ቅድስት ሰለሞን
ጉዞው ወጣ ገባ የበዛበት ነው። በየመሃሉ የሚገኘው ከፍታ አቅምና ብርታት ሆኖ ሲያጀግን፤ ዝቅተኛው ደግሞ ከተለያየ ችግር ጋር ሲያላትም ዛሬ ላይ አድርሷል። እንዲያም ሆኖ መንገዱ መከራ ብቻ ሳይሆን ያሳየው ለኢትዮጵያውያንና ለትውልደ ኢትዮጵያውያን መደጋገፍና አብሮነት የዋልታና የማገር ያህል አስተሳስሮ በአንድ ልብ እስኪያስቡ ድረስ ያበቃ ስለመሆኑም ይታመንበታል – ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት።
የመሰረት ድንጋይ የተጣለበትን 10ኛ ዓመት ክብረ በዓሉን ከቀናት በኋላ እንደሚያከብር የሚጠበቀው ይህ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አስረኛ ዓመቱን ሲደፍን በብዙ ድካና አሳር ቢሆንም፤ በእነዚህ ዓመታት ሁሉ በተጋፈጣቸው ፈተናዎች አንዴም ቢሆን እጅ አለመስጠቱ የአደባባይ ምስጢር ነው። እርግጥ ነው ብዙ ፈተና፤ ብዙም ስኬት ያለው ታላቅ ፕሮጀክት ስለመሆኑ አፍሪካውያንን ብቻ ሳይሆን ሌላውን የዓለም ህብረተሰብ ማነጋገር መቻሉ አንዱ ማሳያ ሆኖ ሊጠቀስ ይችላል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሰሞኑን በፓርላማ ቀርበው ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት፤ ‹‹የፈለገው ዓይነት ፈታኝ ሁኔታ ቢያጋጥም እንኳ ግድቡ ለህዝብ በተገባው ቃል መሰረት ይፈጸማል›› ሲሉ ተደምጠዋል። የህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት ኢትዮጵያ በጣም እየተፈተነችበት ያሉ ብዙ ጉዳዮች ቢኖሩባትም ግድቡን ግን ለኢትዮጵያ ህዝብ ቃል በተገባው መሰረት ለማሳካት ዝግጁ መሆኗን ያለምንም ጥርጥር ተናግረዋል። ይህም ቃል የሚታጠፍ ሐሳብ አለመሆኑንም ነው አበክረው የገለጹት።
እርግጥ ነው ፈተናው ብዙ ነው። ውጤቱ ደግሞ አመርቂ ስለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። ኢትዮጵያ የቱንም ያህል የጠበቀችውም ያልጠበቀችውም ትንኮሳ ቢበዛባትም ሁሌም ቢሆን ዓላማዋ አንድ ነው፤ በልጽጎ የሕዝቧን የኑሮ ሁኔታ መቀየር። ይህን ስታደርግ የትኛውንም አካል ጎድታ እንደማይሆንም ደጋግማ ገልጻለች። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉትም ፍላጎቷ አብሮ ማደግ ነው። ኢትዮጵያ ግብፅንም ሆነ ሱዳንን የመጉዳት ፍላጎት እንደሌላት በየአጋጣሚውና ለድርድር በሚቀመጡበት ጊዜ ሁሉ ከመግለጽም ቦዝና አታውቅም።
ለዚህ ደግሞ ማሳያ የሚሆነው ከ86 በመቶ በላይ የውሃ አበርክቶ ያላት አገር እንደመሆኑ በራሷ መንግሥትና ህዝብ፤ በገዛ ምድሯ እየገነባች ባለው የህዳሴ ግድብ ለሱዳን ቀደም ሲል እንደልቧ መሬቷን በመጠቀም የመስኖ ሥራ እንኳ እንዳትሠራ ጋሬጣ የሆነባትን የጎርፍ አደጋ መቀነሱ እንዲሁም ከህዳሴ ግድቡ የኤሌክትሪክ ኃይል በተመጣጣኝ ዋጋ ማስገኘት መቻሉ ከብዙ ጥቂቱ ስለመሆኑ ማንሳት ይቻላል። ግብፅም ብትሆን የተመጠነ ውሃ እንድታገኝ የሚያስችላት ነው።
ደግሞም ኢትዮጵያ የአባይን ውሃ መሰረት አድርጋ በምታለማው ልማት ማንንም ከጨዋታ ውጪ እያደረገች አለመሆኑ እሙን ነው። ግብፅ ከሱዳን ጋር እኤአ 1959 ላይ በዓባይ ወንዝ ላይ የተፈራረመችው ስምምነት ግን ከ86 በመቶ በላይ የውሃ አበርክቶ ያላትን ኢትዮጵያ፣ 55 ነጥብ 5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ለግብፅ፣ 18 ነጠብ 5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ደግሞ ለሱዳን በማድረግ ኢትዮጵያን ያገለለ ስምምነት ፈጽመዋል። የቀረውን የውሃ ድርሻ ደግሞ በበርሃ እንዲሰርግ አድርገዋል። ይህ እንግዲህ በኢትዮጵያ ላይ ክህደት የመፈጸም ያህል የሚቆጠር ነው።
በዚያን ወቅት የአባይን ውሃ ለራስ ብቻ ለማድረግ ደፋ ቀና ብለው መብታቸውን ያከበሩ የመሰላቸው እነግብፅ፤ ዛሬ ኢትዮጵያ በራሷ ገንዘብ የህዳሴ ግድብን ገንብታ ህዝቧን ከጨለማና ከድህነት ለመውጣት በምትታትርበት በዚህ ጊዜ ‹‹ለምን ሲባል ህዝቧ የመብራት ጭላንጭል ይመለከታል፤ ለምንስ ከድህነት ወለል በታች አንገቱን ቀና ያደርጋል›› በሚል ዓይነት አካሄድ የህዳሴ ግድባችን ከጫፍ እንዳይደረስ ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም ማለት ይቻላል።
የግብፅ አጋሮችና ግብፅ ሲሻቸው በወታዳራዊ ኃይል ለማስፈራራት፤ ሲፈልጉ ደግሞ ኢትዮጵያን የሚቃወሙ ኃይሎችን ወገባቸውን ታጥቀው በመደገፍ ኢትዮጵያን ለማዳከም ብዙ ተሰቃይተዋል። ይህም ያሰቡትን ያህል ወደፊት አልሄድ ብሎ ሳይሳካላቸው ሲቀር ደግሞ በኢትዮጵያውያን መካከል የተለያዩ ከፋፋይ አጀንዳዎችን በማቀበል አገሪቱን የማፍረስ ጥማታቸውን ለማርካት ሲንገላቱ ሰንብተዋል። በዚህም ህልማቸው እውን መሆን ሲያቅተው ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር መልካም ጉርብትና እንዳይኖራት በብዙ ተፍገምግመዋል።
ይሁንና የኢትዮጵያውያንና የትውልደ ኢትዮ ጵያውያን ሁሉ አሻራ ያረፈበት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግን በሀገር አቀፍ ደረጃ ላሉ ኢትዮጵያውያንም ሆነ ከአገር ውጭ ላሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በታላቅ ደረጃ ተግባቦትን የፈጠረ መለያ ሰንደቅዓላማቸው ሆኖ ዘልቋል።
በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል የተፈጠረውን የድንበር ውዝግብ ተንተርሰው የራሳቸውን አጀንዳ ለማስፈጸም ደፋ ቀና የሚሉ አካላትና ግብረአበሮቻቸው የአቅማቸውን ያህል ብቻ ሳይሆን ከአቅማቸውም በላይ ለሴራና ለተንኮል ሲፍገመገሙ ከሰሞኑ መስተዋላቸው፤ በህዳሴ ግድብም ሆነ በአገር ድንበር ጉዳይ የኢትዮጵያ ህዝብ እንዴት እንደሚተባበር ያለውን ታሪክ ካለማወቅ የመጣ ወይም ደግሞ እያወቁ ለማለቅ አስበውም ሊሆን ይችላል የሚል እምነት አለኝ።
የህዳሴ ግድብ የሚጠናቀቅበት ጊዜ ቀርቧል፤ ከጥቂት ወራት በኋላ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ይጀመራል። የውሃ ሙሌቱን ደግሞ የትኛውም ኃይል ማስቆም እንደማይችል ሳይፈታ የታለመ ሐቅ ነው። ኢትዮጵያን ሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት ሊያግዳት የሚችል አካል እንደማይኖርም በተደጋጋሚ በመንግሥት በኩል ሲገለጽ ቆይቷል። ይህ የሚሆነው ግን ግብፅና ሱዳን እንደሚሉት በእብሪት አሊያም በማንአለብኝነት ሳይሆን ኢትዮጵያ የመልማት መብቷን ተጠቅማ ሌሎቹን የታችኛዎቹን ተፋሰስ አገሮችን ሳትጎዳ እንደሆነም ግልጽ ነው። ለዚህም የኢትዮጵያ መንግሥት እርግጠኛ መሆኑን ጠቅሷል።
አሁን ምንም እንኳ ጨለማው የበረታ ቢመስልም የሕዳሴ ግድቡ ማጠናቀቂያ ጫፍ ላይ የደረስን በመሆኑ ሊገፍ ጥቂት ጊዜ ብቻ ቀርተውታል። በሐሰት የተጠነሰሱብን ዘመቻዎች ሁሉ በእውነት እየተገለጡ ነው። በእብሪት የተጠነሰሰብን ሴራዎች እየከሸፉ ከመሆናቸው በተጨማሪ ኢትዮጵያውያኑን ወደብልጽግና ጎዳና እየገፏቸው ይገኛሉ። ኢትዮጵያን ለማሳጣትና ለማሸማቀቅ የተቃጡ የትኞችም የሦስተኛ ወገን አድማዎች እየተፈረካከሱ ስለመሆናቸው ማሳያዎች ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል። ኢትዮጵያ በጉርብጥብጡ የአስር ዓመት የህዳሴ ግድብ ግንባታ ጉዞዋ አንዴም ቢሆን እጅ አለመስጠቷ ስኬቷን የማይወዱ አካላት ጠንቅቀው ቢያውቁም ይህን ጥንካሬ ግን ለራሳቸው እንኳ መልሰው ማሰብ እንደሚከብዳቸው ከድርጊታቸው ማስተዋል ይቻላል።
ዛሬ በትናንቱ ያረጀና ያፈጀ ቅኝት ኢትዮጵያ መደነስ እንደማትሻ እነግብፅ ሊረዱ ይገባል፤ ትናንት እስከነበረው ክፋቱ እብስ ብሏል፤ ዛሬ አዲስ ቀን ነው፤ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ግድብ ሠርታ ልማቷን ለማስቀጠል የነበራት ፍላጎት ጥንት ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ማድረግ ባትችልም ዛሬ ግን በልጆቿ አንጡራ ገንዘብ ጥንት ያለመችውን ፕሮጀክት ለማሳካት ጫፍ ላይ ደርሳለችና አሁንም እንዳለፉት አስር ዓመታት የብዙዎቻችንን ትኩረት ትሻለች። ጤና ይስጥልኝ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 18/2013