የምግብ ደኅንነትን ለማስጠበቅ ውጤታማ የተቋማት ቅንጅት ተፈጥሯል ተባለ

-ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ የምግብ ምርቶች ላይ ጠንካራ ቁጥጥር እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ፣ የምግብ ደኅንነትን ለማስጠበቅ በተለይ ሕገወጥ ምርቶች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ በማድረግ ረገድ ውጤታማ የተቋማት ቅንጅት መፈጠሩ ተገለፀ። ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ የምግብ ምርቶች ላይ ጠንካራ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባ፣ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የምግብ ደኅንነት ማረጋገጥ ከእርሻ እስከ ጉርሻ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ትኩረትና ቅንጅት የሚፈልግ ነው። ይህም በኢትዮጵያም የምግብ ደኅንነት በምግብና ሥርዓተ ምግብ እንዲሁም በጤና ፖሊሲው ውስጥ በልዩ ትኩረት የሚታይ ነው። ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱም ይህን የፖሊሲ አቅጣጫ ውጤታማ በሆነ መልኩ ለማስፈፀም ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅት በመፍጠር በተለይም ሕገ ወጥ ምርቶች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ በማድረግ ረገድ ውጤታማ ሥራዎች እየሠራ ይገኛል ብለዋል።

‹‹ባለፉት አስር ወራትም በተለይ በገቢ ምግቦች የደኅንነትና የጥራት ቁጥጥር፣ በተለይ በሕፃናት ወተት፣ በምግብ፣ በምግብ ጭማሪና በምግብ ጥሬ እቃዎች ላይ በድምሩ ከአንድ ነጥብ 9 ሚሊዮን ቶን በላይ ምግብ በጥቅም ላይ እንዲውል የመልቀቂያ ፈቃድ ተሰጥቷልም›› ብለዋል።

ወደ ሀገር ከመግባታቸው በፊት ከተመረመሩ 305 ናሙናዎች ውስጥ 12 መስፈርቱን የማያሟሉ በመሆናቸው ወደ ሀገር እንዳይገቡ መደረጉን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሯ፣ በአጠቃላይ በቁጥጥሩ ሂደት ሆነ በኅብረተሰብ ጥቆማ በአጠቃላይ ከ212 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የምግብ ምርቶች ለኅብረተሰብ ጥቅም እንዳይውሉ መደረጉንም ገልፀዋል። እነዚህ የምግብ ምርቶች ተጠቃሚ ዘንድ ቢደርሱ የሚያስከትሉት ጉዳት እጅግ ከፍተኛ እንደነበርም አመላክተዋል።

‹‹አሁን ላይ የሀገር ውስጥ የምግብ ተቋማት የኦዲቲንግ ኢንስፔክሽን ሽፋናችን 79 በመቶ ደርሷል›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ፣ በተለያዩ ምክንያቶች መድረስ ያልተቻሉ ቦታዎች ቢጨምሩ ከዚህም በላይ አቅም እንደሚፈጠርም ጠቁመዋል።

ሕግና ሥርዓትን ተከትለው ባልሠሩ የምግብ አምራቾች አስመጪዎችና አከፋፋዮች ላይ የተለያዩ ርምጃዎች መወሰዳቸውን ጠቁመው፣ 74 የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ፣ በ97 ላይ ስረዛ፣ 33 እሸጋና በ138 ላይ የእገዳ ርምጃ መወሰዱንና በወንጀል የሚያስጠይቁትን ክስ በመመስረት በዚህ አግባብ እንዲታዩ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።

ከችግሩ አሳሳቢነት አንፃር ምግብ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ጨምሮ፣ የምግብ አገልግሎት ሰጪዎች እንዲሁም የመንግሥት ተቆጣጣሪ አካላት የምግብ ደኅንነትን በማስጠበቁ ይበልጥ ሊበረቱ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። የምግብ አያያዝ ልማዶችን ማሻሻል፣ ምግብን በአግባቡ ማብሰል፣ ሲከማችና ሲጓጓዝ ጥንቃቄ ማድረግ፣ የቁጥጥር ባለሙያዎችንም አቅም ማጎልበት እንደሚገባ አፅንዖት ሰጥተውታል።

የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መሠረት በቀለ (ዶ/ር)፤ በበኩላቸው፣ ኢንስቲትዩቱ የኅብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅና የምግብ ደኅንነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ደረጃዎችን ከማውጣት ጀምሮ እስከ ትግበራ ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ ቅንጅታዊ ሥራዎች በመሥራት ላይ መሆኑን ጠቁመው፣ ከኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ጋር በመተባበር በተለይ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን ላይ ጠንካራ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን የእንስሳት ምርት ሬጉላተሪ መሪ ሥራ አስፈፃሚ አያሌው ሹመት(ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የተቋሙ ከምግብ መለስ ያሉና ለምግብ ግብዓት የሆኑ ጥሬ ምርቶችን በመቆጣጠር የምግብ ደኅንነትን ለማረጋገጥ ለሚከናወኑ ተግባራት ተጨማሪ አቅም እየፈጠረ መሆኑን አብራርተዋል። ‹‹በተለይ ሕገ ወጥነትን ለመከላከልና በዘርፉ የወጡ ደረጃዎች በአግባቡ እንዲተገበሩ በማድረግ ሂደት ከምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ጋር ውጤታማ ቅንጅት ፈጥሯልም›› ብለዋል።

መረጃዎች እንደሚያ መላክቱት በየዓመቱ 600ሺህ ያህል ሰዎች በምግብ ወለድ በሽታዎች የሚያዙ ሲሆን 420 ሺህ የሚሆኑት ለሞት ይዳረጋሉ። ዓለም አቀፍ ምግብ ደኅንነት ቀን “የምግብ ደኅንነት ሳይንስ፤ በተግባር” በሚል መሪ ቃል ባሳለፍነው ግንቦት 30 መከበሩ ይታወሳል።

በታምራት ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 10 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You