በሀገራችን በተለይም በመዲናችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውንና ሕብረተሰቡን ፈተና ውስጥ የከተተውን የኑሮ ውድነት ለማርገብ መንግስት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል። ከዚሁ ጎን ለጎንም ነዋሪው የተረጋጋ ኑሮ መኖር እንዲችል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ ያሉ ቤት አከራዮችን አስመልክቶ መመሪያ አውጥቷል። ከነሀሴ 18 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገው መመሪያ ለቀጣዮቹ ሦስት ወራቶች ማንኛውም የመኖሪያ ቤት አከራይ የኪራይ ዋጋ እንዳይጨምር እንዲሁም ተከራዮችን እንዳያስወጣ የሚል ነው።
የከተማው አስተዳደር መመርያውን ያወጣው አሁን ሀገሪቱ ካለችበት ተጨባጭ ሁኔታና ጎልቶ ከሚታየው የኑሮ ውድነት አንፃር ሕብረተሰቡ እርስ በእርስ ተደጋግፎ አስቸጋሪውን የፈተና ወቅት ማለፍ እንዲችል በማሰብ ጭምር ነው። ነገር ግን መመሪያው አብዛኞቹን ተከራዮች ጮቤ በማስረገጥ ሲያስደስት አንዳንድ አከራዮችን ቅር አሰኝቷል ።
ይሁን እንጂ የመመሪያው ዓላማ ተከራዮች ቆም ብለውና አሁን ያለውን የከፋ የኑሮ ውድነት አገናዝበው በተለያየ መልኩ ለአከራዮቻቸው እንዲያስቡ ፤ አከራዮችም ሰብዓዊነት ተሰምቷቸው የኮቪድ ወረርሽኝ በሀገራችን በተቀሰቀሰበት ወቅት አንዳንድ አከራዮች እንዳደረጉት የቤት ኪራይ በመቀነስ፣ ባለማስከፈል ሲረዳዱ እንዳሳለፉት ሁሉ አሁንም ሀገሪቱና ህብረተሰቡ ያጋጠመውን ችግር በመገንዘብ፣ በመረዳዳትና በመተሳሰብ እንዲያሳልፉ የሚያደርግ ነው።
በመመሪያው ዙሪያ ያናጋገርናቸው የከተማው ነዋሪዎችና የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የሚከተለውን ሀሳብ ሰጥተውናል።አቶ ታምራት ደበበ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ናቸው። የግል የመኖሪያ ቤት አላቸው። የሚተዳደሩት በጡረታ በሚያገኙት ሶስት መቶ ብር እና ኑራቸውን ለመደጎም ሰርቪስ ሰርተው ባከራዩት የኪራይ ገንዘብ ነው። በአካባቢው የቤት ኪራይ ዋጋ ረከስ ያለ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ቀደም ሲል ቤቶቻቸውን ያከራዩት በዝቅተኛ ዋጋ ነው። አብዛኖቹ ተከራዮቻቸው ሰፊ ቤተሰብ ያላቸው ናቸው። እየኖሩ ያሉትም የዛሬ 10 ዓመት ባከራይዋቸው ዋጋ ነው። ሆኖም ዛሬ ሁሉ ነገር ጨምሯል።በመሆኑም ወጪዎቻቸውን መሸፈን አልቻሉም። በመሆኑም ዘንድሮ ካለው የኑሮ ውድነት ጋር ተቀራራቢ የሆነ የኪራይ ማሻሻያ ለማድረግ በወሰኑበት ጊዜ መመሪያው መውጣቱ አላስደሰታቸውም።
ወይዘሮ ደብሪቱ ቁምሳ የአዲሱ ገበያ አካባቢ ነዋሪ መሆናቸውን ይናገራሉ። የመኖሪያ ቤት አከራዮችን በሚመለከት የወጣው መመሪያ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ካለው እጅግ የከፋ የኑሮ ውድነት አንፃር የአከራዩንም የተከራዩንም ችግር ያማከለ ነው ብለው አያስቡም። መንግስት ቆም ብሎ ይሄን ማገናዘብ እንዳለበትም ይመክራሉ። ሆኖም አሁን ሀገራችን ካለችበት አስቸጋሪ ሁኔታ አንፃር በተለይ ጥቂት ራስ ወዳድ አከራዮች ተከራዩን ከደላላ ጋር በመወገን በአስከፊ ሁኔታ እያማረሩ ባለበት ሁኔታ መመርያውን መሰረት አድርጎ መደጋገፉም ህግ ማክበሩም ተገቢ እንደሆነ ያምናሉ።
ወጣት ዳዊት ክንፈ አራት ኪሎ አካባቢ በሚገኝ ዘመዱ ካፌ ውስጥ በቡናና ሻይ ማሽን ላይ ተቀጥሮ ይሰራል። ባለ ትዳር ሲሆን ሽሮ ሜዳ አካባቢ አንድ ክፍል ቤት ተከራይቶ ከባለቤቱ ጋር ይኖራል።በቤቱ መኖር ከጀመረ ሁለት ዓመቱን ይዟል።ዋጋዋ አንድ ሺህ 200 ብር ነው። በወር የሚያገኛት ደመወዝ ከኪራዩ ብዙም የምትበልጥ ባለመሆኗ እየተቸገረ መሆኑን አልሸሸገም። እንደ ዕድል ሆኖ ፈጣሪ ሰጠኝ የሚላቸው አከራዩ አቅሙን አሳምረው የሚረዱና መልካም በመሆናቸው እስካሁን ኪራይ ባይጨምሩበትም ሁለቱን ዓመት በተለይም የኑሮ ውድነቱ እየናረ ሲመጣ ይጨምሩብኝ ይሆን በሚል ስጋት ሲናጥ መኖሩንም ይገልፃል። መመሪያው ከዚህ ስጋት ነፃ እንዳወጣውና በነፍስ እንደደረሰለትም ይናገራል።
ወጣቱ እንደሚለው የተወሰደው እርምጃ ተገቢና ወቅታዊ ነው። እንደ እሱ ዝቅተኛ ገቢና ደረጃ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ችግር ያገናዘበ ነው ይላል።ሀገሪቱም ሆነች ዜጎች የኑሮ ውድነቱ ካስገባቸው ቀውስ ውስጥ እስኪወጡና እስኪረጋጉ መቀጠል እንዳለበት ያሳስባል። ቢሆንም የአሁኗን አከራዩን ከፊቱ አከራዩ ጋር በማነፃፀር ሳያመሰግን አላለፈም።ቀደም ሲል የነበሩት አከራዩ በየወቅቱ በሚያደርጉበት የቤት ኪራይ ጭማሪ የሚበላው እስከማጣት ያደረሰው እንደነበር ያስታውሳል። በ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤት ተመዝግቦ ለስቱዲዮ ሲቆጥብ የነበረውን አውጥቶ ለኪራይ በማዋል ቁጠባውን ማቋረጡን በቁጭት ይናገራል።
‹‹ አሁን ባለሁበት ቤት አከራዮቼ ሌላ ገቢ የላቸውም።ልጆቻቸው በሥራ ምክንያት በተለያየ ቦታ ናቸው።እኔና ባለቤቴን እንደ ልጆቻቸው ነው የሚያዩን።የበሉትን ያበሉናል። የጠጡትን ያጠጡናል የሚተዳደሩት ከእኛ በሚያገኙት ኪራይ ነው። እኔ ከገቢዬ ዝቅተኛነት አንፃር እንጂ ፊት እከፍል ከነበረው ጋር ሲነፃፀር ኪራይ እየከፈልኩ ነው አልልም›› ሲል አጫውቶናል። ኮረና እንደገባ ሰሞን አንዳንድ አከራዮች የቤት ኪራይ መቀነሳቸውን ያስታወሰው ወጣቱ እሳቸው እንዳይቀንሱ መተዳደርያቸው ሆኖ ግራ ቢገባቸው በቤቴ ውስጥ መደገፍ የሚገባቸው ችግርተኛ ነዋሪዎች አሉ በማለት የአምስት ኪሎ ማኮሮኒ ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረጋቸውን ይመሰክራል።
ሌላው ያነጋገርናቸው አቶ ዳኛቸው ወልዴ ባለ ትዳር ሲሆኑ ሳሪስ አካባቢ በተከራዩት የግለሰብ ቤት መኖር ከጀመሩ ስምንተኛ ወራቸውን ይዘዋል። ‹‹በእነዚህ ወራት ውስጥ አከራዮቼ መልካም በመሆናቸው የገጠመኝ ባይኖርም ከዚህ በፊት ያጋጠሙኝ አከራዮቼ ቁም ስቅሌን ሲያሳዩኝ ነበር›› ሲሉ በምሬት ያስታውሳሉ። ኪራይ በመጨመራቸው የተነሳ ከአንዱ ቤት አንዱ ቤት ሲዘዋወሩ ለዕቃ ማጓጓዣ ያወጡት ወጪ ቤት ይሰራ እንደነበርም ይጠቅሳሉ።በኪራይ ጭማሪ ፣በቤት ውስጥ እየኖሩ መብራት ለማብራት፣ውሀ ለመቅዳት ፣ልብስ ለማጠብና እንደልብ ለመውጣትና ለመግባት መሳቀቁንም አይዘነጉትም። ኪራይ ይጨመራል በሚል ስጋት ገቢያቸውን በዕቅድ ለመመራትና በአጠቃላይ ተረጋግቶ ለመኖር ይቸገሩ እንደነበር ይናገራሉ።
የከተማ አስተዳደሩ ያወጣውን መመሪያ የተከራዩን ችግር ያገናዘበ በመሆኑ ከልባቸው ይደግፉታል።መመርያው ከመውጣቱ በፊት የባለቤታቸው ጓደኛ የተከራየችበት አከራይ ሆቴል ላደርገው ነው በሚል ሰበብ ሁሉንም ተከራዮች በ15 ቀን ውስጥ ለቀው እንዲወጡ በመጠየቁ ሲጨነቁ የነበረ መሆኑንም አጫውተውናል።አዋጁ ለነዚህ ተከራዮች በነፍስ የደረሰላቸው መሆኑንም አልሸሸጉንም።በዚህ የኑሮ ውድነቱንና ሀገሪቱ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ አስታከው ኪራይ ለሚጨምሩ አከራዮች መመሪያው ጥሩ መፍትሄ ነው።
መመሪያው የኑሮ ውድነት በተባባሰበት ፣በዓላት በደረሱበት ፣ ትምህርት ቤት በሚከፈትበትና በከፍተኛ ሁኔታ የገንዘብ እጥረት ባለበት ወቅት በመደረጉ ወቅታዊ እና አስፈላጊ ነው። በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የህብረተሰብ ክፍል በእጅጉ የሚጠቅም ነው ሲሉ የኢኮኖሚ ባለሙያውና የአፍሪካ አመራር ልዕቀት አካዳሚክ ጉዳዮች ዳይሬክተሩ ረዳት ፕሮፌሰር ስሜነህ ቤሴ ጠቅሰዋል።
በአሁኑ ወቅት በቤት ኪራይ ላይ ብቻ ሳይሆን በማንኛውም መንገድ የሚደረግ የዋጋ ጭማሪ የኢኮኖሚ ቀውሱን ስለሚያባብስ ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ አለበት ። የሀገሪቱን ኢኮኖሚም ሆነ ህዝቡን ማረጋጋት የሚቻለው የዋጋ ንረቱንና የኑሮ ውድነቱን በመቀነስ ፤ መቀነስ ካልተቻለ ደግሞ ባለበት ደረጃ እንዲቀጥል በማድረግ ነው።
የዋጋግሽበት የሚፈጠረው ብዛት ያለው ብር ወደ ገበያው ውስጥ ሲገባና የሸቀጥ ወይም የአገልግሎት መጠን ደግሞ ሲቀንስ ወይም ባለበት ሲቆም ነው። ይህም ማለት ተጠቃሚው አንድን ዕቃ ለመግዛት እጁ ላይ ከዚህ ቀደም ከነበረው የበለጠ ገንዘብ ሲኖረው የዕቃው አቅርቦት ግን ባለበት ከሆነ ወይም ከቀነሰ እጥረት ስለሚፈጠር ተጠቃሚው ተጨማሪ ብር አውጥቶ ዕቃውን ይገዛል ማለት ነው።
የተጠቃሚው የመግዛት ፍላጎት ሲጨምር የገበያው የአቅርቦት መጠን ሲቀንስ ልክ አሁን በገበያ ላይ እንደምናየው የዕቃ ዋጋ ይጨምራል፤ በዚህም የተነሳ የዋጋ ግሽበት ይፈጠራል። ይሄ የዋጋ ንረትን የሚያመጣና ከገንዘብ ጋር ተሰናስሎ የሚፈጠር የኢኮኖሚ ችግር በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ያለውንና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘውን ሕብረተሰብ ክፍል የበለጠ ይጎዳል። የአዲስ አበባ መስተዳድር ያወጣው መመሪያ በአጭሩ እነዚህን የሕብረተሰብ ክፍሎች የሚታደግ ነው።
አሁን ላይ በየቀኑ የዋጋ ግሽበት እየጨመረና ከመንግስት ቁጥጥር ውጪ እየሆነ የዜጎችን በተለይም የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ኑሮ እየተፈታተነ አስቸጋሪ አድርጎታል። መንግስት ችግሩን ለመቀነስ በታክስና በገንዘብ ፖሊሲ የብር ኖቶችን ከመቀየር ጀምሮ የተለያዩ ጥረቶችን ቢያደርግም ግሽበቱ ውጤታማ ለውጥ ሊያመጣ አልቻለም። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት የሀገሪቱ ዜጎች ከጠቅላላ ገቢያቸው ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የሰው ልጆች መሰረታዊ ፍላጎት ለሆነው ምግብ የሚያውሉበት ሁኔታ ፈጥሯል።ወጪው የጤናውን፣የትራንስፖርቱንና ሌሎች መሰረታዊ ወጪዎችን አይጨምርና ታሳቢ አያደርግም።
የቤት ኪራይ ወጪ ደግሞ ከምግቡም በላይ አብላጫውን የሚወስድበት ሁኔታ ነው ያለው። በመሆኑም ዜጎች ወጪዎቻቸውን የመሸፈን አቅም ከማጣት አልፈው መኖር እስኪያቅታቸው እያደረገ ይገኛል።
እንደ ኢኮኖሚ ባለሙያው ታድያ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወሰደው የፊዚካል ፖሊሲን የተንተራሰ የሚመስል የቤት ኪራይ መገደብ እርምጃ አንድም ገቢ መጨመር ሊሆን ይችላል። ሁለተኛ የመንግስትን ወጪ መቀነስ ላይ ያተኮረ ሊሆን ይችላል። ቢሆንም ዝቅተኛ ገቢ ያለውና በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኘው የሕብረተሰብ ክፍል በተወሰነ መልኩ በጣም እንዳይጎዳ ያድናል። የዜጎች ኑሮ በማሻሻል ረገድም አስተዋጾው የጎላ ነው።
‹‹በዚህአጋጣሚ አከራይ ማግኘት የሚገባውን ገቢ ላያገኝ ይችላል›› የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ስሜነህ በእርምጃው ቢያንስ የዋጋ ግሽበቱ ከዚህ በላይ ተባብሶ በመሄድ እነሱን ጨምሮ አጠቃላይ የዜጎችን የመኖር ዋስትና እስከማሳጣት ሳይዘልቅ አሁን ባለበት ሁኔታ እንዲቀጥል የሚያስችል መሆኑን መረዳትና ፈታኙን ወቅት ተደጋግፎ ማለፍ እንደሚገባ ያሳስባሉ።
በተለይ የሕዝብ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ በመምጣቱ የቤት ኪራይ ዋጋ እጅግ በመናሩ ተከራይ በከፋ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ መግባቱ ሊያሳስባቸው እንደሚገባም ይጠቁማሉ። ሀገሪቱ በኮቪድ፣እያንዳንዱ የግብርና ምርትና የሸቀጥ ዋጋ ንረት በወለደው በኑሮ ውድነት እንዲሁም በሰላም ዕጦትና ጦርነት ውስጥ በተዘፈቀችበት ቀውስ ወቅት በተከራይ ላይ ኪራይ መጨመር ኢሰብዊነት እንደሆነም ይጠቅሳሉ።
እንደ ባለሙያው ጦርነቱ በመሰረታዊነት ከፈጠረው የኑሮ ውድነት ጀምሮ በኢኮኖሚው ላይ የፈጠረው ጫና በራሱ ቀላል አይደለም። ለልማት መዋል የሚገባው የሰው ኃይልና ገንዘብ ለጦርነትና ለጦር መሣርያ መግዣ ውሏል።በየአካባቢው በሚቀሰቀሱ ግጭቶች ከፍተኛ የሰላም ዕጦት አለ። በዚህ ምክንያት አርሶ አደሩ ከቀየው ተፈናቅሏል። ወጣቱም ሀገሩን ወደ ማዳን ተልዕኮ እየገባ ነው።
ጦርነቱ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን ተፈጥሯዊና ምድራዊ ሀብቶቿንም ጎድቶታል።ይሄን ወደ ነበረበት ለመመለስ ከ10 እስከ 20 ዓመታት ሊወስድ ይችላል።አሁን ላይ አርሶ አደሩ፣ ወጣቱ፣ ህፃናት ተፈናቅለዋል።የዋጋ ንረቱ በማያባራ አዘቀት ውስጥ ገብቶ የኑሮ ውድነቱ ከሚገባው በላይ ከፍቷል ፣ሥራ ማግኘት አስቸጋሪ ሆኗል።በዚህ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞችና የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተከራይተው በሚኖሩበት ቤት ላይ መንግስትም ሆነ ማንኛውም አካል ዋጋ መጨመሩ አላስፈላጊና ፍትሃዊነት የሌለው ነው።የኑሮ ውድነቱን የበለጠ በማባባስ ፤ ሰው ወደ ሌብነት፣ ወንጀልና የተለያዩ ነገሮች የሚገባው እንዲህ ዓይነቱ የመጨረሻ ደረጃ ሲደርስ በመሆኑ ኢኮኖሚያውና ማህበራዊ ቀውሱን ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ እንዲያመራ ያደርገዋል።
በአሁኑ ወቅት በቤት ላይ ብቻ ሳይሆን በማንኛውም መንገድ የሚደረግ የዋጋ ጭማሪ የኢኮኖሚ ቀውሱን ስለሚያባብስ ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ አለበት።ሕዝቡንም ሆነ ሀገሪቱንና ኢኮኖሚውን ማረጋጋት የሚቻለው የዋጋ ንረቱንና የኑሮ ውድነቱን መቀነስ ካልተቻለም ባለበት በማስኬድ ብቻ ነው ሲሉ ሀሳባቸውን ይቋጫሉ።
ሰላማዊትውቤ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 29/2013