በከተሞች ላይ የሚታየው የኑሮ ውድነት እጅግ ከፍተኛ ነው። የአዲስ አበባ ከተማ እንደ ኢትዮጵያ መዲናነቷ ለምርት ዋጋ ንረትና ኑሮ ውድነት አዲስ ባትሆንም ዘንድሮ እየገጠማት ያለው ግን ባስ ያለ ነው። በተለይ የግብርና ምርት ዋጋ ዕለት በዕለት ብቻ ሳይሆን በየሰዓቱ የዋጋ ጭማሪ ይታይበታል። በተለይ አንዳንድ ምርቶች ደግሞ ከዋጋ ንረቱ በተጨማሪም በምርት እጥረት ነዋሪውን ይፈትናሉ። ይሁን እንጂ ሰሞኑን በፍራፍሬ አቅርቦትና ዋጋ ዙሪያ መረጋጋት ተስተውሏል። ሽንኩርትን ጨምሮ በአትክልት መሸጫ ዋጋ ደግሞ አየል ብሎ ታይቷል። ይሄ የተዘበራረቀ የገበያ ስርዓት፣ የተጋነነ ዋጋ እና የምርት አቅርቦት እጥረት ሆን ተብሎ የተፈጠረ ወይንስ እውነታው ላይ የተመሰረተ ይሆን ? በሚል የተለያዩ ሰዎችን አነጋግረናል። አንዳንድ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ግን ‹‹የለም የኢኮኖሚ አሻጥር ነው›› ሲሉ ምላሽ ሰጥተውናል። የአምራቾችና ሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራት አባላትና አመራሮችም ይህንኑ ይጋራሉ። ከነዋሪዎችና ከማህበራት የሰማነውን ምላሽ ደግሞ የንግዱን ማህበረሰብ በማወያየትና እውነትነቱን ያረጋገጡልን የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ናቸው።
‹‹ምርት እያለ ነጋዴ በመጋዘን ውስጥ ደብቆ ነው የሚያሰቃየን። ይሄ ደግሞ የአሸባሪው ህወሓት ቡድንና ሸኔ ከከፈቱት ጦርነት ባልተናነሰ በአዲስ አበባ ሕዝብ ላይ የተከፈተ የኢኮኖሚ ጦርነት ነው ›› ይላሉ አንድ ኪሎ የስንዴ ዱቄት 55 ብር፣ ጤፍ 50 ብር መዲናችን ባሉ ገበያዎች መገብየታቸውን የነገሩን የአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስምንት ነዋሪ ቄስ አብርሃም ሲሳይ።
ሌላዋ አስተያየት ሰጪ የልደታ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ተዋበች በንቲ የቄስ አብርሃምን ሀሳብ ይጋራሉ። በኢኮኖሚው ላይ ከሚሰራው አሻጥር አንዱ ነጋዴው ሸቀጣ ሸቀጦችን አከማችቶና ደብቆ ለአንዱ ሸማች የጠየቀውን አለ ብሎ ሲሸጥ ለሌላው የለም ብሎ በመመለስ ህብረተሰቡ እንዲማረር ያደርጋል። ነጋዴው ሰው እየለየ መሸጡ ምርቱ እያለ ለሸፍጥ ያደረገው መሆኑን ያረጋግጣል ። የእህልና የሸቀጣ ሸቀጥ ዋጋ ከገቢያቸው በላይ ከሆነባቸው ቆይቷል። አሁን ወር መድረስ ሲያቅታቸው ብድር መበደርን አማራጭ አድርገዋል። አሁን ግን ‹‹ማርም ሲበዛ ይመራል ይባላልና አበዳሪዬም ሰለቻቸው ። እኔም የምይዘውን የምጨብጠውን አጥቻለሁ››ብለውናል።
የፌዴራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ በከተሞች በሚኖረው ሸምቶ አዳሪ ሕብረተሰብ የኑሮ ውድነት ጫና መፍጠሩ ሌላው የኢኮኖሚ ጦርነት ነው ይላል።ኤጀንሲውን በዋና መዲናችን አዲስ አበባና በሀገሪቱ ሌሎች ዋና ዋና ከተሞች ያጋጠመ የግብርና ምርቶች ዋጋ ንረትና አቅርቦት እጥረት በእጅጉ አሳስቦት ነው የሰነበተው። አስቦ ብቻ ሳይቀርም ከተሜው የኑሮ ውድነቱን ለመቋቋም እንዲችልና ከኢኮኖሚ አሻጠሩ እንዲድን ለማድረግ የአምራችና ሸማች የገበያ ትስስርን አመቻችቷል። በዚህ ትስስር መድረክ 31 አምራች ሕብረት ሥራ ዩኒየኖች ፣ 13 ሸማች ሕብረት ሥራ ዩኒየኖች እንዲሁም በፌዴራል የተደራጁ ሦስት የሕብረት ሥራ ማህበራት ተገኝተዋል ። የመገኘታቸው ዓላማ አምራች ሕብረት ሥራ ማህበራት ከሸማች የህብረት ሥራ ማህበራት ጋር የግብርና ምርት የግብይት ትስስር እንዲፈፅሙ ማድረግ ነበር። በአሁኑ ወቅትም ምርቶችን ወደገበያ እያስገቡና እያረጋጉ ናቸው።
አቶ አረጋ መኮንን በትስስሩ በከተሞች የሚታየውን የዋጋ ንረትና የምርት አቅርቦት እጥረት ለማረጋጋት ከተመረጡ አምራች ዩኒየን የሥራ ኃላፊዎች አንዱና በአማራ ክልል የሚገኘው የወደራ ሁለገብ የገበሬዎች ሕብረት ሥራ ዩኒየን ሥራ አስኪያጅ ናቸው።
የግብርና ምርት የዋጋ ንረትንና የምርት እጥረቱን ከመቅረፍ አንፃር ዩኒየኑ አዲስ አበባን ጨምሮ በሀገሪቱ ከተሞች ያደረገውንና እያደረገ ያለውን አስተዋጽኦ ይናገራሉ። ገበያውን ከማረጋጋትና ሸማቹ ሕብረተሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲገበያይ ከማድረግ አንፃር ዘንድሮ ከመሰረታዊ ማህበር አባል አርሶ አደሩ መሰብሰብ ከቻሉት 42 ሺህ ኩንታል የስንዴ፣ጤፍና ባቄላ ምርቶች በደብረ ብርሃን ከተማ ለሚገኝ ለህዳሴ ሸማች ማህበር በሶስት ወር ክፍያ ጤፍን ጨምሮ የተለያዩ የግብርና ምርቶችን ውል በማሰር ትስስር ፈጥረው አቅርበዋል። ማህበሩም በከተማው ለሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ፤በተጨማሪም ለዞኑ ጭምር በረጅም ክፍያና በተመጣጣኝ ዋጋ ያቀረበበት ሁኔታ አለ። እንዲሁም ለደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ ምርቶች እያቀረበ ይገኛል።በአጠቃላይ ለ 10 ክፍለ ከተማ ለሚገኙ ሸማቾች፣ በዞኑ ውስጥ ላሉ ሸማቾች ፣ ለመንግሥት የልማት ድርጅቶችና ለበጎ አድራጊዎች እጁ ላይ የሚገኘው ምርት ተደራሽ እንዲሆንና የዋጋ ንረቱንና የምርት አቅርቦት እጥረቱን እንዲቀንስ መስራታቸውን ይናገራሉ ።
‹‹ዓላማችን ትርፍ ማግኘት ሳይሆን የግብርና ምርቶችን ለሕብረተሰቡ በማቅረብ ገበያ ማረጋጋት ነው›› የሚሉት አቶ አረጋ የከተማውን የኑሮ ውድነት ለማርገብና ገበያውን ለማረጋጋት የስንዴ ዱቄት ለነዋሪዎች ያቀረቡበትና አሁንም እያቀረቡ ያሉበት ሁኔታ እንዳለ ገልፀውልናል። ስንዴው በአካባቢው ነዋሪ ለሆኑና ጥያቄ ላቀረቡ ለዩኒየኑ መሰረታዊ ማህበር አባልትም እየቀረቡ መሆናቸውን አጫውተውናል።
የፌዴራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ አዳማ ከተማ ባካሄደው መድረክ ላይ በአምራችና ሸማች ሕብረት ሥራ ማህበራት መካከል የከተማውን ነዋሪ የኑሮ ውድነት ችግር ለመቅረፍ የሚያስችሉ አዳዲስ የግብይት ትስስሮች እንዲካሄዱ ያደረገበት ሁኔታ ነበር። በመድረኩ የነዋሪውን ችግር ከመሰረቱ መቅረፍ የሚያስችሉ 150 ሺህ ኩንታል የግብርና ምርቶች የግዢና ሽያጭ ውልም ተፈጽሟል። ከ300 ሺህ ኩንታል በላይ የግብርና ምርት የግዢና ሽያጭ የመግባቢያ ሰነድ ውል የተፈፀመበት ነበር። በዚህ መሰረት ዩኒየኑ አሁን ላይ በመጋዘኑ የሚገኘውን 14 ሺህ 226 የተለያዩ ሰብሎች በተለይ ለአዲስ አበባ ከተማ በተመጣጣኝ በማቅረብ በዋጋ ንረትና ምርት አቅርቦት እጥረት ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ሰለባ የሆነውን ሕዝብ ለመታደግ ተዘጋጅቷል ። ለማቅረብ ካሰበው የግብርና ምርቶች መካከልም 13ሺህ 20 ኩንታሉ ጤፍ ነው።
በኦሮሚያ ክልል ሎሚ አዳማ የገበሬዎች ሕብረት ሥራ ዩኒየንም በዚህ በኩል መሰል አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል። ሥራ አስኪያጁ አቶ ታደለ አብዲ እንደሚሉት፤ በአካባቢያቸው የሚመረቱትን ጤፍ ፣ ቦሎቄ ፣ በቆሎ፣ ሽንብራና ምስር እንዲሁም ስንዴ ዱቄት የሚያቀርቡት በአብዛኛው ለከተሞች ነው። ይሁን እንጂ በተለያየ መልኩ ለአዲስ አበባ ይቀርባል። ምክንያቱም አዲስ አበባ በተለያየ ምክንያት የኑሮ ውድነት ጫና ገፈት ቀማሽ ትሆናለች ተብላ ስለምትታሰበው ፤በተጨባጭም ስትሆን ስለምትታይ ነው። ዘንድሮ ሰብስቦ በመጋዘኑ ካስገባው 61 ሺህ የተለያየ የግብርና ምርት ለአዲስ አበባ ከተማ ሸማቾች ማህበር ፣ለኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ለአደጋ መከላከል እና ዝግጁነት ኮሚሽን እንዲሁም ለተለያዩ አካላቶች ሲያቀርብ ቆይተዋል። አሁን ላይም እያቀረበ ይገኛል። በቅርቡ ዩኒየኑን ለየት የሚያደርገው ግብይት የሚያደርገው በመጋዘን ያለ ምርት ላይ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ አቶ ታደለ ይገልፃሉ ።በሁለተኛም ከህብረት ሥራ ማህበራቱ ከሚሰበሰበው ነው። በመሆኑም ውል ፈፅመው የፈረሰባቸው አንድም የሉም።
ማህበሩ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 2ሺህ 400 ኩንታል ጤፍ ማቅረቡን ነግረውናል። በተጨማሪም አዲስ አበባ ውስጥ ላሉ ሁሉም ሸማቾች ማህበርም አቅርቧል ።በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ 10ሩም ክፍለ ከተሞች ወደ አዳማ እየዘለቁ ምርት ከነሱ በመውሰድ ለገበያ የሚያቀርቡበት ሁኔታ መኖሩንም አብራርተዋል። በዚህ ብቻ ሳይሆን ዩኒየኑ በበዓላት ወቅት በከተሞች በተለይም በመዲናችን አዲስ አበባ የሚኖረውን ከፍተኛ የሥጋ ፍላጎት ለማርካትም የደለበ ከብት የሚያቀርብበትና የሥጋ ገበያውን የሚያረጋጋበት ሁኔታም እንዳለ ሥራ አስኪያጁ አጫውተውናል። ይሄንኑ አቅርቦት በፌዴራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ አማካኝነት በቅርቡ አዳማ ከተማ ላይ በተደረገ የአምራችና ሸማቾች ሕብረት ሥራ ማህበራት ትስስር እንደ አዲስ ማደሳቸውንና ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ በመጋዘን እና በመሰረታዊ ማህበራት እጅ ያለውን የግብርና ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ በማቅረብ ገበያውንና ነዋሪውን የማረጋጋትና ከኑሮ ውድነት የማላቀቅ ሥራ ለመስራት መዘጋጀታቸውን ይናገራሉ።
በተለይ ደግሞ ገቢው ዝቅተኛ የሆነውን ታች ያለውን የከተማዋን ነዋሪ ሕብረተሰብ ተደራሽ የማድረግ ዕቅድ አለው።ሥራ አስኪያጁ ዩኒየኑ የሚያቀርብበትን ዋጋ አስመልክተው እንደገለፁልን በነጋዴው እጅ የስንዴ ዱቄት እስከ 55 ብር በገባበት በአሁኑ ወቅት እንኳን ማህበሩ ኪሎውን በ32 ብር ነው። ኩንታሉን ጤፍ በ4ሺህ 650 ብር ነው ።
አቶ አበበ ወርቅነህ የአድማስ የገበሬዎች ሕብረት ሥራ ዩኒየን ሥራ አስኪያጅ ናቸው።ዩኒየናቸው ቸመና የተሰኘውን ዘይት በማምረትና ለገበያ በማቅረብ ይታወቃል ።በቀን አምስት ሺህ ዘይት የማምረት አቅም ሲኖረው በተለይ በዘይት ምርት ላይ የዋጋ ንረት ከገጠመና ምርቱም ከገበያ ከጠፋ ጀምሮ ገበያውን ለማረጋጋት በከተሞች አካባቢ ምርቱን ማቅረብ ከጀመረ ሰንብቷል ። በአሁኑ ወቅትም ከተሞች ላይ ትኩረት በማድረግ እንደሚያቀርብ ይናገራሉ።
በፌዴራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ አማካኝነት የአምራች ሸማች ትስስር በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወኪልነት የዘይት እጥረትና የዋጋ ንረት ለሚታይባት አዲስ አበባ ከተማ ለማቅረብ ውል ወስዷል።ይሁን እንጂ የዘይቱ ዋጋ ውድ በሚባል ደረጃ ነው የሚቀርበው። ሥራ አስኪያጁ አቶ አበበ ለመወደዱ ብዙ ምክንያቶች መኖሩን ይናገራሉ። አንደኛው ዘይቱ ጥራት ያለው ከኑግ ብቻ የሚመረት በመሆኑ ነው። ሁለተኛው ከኩንታል ኑግ ዘይት የሚወጣው 30 በመቶው ብቻ ነው።ከ እስከ ስድሳ በመቶው ፋጉሎ 10 በመቶው ደግሞ ቆሻሻ ነው። ሦስተኛው ምክንያት በአሁኑ ወቅት የኢንዱስትሪ ጥሪ ዕቃዎች ከመወደዳቸው ጋር የተያያዘ መሆኑን አንስተዋል።
በቅርቡ አዳማ ከተማ ላይ በአዲስ አበባ ከተማ የግብርና ምርት የዋጋ ንረትና የምርት አቅርቦት እጥረት ዙሪያ የሚመክር መድረክ ተካሂዶ ነበር።መድረኩ በከተሞች አካባቢ ፤ከከተሞችም የሀገሪቱ ዋና መዲና በሆነችው አዲስ አበባ የሚታየውን የግብርና ምርቶች ዋጋ ንረትና የምርት እጥረት የዳሰሰ ነበር።ዩኒየኖች ሀገሪቱ ያለችበትን ተጨባጭ ሁኔታና በተለይ ከተሞች ላይ የሚታየውን የኑሮ ውድነት ባማከለ ዋጋ ምርታቸውን ሊያቀርቡ እንደሚገባ ስምምነት ላይ ተደርሷል ።
ሠላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 22/2013