ፍሬህይወት አወቀ
ለነዋሪዎቿ በቂ መጠለያ ማቅረብ የተሳናት አዲስ አበባ ከተማ ዕለት ዕለት ህገ ወጥ የቤቶች ግንባታና ለሰው ልጆች መኖሪያ ምቹ ያልሆኑ የላስቲክና የሸራ ቤቶች ሊታዩባት የግድ ሆኗል። በተለይም በአሁኑ ወቅት ችግሩ ከምንግዜውም በላይ ሰቅዞ ይዟታል። ታዲያ መንግሥት እጅግ ተባብሶ ለመጣው የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ችግር እስካሁን ሲሰጥ ከነበረው ምላሽ በተለየ መንገድ አማራጮችን ወስዶ መንቀሳቀስ ያለበት ጊዜ አሁን ስለመሆኑ እና የግሉን ዘርፍ በተሻለ ሁኔታ ማሳተፍ እንደሚገባ ባለሙያዎች ያነሳሉ።
ሀገሪቱ በቀደመው ጊዜ በከተማ ቤቶች ላይ ምንም አይነት ፕሮግራም ወይም ስትራቴጂ ያልነበራት መሆኑን አስታውሰው ነገር ግን ካለፉት 15 እና 16 ዓመታት ወዲህ መንግሥት በቤት ልማት ዘርፍ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ማድረጉ መልካም ጅማሮ እንደነበር የፍሊንት ስቶን ሆምስ ምክትልሥራ አስኪያጅ አቶ ብሩክ ሽመልስ አንስተዋል።
መንግሥት የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ እስካሁን በተጓዘበት መንገድ የወሰዳቸው የመፍትሔ አማራጮች የተወሰነ ለውጥ ቢመጣም ችግሩን ማቃለል ግን አልተቻለም። በርግጥም ያኔ በነበረችው አዲስ አበባ እና አሁን ባለችው አዲስ አበባ መካካል ሰፊ ልዩነት መኖሩ ዕሙን ነው። በዛው መጠን ደግሞ የቤት ፍላጎቱ ሰፍቷል። ስለዚህ ችግሩን ለመቅረፍ እስካሁን የተኬደበትን መንገድ መቀየር ያስፈልጋል። ምክንያቱም ወቅቱ ከችግሩ ግዝፈትና ፍጥነት እንዲሁም ከሚቀርበው መፍትሔ ጋር መጣጣም አልቻለም። ስለዚህ የግድ ሌላ አይነት አማራጮችን ለመጠቀም ወቅቱ በራሱ እያስገደደ ነው።
‹‹የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ ጥረታችን በሌላ አቅጣጫ እንድንቀጥል ወቅቱ እየመራን ነው›› የሚሉት አቶ ብሩክ፤ የከተማ ፖሊሲውን ጨምሮ አጠቃላይ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ከከተማ አስተዳደር አሰፋፈር፣ የከተሜነት አስተሳሰብን ሙሉ በሙሉ መከለስ ያስፈልጋል። የቤት አቅርቦቱ በምን መንገድ መቅረብ እንዳለበት፣ ማን ምን ማቅረብ እንዳለበት፣ ሌሎች አማራጮችስ ምንድናቸው ብሎ ማስብና መወያየት ይጠይቃል።
ለዚህ ደግሞ የግሉ ዘርፍ ያለው ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ መንግሥት ሊጠቀምባቸው ይገባል። በቤት ልማት ዘርፍ የግል አልሚዎች ወይም ሪልስቴቶች የማይተካ ሚና አላቸው። ይሁንና በሀገሪቱ ባለው የንግድ ስርዓት የተነሳ እንዲሁም ከዘርፉ ባህሪ በመነሳት ያላቸው የገበያ ድርሻ አነስተኛ በመሆኑ የግል አልሚዎች ሚናቸው ጎልቶ አይታይም። ነገር ግን ካምፓኒዎቹ ምቹ ሁኔታ ከተፈጠረላቸውና መንግሥት ቀርቦ ያለባቸውን ችግር በመፈተሽ መቅረፍና በስፋት ወደ ዘርፉ እንዲገቡ ማድረግ ከተቻለ ችግሩን የመቀነስ አቅም አላቸው።
ያደጉ ሀገራትም ሆኑ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ችግርን መፍታትና ዋጋውን ማረጋጋት የቻሉት በግል ዘርፍ አስተዋጽኦ ነው። ኢትዮጵያም ለመኖሪያ ቤት አቅርቦት የመጨረሻው መልስ ሰጪ መሆን የሚችለውን የግሉ ዘርፍ ተሳታፊ በማድረግ ችግሩን ማቃለል ይቻላል። አለበለዚያ መንግሥት አሁን እየወሰደ ያለውን አማራጭ ብቻ ተከትሎ መጓዙ የማያዋጣ እንደሆነ አቶ ብሩክ ይመክራሉ።
በሀገሪቱ የሚገኙ ጥቂት የማይባሉ የግል አልሚዎች ሰፊውን የማህበረሰብ ክፍል ተደራሽ ሲያደርጉ አይታይምና እንዴት ተደራሽ ይሁኑ? በማለት ላነሳንላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፤ ቤት በባህሪው ከፍተኛ ኢንቨስትመንትን የሚጠይቅ በመሆኑ አንድ ቤተሰብ ከፍተኛ ወጪ አውጥቶ የተለያዩ ሸቀጦችን ለቤተሰቡ ይገዛል። ነገር ግን ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቀው ቤት ምንም ያህል በተመጣጣኝ ዋጋ ቢቀርብም ዋጋው ቤተሰቡን መፈታተኑ አይቀርም። ለዚህም ሲባል በመላው ዓለም የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም ሰዎች የቤት ባለቤት እንዲሆኑ ይደረጋል።
በሀገሪቱም መንግሥት ባስቀመጠው አማራጭ በ10/90፣ በ20/80ና በ40/60 ፕሮግራሞች ዜጎችን የቤት ባለቤት ለማድረግ በተደረገው የ17 ዓመት ጥረት አራት መቶ ሺ የሚደርስ ቤት እንኳን መገንባት አልተቻለም። ይህ የሚያሳየውም ደግሞ ዘርፉ ከፍተኛ የሆነ ኢንቨስትመንት የሚጠይቅና በአንድ ጊዜ ማዳረስ ባለመቻሉ ነው። ይሁንና መንግሥት እስካሁን ያቀረበው ቤት ካለው ፍላጎት አንጻር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።
የግል አልሚዎችም እንዲሁም ላለፉት 25 ዓመታት ከጀመረው ከሀያት ሪልስቴት ጀምሮ ጠቅላላ በሀገሪቱ የሚገኙት አልሚዎች የገነቡት ቤት ቢደመር 30 ሺ አይሞላም። ነገር ግን እነዚህ ቤቶችም ተደራሽ መሆን የቻሉት የገቢ መጠናቸው ከፍተኛ ለሆኑ ጥቂት ዜጎች እንጂ አቅም ያላቸው በሙሉ ማግኘት አልቻሉም። ይህም የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ያለውን ችግር አመላካች ነው። ይሁን እንጂ መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የማኅበረሰብ ክፍሎች መንግሥት በሚያቀርባቸው አማራጮችም ሆነ በግሉ ዘርፍ አማካኝነት ተደራሽ ለማድረግ ሌሎች ዘዴዎችን መቀየስ ይገባል።
ለዚህም መንግሥት ከግል አልሚዎች ጋር ተቀናጅቶ እስካሁን ያልሰራውን ሥራ አሁን ላይ መስራት ይኖርበታል። ምክንያቱም በመንግሥትም ሆነ በግሉ ዘርፍ የተገነቡት ቤቶች በየዕለቱ እየጨመረ ከመጣው ፍላጎት ጋር ፍጹም መጣጣም አልቻለም። ካለፉት አሥር ዓመታት ወዲህ አዳዲስ የመጡ ቤት ፈላጊዎች አዲስ አበባ ውስጥ ብቻ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ይሆናሉ። ይህ የሚያሳየውም እየተወሰዱ ያሉት ሙከራዎች አሁን ላይ እንደማይሰሩና ብዙ ርቀት የሚያስጉዙ አለመሆናቸውን ነው ።
ስለዚህ አሁን ያለው አማራጭ የመንግሥትና የግል አጋርነትን አጠናክሮ መስራት ነው። ለተግባራዊነቱም የግልና የመንግሥት አጋርነት የሚባል አዋጅ መኖሩን አቶ ብሩክ ያነሳሉ። አዋጁም መንግሥትና የግል ባለሀብቶች ትላልቅ በሆኑ ኢንቨስትመንቶች እንዴት በጋራ እንደሚሰሩ የሚያሳይ ነው። ይህን በቤቶች ልማት ላይ ተግባራዊ ማድረግ ይቻላል። ለአብነትም በመልሶ ማልማት ፕሮግራም የግል ባለንብረቶች ተደራጅተው መንግሥትም መሬቱን ይዞ አንድ አካል በመሆን ቤቶቹን ባለሀብቱ እንዲገነባ በማድረግ ነዋሪዎቹ መሬቱ እንዲለማ በመፍቀዳቸው ብቻ በተሻለ ቤት መኖር ይችላሉ ። ተጨማሪ ቤቶችን በመገንባትም ሌሎች ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል።
መንግሥት በዚህ አይነት የተቀናጀ አቀራረብ ከግሉ ባለሀብት ጋር በጋራ ለመስራት የግንባታ ፈቃድና ሌሎች መመሪያዎችን አመቻችቶ ህጋዊ ዕውቅና በመስጠት ካልሄደበት ችግሩን መፍታት አይቻልም።በተጨማሪም የውጭ ባለሀብት ገንዘብ ይዞ ተጋሪ መሆን የሚፈልግ አካል ካለም አገልግሎቱን ቀልጣፋ የሚያደርገው በመሆኑ ማበረታታት ያስፈልጋል። በዚህ መንገድ በትብብር በጋራ መስራት ካልተቻለ አሁን ባለው ፍላጎት በዓመት አንድ ሚሊዮን ቤት እየተፈለገ ነገር ግን 20 እና 30 ሺ ቤት ብቻ እየቀረበ ችግሩን ማቃለል አይቻልም። ዛሬ የተለያዩ አዳዲስ አማራጮችን በማምጣት ፍላጎትና አቅርቦቱን ለማጣጣም ካልተቻለ ችግሩ ነገ ከነገ ወዲያ እጅጉን የከፋ ይሆንና ማጣፊያው ያጥራል።
የተለያዩ አማራጮችን ለመጠቀም የምንገደደውም በሀገሪቱ ያለው የፋይናንስ እጥረት ከፍተኛ በመሆኑ ነው። ምክንያቱም ባንክ ለጋራ መኖሪያ ቤቶች እያቀረበ ያለውን ፋይናንስ ለቤት ፈላጊዎች በሙሉ ማቅረብ ቢችል አሁን የሚስተዋለው ሰፊ የመኖሪያ ቤት ችግር ላይፈጠር ይችላል። ነገር ግን ሀገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የፋይናንስ ችግር አለባት። ያ ባይሆንና ፋይናንሱ ቢኖር ሁሉም ባንኮች ለቤት ልማቱ ከፍተኛ በጀት መድበው ብድር ቢሰጡ በቀላሉ ቤት ሰርቶ ማቅረብና ችግሩን ማቃለል ይቻል ነበር።
ስለዚህ ሀገሪቷ ያለባትን የፋይናንስ ችግር በመረዳት አማራጮችን ተጠቅመን በጊዜ መፍትሔ ካልሰጠነው ችግሩ ይበልጥ ይወሳሰባል። በተለይም አዲስ አበባ ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ለኑሮ የማትመች፤ የመኖሪያ ቤት እጅግ የተወደደባት፤ የትራንስፖርት አገልግሎቷ እጅግ የተጨናነቀባት፤ ዜጎች የሚማረሩባት ከተማ ሆናለች።
ከተሞች መሠረተ ልማት ሳይሟላላቸው ሰው ብቻ የሚከማችባቸው እየሆኑ ችግሩ በክልል ከተሞችም ተመሳሳይ እየሆነ መምጣቱ እጅግ አሳሳቢ ነው የሚሉት አቶ ብሩክ፤ አጠቃላይ የከተሞች አከታተም ሊቃኝ ይገባል። ከተማ ሲባል ዋና ዋና የክልል ከተሞችን ብቻ ሳይሆን፤ የገጠር ከተሞችን ጭምር ማካተት የግድ ነው። የመንግሥት ፕሮግራም የከተማ ማዕከላትን አርሶ አደሩ ጋር መፍጠር የሚለውን ዓላማ አድርጎ የተነሳ ቢሆንም አልተሰራበትም።
የክልልና የገጠር ከተሞች ማዘጋጃ ቤት ተቋቁሞላቸው በፕላን መምራት ከተቻለ ከተሜነትን በማፋጠን በመላው ሀገሪቱ የተመጣጠነ የከተሜነት ባህልና የከተማ ዕድገትን መፍጠር ይቻላል። ይህም ማለት ደግሞ አውራ ከተማ በሆነችው አዲስ አበባ ላይ የሚፈጠረውን ጫና መቀነስ ማለት ሲሆን፤ የክልል ከተሞችን ከአውራ ከተማው ጋር ማመጣጠን የሚያስፈልግ መሆኑንም አቶ ብሩክ ያስረዳሉ።
በአንድ ሀገር ጤናማ የከተሞች አሰፋፈር አለ የሚባላው ከትልቁ ከተማ ሁለተኛው ትልቅ ከተማ በግማሽ የሚያንስ መሆን አለበት። ነገር ግን ከአዲስ አበባ ቀጥሎ ያለው ከተማ አዳማ መሆኑን ጠቅሰው አዳማ ደግሞ የአዲስ አበባን ግማሽ አይደለም 1/20ኛ እንኳን አትሆንም፤ ስለዚህ በሀገሪቱ ያለው የከተሞች አሰፋፈር ጤናማ አይደለም። ይህ ደግሞ ችግሩን የከፋ ያደርገዋል ይላሉ።
ጤናማ የከተሞች አሰፋፈርን ለመፍጠር የክልልና የገጠር ከተሞችን በስርዓት መምራት ያስፈልጋል። ይህም ሲባል የህዝቡ አሰፋፈር ስርዓትና ፕላን ያለው እንዲሆን ማድረግ አንዱ ነው። ሌላው የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትንና የማምረቻ ኢንዱስትሪ ማዕከላትን በዲዛይኑ ማካተት ቁልፍ ጉዳይ ነው። ይህ ካልሆነና አሰፋፈራችን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ካልተገራ በቀጣይ ችግሩ ከዚህም በበለጠ ገዝፎ ከተሞቻችን ለምንም የማይመቹ ይሆናሉ። በዚህም የህዝቡ ኑሮ ይበልጥ እየዘቀጠ፤ የአኗኗር ዘዴዎች እጅግ እየወረደ፤ ለመኖር ሳይሆን መች ለቅቄ በወጣሁ የምንላት ከተማ ትሆናለች።
ለእርሻና ለኢንዱስትሪ ምቹ የሆነች ሀገር ተፈጥሮ ከተሜነት ካላደገ ኢኮኖሚውም አያድግም ። ገጠሩ መሸከም የሚችለውን ያህል ተሸክሞ ያልቻለውን ወደ ከተሞች ይተፋል። በመሆኑ ከተሞች ተዘጋጅተው መጠበቅና መቀበል ይኖርባቸዋል። ነገር ግን የገጠር ከተሞችን በፍጥነት ማመጣጠን ካልተቻለ ችግሩ አሁን ባለው ፍጥነት ከቀጠለና ምላሽ መስጠት ካልተቻለ የከፋ ቀውስ ውስጥ እንደምንገባ ያነሳሉ።
መንግሥት ዕለት ዕለት እየተባባሰ የመጣውን የመኖሪያ ቤት ችግር ከወዲሁ ለመፍታት የመጨረሻ አማራጭ ከሆኑት የግል አልሚዎች ጋር በጋራ መስራት እንዳለበት አበክረው የሚያነሱት አቶ ብሩክ፤ በተለይም የመኖሪያ ቤት ችግር የኅብረተሰቡ መሠረታዊ ችግር በመሆኑ የሚመለከታቸውን ባለሙያዎች በሙሉ በማሳተፍ አዳዲስ የመፍትሔ ሀሳቦችን መለዋወጥ ያስፈልጋል።
ምክንያቱም ችግሩን በሚገባ በመረዳት መፍትሔ መስጠት የሚችለው ስለ ጉዳዩ የሚያውቅ ባለሙያ በመሆኑ ነው። ስለዚህ ዜጎችን ጨምሮ ባለሙያው በመሰባሰብ ከመንግሥት ጋር ሊወያይ ይገባል። በዚህ ጊዜ ሀሳብ መስጠት የሚችሉ በርካታ ባለሙያዎች በመኖራቸው የተለያዩ ሀሳቦችን ያቀርባሉ። ባለሙያዎች ተወያይተው ለመንግሥት በሚያቀርቡት ሀሳብና የፖሊሲ አቅጣጫ መሰረት በቁርጠኝነት ከተሰራና ፈጣን ምላሽ መስጠት ከተቻለ አሁን ላይ አንገታችን ድረስ ሊውጠን የደረሰው የመኖሪያ ቤት ችግር መቃለል ይችላል። በዛው ልክ የአኗኗር ዘዴያችንን በመቀየር የዜጎችን ገቢ ማሻሻል የሚቻል መሆኑን ያብራሩት አቶ ብሩክ ይህን ዕውን ማድረግ የሚቻለው ግን መንግሥት ከባለሙያዎች ስብስብ ጋር በጋራ መስራት ሲችል መሆኑን አስምረውበታል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 18/2013