‹‹የትራንስፖርት ዘርፍ ለእያንዳንዱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ውጤታማነት መሰረት ነው። ከዚህ አንፃር የአዲስ አበባ መስተዳድር ባለፉት የለውጥ ዓመታት በተለይም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት አቅርቦቱን ለማስፋት በርካታ ሥራዎች መስራት በመቻሉ መሻሻሎች ታይተዋል። ›› ያሉን በአራዳ ክፍለ ከተማ በበዓታ ዳቦ ቤት ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ወይዘሮ ሳምራዊት ናቸው። ከስራቸው ጋር ተያይዞ ዘወትር የትራንስፖርት አገልግሎት ይጠቀማሉ። አገልግሎቱን የሚጠቀሙት በተለይ ከገብርኤል መሳለሚያ፤ አልያም ከአራት ኪሎ አንዳንዴም ከአቧሬ መርካቶ ለመጓዝ ነው።
አገልግሎቱን ካለፉት ዓመታት ጋር ሲያነፃፅሩት በብዙ ነገር መሻሻል አሳይቷል። አቅርቦቱ በመኖሩ እንደ ፊቱ አሁን ላይ አገልግሎቱን ለማግኘት ብዙ ጊዜ አያባክኑም። በመሆኑም እንደከዚህ ቀደሙ ለትራንስፖርት የሚያባክኑት ብዙ ጊዜ የለም። ረጃጅም ሰልፎች ቢታዩም አቅርቦቱ በመኖሩ ቶሎ ማግኘት ይችላሉ። በዚህም ደስተኛ ናቸው።
የትራንስፖርት ዘርፉ በተለይም በአቅርቦት በኩል ያሳየው መሻሻል የሚደነቅና የሚበረታታ ነው። ከታሪፍና ከስምሪት ጋር ተያይዞ ባለ ቁጥጥርና ክትትልም በኩል እንደ ወትሮው ዝምታ የለም። ተገልጋዩም ሆነ ተራ አስከባሪው የባለቤትነት ስሜት ስለሚሰማቸው ተስተካክሏል። አገልግሎት ሰጪው እንደ ቀድሞው ታፔላ ቀይሮ ወይም አንስቶ መስመሩን በመቀየር አገልግሎቱን ዘግቶ የሚሄድበት ሁኔታ ቀንሷል። ተራ አስከባሪው ስለሚያስገድደው ሕብረተሰቡም በያገባኛል ስለሚጠይቅ በዚህ በኩል ለውጥ እና መሻሻል አለ። ሆኖም እንደ አጠቃላይ ሲታይ ግን በተለይ በበዓላት ወቅት፣ በሥራ መግቢያና መውጫ እንዲሁም ተራ አስከባሪ በማይኖርበት ሁኔታ ተገልጋዩ የትራንስፖርት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ያገኛል የሚል ዕምነት የላቸውም። በመሆኑም ተገልጋዩ አገልግሎቱን ለማግኘት እየተቸገረ መሆኑን ራሳቸውን አብነት አድርገው ይናገራሉ ።
ይህ ችግር ደግሞ አንድም አቅርቦትና ፍላጎቱ ባለመጣጣሙ ሁለትም የስምሪትና ቁጥጥር ስርዓቱ ጠበቅ ላላ የሚልበት ሁኔታ በመፈጠሩ ነው ብለው ያምናሉ። ዛሬ በተያዘው በአዲሱ በጀት ዓመት በዚህ በኩል ጠበቅ ያለ ሥራ መስራትና ማስተካከል እንደሚገባም ምክራቸውን ለግሰዋል።
የፐብሊክ ሰርቪስ ተጠቃሚ እንደሆኑ የሚናገሩት አቶ ዳባ ጉርሙ ለትራንስፖርት እጥረት መቀረፍና ለአገልግሎት መሻሻል መንግስት ለሠራተኛው ፐብሊክ ሰርቪስ መመደቡን ማንሳት በቂ መሆኑን ይጠቅሳሉ። ነገር ግን አሁንም መንገዶች በተያዘላቸው ጊዜ አለመጠናቀቅ ዘርፉን አለማዘመን ችግሮች ጎልተው እንደሚስተዋሉ ያነሳሉ። ‹‹ከቃሊቲ መናኸርያ እስከ አቢሰኒያ ያለው መንገድ ከተጀመረ ስድስት ዓመታትን አስቆጥሯል›› በማለት ጠቅሰው እንኳን መኪና ሊሄድበት ለመርገጥም አይመችም። አሁን ላይ ገና ድሬኔጅ እየቀበሩ ነው ይላሉ።
መንገዱን ለማጠናቀቅ ሁለት ዓመት ይፈጃል። ቅዳሜና እሁድ ከቃሊቲ ስቴዲየም 15 ብር የሚሄዱበት አሁን 20 ብር ሆኗል። ከታሪፍ በላይ ለማስከፈላቸው ምክንያት እየሆነ ነው። ትምህርት ቤት ሲከፈትና መጨናነቁ ሲጨምር ታሪፉ መጨመሩ አይቀርም። በመሆኑም መኪና መብዛት ሳይሆን የትራንስፖርት ማሳለጫ መንገዶችን ማዘመን ያስፈልጋል ባይ ናቸው።
ወጣት አማኑኤል አበበ ለግማሽ ቀን መገናኛ አካባቢ የራይድ ትራንስፖርት አገልግሎት ስለሚሰጥ የአገልግሎቱን ሁኔታ በሚገባ እንደሚያውቀው ይናገራል። አገልግሎቱ ፊት ከነበረው አንፃር ሲቃኝ በየጊዜው መሻሻል ማሳየቱን ይጠቅሳል። መንግስት አቅርቦትና ፍላጎቱን ከከተማዋ እድገት ጋር ለማዋደድ አንበሳ የከተማና የሸገር አውቶቡሶችን እንዲሁም ሌሎች አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ ድጋፍ ሰጪዎችን በየጊዜው ወደ አገልግሎቱ እንዲገቡ ማድረጉንም ይገልፃል።
ፐብሊክ ሰርቪስ በራሱ የመንግስት ሰራተኛውን በመያዝ ከአቅርቦትና ከፍላጎት ጋር ለረጅም ጊዜ ሳይመጣጠን የቀረውን የአገልግሎቱን ችግር በመፍታታት ያደረገውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበክሮ ያነሳል። ‹‹ቅድሚያ ለብዙሃን ትራንስፖርት›› በሚል የተጀመረው አሰራር አገልግሎቱን ፈጣንና ቀልጣፋ ብሎም የተሻለ ለማድረግ ከፍተኛ አበርክቶ አለው። ይሄ አሠራር ለአውቶቡሶች ቅድሚያ በመስጠቱ እጥረቱን በመፍታትና አገልግሎቱን የተሳለጠና ቀልጣፋ በማድረግ በኩል ለውጥ እያመጣ መሆኑን ይናገራል።
ሆኖም የትራንስፖርት እጥረት ችግሩ አሁንም መቀረፍ አለመቻሉንም ይጠቅሳል። ሕብረተሰቡ ሥራ ውሎ ደክሞት ቤቱ ገብቶ በማረፊያው ሰዓት እንደገና ረጃጅም ሰልፎችን ለመጠበቅ መገደዱን ይጠቅሳል። ከዚህ ሰልፍ ጥበቃ ለመገላገል ብር ያለው ሰው ራይድም ሆነ ላዳ ታክሲ ተጠቅሞ ሊሄድ ይችላል። የሌለው ግን ረጅም ሰልፍ መጠበቁ ግድ ነው። ይህ ደግሞ ያሰበበት ቦታ ባቀደው ጊዜ ለመድረስ አያስችለውም። ሰርክ የሚመለከተው ትዕይንት ወጣቱን ያሳስበዋል። ብዙ ጊዜ እንደዚህ ዓይነት ችግር ሲከሰት የሚስተዋለው መንግስት ድጋፍ ሰጪ ብሎ ያስገባቸው የሸገር አውቶቡሶች ሙሉ ለሙሉ ድጋፍ ባለመስጠታቸው ነው።
ይሁንና በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች የሚታየውን ረጃጅም የትራንስፖርት ሰልፍ ለማስቀረት ብሎም ለመቀነስ የተለያዩ አውቶቡሶችን ወደ ዘርፉ በማስገባት ቁጥራቸውን ማብዛት መፍትሄ ሊሆን እንደሚችል ይናገራል። በስርዓት አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ቁጥጥርና ክትትል ማድረግም ያስፈልጋል። ሁሉም በዘርፉ የተሰማሩ አገልግሎት ሰጪዎች በሥራ መግቢያና መውጫ አገልግሎቱን በተገቢው መንገድ እንዲሰጡም ማድረጉ አሁን ያለውን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ ይጠቅማል።
የመርካቶ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ታዳጊ ወጣት የአብ ሥራ አሸናፊ የትራንስፖርት እጥረት ቢኖርም ለተማሪ ቅድሚያ መሰጠቱ እንደሚያስደስተውና በአዲሱ ዓመትም ይሄ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተስፋ ያደርጋል።
የራጉኤል አካባቢ ነዋሪና የዘጠነኛ ክፍሉ ተማሪ ታዳጊ ወጣት ናሆም ካሳሁን በበኩሉ፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት መንግስት ለተማሪው ትልቅ ትኩረት መስጠቱንና ምግብ፣ ጫማና ዩኒፎርም ከመቻል አልፎ ትራንስፖርት ያቀረበ መሆኑን ይገልጻል።
‹‹በትራንስፖርት ዙሪያ ሰው እጅግ እየተጨናነቀ ነው›› ያሉን ነዋሪነታቸው ልኳንዳ አካባቢ የሆኑት አቶ ኃይሉ አያሌው ናቸው። በዘርፉ ለውጥ መኖሩ የሚካድ አለመሆኑን ይጠቅሳሉ። ሆኖም አሁንም በአዲስ አበባ ከተማ ያለው የትራንስፖርት አገልግሎት ከከተማዋ ዕድገትና ከሕዝቧ ብዛት ጋር ሲነፃፀር መመጣጠን ባለመቻሉ ችግሩ አሁንም ሊፈታ አለመቻሉን ይገልፃሉ። ባሳለፍነው የክረምት ወራት ትምህርት ቤት ሲዘጋ እንኳን መጨናነቁ አለመቆሙንና አለመቀነሱን ያነሳሉ። ለእመጫት፣ ለነፍሰ ጡር፣ ለአካል ጉዳተኛና ለአረጋዊያን ቅድሚያ መስጠቱ ባህል ቀርቷል ሲሉም ቅሬታቸውን ያሰማሉ። በበዓላትና ትምህርት ቤት በሚከፈትባቸው ጊዜያት ደግሞ ችግሩ የሚባባስ መሆኑ እንደማይቀርም ይናገራሉ። ችግሩን በአዲሱ ዓመት ለመቅረፍ የከተማው ትራንስፖርት ባለስልጣንና ከተማ አስተዳደሩ ምን አስበዋል ሲሉም ይጠይቃሉ። አዲሱ ዓመት እነዚህ ሁሉ የአገልግሎቱ ችግሮች የሚቀረፉበት እንዲሆን በመመኘት ሀሳባቸውን ቋጭተዋል።
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለስልጣን ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ወይዘሪት እፀገነት አበበ ተገልጋዮች ከአገልግሎቱ ጋር አያይዘው ላነሱት ሀሳብና ጥያቄ ምላሽ ሰጥተውናል። የትራንስፖርት ፍላጎትና አቅርቦት ከከተማዋ ዕድገት ጋር የተመጣጠነ ያለመሆን ችግር ጎልቶ መስተዋሉን ይናገራሉ። በ2013 ዓ.ም ችግሩን ለመቅረፍ የተለያዩ ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል። የመፍትሄ እርምጃዎችም ተወስደዋል። በተያዘው በ2014 በጀት ዓመትም ይሄንኑ የዘርፉን ችግር የመፍታት ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል። ችግሩን ለመፍታት 500 የሸገር ድጋፍ ሰጪ አውቶቡሶችን ውል ፈፅሞ ያስገባበት እንደተጠበቀ ሆኖ ከተማ አስተዳደሩ የበለጠ አገልግሎቱን ለማመጣጠን ሶስት ሺ የሚሆኑ አውቶቡሶችን ግዢ ለመፈፀምም በሂደት ላይ ነው። በተጨማሪም በአዲሱ በጀት ዓመት 400 የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎችን ይረከባል።
በ2013 በጀት ዓመት በተለያየ መልኩ ወደ ዘርፉ እንዲቀላቀሉ ሲሰራ ቆይቷል። በቅርቡም የግል ባለ ሀብቱ ድጋፍ በመስጠት ወደ ዘርፉ እንዲገባ የማድረግ ሥራ ይሰራል። የአቅርቦትና ስምሪት ቁጥጥር ድጋፉን ያጠናክራል። ባለስልጣኑ በተሰጣቸው መስመር ገብተው አገልግሎት እንዲሰጡ የተሰጠውን ስልጣን በመጠቀም አገልግሎቱ የተሳለጠ እንዲሆን እየሰራ ይገኛል። በ2014 ተጠናክሮ የሚቀጥልና የቁጥጥርና የስምሪት ስርዓቱም አሁን ካለው በተሻለ መልኩ እንዲሆን ያስችላል የሚል ዕምነት አላቸው።
በቀጣይ ከባለ ድርሻ አካላቶች ጋር በመነጋገር ዘርፉን ወደ ማዘመን የሚሄድበት አሠራር ይዘረጋል። መሰረተ ልማትን ከማስፋት ጋር ተያይዞ ዲፖዎችንና ተርሚናሎችን በመገንባት መሰረተ ልማቱን የማስፋት ሥራ በስፋት የሚከናወን ይሆናል። ይህ ሥራ በ2014 በጀት ዓመት የበለጠ ተስፋፍቶ የሚሰራ መሆኑን ዳይሬክተሯ አንስተዋል። ከመሰረተ ልማቱ ጋር ተያይዞ ከ2014 እስከ 2034 ያሉ ችግሮችን በመፍታት የትራንስፖርት ዘርፉን የተሳለጠ የማድረግ አብይ ተግባራት ይከናወናሉ።
ባለስልጣኑ ከያዝነው አዲስ ዓመት መግባትና የትምህርት ቤቶች መከፈት ጋር ተያይዞ የትራንስፖርት አቅርቦቱ ይበልጥ ሊሰፋ፤ ስምሪቱና አገልግሎቱም ከዚሁ ጋር ለማሳለጥ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል።
ከአዲስ ዓመት በዓል ዋዜማ ጀምሮ በተለይም ከመባቻው አንስቶ እንቅስቃሴዎች ይበዛሉ። ለበዓል ገበያ፣ ለሥራ፣ ለትምህርት የሚደረጉ ዝግጅቶች አሉ። ከዚህ ጋር ተያይዞ የትራንስፖርት አገልግሎት ፈላጊው ቁጥር በእጅጉ ይጨምራል። በተለይም ትምህርት ቤት ሲከፈት ተማሪም አገልግሎቱን በእጅጉ ከመፈለጉ ጋር ተዳምሮ የትራንስፖርት አገልግሎት በፈላጊ ህብረተሰብ የሚጨናነቅበት ሁኔታ ይፈጠራል። መጨናነቁ ደግሞ ብዙ መዘዞች አሉት። በራሱ ለአደጋ መንስኤ የሚሆንበት ጊዜም ቀላል አይደለም።
በተጨማሪም ከመንግስት ሠራተኛ ውጪ በግሉ የሥራ መስክ የተሠማራው የሕብረተሰብ ክፍል ዘግይቶ ወደ ሥራው የሚገባበት፤ ምን አልባትም ከሥራው የሚስተጓጎልበት ሁኔታ ይፈጠራል። እንዲሁም ሰርቪስ ተጠቃሚ ያልሆኑና በትራንስፖርት አገልግሎት የሚጠቀሙ ብዙ ተማሪዎች አሉ። እነዚህ ተማሪዎች በትራንስፖርት ዕጦት ከትምህርት ገበታቸው ሊዘገዩ ብሎም ሊቀሩ የሚችሉበት ምክንያት ሊፈጠር ይችላል።
አጠቃላይ በዚህ ወቅት በዓላቱ፣ ገበያው፣ ከገበያ መልስ የጓዝ መብዛት፣ ቤተሰብ መጠየቅ፣ ትምህርት ቤት መከፈቱ ከሠራተኛው ጋር ተዳምሮ የትራንስፖርት ምልልሱ፤ እንዲሁም የተጠቃሚው ቁጥር ቀድሞ ከነበረው የሚበዛበት ሁኔታ ይኖራል። ውይይቱ የትራንስፖርት ተጠቃሚው ሕብረተሰብ ሳይቸገር እነዚህን ጉዳዮች ከወትሮው በተሻለ መንገድ እንዲከውን ማስቻልን ያለመ ነበር። ከ10ሩ የባለስልጣን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በተጨማሪ የታክሲና የሀይገር ማህበራት እንዲሳተፉበት ተደርጓል። በተጨማሪም የተራ ማስከበር ማህበራት እንዲሳተፉበት ሆኗል። ሁሉም አካላት ግንዛቤ እንዲጨብጡ ከማድረግ ባሻገር በዚህ ወቅት ሥራቸውን በምን መንገድ ማከናወን እና ሕብረተሰቡን ማገልገል እንደሚገባቸው ራሱን የቻለ የትራንስፖርት አገልግሎቱን ዘርፍ በተገቢው መንገድ የሚያዘመን፣ የሚያቀላጥፍና የሚያሳልጥ አቅጣጫ ተቀምጦ ከበዓል ዋዜማ ጀምሮ በዚሁ አግባብ እየሰሩ ይገኛሉ።
በተለይም የተቀመጠው አቅጣጫ ከትምህርት ቤት መከፈት ጋር ተያይዞ የነገ ሀገር ተረካቢ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንዳይዘገዩም ሆነ እንዳይስተጓጎሉ በማድረግ በኩል ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል። በዚህ በኩል የባለስልጣኑ ተራ አስከባሪዎች ተማሪዎች ቅድሚያ አገልግሎት የሚያገኙበትንና ወደ ትምህርት ገበታቸው በጊዜ የሚደርሱበት ሁኔታ ተመቻችቷል።
ከተማሪ በተጨማሪ ለነፍሰ ጡሮች፣ ለአካል ጉዳተኞች፣ ለአቅመ ደካሞችና ለአረጋውያን ጭምር ቅድሚያ የሚሰጥ ይሆናል። አቅጣጫው አሁንም በዚሁ መንገድ እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎቱን ቅድሚያ የሚያገኙበትን የበለጠ ያጠናክርና በተገቢው መንገድ እንዲተገበር ያደርጋል። ከዚሁ የትራንስፖርት ተገልጋዩ ቁጥር ከመብዛቱ ጋር ተያይዞ ሕብረተሰቡ ምንም አይነት ችግር ሳያጋጥመው በሰላም ወጥቶ እንዲገባ የቁጥጥርና ስምሪት ስርዓቱን ቀድሞ ከነበረው የበለጠ የማጠናከር ሥራ ይሰራል። የትራንስፖርት አቅርቦትና ፍላጎቱ ተመጣጥኖ ባለመገኘቱና ተርሚናሎች፣ የአውቶቡስ መጠለያዎች አለመኖራቸው የመንገድ ትራፊክ መጨናነቅ ችግሮች ነበሩ።
ከትራንስፖርት ስምሪትና ቁጥጥር ጋር ተያይዞ በዘርፉ ያልተሰማሩና የግል ጥቅማቸውን በማሳደድ አገልግሎት ሰጪ መስለው ሕብረተሰቡን ለሌላ አደጋ የሚያጋልጡትን ለይቶ ለሚመለከተው አካል የማቅረብ ሥራ ለማከናወን ታቅዷል።
ባለስልጣኑ በበዓላት ወቅት ከሚፈጠር ጥድፊያና ግርግር ከተሞላበት እንቅስቃሴ በመቆጠብ ሊደርስ ከሚችል የትራፊክ አደጋና ዘረፋ እና ሌሎች ችግሮች ህብረተሰብ ራሱን እንዲጠብቅ አሳስቧል። በተለይ አጫጭር ጉዞዎችን በእግር በመጓዝ ራሱንና ቤተሰቡን እንዲጠብቅ በእግር የመሄድ ልምድን ማዳበር እንደሚገባም መክሯል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን መስከረም 1 ቀን 2013 ዓ.ም