እፎይ

ለምን እንደሆነ አላውቅም አራት ሰዓት አለፍ ሲል ይደብተኛል፡፡ ድብርቴን የምሸሸው የሆረር ፊልም በማየትና በደረቴ በመተኛት ነው፡፡ የዛሬውም አራት ሰዓት እንደተለመደው ምርግ ነበር፡፡ አብሮኝ ከሚኖረው ፊታወቅ ጋር አዋተን በገዛናት ፍራሽ ላይ በደረቴ ተኝቼ የረፋድ ድብርቴን አጎንብሼ አሳልፋለሁ፡፡ በጣቴ መሬት እየጫርኩ የማላውቀውን ነገር ሚዲያው ላይ እጽፋለሁ። በዚህ መሐል ስሜን ከውጪ ሲጠራ ሰማሁት..ሮቤል? አንተ ሮቤል?

ነፍሴ ሳቀች..ጀምበር ፈንጥቃ ስፍራዋን ለረፋድ ስትለቅ ማንም የማያስቀኝ ሰው ነበርኩ፡፡ ከሰዓት እስኪሆን ማለዳ በጉያው ውስጥ የሸሸገው የአራት ሰዓት አጋንንት ከላዬ ላይ ጮሆ እስኪወጣ ድረስ ማንም የማያዝናናኝ ሰው ነበርኩ፡፡ ለዘመናት የተላመድኩት ድባቴዬ የት እንደገባ ሳላውቀው በሄመን ድምፅ ነቃሁ። ‹ሮቤል..አንተ ሮቤል? ድምፅዋ ወዳለሁበት እየቀረበ መጣ፡፡ ከአልጋዬ ላይ እንዴት እንደተፈናጠርኩ አላውቅም ራሴን በሩ ላይ አገኘሁት። እኔ ስወጣ እሷ ስትገባ ተጋጨን፡፡ መቼም የማይደገም ግጭት። አይኖቼን የት ላድርጋቸው? አፈርኳት፡፡ ፊት ለፊቴ በግንባሬ የተገጨ ግንባሯን እያሻሸች ቆማለች። ዓይኖቿ የእፍረት ዝናር ታጥቀው ያዩኛል፡፡ ጡቶቿ በስስ የቤት ውስጥ ፒጃማ ተወድረው ደረቴ ላይ ተነጣጥረዋል። ከንፈሯ ሩብ ያህሉ በጥርሶቿ በቄንጥ ተነክሶ ተደቅኖብኛል፡፡ አይኖቼን የት ላድርጋቸው?

መደናበሬን አይታ ይሆን እንጃ ‹ቤት ማንም የለም ናና ተጫወት› ብላኝ ወደ ቤት ተመለሰች፡፡

ከበሩ ላይ አልተንቀሳቀስኩም፡፡ ፊልም የሚመስ ለውን አጋጣሚ በአዕምሮዬ እየመለስኩ ቆሜአለሁ። ቆይቼ ሳስበው ከመጋጨትም በላይ የሆነ ነገር ያስተናገድን ይመስለኛል፡፡ ደረቴ ላይ አሁንም ድረስ የሚሰማኝ ደስ የሚል የውጋት ሕመም አለ..በጡቶቿ የተወጋሁት፡፡ ጉንጬ ላይ ፀጉሯ የገረፈኝ አንዳች የሚያክል ሰንበር አለ፡፡ ራሴን በመስተዋት ሳየው ቀይ የከንፈር ቀለም ከንፈሬ ላይ ተለጉዶ ነበር፡፡ ይሄ እንዴት ሆነ? ደስ የሚል የሚያሳፍር ሳቅ ሳኩኝ፡፡ ሰው እንዴት በአንድ ጊዜ ደስ የሚልና የሚያሳፍር ሳቅ ይስቃል? ሄመንን አፈርኳት፡፡ መንገድ ላይ ስንገናኝ ለመሳሳም የተቀጣጠርን እንጂ ለመጋጨት የተገናኘን አንመስልም ነበር፡፡

አንዳንድ ቀኖች አሉ..የሰው ልጅ አስቦና ተዘጋጅቶ የማይደግማቸው፡፡ አንዳንድ አጋጣሚዎች አሉ እንዴት እንደመጡ፣ እንዴት እንደሆኑ ታስቦ የማይደረስባቸው። ከሄመን ጋር የተጋጨንበትን የዛሬውን ቀን ጻፍኩት፡፡ መቼም እንዳይረሳኝ ስለምፈልግ፡፡

እፎይ ብያለሁ..መቼም እንደዛሬ እፎይ ብዬ አላውቅም፡፡ አንዳንድ ድምፆች አሉ ከሕይወት እስራት፣ ከመኖር ስብራት ነፃ የሚያወጡ፡፡ አንዳንድ አንደበቶች አሉ ከካህን አፍ ጥመው ለጆሮ የሚጣፍጡ፡፡ አንዳንድ ቀኖች አሉ ሚሊዮን ዘመነ ፍዳን ሽረው አርነት የሚያወጡ፡፡ እንዲህ ባለው የድባቴ ጊዜ ውስጥ ድንገት ተከስተው ወደ ገነት የሚወስዱኝ አንዳንድ ድምፆች አሉ..የሄመንን አይነት ድምፅ፡፡ ነፍሴ ሳቀች፡፡ በሕይወት ውስጥ ነፍስ የምትስቅበት ቅጽበት አለ እላለሁ..ለእኔ ያ ቅጽበት የሄመን ጥሪ ነው፡፡ ለእኔ ያ ቅጽበት ቆንጆ ሴት በርህን ቆርቁራ ካለህበት ስትመጣ ነው፡፡ ዓለም ከነግሳንግሷ ከፊቴ ላይ ገለል ያለችልኝ ሄመን ስትጠራኝ ነው፡፡

ተነስቼ ወደነሄመን ቤት ሄድኩ፡፡ ሁሌ እንዲህ እንደአሁኑ ቤት ብቻዋን ስትሆን ትጠራኛለች፡፡ እንደ እኔ አራት ሰዓት ይደብራት ይሆን አላውቅም ብዙ ቀን ደብቶኝ በተኛሁበት የአራት ሰዓት ማግስት ላይ ጠርታኝ ቤት ሄጄ አውቃለሁ፡፡ እነሄመን ቤት ከተከራየሁ ስምንተኛ ወሬን ይዣለሁ፡፡ በወር አንድ ጊዜ የሚመጣ ፊታወቅ የሚባል ጓደኛ ቢኖረኝም አብሮኝ እንዳለ አልቆጥረውም፡፡ እሷም ይሄን ብቸኝነቴን ስለምታውቅ ነው መሰለኝ ቤተሰቦቿ ወጣ ሲሉ መጥህ ተጫወት ብቻዬን ነኝ ትለኛለች፡፡

ቤት ስገባ ለስለስ ያለ ሙዚቃ ተቀበለኝ..ዛሬም ሚኪያ እየዘፈነች ነው፡፡ ሁሌ እዛ ቤት ጠርታኝ ስሄድ በሚኪያ በላይነህ ሙዚቃ ነው የምትቀበለኝ።

እዛ ቤት የሚኪያ በላይነህ መብዛት አልገባህ እንዳለኝ ወደ ሳሎን አቀናሁ፡፡ ሄመን ከሙዚቃው ጋር አብራ እየሞዘቀች ቅድም በተላተምኩበት ፒጃማዋ አገኘኋት።

‹ምነው ብቻሽን..እነማዘር የት ሄደው ነው? አልኳት ድምፄን አጥፍቼ ከምገባ ብዬ፡፡

‹ማዘር ክፍለ ሀገር ሄዳለች…

‹እና ብቻሽን ነሻ!..

‹አዎ ሰሞኑን ብቻዬን ነኝ…› አለችኝ በሚያሳዝን ድምፅ፡፡ ድምፅዋ ውስጥ ከብቸኝነት የገዘፈ ሌላ ብቸኝነትን አደመጥኩ፡፡ እኔ ሆኜ እንጂ ፊታወቅ ቢሆን ከዚህ ንግግሯ ውስጥ ብዙ እውነቶችን መዞ ያወጣ ነበር። ብዙ ጊዜ ነገር አይገባህም ይለኛል፡፡ እሱ ብቻ አይደለም እስከዛሬ የተዋወኳቸው ሴቶች ነገር አይገባህም ሲሉኝ አድምጫለሁ፡፡ የሄመን ‹ሰሞኑን ብቻዬን ነኝ› ማለቷ ከወሬ ባለፈ ምን ማለት እንደሆነ ሳይገባኝ ዝም አልኩ። ወር ሙሉ ከአጠገቤ ሲርቅ ያልናፈቀኝ ጓደኛዬ በዓይኔ ላይ አንጃበበ፡፡

‹አባዬም እንደምታውቀው በሥራ ምክንያት አምሽቶ ነው የሚገባው..› ሳልጠይቃት ነገረችኝ። ይሄን ብላ ትታኝ ወደሚቀጥለው ክፍል አመራች። ምሳ እየሠራች እንደሆነ ከሚሰነፍጠኝ የወጥ ሽታ ተረዳሁ። ማዕድ ቤቱ ከሳሎኑ ፊት ለፊት ስለሆነ እንቅስቃሴዋ ሁሉ ይታየኛል፡፡ እኔ ሳሎን ሶፋ ላይ ሆኜ እሷ ማዕድ ቤት ሆና እስኪበቃኝ ቀላወጥኳት፡፡

ቤት ጠርታኝ የሆነ የምወደውን ነገር ሳታደርግልኝ ቀርታ አታውቅም፡፡ ሁሌም አዲስ ነገሬ ናት፡፡ ማዕድ ቤት በስስ ፒጃማዋ ውስጥ የማይታየኝ ነገር የለም። እንደ ጣዝማ ማር የጠየመ ገላዋ የጠለለ የምንጭ ውሀ ይመስል ነበር፡፡ ቀይ ፓንት፣ ጥቁር ጡት ማስያዣ ደረቷንና ወገቧን ዞረው ሳይ ኃጢየት ተሰማኝ፡፡ እዛ ቤት ስገባ የማያቸው የሁልጊዜም ትዕይንቶቼ ነበሩ፡፡ ብዙ ጊዜ አትገባኝም..የማልረዳት ሴት ናት፡፡ ለምንና እንዴት እንደምታስበኝ ሳላውቅ በምትሆነው መሆን እጨነቃለሁ፡፡ ቆይ አንድ ሴት ለአንድ ወንድ እህት ብቻ መሆን አትችልም? እኛ ወንዶች ሴት ልጅ ለፍቅር ብቻ ነው የቀረበችን ብለን እንድናስብ የሚያደርግ የተሳሳተ ሶፍት ዌር የጫነብን ማነው?

በእጇ ምሳ ይዛ ወደሳሎን ተመለሰች፡፡ የዛሬ አዲስ ነገር አብሬአት ምሳ መብላት ነው፡፡ ከእሷ ጋር ምሳ መብላት ምን እንደሚመስል ዛሬ ላየው ነው፡፡ እስከዛሬ ቤታቸው ሄጄ ብቻዬን ነበር ስበላ የነበርኩት፡፡ ከእሷ ጋር መብላትን በእለተ ሐሙስ ከጌታ ጋር በአንድ ማዕድ ከመቀመጥ ጋር አገናኘሁት፡፡ ሳላውቀው ሄመንን እንደ እህት አምኖ መቀበል እየከበደኝ መጣ፡፡ አውቃም ይሁን ሳታውቅ የምታደርገው ነገር ወደማላውቅ ደስታ እየወሰደኝ ነው፡፡

እጄን አስታጥባኝ የመጀመሪያውን ጉርሻ ወደ እኔ ስትሰነዝር የሆንኩትን አረሳውም፡፡ ጉርሻዋ ብርቅ ሆኖብኝ ለረጅም ጊዜ አላመጥኩት፡፡ ያን ጉርሻ ወደ ሆዴ ሳልሰድ ቀን ሙሉ እያላመጥኩት ብውል በወደድኩ ነበር፡፡ ከዛ በኋላ ያልቆጠርኳቸውን ብዙ ጉርሻዎች አጎረሰችኝ፡፡ ሳላጎርሳት ዝም ብዬ መብላት ጀመርኩ፡፡ ባልተቀየመ ልብ ማጉረሷን ተያያዘችው፡፡

እፎይ አልኩ..

ሕይወት እፎይ ማያ ሲኖራት ምን እንደምትመስል ያን ቀን አወኩ፡፡ ፍቅር የሕይወት ሱስ ነው..ሳላውቀው በምታደርግልኝ ነገር ሄመንን ወደድኳት፡፡ ነፍሷ እፎይ ማያዬ ሆኖ አረፈ..

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን መስከረም 10/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You