አዳማ ከተማ አሁን ላይ በዕለት ተዕለት ውሎዋ ሀገር በማዳን ተልዕኮ ተጠምዳለች። ሀገር ወዳዱ ነዋሪ ደጀንነቱን በይፋ እያስመሰከረም ይገኛል። ከዕለት ሥራው ባሻገር ቀዳሚ አጀንዳ ያደረገው የሀገር ጉዳይ ነው። ሴቶች በየአካባቢው ተሰባስበው ወደ ግንባር ለሚዘምተው ሠራዊት ስንቅ ያዘጋጃሉ። ቆሎው ይቆላል፣ ዳቦ ቆሎው ይቆረጣል፣ በሶው ይወቀጣል፣ እንጀራው እየተጋገረ ይደርቃል። የደም ልገሳውም ተቀናጅቶ እየተካሄደ ይገኛል።
በእርድ ሠንጋውም ሆነ በገንዘብ መዋጮ ያልተሳተፉ እናቶችና አባቶች የሉም፡፡ የደጀንነት አጋርነታቸውን በተግባር ለመወጣትም ወጣት ልጆቻቸውን ለማዝመትና እራሳቸውም ለመዝመት ቃል ይገባሉ። ይህ ሁሉ እንቅስቃሴ በባህላዊ አልባሳት ባሸበረቁ ወጣት ሴትና ወንዶች፤ እንዲሁም ዘፈን፣ ሽለላና ቀረርቶ በመታጀብ ነው፡፡
ወይዘሮ ፋጤ ዲሳሳ በአዳማ ከተማ የቦሌ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ናቸው። ቀደም ሲል ነዋሪው የመንግስት መስሪያ ቤት አገልግሎትን ለማግኘት በውስጡ ለተሰገሰጉ አገልጋዮች ጉቦ መስጠት የግድ እንደነበር አንስተው ይህም ላልተገባ ወጪና እንግልት ዳርጎናል ይላሉ፡፡ ከመሬት ጋር የተያያዘ ጉዳያቸው ከሦስት ዓመት በላይ ምላሽ ባለማግኘቱ ሲንገላቱ መቆየታቸውን የሚናገሩት ወይዘሮዋ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በመጀመሩ ዘንድሮ የተሻለ አሰራር እንዳለ ነግረውናል።
የደምበላ ክፍለ ከተማ የእሬቻ ቀበሌ ነዋሪው ወጣት ጅፋር ሻፎ በበኩሉ የለውጥ አመራሩ ከዚህ ቀደም በህገ ወጥ መንገድ በግለሰብ ተይዘው የነበረው መሬት ወጣቱ እረፍቱን ለሚያሳልፍባቸው አረንጓዴ ቦታዎች እንዲውሉ ማደረጉ ከተማዋ ልዩ ገፅታ እንድትላበስ አድርጓታል። ለወጣቱም የስራ ዕድል መፍጠር እንደቻለና የለውጥ አመራሩም ከተማዋ ያላትን ዕምቅ ሀብትና አማራጮች በአግባቡ በመረዳት በመቻሉ የመጣ ነው ይላል፡፡
አዳማ ከተማን የከበቧት ቀጨማና ቦሰት የተንሰላሰሉ ተራሮች በድቅድቅ ጨለማ ሳይሆን ልዩ ትዕይንት በሚፈጥሩ አንፀባራቂ ቀለማት በተጎናፀፉ ኮኮቦች በመዋባቸው ታይተው አይጠገቡም። ለቱሪዝም መስዕብነት የሚመጥኗት ሁለት ባለ አንድ ኮኮብ፤ ሦስት ባለ ሁለት ኮኮብ፤ ስድስት ባለ ሦስት ኮኮብ ሆቴሎች፤ 359 ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች፤ 412 መኝታዎች፤ 783 ሬስቶራንቶች፤ 1ሺህ 151 ካፌዎች እንዲሁም በአንድ ግዜ 23 ሺ 175 ሰዎችን ማስተናገድ በሚችሉ 129 የመሰብሰቢያ አዳራሾች ያሏት መሆኑን ከከተማ አስተዳደሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ትላልቅ ሆቴሎቹ አዝወትረው የሚጎበኙት በውጪ ዜጎች መሆናቸውንም አስተውለናል። በስብሰባ ቱሪዝም መዳረሻነቷም ቀልብ የሚስቡ የቦኩ እንፋሎት፤ መንፈስን የሚያድሱ የምድር ገነት የሆኑ የመዝናኛ ሥፍራዎች አሏት። ከታሪክ አንፃርም የኦሮሞ ሰማዕታት ሀውልት ይገኝበታል። ፀአዳነቷ አረንዴ ምንጣፍ ከሚመስለው ልምላሜን የተላበሰ ገፀ ምድሯ ጋር ተዳምሮ ሲታይ ልቦናን በሀሴት ያዋልላል። ብቻም ሳይሆን አዳማን ከማንኛውም የቆሻሻ ዓይነት ነፃና ፅዱ ለማድረግ፤ እንዲሁም ቆሻሻን የሚጠየፍ ማህበረሰብ ለመፍጠር ከፍተኛ ሥራ መሰራቱን ይናገራል። የአረንጓዴ ልማትና የመናፈሻ ስፍራ መዳረሻዎችን ማስፋፋት ጋር ተሰናስለው የተሰሩ ሥራዎች አሻራ መኖሩንም ያሳያል። በቦሌ ክፍለ ከተማ ጎሮ ቀበሌ በ 4 ነጥብ 6 ሄክታር መሬት ላይ 9 ሚሊዮን 710 ሺህ 189 ብር የማስፋፍያ ግንባታው የተከናወነውና አገልግሎት እየሰጠ ያለው የኦቦ ፓርክ፤ በስምንት ሚሊዮን ብር በበጎ ፈቃደኛ ባለሀብት ለምቷል፡፡ ይህም ለወጣቱ አማራጭ የመዝናኛ ቦታ በመሆን እያገለገለ ይገኛል።
ከተማዋ የኢንተርኔት ኔትወርክ ችግር እንደሌለባት ተንቀሳቃሽ ስልክ ይዘው የሚጠቀሙ ወጣቶች ያሳብቃሉ። በቴክኖሎጂ የበለፀገ የመረጃ ቋት አገልግሎት ተጠቃሚ መሆኗንም ያንፀባርቃሉ። የምሽት የአየር ንብረቷ ቅዝቃዜውን እየዋጠ የሚረጨው ውጫዊ ለብ ያለ ወበቅ መሰል ሙቀት ውስጣዊ ምቾት ይሰጣል። ለዚህም ይመስላል ‹‹ምሽቱን በናዝሬት በአዳማ ከተማ›› ተብሎ የተዜመላት የአዳማ ከተማ አመሰራረት የድሬድዋ አዲስ አበባ (ፊንፊኔ) የባቡር መንገድ ልማትን ታሪክ ተንተርሷል።
የምስራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ ፈርጧ አዳማ ከባህር ጠለል በላይ ከ1 ሺ 600 እስከ 1 ሺ 700 ከፍታ ላይ መገኘቷ ለኑሮ፣ ለንግድ፣ ለስብሰባ ማዕከልና ለሁለገብ መዋለ ንዋይ እንቅስቃሴ ተመራጭና ምቹ አድርጓታል። ከዚህ አንፃር እየሰፋች የመጣች ወደፊትም የምትሰፋ መሆኗን መገመት ባያዳግትም አሁናዊ የቆዳ ስፋቷ 31 ሺ 185 ሄክታር ላይ ማረፉን ከከተማ አስተዳደሩ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።
የከተማዋ መስፋት አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ለመገንባትና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴውን ለማፋጠን ከፍተኛ እገዛ እያደረገ የሚገኝ መሆኑን የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ ኃይሉ ጀልዴ ይናገራሉ፡፡ እንደሳቸው ገለጻ፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የመንግስት በጀት ተገንብተው አገልግሎት እንዲሰጡ የተደረጉት 96 ፕሮጀክቶች ማሳያ ናቸው። ለአብነትም የአስፓልት መንገድ፤ በተለይ በከተማ ውስጥ የከባድ መኪና እንቅስቃሴ በመብዛቱና በዚህ ምክንያት ሊፈጠሩ የሚችሉ አደጋዎችን ለመቀነስ ጭምር የአስፓልት ዳር የእግረኛ መንገድ ግንባታ ተከናውኗል።
ከተማዋን ለዓይን ሳቢና ማራኪ ለነዋሪ ደግሞ ምቹ ከማድረግ አንፃር የባለቅርፅ ድንጋይ ምንጣፍ መንገድ፤ የጠጠር መንገድ፤ የከተማዋ የውስጥ ለውስጥ አስፓልት መንገድ እድሳት፤ የድልድይ ግንባታ፤ የጎደና ላይ መብራት እድሳት፤ የኢፋ ቦሩ ትምህርት ቤት ግንባታ፤ የመዝናኛ ፓርኮች ግንባታ፤ የተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች አዳዲስ ግንባታና እድሳት፤ እንዲሁም ደረጃቸውን የጠበቁ የህዝብ መፀዳጃ ቤቶች ግንባታ ይገኙበታል።
‹‹የቆዳ ስፋቷ በመጠን መጨመሩ ከተማዋ የኢንቨስትመንት ማዕከል ከመሆኗ አንፃር ያደረገው አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ ነው›› የሚሉት አቶ ኃይሉ። በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ብቻ 153 ተቋማቶች መያዟንም ማሳያ አድርገዋል። በኢንዱስትሪ 425፤ በአግሮ ኢንዱስትሪ 272፤ በአገልግሎት ዘርፍ 664 የኢንቨስትመንት ተቋማት መኖራቸውንና ስር የሰደደውን የሥራ አጥነት ችግር ከመቅረፍ ጀምሮ በተለያየ መንገድ ዕድገቷን እያፋጠኑ እንደሚገኙ ይናገራሉ።
በአጠቃላይ በከተማዋ 630 ሄክታር መሬት ላይ ያረፉ 1 ሺ 514 የተለያዩ ኢንቨስትመንቶች በ 29 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ካፒታል በመካሄድ ላይ እንደሚገኝም አውግተውናል። ለ13 ሺ 932 ዜጎች ቋሚ ለ8 ሺ 625 ዜጎች ጊዚያዊ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል። በዘንድሮ ዓመት በኢንቨስትመንቱ የተፈጠረውን ጨምሮ በአጠቃላይ ለ29 ሺ 73 ዜጎች በአዳማ ከተማ የስራ እድል ተፈጥሯል። የሥራ ዕድሉ ከተፈጠረላቸው ውስጥ አንድ ሺ 473ቱ የዩኒቨርሲቲና የቴክኒክ ኮሌጅ ምሩቅ ናቸው።
አቶ ኃይሉ፤ እንደገለፁልን የከተማ አስተዳደሩ ለኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ልዩ ትኩረት ሰጥቷል። በመሆኑም አሁንም የዉጭና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በከተማዋ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በስፋት እንዲሳተፉና ለጋራ ብልፅግና አብረው እንዲሰሩ ለማድረግ አዳዲስ ምቹ የኢንቨስትመንት መሬቶችን ከተሟላ መሰረተ ልማት ጋር በማቅረብ ደፋ ቀና ማለቱን ቀጥሏል።
በኢንቨስትመንት ስም ሰፊ የህዝብና የመንግስት መሬት በመውሰድ ለረዥም ዓመታት አጥረው ሳያለሙ በነበሩ ባለሀብቶች ላይ ህጋዊና አስተማሪ እርምጃዎች ተወስዷል። ከተማዋ ያላትን ዕምቅ ሀብትና አማራጮች በአግባቡ በመረዳትና ከተማዋ እንዳታድግ አንቆ የያዘውን ስር የሰደደ ዘርፈ ብዙ ችግር ለመቅረፍ የከተማው የለውጥ አመራር በተለይ በመሬትና ከመሬት ጋር ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች ዙርያ በከፍተኛ ቁርጠኝነትና ተነሳሽነት እየሰራ ይገኛል።
‹‹መሬት ለአንድ ሀገር ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ መሰረታዊ ጉዳይ ነው›› የሚሉት አቶ ኃይሉ፤ ይህን ዕውነታ የተረዳው የከተማው አመራር የአዳማ አንጡራ ሀብት ከሆነው መሬት ጋር ተያይዞ ያከናወነውን ሲገልፁ። የአዳማ ከተማ አስተዳደር የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ስርዓት ለማዘመን ጥረት አድርጓል። ጥረቱ በመሬት ዙርያ የሚካሄደውን ልማት ቀጣይነት ባለው መልኩ በመምራት የከተማውን ነዋሪ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ተግባር ላይ ያተኮረ ነበር። በዚህ መሰረት የመሬት አስተዳድር ተቋምን በቅድመ ዕቅድ ዝግጅት ሪፎርም አድርጓል። በተቋሙ ስር የሰደዱና ለህዝብ ቅሬታ መነሾ የሆኑትን ችግሮችም በጥናት የለየበት አለ። ይሄንም ከአመራር አስከ ባለሞያ ድረስ በማውረድ የስነ-ምግባርና የአቅም ውስንነት በተስተዋለባቸው ፈፃሚዎች ላይ አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ በዘንድሮ 2013 ዓ.ም ወደ ተጨባጭ ስራ ገብቷል።
ወደ ሥራ ከገባ በኋላ ከደምብ በፊት የተገነቡ ህገወጥ ግንባታዎችን ህጋዊ ለማድረግ ባደረገው ጥረት 8 ሺ 79 ግንባታዎችን ወደ ህጋዊነት አምጥቷል። ነባር ይዞታን አስመልክቶም ከነዋሪው የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ በተደረገው ጥረት ለ 1 ሺ 29 ነባር ይዞታ የማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ሰጥቷል። 5 ሺ 105 የመንግስት ቤቶችን ህጋዊ ካርታ እንዲኖራቸው አድርጓል። እንደ አቶ ኃይሉ፤ ገለጻ የህዝብና የመንግስት የሆነውን ሀብት ከብዝበዛና ከብክነት ለማዳን በተሰራው የተቀናጀ ስራ 347 ሄክታር መሬት ወደ መሬት ባንክ ገቢ እንዲሆን ተደርጓል። በጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት ለተደራጁ 38 ሄክታር መሬት ተላልፉል። በማሕበር ለተደራጁ የመኖሪያ ቤት የመሬት ዝግጅትን አስመልክቶም በተሰራው ሥራ 170 ሄክታር መሬት ማዘጋጀት የተቻለበት ሁኔታ አለ። 52 ሺ 162 ሄክታር መሬት ተቀይሶ ተከልሏል። 123 ሺ 600 የመዝገብ ቤትና የብሎክ መረጃዎች በማንዋል ተደራጅቶ የነበረውን የከተማዋን የመሬት ጉዳዮች ፋይል በቅርቡ አዳማን ጨምሮ ለስድስት ከተሞች በተላለፈው የከተሞች ዲጅታል ፖርታል ቴክኖሎጂ በመታገዝ የተደራጀበት ሁኔታ አለ። ይህም ዘንድሮ በመሬት ዙርያ የተሰራው ሥራ በዓይነት፣ በመጠንና በጊዜ የተሻለ አፈፃፀም እንዲኖረው አስችሎታል።
የከተማ መሬት ይዞታና ማረጋገጫ (ካዳስተር) አስመልክቶ በተሰሩ ስራዎች 155 ጎረቤት፤ 31 ሺ 450 ቁራጭ መሬት የመቀየስና የመከለል ስራ በተጨማሪም 14 ሺ 56 ይዞታ የማረጋገጥ ስራ ተከናውኗል። በዚህ ዓመት ልዩ ዕቅድ በማቀድ ከነባር ይዞታና ከህገ-ወጥ ግንባታ 55,520,000 ብር ገቢ መሰብሰብ ተችሏል።
ለሀገር እድገት ብቻ ሳይሆን መሰረተ ልማቶችን ለማሟላት አስፈላጊ መሆኑን አበክረው ይገልፃሉ። የከተማን ዕድገት ከማሳለጥ አንፃርም የማይተካ ሚና አለው። ከዚህ አንፃር የከተማዋ ወጪን የመሸፈን አቅም ማደጉን የጠቀሱት አቶ ኃይሉ፤ በዘንድሮ በጀት ዓመት የከተማዋን የውስጥ ገቢ ከፍ ለማድረግ የተለያዩ የገቢ ምንጮችን በመፈተሽ ቫትን ጨምሮ ከማዘጋጃ ቤትና ከመደበኛ ገቢ 2,179,298,826.2 ቢሊዮን ብር ተገኝቷል። ገቢው ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ 431,854,099.82 ብር ብልጫ አለው።
በከተማዋ የመንግስት መሥሪያ ቤቶች የዘመነ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እንዲሰጥ አስችሏል። ማዕከሉ አገልግሎት መስጠት ከመጀመሩ በፊት በቀበሌ፣ በክፍለ ከተማና በከተማ ደረጃ ከመልካም አስተዳደር ችግር ጋር የተያያዙ 3 ሺ 756 ቅሬታዎች ቀርበው ነበር። ማዕከሉ ወደ ሥራ በገባ በአጭር ጊዜ ከቀረቡለት ቅሬታዎች የከተማው ስራ አስፈፃሚና አመራሮች በተገኙበት ለ2 ሺ 775 አፋጣኝ ምላሽ መስጠት ችሏል። የባለጉዳይ ምልልስን፣ እንግልትና ቅሬታ ቀንሷል፡፡ የስራ ከባቢን ምቹ በማድረግ፤ የፋይል አያያዝ ለአገልግሎት አሰጣጥ አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮችን በማሟላት፣ አገልግሎቱን በመረጃ ቋት ማሳለጥ፣ ማዘመን፣ ፈጣንና ቀልጣፋ ማደረግ ተችሏል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 15/2013