
ዜና ሐተታ
የመልክዓ ምድር ጥበቃ የተደረገላቸው ምርቶች ሸማቹ ስለምርቱ መተማመን እንዲኖረው እና አምራቹ የመደራደር አቅሙ ከፍ እንዲል ስለሚያስችል የምርቱ ዋጋ 50 በመቶ ከፍ እንዲል የማድረግ ዕድል ከፍተኛ መሆኑን የአዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን መረጃ ያሳያል።
ነገር ግን እንደ ሀገር ያለው የንግድ ሥርዓት በተለምዶ የሀላባ በርበሬ፤ የሲዳማ ቡና፤ የአርባምንጭ ሙዝ፤ የምንጃር ጤፍ ተብሎ እንደ ብራንድ ከመቅረብ ያለፈ ሕጋዊ በሆነ መንገድ ማረጋገጫ ተሰጥቶት ለገበያ ሲቀርብ አይታይም።
ከዚህ አንጻር የአዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን ለተለያዩ ምርቶች የመልክዓ ምድር አመልካች ጥበቃ ሥርዓት በመዘርጋት ማረጋገጫ ለመስጠት ወደ ሥራ እየገባ መሆኑን ተከትሎ ባለፈው ወር መጨረሻ ዓለም አቀፍ ጉባኤ እና ኤግዚቢሽን አዘጋጅቷል። በወቅቱ ኤግዚቢሽኑ ላይ ምርቶቻቸውን ይዘው የቀረቡ ተሳታፊዎችን የመልክዓ ምድር ጥበቃ ሥርዓት ለምርታቸው ምን ዓይነት ጠቀሜታ እንደሚኖረው አነጋግረናቸዋል።
የተለያዩ ፍራፍሬዎችን በኤግዚቢሽኑ ይዘው የቀረቡት የጋሞ ገበሬዎች አትክልትና ፍራፍሬ ግብይት ኅብረት ሥራ ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ መላኩ ዳርጮ፤ ማኅበሩ ሙዝን ጨምሮ የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬዎችን ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ገበያ እንደሚያቀርብ ይናገራሉ።
አቶ መላኩ እንደሚናገሩት፤ እንደ ሀገር በንግድ ሥርዓቱ የምርቶች መገኛ የሚጠቀሰው በልምድ ነው እንጂ የማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸው አይደለም። ከዚህ ቀደም የአርባምንጭ ሙዝ እና የጬንቻ አፕል በአዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን እውቅና ማግኘቱን በመግለጽ፤ የመልክዓ ምድር ጥበቃ ሥርዓት ወደ ሥራ ሲገባ ደግሞ የምርቱን ዓለም አቀፍ ተፈላጊነት የበለጠ ያሳድጋዋል ተብሎ ይጠበቃል ይላሉ።
ረቂቅ መመሪያው አሁን በዝግጅት ምዕራፍ ላይ እንዳለ በማንሳት፤ አንድ ግለሰብ ባመረተው ምርት ሌላኛው ተጠቃሚ እንዳይሆን የሕግ ማሕቀፉ ተጠያቂነትን ባካተተ መልኩ ተዘጋጅቶ ተግባራዊነቱ ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት ያስፈልጋል ይላሉ።
ከምዕራብ ኦሮሚያ ኢሉ አባቦራ ዞን ከሶርገባ የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ሁለገብ ማኅበር የማር ምርት ይዘው የቀረቡት አቶ መለስ ተክሌ፤ በበኩላቸው “ለገበያ የምናቀርበው ማር ገተሜ ከሚባል ዕፅዋት የሚገኝ ማር ነው፤ እስከ አሁን ምርቱን ለሀገር ውስጥ ገበያ ብቻ እያቀረብን እንገኛለን፤ ወደ ውጭ ሀገራት ለመላክም ዝግጅት እያደረግን ነው።” ይላሉ።
በአዕምራዊ ንብረት ባለሥልጣን በኩል የመልክዓ ምድር አመልካች ጥበቃ ሥርዓት ተጠያቂነት ባለው መልኩ በመመሪያ ደረጃ ተዘጋጅቶ ለምርቶች ማረጋገጫ መሰጠቱ የምርት ጥራት እንዲጠበቅ እና አርሶ አደሩም ካመረተው ምርት ተጠቃሚ እንዲሆን ያደርጋል ሲሉ ይገልጻሉ።
እንደ ማኅበር ከዚህ ቀደም የማር ምርቱን የምናስተዋውቀው ማሩ በተገኘበት ዛፍ ወይም በማሩ ዓይነት ነው። ይህ ደግሞ ከጥራት እና ከተጠያቂነት አንጻር ምንም ለውጥ አላመጣም። አሁን በቦታ ደረጃ እውቅና ተሰጥቶ ወደ ሥራ መገባቱ የተሻለ ለውጥ ያመጣል ተብሎ ይጠበቃል ይላሉ።
እርግጠኛ ቦታው ተቀምጦ እና ጥራቱ ተረጋግጦ ለገበያ መቅረቡ ከሌሎች የማር ምርቶች ጋር በዓለም ገበያ እንዲወዳደር፤ በሌሎች ተመሳሳይ ምርቶች ዋጋው እና ጥራቱ እንዳይበላሽ ያስችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ገዢዎችም የዚህ አካባቢ ማር በሚል መለያው መርጠው እንዲገዙ ስለሚረዳ እንደ ሀገር ጥቅሙ ብዙ እንደሆነ ያስረዳሉ።
የበለጠ ስለ ጉዳዩ ለማወቅ የሚረዱ የግንዛቤ መድረኮች ቢዘጋጁ መልካም ነው የሚሉት አቶ መለስ፤ መመሪያው ሲዘጋጅ ተጠያቂ በሚያደርግ መልኩ ቢዘጋጅ የተሻለ እንደሚሆንም ሀሳብ ሰጥተዋል።
ከዳራክ ክራፍት ድርጅት የጌጣጌጥ ሥራዎቿን ይዛ የቀረበችው ትዝታ ሙረዳይ ከወንድሟ ጋር በመሆን የተለያዩ በሰፌድ መልክ የሚሠሩ የግድግዳ ጌጣጌጦችን እና የአበባ ማስቀመጫዎችን ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ገበያ ታቀርባለች።
የመልክዓ ምድር አመልካች ጥበቃ ሥርዓት መመሪያ ተዘጋጅቶለት ወደ ሥራ መግባቱ ምን አንድምታ እንደሚኖረው ጠይቀናት እንዳስረዳችን፤ “እኔ የማመርታቸው ጌጣ ጌጦች በቀለም ቢለያዩም ሌሎች ክልሎችም ይመረታሉ፤ ከዚህ አንጻር ምርቴ የመልክዓ ምድር ጥበቃ ሥርዓት ውስጥ ገብቶ እውቅና ማግኘቱ የገበያ ተፈላጊነቱ እንዲጨምር ያደርጋል።” ትላለች።
የአዕምሯዊ ጥበቃ ሥርዓት አካል ሆኖ ለምርቶች አካባቢያቸው ጥበቃ መደረጉ ወጣቱን ለሥራ ከማነሳሳት ያለፈ፤ የሚመረቱ ምርቶች ዓለም አቀፍ ተቀባይነትን እንደሚያሳድግ በመግለጽ፤ የሥርዓቱ መዘርጋት ሙያውን ለትውልድ ለማስተላለፍ ጠቃሚ እንደሚሆንም ትናገራለች።
በዳዬ በንሳ ካምፓኒ የቡና ባለሙያ የሆነው አቶ በጢሶ ዱባለ በበኩሉ የመልክዓ ምድር አመልካች ጥበቃ ሥርዓት በአዕምሯዊ ንብረት ተዘጋጀቶ ወደ ሥራ መግባቱ ቀጥታ የቡና ምርቱ የመጣበትን ቦታ ስለሚያረጋግጥ ጠቀሜታው ትልቅ ነው ሲል ይገልጻል።
በዓመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 10 ቀን 2017 ዓ.ም