ጽጌረዳ ጫንያለው
በዓለም ዙሪያ ሰዎች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ ለመሆን ከቦታ ቦታ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ መጨመሩን ተከትሎ ከተሞች በፍጥነት እያደጉ መጥተዋል። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገራት ላይ ከገጠር ነዋሪው ይልቅ ከተሜው ብዙና የገቢ ምንጩ ግን ያነሰ እንደሆነ ስራ አጡን ወጣት መመልከት ብቻ በቂ ነው። ይህ ሁኔታ በቀጣይ ጊዜያትም የሰዎች እንቅስቃሴ እየጨመረ ስለሚመጣ የከተማው ኑሮ ከባድና አስቸጋሪ መሆኑ አይቀሬ ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በፈረንጆቹ 2018 ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው አሃዙ በምዕተ ዓመቱ እኩሌታ ላይ 68 በመቶ ይደርሳል ይላል። አሁን ደግሞ ምን ያህል እየጨመረ እንደሚሄድ በዚህ ፍጥነት መመልከት እንደሚቻልም ያብራራል። እናም መፍትሄው ምን ይሁን ሲባል በከተሞች የገቢ ምንጮችን ለመጨመር የሚያስችሉ ሥራዎች ያስፈልጋሉ ሲልም ይጠቁማል።
ህዝቡን በተመጣጣኝ ገቢ መያዝ ከሚያስችሉ ነገሮች መካከልም ራስን በምግብ ለመቻል የሚሰሩ ሥራዎች ቅድሚያ ይሰጣቸዋል። ከእነዚህ መካከል አንዱ በክፍት ቦታዎች ላይ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ማከናወን ነው። በተለይም የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን አምርቶ መጠቀም በርካታ ጥቅሞች አሉት ።ምክንያቱም ይህ ሥራ የገቢ ምንጭ፤ ለራስ መትረፍ፤ አካባቢያዊ ውበት መስጠት፤ የአየር ንብረት ለውጥን መቆጣጠሪያ አድርጎ መጠቀም ፤ አረንጓዴ በልቶ ንጹህ አየር መተንፈስ በመሆኑ ነው።
በብዙዎች እሳቤ ከተሞች የፋይናንስ፣ የባህል እና የፖለቲካ ማዕከል ተደርገው ይወሰዳሉ። ይሁን እንጂ ከተሞች ከአረንጓዴ ልማት ውጪ አይደሉም።ሁሉም የሚታሰቡት ንጹህ አየር በመተንፈስ ውስጥ ነው። ለዚህ ደግሞ አረንጓዴ ተክሎችን በተገኘ ቦታ ብቻ ሳይሆን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ እንዲጸድቁ መትከልና መንከባከብ ፍቱን መድኃኒት ነው። የገቢ ምንጭን ከእነጥቅሙ ማጎልበትም ይገባል።
እንደ ኢትዮጵያ ባህል ማለት ልምላሜ ነው። እናም ከተሞች የዓለምን የምግብ ዋስትና የማረጋገጥ እና የመመገብ ሚና እንዲኖራቸው ተፈጥሮን መንከባከብና ከተፈጥሮ መጠቀም ያስፈልጋቸዋል። ለዚህም ማሳያው አሁን በየከተሞቹ ላይ የምናየው የተለመደ የግቢ አትክልት እና ፍራፍሬ ልማቶች ከውበታቸው ባሻገር ለነዋሪዎች ትኩስ ምርት እንዲቀርብ እያደረጉ መምጣታቸው ነው። የምግብ ዋስትናን በማረጋገጡ ረገድ ቁልፍ ሚናም እየተጫወቱ እንደሆነ ተጠቃሚው ይናገር።
በከተሞች በግለሰቦች ደረጃ ባሉ የአትክልት ስፍራዎች ላይ ሰዎች የሚወዱትን የአትክልት ወይም ፍራፍሬ ዓይነት በመምረጥ ባለቻቸው ውስንና ጠባብ ቦታዎች በቀላሉ ሊያለሙ ይችላሉ። በዚህም የመልከዓምድሩም ሆነ የአየር ጠባዩ ጥሩ ለውጦችን እያሳየ ይመጣል። ይህ ሲሆን ደግሞ ለምርትና ምርታማነት ማደግ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። እንዲህ ያለው የልማት ሥራ ባህል ሲጎለብት ዛሬ እየተስተዋለ ያለው የኑሮ ውድነት ይቃለላል።በአካባቢው ንጹህ አየር ሲኖር የሰው ልጅ የጤና ሁኔታም ለጤና ችግር መጋለጡ ይቀንሳል።በመሆኑም ውበትን ለምድሪቱ አጎናጽፎ ጥሩ አየር ለማግኘት የተጀመረው የግቢ ልማት ሊጠናከር ያስፈልጋል።
በጅማ ከተማ በቆየንባቸው ቀናት የከተማ ግብርና ተሞክሮ ያላቸውን ሰዎች አግኝተን አብረናቸው ቆይታ አድርገናል። የከተማ ግብርና ስላለው ጠቀሜታ፤ፋይዳው የት ድረስ ሊያሻግር እንደሚችል ተጠቃሚዎችንና በከተማዋ አረንጓዴ ልማት እንዲስፋፋ እገዛ ያደረጉትን አካላት አነጋግረናል።
በአንደኛው የአረንጓዴ ሥፍራ ተገኝተናል።ግቢው የህጻናት መዋያ ነው። ጠባብም ነው። ነገር ግን በዚህች ጠባብ ግቢ ውስጥ የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬ ተክሎች ውብ ሆነው ነበር ያየነው።አትክልቶቹ በአግድምና ወደላይ በሆነ መደርደሪያ ላይ ነው የተተከሉት።ሰፋ ያለው ቦታ ላይ ደግሞ ክብ ቅርጽ ይዞ ውበት በሚፈጥር መልኩ ተዘርግቶ በቅሏል።አትክልቶቹ ከአቀማመጣቸው ጀምሮ ቀልብን ይስባሉ።አትክልቶቹ ውበት ብቻ ሳይሆኑ ለምግብነትም ስለሚውሉ የተመጣጠነ ምግብ ለማግኘት ወደ ገበያ መሄድ አያስፈልግም።ከዚያው ይጠቀማሉ።በግቢው ውስጥ የሚውሉ ህጻናትም አቧራ ሳይነካቸው ለሳምባቸውም ንጹህ አየር እያገኙ ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ።አትክልትና ፍራፍሬው እንክብካቤ ሲደረግላቸው ግቢውም አብሮ ጽዳት ስለሚደረግለት ግቢው ሁሌም ጽዱ ነው።
ከተጠቃሚዎች መካከል አንዷ የሆነችው ዘመናይ አስፋው ትባላለች። ሰው ለሰው የሚባል በጎአድራጎት ድርጅት መስርታ በጅማ ከተማ መኖር ከጀመረች ሦስት ዓመታትን አስቆጥራለች።ይህን ያህል ዓመት ስትቆይ አትክልት ለመግዛት ገበያ ወጥታ አታውቅም።ለህጻናቱ ከአትክልት ምግብ የምታዘጋጅላቸው ከራስዋ አትክልት ነው።በጥምረት ዶሮ እርባታንና አትክልትና ፍራፍሬ ላይ በመስራቷ አንዱን በአንዱ በማመጋገብ ተጠቃሚ ለመሆን ችላለች።ለገበያ ቢዋልም ሌሎች የሚያስፈልጓትን ነገሮች ለማሟላት ችላለች።ከተማ ላይ እነዚህን ተግባራት ማከናወን ራስን በምግብ ለመቻል ብቻ ሳይሆን ሌሎችን ጭምር ለማገዝ ሰፊ አማራጭ እንደሚሰጥ ታስረዳለች።
የአየር ንብረት ለውጡ ላይም ቢሆን የማይተካ ሚና እንደሚኖረው ትናገራለች። ጽዱ አካባቢን ከመፍጠር አኳያም ሚናው የጎላ እንደሆነ ትገልጻለች።ስለዚህም ሰዎች ተጠቃሚነታቸውን በጠባብ ቦታም ማስፋት ይችላሉ ባይ ናት።
እገዛ በማድረግ በከተሞች ላይ አረንጓዴ ልማቱ እንዲስፋፋ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ግብርና እና የእንስሳት ህክምና ኮሌጅ እገዛ እያደረገ ይገኛል።የኮሌጁ የእንስሳት ሳይንስ መምህር አርሴ ገበየሁ የተባበሩት መንግሥታትን መረጃ መሠረት አድርገው እንደተናገሩት 821 ሚሊየን ሰዎች በዓለም ዙሪያ በቂ እና የተመጣጠነ ምግብ አያገኙም። ለተመጣጠነ ምግብ ፍላጎት መሟላት ደግሞ አትክልትና ፍራፍሬዎች ዋነኛ መፍትሄ ሰጪ መሆናቸው አያጠያይቅም። ስለዚህም እንደነ ዘመናይ በልማቱ በመሳተፍ ላይ ያሉ ሰዎች በከተሞች አካባቢ አትክልትና ፍራፍሬን ማልማት መጀመራቸው በምግብ ራስን ያለመቻል ችግር በብዙ መንገድ ለመፍታት ያግዛል።
በከተሞች አካባቢ በሚከናወን የግብርና ሥራ ዜጎች በምግብ ራሳቸውን ለመቻል የቤታቸውን ጣሪያ ወይም መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ የሚገኝ አነስተኛ ስፍራን ይጠቀማሉ። ቲማቲምን ጨምሮ ሌሎች የጓሮ አትክልቶችን እያለሙ ትኩስ፣ በማእድን የበለፀገ ጤናማ አትክልትን ከጓራቸው መጠቀምን ልምዳቸው ያደርጋሉ። ይህ ደግሞ የከተማ ግብርናን በማስፋፋት የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ለከተማ የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የገቢ ምንጭ ትልቅ ፋይዳ አለው። የዕፅዋት ምርት እና ምርታማነት ማሳደግ እና ንፅህናው የተጠበቀ ምርት በማምረት ለተጠቃሚ ማድረስ ላይም አስተዋዕጾ ያደርጋል ይላሉ።
አረንጓዴ አገርን ለትውልድ ለማስተላለፍ የሚቻለውም እንዲህ አይነት ተግባራት ልምድ ሆነው ሲቀጥሉ ነው የሚሉት መምህሩ፤ ኢትዮጵያ በተፈጥሮና በደን ሀብቶቿ የታደለች ለምለም ሀገር ብትሆንም ተፈጥሮን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ተጠቅሞ በገቢ፤ ራስን መቻያና የአየር ንብረትን መጠበቂያ ማድረግ አልተቻለም። እንደውም ከደን አንጻር ብናነሳ ባለፉት አሥርት ዓመታት በከፍተኛ ሁኔታ መመንመናቸው ግልጽ ነው። ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት የነበረው የደን ሽፋን 40 በመቶ ቢሆንም አሁን ወደ 15 በመቶ ያሽቆለቆለው።የግቢ ውስጥ አትክልትና ፍራፍሬ ልማቶች በግብርናው ዘርፍ ሰፊውን ድርሻ ይይዛሉ። በተለይም በከተሞች በስፋት የሚከናወን ከሆነ በዘርፉ የሚስተዋሉትን መጠነ ሰፊ ችግሮች መቀነስ ይቻላል።
አትክልትን መትከል ለአፈር ለምነትና ጥበቃ፣ ለከርሰ ምድር ውሃ ሃብት ጥበቃ ያለው ፋይዳው የጎላ እንደሆነ የሚናገሩት መምህር አርሴ፤ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ ሊያጋጥሟት ይችላሉ ተብለው ለሚገመቱት ያልታሰቡ የድርቅ አደጋዎች የልማት ሥራዎቹ ፍቱን መፍትሔ ይሰጣሉ። የስነ-ህይወታዊ ዘዴንም ያጠናክራሉ ። በከተማውና አካባቢው እየተሰሩ የሚገኙ ልማቶች አበረታች ውጤት እያስገኙ ያሉ ለአረንጓዴ ልማት ተስፋ ሰጪ ምልክቶች መሆናቸውንም ያብራራሉ። ማህበረሰቡ ጥቅሙን እየተረዳው ሲሄድ በእኔነት ስሜት አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚችልም ተናግረዋል።እርሳቸው እንዳሉት የአረንጓዴ ልማት ሥራው ሀገራዊ ጠቀሜታውም የጎላ እንደሆነ ለማህበረሰቡ ጎን ለጎን ግንዛቤ መፍጠር ይገባል። መንግሥትም በቂ ሀብትና ፋይናንስ በማፍሰስ ሥርዓት በመዘርጋት ኃላፊነቱን ከተወጣ የበለጠ ውጤታማ መሆን ይቻላል።በተጓዳኝ ድርሻው የመንግሥት ብቻ ሳይሆን ከግለሰብ እስከ ቤተሰብ መሆኑን ማሳወቅ፣ማስተማርና በተግባርም እያሳዩ የጋራ ኃላፊነቱን ማረጋገጥ ይገባል።
በመጨረሻ ያነሱት ነገር ከተሜው የገበሬውን ችግር ሁሉ የሚፈታበት አማራጭ እንዳለው መገንዘብ እንዳለበት ነው።እርሳቸው እንዳሉት ዝናብን ጠብቆ የሚከናወን የግብርና ሥራ መቀየር አለበት።መስኖንና የግቢ ውሃን በመጠቀም ልማት ማከናወን ብዙ እድሎችን ይሰጣል።‹‹የአረንጓዴ ልማት የህልውና መሠረት በመሆኑ ሁሉም የራሱን አሻራ ማሳረፍ አለበት››ሲሉም ገልጸዋል።ዩኒቨርሲቲው በልማቱ እያደረገ ያለው እገዛ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 18/2013