ። የጊፋታ አከባበር ስነ-ስርዓት የሚጀመረው ከሰኔ ወር መጨረሻ ጀምሮ መሆኑን የሚያስረዱት ኃላፊው፤ ሴቶች፣ ወንዶች፣ ወጣቶች የተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚደረጉ ይገልጻሉ። በዓሉ ከመድረሱ ከ15 ቀናት በፊትም ታዋቂ ገበያዎች (ቦሾ፣ ቃዬ እና ሌሎችም ስያሜ ያላቸው) እንደሚካሄዱም ይገልፃሉ።

እንደ መምሪያ ኃላፊው ማብራሪያ፤ በእነዚህ የገበያ ቀናት እናቶች ከሰኔ ወር መጨረሻ አካባቢ ጀምሮ ለተለያዩ ባሕላዊ ምግቦች የሚያገለግሉ /ማለትም “ለቆጮ፣ ለሙቹዋና ለባጪራ” በመባል ለሚታወቁ ባሕላዊ ምግቦች የሚሆኑ የደረሱ እንሰቶችን ከጓደኞቻቸውና ከሴት ልጆቻቸው ጋር ሆነው በመፋቅ ዝግጅት ያደርጋሉ። ለዝግጅቱ የሚረዳቸውንም ቁሳቁስ ወደ ገበያ በማውጣት ይሸምታሉ። በዚህም ዳጣ በርበሬን፣ የተለያዩ መጠጦች ማለትም ቦርዴ፣ ጠላ፣ ጠጅ፣ ቃሪቦ እንዲዘጋጅ ያደርጋሉ፡፡

በተጨማሪ “ጋዚያ” በመባል ለሚታወቀው ባሕላዊ ጨዋታ የሚሆን ሎሚ ገዝተው በቀዝቃዛ ቦታ ያስቀምጣሉ፤ የተለያዩ መዋቢያ ጌጣጌጦችን ይገዛሉ፤ ለምግብነት የሚውሉ የተለያዩ የእህል ዓይነቶችን ገዝተው ያጠራቅማሉ፡፡ ስነ-ስርዓቶቹ ለማሕበረሰቡ የማንነቱ መገለጫዎች ለመላው ኢትዮጵያውያንም የአብሮነትና የአንድነት ተምሳሌት እንደሆነ ይናገራሉ። ከዚያ ባሻገር በቱሪዝም ዘርፉ ላይ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር በዓል መሆኑንም ያብራራሉ።

የባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊው እንደሚናገሩት፤ የወላይታ አባቶች በጊፋታ ወቅት የራሳቸው ሚና አላቸው። ከዚህ ውስጥም የተለያዩ የምግብ ዓይነቶችን በዘር ወቅት መዝራት፣ መሰብሰብና ለጊፋታ ለይቶ ማስቀመጥ፣ በዓሉ ሲቃረብ ለልጆች አዳዲስ ልብሶችን መግዛት፣ ለማጣፈጫና ለቅመማ ቅመም መግዣ የሚሆን ገንዘብ ለእናቶች መስጠት እና ለጊፋታ የሚታረድ በሬ መግዛትና እርድ ማከናወን የአባወራ ተግባራት ናቸው፡፡

የወላይታ ማሕበረሰብ የጊፋታ በዓል የሚውልበትን ቀን የሚወሰንበት የራሱ የዘመን መቁጠሪያ እንዳለው የሚናገሩት አቶ ተሾመ፤ በዚህ ባሕላዊ የዘመን መቁጠሪያ መሰረት በዓሉ ሁሌም እሁድ ቀን እንደሚከበር ይገልፃሉ። በዚህም ምክንያት በመስከረም ወር ከ8 እስከ 14 ባለው ቀን ላይ የሚውለው እሁድ የማሕበረሰቡ የዘመን መለወጫ (ጊፋታ) የሚከበርበት መሆኑን ያስረዳሉ። አባቶችም ጨረቃን አጥንተው፣ የፀሀይ ኡደትን ተመልክተው ይህ የጊፋታ በዓል የሚውልበትን ቀን በመለየት ሕግ እንዲፈፀም የራሳቸውን ድርሻ አንደሚወጡም ይገልፃሉ።

የባሕልና ቱሪዝም መምሪያው ድርሻ

የወላይታ ዞን የባሕልና ቱሪዝም መምሪያ የጊፋታ በዓልን ለማክበር ሁሌም በየዓመቱ ትልቅ ዝግጅት እንደሚያደርግ የሚናገሩት ኃላፊው፤ በዋናነት ጊፋታ ቀጣይነት ኖሮት ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ አንዲከበር ለማድረግ እንደሚሰራ ይገልፃሉ። አስተዳደሩም የማሕበረሰቡ ባሕል ቋንቋ ተጠብቆና ለምቶ አንዲቀጥል ለማድረግ ጊፋታን የመሳሰሉ እሴቶች ጠቃሚ መሆናቸውን በማመኑ ይህንኑ ስነ ስርዓት ለማስቀጠል እየሰራ መሆኑን ያስረዳሉ።

ባለፉት ሁለት ዓመታት ጊፋታ በደማቅ ሁኔታ ሊከበር ስለመቻሉ የገለፁት አቶ ተሾመ፤ በዞኑ በሚገኙ 18 ወረዳዎችና 7 የከተማ መዋቅሮችና በሁሉም አካባቢዎች የበዓሉ እሴቶች፣ ቱባ ስነስርዓቶቹን በጠበቀ መልኩ መከበሩን አስታውሰዋል።

ጊፋታ ለቱሪዝም

በኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ የማይዳሰሱ ባሕላዊና ኃይማኖታዊ እሴቶች አሉ። እነዚህ እሴቶች ከማሕበረሰቡ ማንነት መግለጫና ዓመታዊ በዓላት ባለፈ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ጎብኚዎችን በቱሪዝም ዘርፍ የመሳብ አቅማቸው ከፍተኛ ነው። የጊፋታ በዓልም ይህንን መስፈርት እንደሚያሟላ ባሕላዊ ክብረ በዓሉን በሳይንሳዊ መንገድ ለማጥናት የሞከሩ ባለሙያዎች ይገልፃሉ።

ይህንን እሳቤ አስመልክቶ የወላይታ ዞን ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ሲገልፁ፤ እንደ አገርም ይሁን እንደ ወላይታ ዞን አስተዳደር ትልቅ ትኩረት ካገኙ ዘርፎች መካከል አንዱ ቱሪዝም መሆኑን ገልፀው፤ ጊፋታ በቱሪዝም እንዲመጣ ቢደረግ የሚፈለገውን እድገት ለማጠናከር ትልቅ ሚና መጫወት እንደሚችል ይናገራሉ። በዚህ ምክንያት የወላይታ ባሕል የሆነው ጊፋታ ከማይዳሰሱ የሰው ለጅ ወካይ ቅርሶች ዝርዝር በዓለም አቀፍ ደረጃ በዩኔስኮ እንዲመዘገብ ስራ ከተጀመረ መቆየቱን ያነሳሉ።

‹‹ጊፋታ በዩኔስኮ ሲመዘገብ ከብሔራዊ ቅርስነት አልፎ የዓለም ቅርስ ይሆናል›› የሚሉት የመምሪያው ኃላፊ፤ ይህንን ተከትሎ ጎብኚዎች በዓሉ በሚከበርባቸው ቀናት ወደ አካባቢው በመሄድ ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ ምዝገባው መደረጉ አስተዋፆው ከፍተኛ እንደሚሆን ያስረዳሉ። የዞኑ አስተዳደር ይህ የጊፋታ በዓል አንዱ የቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆን፣ ማሕበረሰቡም በዓሉን ተከትሎ በሚመነጨው ኢኮኖሚ እንዲጠቀም ትኩረት ሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በዓሉ ሲከበር ከልዩ ልዩ የዓለማችን ክፍሎች፤ ከኢትዮጵያ ሁሉም አቅጣጫዎች በዓሉ በሚከበርባቸው የዞኑ አካባቢዎች ጎብኚዎች እንደሚገኙና በጋራ ከማሕበረሰቡ ጋር እየተዝናኑ እንደሚያከብሩ የሚናገሩት የመምሪያው ኃላፊ፤ በልዩ ሁኔታ በጊፋታ ወቅት በወጣት፣ በሴት ልጅ አገረዶች እና በሁሉም የብሔሩ ተወላጆች የሚካሄዱ ደማቅ ዝግጅቶች ላይ በመገኘት እነርሱ ከሚያውቁት የተለየ ልምድ እውቀትና አዝናኝ ሁነቶች ገብይተው እንደሚመለሱ ያስረዳሉ። ይህንን ልምድ በየዓመቱ በማሳደግ የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምርና የጊፋታ ክብረ በዓልም የወላይታ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም የሚገኙ የሰው ልጆች በጉጉት የሚጠብቁት ለማድረግ እየተሞከረ መሆኑን ገልፀውልናል።

በዘንድሮው የጊፋታ ክብረ በዓል ላይም ከዚህ ቀደም ይገኝ ከነበረው ጎብኚ ቁጥር ከፍያለ አሀዝ እንዲመዘገብ በልዩ ልዩ የመገናኛ አማራጮች የማስተዋወቅ ስራ እየተከናወነ መሆኑን የሚያነሱት አቶ ተሾመ፤ ከዚህ ባሻገር ባሕላዊ ስነስርዓቱ ዓለም አቀፍ እውቅና ከዩኔስኮ እንዲቸረው የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲም የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል። በተለይ በእጩነት እንዲቀርብ ሰነዶችን ከማዘጋጀት ጀምሮ የሚያስፈልጉትን ጥናቶች በማድረግ አሁን ላይ የመጨረሻው ደረጃ ላይ መድረሱን ዩኔስኮም ጉዳዩን ለመመርመርና ለማፅደቅ እየሰራ መሆኑን ይገልፃሉ።

‹‹ጊፋታ በዩኔስኮ አውቅና አግኝቶ ሲመዘገብ የወላይታ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያና የዓለም ቅርስ ሆኖ ነው›› የሚሉት የመምሪያ ኃላፊው፤ ይህ ስኬት ቢገኝ በማይዳሰስ ቅርስ አያያዝ፣ ጥበቃ፣ ማስተዋወቅና ልማት ላይ ጉልህ አስተዋፆ እንደሚኖረው አስረድተዋል። የዘንድሮው ጊፋታ ክብረ በዓልም ይህንን መስፈርት ሊያሟላ በሚችል መልኩ ለማክበር ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል። የንቅናቄ መድረኮችን በማካሄድም ያለ ሀይማኖት፣ ያለ ጎሳ እንዲሁም ዘርና ቀለምን ሳይለይ ለማክበር ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን ነግረውናል።

ጥቂት ስለ ባሕላዊ ስርዓቱ

በወላይታ ጊፋታ ባሕላዊ አከባበር ዙሪያ ጥናት ያደረጉት፣ የዞኑ ተወላጅ፣ የባሕልና ታሪክ ተመራማሪ የሆኑት አቶ አዳነ አይዛ ጊፋታ ከመከበሩ አስቀድሞ ስለሚደረጉ ዝግጅቶች እንዳስታወቁት፤ ወላይታዎች ሳምንታትን የሚቆጥሩት በአካባቢው የሚውለውን ትልቁን ገበያ መነሻ በማድረግ ነው። ጊፋታ የሚውልበት ቀን የሚታወቀውም በዚህ ባሕላዊ የዘመን አቆጣጠር ነው።

በዚህም የወላይታ አባቶች ከአንዱ የገበያ ቀን እስከሚቀጥለው የገበያ ቀን ያለውን ጊዜ እንደ አንድ ሳምንት እንደሚቆጥሩት ያስረዳሉ፡፡ ይህም አንድ ወይም ሁለት ገበያ ማለት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ይህንን ጥበብ በምሳሌ ሲያስቀምጡት፤ በአንድ አካባቢ የሚውል ትልቁ ገበያ ቅዳሜ ከሆነ እስከሚቀጥለው ቅዳሜ ድረስ ያለውን ጊዜ የመጀመሪያውን ቅዳሜ አንድ ብሎ ቀጥሎ በሳምንቱ የሚመጣውን ቅዳሜ ሁለት በማለት ሁለት ገበያ በማለት እንደሚጠሩት ያብራራሉ፡፡ በዚህም መሠረት አምስት ገበያ አንድ ሙሉ የጨረቃ ኡደት አንድ ወር መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ጨረቃዋ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየችበትን ቀን አንድ ብሎ መቁጠር እንደሚጀምሩ ነው የሚገልፁት፡፡

እንደ አቶ አዳነ ገለፃ፤ በዓሉ ከመድረሱ አስቀድሞ ከሚከናወኑ ባሕላዊ ስነ ስርዓቶች መካከል እማወራዎች ለጊፋታ በዓል ከሚያደርጉት ዝግጅቶች የመጀመሪያው ቁጠባ መሆኑን ይናገራሉ። ይህ ቁጠባም የቅቤ እቁብ እየተባለ እንደሚጠራም ይገልፃሉ። በዚህም መሰረት ዓመቱን በሙሉ የቆጠቡትን በጊፋታ ሰሞን ሁለተኛ ሳምንት ገበያ አጥቢያ በቅቤ ዕቁብ ሰብሳቢዋ ቤት የቅቤ ቡና ከጠጡ በኋላ የየድርሻቸውን ተከፋፍለው ይወስዳሉ፡፡ ጊፋታ ካለፈ በኋላም ለቀጣይ ዓመት በየሳምንቱ ቁጠባው እንደሚቀጥል ይገልፃሉ፡፡

ሌላው የበዓሉ ድባብ የመንፃት ስነስርዓት እየተባለ የሚጠራው መሆኑን ይናገራሉ። በዚህም በወላይታ ነባር ባሕል የዘመን መለወጫ በዓሉ እንደነገ ሊከበር (እኩለ ሌሊት ላይ) ሁሉም የማሕበረሰቡ አባላት ‹‹ከአሮጌው ዓመት እድፍና ቆሻሻ ጋር አዲሱን ዓመት አንቀበልም›› በሚል እምነት ውሃ አሙቀው ገላቸውን ይታጠባሉ፡፡ ምክንያቱም ወላይታዎች ሁልጊዜ አዲሱን ዓመት የሚቀበሉት በሽታ፣ ረሃብ፣ ድርቅ የሌለበት መልካም ዝናብ የሚጥልበት፣ መልካም ነፋስ የሚነፍስበት፣ የጥጋብ ዓመት እንዲሆን ካለፈው ዓመት ሃጥያት መንጻት አለብን ብለው ስለሚያምኑ መሆኑን አቶ አዳነ ይናገራሉ፡፡

ለሕዝቡ አዲስ ዓመት ሁል ጊዜ አዲስ ተስፋ ይዞ ስለሚመጣ ንፁህ ሆነን መቀበል አለብን የሚል የፀና እምት በወላይታ ማሕበረሰብ ዘንድ አለ ሲሉም ያብራራሉ፡፡ መልካም የአዲስ ዘመን መለወጫ (ጊፋታ) በአል!!

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን መስከረም 7/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You