ታምራት ተስፋዬ
የአዋሽ – ኮምቦልቻ – ሀራ ገበያ የባቡር መስመር ዝርጋታ የተጀመረው በየካቲት 2007 ዓ.ም ነው፡፡ፕሮጀክቱ ከአዋሽ-ኮምቦልቻና ከኮምቦልቻ- ሀራ ገበያ በሚል በሁለት ምዕራፍ የሚሠራ ሲሆን አጠቃላይ 390 ኪሎ ሜትር ይረዝማል፡፡
በ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚገነባውን ይህ ፕሮጀክት በ2012 ዓ.ም መጨረሻ ለማጠናቀቅ ቢታቀድም ይሕ ግን አልተሳካም፡፡አስቀድሞ ለፕሮጀክቱ ማስፈፀሚያ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆነው ወጪ ከውጭ መንግሥታት በብድር ይገኛል የሚል እሳቤ ቢኖርም ገንዘቡ ግን አልተገኘም፡፡
ከመንግሥት ወጪ እንደሚደረግ የታሰበው ቀሪ ድርሻም በሚፈለገው መጠን ባለመገኘቱም ፕሮጀክቱን ለማስቀጠል አስቸጋሪ ሁኔታዎች ተፈጥረው ነበር፡፡ይህ ውስንነትም የባቡር መስመሩ ግንባታ በሚፈለገው ልክ እንዳይቀላጠፍ ሲጎትተው ቆይቷል፡፡
በአጠቃላይ ከኤሌክትሪክ አቅርቦትና ከካሳ ክፍያ ጋር በተያያዘ በሁለቱም ምዕራፎች የባቡር መስመር ዝርጋታ ስራው ለስምንት ወር ተስተጓጉሎ ቆይቷል፡፡ ይሁን እና በአሁን ወቅትም አዋሽ-ኮምቦልቻ የሚዘረጋው የመጀመሪያው ምዕራፍ ሥራ 99 በመቶ ከተጠናቀቀ ሁለት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ከኮምቦልቻ – ሃራ ገበያ ያለው 122 ኪሎ ሜትር የባቡር መስመር ዝርጋታ አጠቃላይ ሥራ 82 በመቶ ላይ ደርሷል፡፡
በተለይ የአዋሽ ኮምቦልቻው መስመር ሙከራ በማድረግ ለትራፊክ ክፍት ለመሆን ዝግጁ ቢሆንም የኤሌክትሪክ ኃይል ሲጠባበቅ ሥራ መጀመር አልቻለም፡፡ የኃይል አቅርቦት ጥያቄው ያልተመለሰው በገንዘብ አቅርቦት ችግር መሆኑን በተደጋጋሚ ተገልጿል፡፡በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽንና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅራቢው መሥሪያ ቤት መካከል በነበረ እሰጥ አገባም ችግሩ እልባት ሳያገኝ ረጅም ጊዜ እንዲያስቆጥር ምክንያት ሆኖ ቆይታል፡፡
በመጨረሻም ለጉዳዩ መንግሥት ጣልቃ ገብቶ እልባት ሰጥቶታል፡፡ በአዋሽ – ኮምቦልቻ – ሃራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት ቀሪ ሥራ መሸፈኛ የሚሆን ወጪ ከመንግሥት ግምጃ ቤት እንዲሰጥና ለኃይል ማገናኛ መስመሮቹ የሚውል የግዢ ጨረታ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በኩል ወጥቶ ስራው እንዲጀመር ከአንድ ዓመት በፊት ከስምምነት ላይ ተደርሳል፡፡ይህም ሆኖ ፕሮጀክቱ ተጨማሪ ሥራ ሳይከናወን በነበረበት መቀጠል ግድ ብሎታል፡፡
አዲስ ዘመን ጋዜጣም ፕሮጀክቱ የኤሌክትሪክ ረሃብ የገጠመው ለምን ይሆን፣ የኤሌክትሪክ ረሃቡን ለማስታገስ በአሁን ወቅት ምን አይነት መፍትሄ ተቀመጠ የሚል ጥያቄውን በማቅረብ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይልን አነጋግሯል፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን፣‹‹የባቡር ፕሮጀክቱ ወደ ሥራ መግባት ያልቻለው የኤሌክትሪክ ሃይል ባለመኖሩ ሳይሆን ለሃይል ተደራሽነት የሚያስፈልገው መሠረተ ልማት ስላልተሟላለት፣ ስላልተ ዘረጋ ነው››ብለዋል፡፡
የሃይል መሠረተ ልማት ዝርጋታ የሚጠይቀው ወጪ በመክፈል ረገድ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል እና የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አለመግባባት ውስጥ ገብተው እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ ሞገስ፣መንግሥት በጉዳዩ ጣልቃ ገብቶ ፕሮጀክቱ ሲታሰብ ጀምሮ የኤሌክትሪክ መሠረተ ዝርጋታውም አንድ አካል መሆን እንዳለበት አስምሮበት፣ የሚያስፈልገውን ወጪ ለመሸፈን መስማማቱንም አብራ ርተዋል፡፡
የሃይል ማስተላለፊያ መስመሩ የሚሰራው ፒንግ አዎ ግሩፕ የተሰኘ የቻይና ካምፓኒ ነው፡፡ አጠቃላይ ወጪውም አስራ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊየን ዶላር ነው፡፡የማከፋፈያ ጣቢያ፣ሰብ እስቴሽኑ ግንባታ ቲቢኤ የሚባል የቻይና ኩብንያ ነው፡፡ አጠቃላይ ወጪውም አምስት ነጥብ ሦስት ሚሊየን ዶላር ነው፡፡
በአሁን ወቅትም ገንዘቡ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል እንደደረሰው የጠቆሙት አቶ ሞገስ፣እስካሁን ባለው ሂደትም ዲዛይኑን በአግባቡ ከመቃኘት ከመፈተሽ ጀምሮ የአፈር ምርመራና ሌሎች ለቀጣይ ሥራ መደላድል የሚፈጥሩ ስራዎች መሰራታቸውን አብራርተዋል፡፡በአሁን ወቅትም አስፈልጊውን ቅድመ ዝግጅት በማጠናቀቅ ከአንድ ወር በኋላ በግንባታውን ሙሉ አቅም እንደሚጀመር አስታውቀዋል፡፡
የአዋሽ – ኮምቦልቻ – ሀራ ገበያ የባቡር መስመር ዝርጋታ አካል የሆነው ከኮምቦልቻ – ሃራ ገበያ ያለው 122 ኪሎ ሜትር የባቡር መስመር ዝርጋታ አጠቃላይ ስራ 82 በመቶ ላይ ደርሷል፡፡ቀሪውን ሥራ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ቀደም ሲል ተገልጿል፡፡
የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር አብዱልከሪም መሃመድ የባቡር መስመር ዝርጋታ ፕሮጀክቱ በጊዜ መራዘም ምክንያት ተጨማሪ ወጪ እንዳይጠይቅ ባለድርሻ አካላትን በማሳታፍ እየተሰራ ነው ማለታቸው ይታወሳል፡፡
መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ፕሮጀክቱ በቱርኩ ዓለም አቀፍ ተቋራጭ ‹ያፒ መርከዚ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን› የሚሠራ ነው። መነሻውን አዋሽ አድርጎ መዳረሻውን ሃራ ገበያ የሚያደርገው የባቡር ፕሮጄክቱ 7 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው ከሃምሳ በላይ ድልድዮች፣ 10 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው 12 ዋሻዎችና 827 የውኃ ማፋሰሻዎች አሉት።
ስምንት የኃይል ማስተላለፊያና አስር የባቡር ጣቢያዎችም አሉት። ባቡሩ በሰዓት 120 ኪሎ ሜትር ይጓዛል። የባቡሩን አጠቃላይ ኦፕሬሽን ሥራና እንቅስቃሴ መቆጣጠሪያ ማዕከል በኮምቦልቻ ከተማ እየተገነባለት ይገኛል፡፡ግንባታው ሲጠናቀቅ 26 ባቡሮች ይኖሩታል። 20ዎቹ የዕቃ መጫኛ ስድስቱ ደግሞ የሕዝብ ማመላለሻ ይሆናሉ። አንዱ የሰው ማጓጓዣ ባቡር በአንድ ጊዜ 720 ሰዎችን ያጓጉዛል። ባቡሮቹ በቀን 4 ሺህ 320 ሰዎችን ማመላለስ ይችላሉ።
አንዱ የዕቃ ማመላለሻ ባቡር ደግሞ 1 ሺህ 350 ቶን የመሸከም አቅም አለው። አንዱ የዕቃ መጫኛ ባቡር 30 ተጎታቾች ይኖሩታል። አንዱ የዕቃ መጫኛ ባቡር 30 መኪኖች ከነተሳቢያቸው የሚጭኑትን ጭነት በአንድ ጊዜ የመሸከም አቅም አለው።የባቡር ትራንስፖርቱ አገልግሎት ሲጀምር ከአዋሽ ሀራ ገበያ ለመድረስ ከ4:30 እስከ 6:30 ይወስድበታል። ፕሮጀክቱ ወደ ጅቡቲ ወደብ ለመድረስ የሚወስደውን ጊዜ 50 በመቶ ይቀንሳል።
ከምስራቅ ወደ ምዕራብ የሚዘረጋው የአፍሪካ የምድር ባቡር መረብ አካል የሆነው ይህ ፕሮጀክት ለመካከለኛውና ሰሜናዊ የኢትዮጵያ ቀጠና የኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይጠበቃል።ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ እንደሀገር የገቢና ወጪ ምርትን የማሳለጥ፤ ከተሜነትንና ልማትን የማፋጠን ተስፋ እንዳለው ይታመናል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 18/2013