ሀላባና – የበርበሬ ምርቷ

ሀለባ የሚባለው ስም ሲጠራ፤ በብዙ ኢትዮጵያውያን አእምሮ ተያይዞ የሚታወሰው የበርበሬ ምርት ነው። በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የምትገኘዋ የሃላባ ዞን በኢትዮጵያ በርበሬ በስፋት ከሚመረትባቸው አካባቢዎች ዋነኛዋ ናት። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሀላባ የሚመረተው በርበሬ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተደራሽና ተወዳጅ ከመሆን ባለፈ፤ ባሕር ተሻግሮ የውጪ ምንዛሬ ለማስገኘትም በቅቷል።

የአካባቢው መለያ እስከ መሆን የደረሰ የበርበሬ ምርት አርሶ አደሩን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ ምን ምን ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ? ስንል ከዞኑ ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊና የእርሻ ዘረፍ ኃላፊ አቶ ሁሴን ሮባ ጋር የነበረንን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

«በርበሬ ለሀላባ ማኅበረሰብ አንደ ሰንደቅ ዓላማ ልዩ መገለጫ ነው።» የሚሉት አቶ ሁሴን፤ የአካባቢው ማኅበረሰብ እና በርበሬ ያለውን ቁርኝት እንዲሁም በዞኑ በስፋት ስለሚካሄደው የበርበሬ ልማት የሚከተለውን ማብራሪያ ሰጥተውናል።

የአካባቢው ነዋሪ ለረዥም ዓመታት ከበርበሬ ምርት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ሕይወት የሚኖር ሲሆን፤ ማኅበረሰቡ ለበርበሬ ልማት ልዩ ቦታ አለው። በተለያዩ ምክንያቶች ካላለፈው በቀር በርበሬ ሳያመርት የሚኖር አርሶ አደር አለ ለማለት አይቻልም። በዚህም የተነሳ ሁሉም ነዋሪ ሊባል በሚያስደፍር ደረጃ ስለበርበሬ ልማት የየራሱ እውቀት አለው ይላሉ። በሀላባ ዞን በሁለት ወቅቶች ማለትም በበልግና በመኧር በርበሬ ይመረታል:: የዞኑ ግብርና መምሪያም በእነዚህ ወቅቶች ለበርበሬ የተለየ ትኩረት ሰጥቶ ይሠራል።

እሳቸው እንደገለፁት፤ በሄክታር በአማካይ ከአስራ ሁለት ኩንታል በላይ ይገኛል:: በአሁኑ ወቅት በዞኑ በርበሬ የሚለማበት ቦታ ከዘጠኝ ሺህ 270 ሄክታር በላይ ነው። እስካሁን በአንድ የምርት ወቅት በየዓመቱ ከ120ሺ ኩንታል በላይ ይሰበሰባል። የአመራረት ሂደቱን ከዘር ዝግጅት ጀምሮ ሲያብራሩ፤ እስካሁን በዘመናዊ መንገድ በጥናት ተረጋግጦ የተለየ የበርበሬ ዝርያ የለም። በአብዛኛው አርሶ አደሩ ለረዥም ዘመን ሲጠቀምበት የኖረው አካሄድ በአካባቢው ጥሩ ዘር ተብሎ የሚለየው በቅድሚያ በማሳ ላይ እያለ በምልከታ ነው።

ዛላ ያለው በመባል ለዘር የተለየው በርበሬ ከማሳ ላይ የሚወሰደውም በከፍተኛ ጥንቃቄ በባለሙያ ነው:: ለዘርነት ዝግጁ እንዲሆን ከተደረገ በኋላ፤ በዘር ማሻ ታሽቶ አስኪዘራ ድረስ በተመሳሳይ በልዩ ጥንቃቄ እንዲቆይ ይደረጋል። በመቀጠል ጎርፍ የማይደርስበት እና ተዳፋታማ ያልሆነ ቦታ ተለይቶ መደብ ይሠራል:: የመደብ ዝግጅቱ በከፍተኛ ጥንቃቄ ይከናወናል::

የችግኝ ዝግጅትን በተመለከተ አዲስ አካሄድ በመከተል፤ አርሶ አደሩ በበጋ የሚጀምርበት አሠራር ተዘርግቷል። ለዚህም የአካባቢው ነዋሪ ገንዳ እየተባሉ የሚጠሩትን ትንንሽ ኩሬዎች በማዘጋጀት አየተጠቀመ ይገኛል። ይህ በአሁኑ ወቅት በሁሉም አርሶ አደሮች እየተተገበረ ባለመሆኑ የበለጠ የማስፋፋት ሥራ ይጠይቃል። በዚህ አይነት ዝግጅት መደረጉ ወደ መኧር የሚሄደውን የእርሻ ወቅት ወደበልግ እንዲያመጣው በማድረግ መሬቱን በተደጋጋሚ ለመጠቀም የሚያስችል ዕድል እንደሚፈጥር ያስረዳሉ።

ተከላ የሚከናወነው በቅድሚያ የቦታ መረጣ ተደርጎ የተለየው ቦታ ላይ ነው:: ይሁንና ከባድ ዝናብ ሊከሰት ስለሚችል፤ በየመሀሉ የውሀ መፍሰሻ ቦይ ይዘጋጅለታል። ይህ የሚሠራው ምርቱ ተመጣጣኝ ውሃ አግኝቶ ምርታማነቱን ለመጨመር ብቻ አይደለም:: በዋናነት በበሽታ የመመታት አድሉን ለመቀነስም ጭምር ነው። ከተከላ በኋላ ምርቱ እስኪሰበሰብ እንደ አያያዙ ከሶስት አስከ አራት ጊዜ የኩትኳቶ ሥራዎች ይከናወናሉ።

በግብርና ሳይንስ አፈራርቆ መዝራት እንደ አንድ የሰብል ምርታማነት መጨመሪያ መንገድ ይወሰዳል። አንድ የሰብል አይነት በተደጋጋሚ በአንድ ቦታ ላይ የሚዘራ ከሆነ፤ የምርቱ መጠን ይቀንሳል:: በበሽታ የመጠቃት እድሉ ከፍተኛ ይሆናል። በዚህ መነሻነት በዞኑ በርበሬ የሚመርትባቸውን መሬቶች እንደ ዳጉሳ፤ ቦሎቄ ፤ በቆሎ እንዲዘራባቸው በማድረግ የአፈሩ ለምነት ለመጠበቅና ምርታማነት እንዳይቀንስ እየተሠራ ይገኛል።

ይሁንና ለበርበሬ ምርት ፈታኝ የሆኑ ነገሮች አሉ የሚሉት አቶ ሁሴን፤ ከእነዚህም መካከል የተመረጠ ዘር አለመገኘቱ እና በበሽታ መጠቃት በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። በምርጥ ዘር ረገድ እስካሁን ድረስ የተካሄዱና በመካሄድ ላይ ያሉ ጥናቶች ቢኖሩም፤ የተረጋገጠ ውጤት ማግኘት እንዳልተቻለ ያመለክታሉ።

ከበሽታ ጋር በተያየዘ እንደ ዋና የሚነሳው ዝናብ ሲበዛ የሚከሰተው ስረ በስብስ የሚባለው ነው። ይህ በአንድ አካባቢ ከተከሰተ በፍጥነት ወደ ሁሉም ስለሚዛመት በአጭር ጊዜ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል። ይህንን ለመከላከል ከምርምር ተቋማትና ከክልሉ ጋር በመነጋገር፤ ለምርመር የሚፈለጉ ወደ ላብራቶሪ እንዲወስዱ እየተደረገ በቅንጅት እየተሠራ ነው:: ሆኖም አሁንም በቂ ውጤት አልተገኘም:: ችግሩ ዛሬም ከፍተኛ ጥናትና ምርምር የሚጠይቅ ሆኖ ተቀምጧል ይላሉ።

በሌላ በኩል በርበሬን በዘመናዊ መንገድ ለማልማት በዞኑ የተጀመሩና ተስፋ ሰጪ እንቅስቀሴዎች መኖራቸውን ያነሳሉ። ከእነዚህ መካከል ከዩኒየኖች ጋር በመጣመር ጥራትን የጠበቀ የዘር ብዜት እየተሠራ ነው:: በዚህ ረገድ ለበርበሬ ምርት ከፍተኛ አቅም ያላቸው አምስት ቀበሌዎችም ተለይተዋል። በእነዚህ ቀበሌዎች በዩኒየኖቹ ስር ያሉ ማኅበራት በክላስተር እንዲያለሙ እየተደረገ ይገኛል። ከእነዚህ መካከል ወይራ ወረዳ ላይ አንድ የሕብረት ሥራ ማኅበር የዘር ዝግጅቱን ወደ ዘመናዊ አሠራር እንዲያሸጋገር የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ያስረዳሉ።

ምርትና ምርታማነት ሲታሰብ ግብአት ወሳኝ መሆኑ ይታወቃል። ዘር በራስ አቅም ይዘጋጃል። በግብዓት ረገድ ለበርበሬ ምርት ዩሪያና ዳፕ አገልግሎት ላይ ይውላሉ። የበርበሬ ሰብል ማዳበሪያን ከሌላው በእጥፍ ይፈልጋል። ይህን ተከትሎ እስከ ቅርብ ግዜ እጥረት ነበር:: በአሁኑ ወቅት ግን በቂ ማዳበሪያ ተዘጋጅቶ አርሶ አደሩን እየተጠባበቀ ይገኛል። በክፍፍል ወቅት ደላሎች ገብተው ሰው ሰራሽ እጥረት እንዳይከሰት፤ እየተሠራ መሆኑንም አስረድተዋል::

ባለሙያዎች የትኛው አርሶ አደር ምን ያህል መሬት እያመረተ ይገኛል? የሚለውን በየወቅቱ በመለየት የሚመዘግቡ በመሆኑ፤ በዚሁ መሰረት አርሶ አደሩ የሚገባውን ያለምንም ውጣ ውረድ ከመንግሥት ለማግኘት ይችላል። ኬሚካልን በተመለከተ ግን ዛሬም ድረስ ክፍተት አለ ብለዋል።

በአንድ በኩል ኬሚካል ለአርሶ አደሩ ማግኘት ውድ ዋጋ የሚጠይቅ ሲሆን አንዳንድ ግዜ ብሩ ቢኖርም ተፈልጎ የማይኖርበት አጋጣሚ አለ። ለዚህም ዋን ስቶፕ ሾፕ የተባሉ አቅራቢዎች ከግብርና ቢሮ ጋር በመሆን እየሠሩ ይገኛል። ይሁንና የግብርና ቢሮ ፍላጎትን መሰረት አድርጎ ካዘዛቸው በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች በጣም የሚቆዩበት አጋጣሚ አለ። ይህም ሆኖ አንዳንዱ ኬሚካል ከአካባቢው ጋር እየተላመደ ውጤታማ ስለማይሆን፤ በየወቅቱ በአይነቱ ራሱን የቻለ ጥናት ማካሄድ የሚጠበቅ መሆኑን ያነሳሉ:: ይህንን ለማድረግ በቂ ባይሆንም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የተጀማመሩ ሥራዎች መኖራቸውን ያብራራሉ።

እንደ እሳቸው ገለፃ፤ በሌላ በኩል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የአርሶ አደር ተጠቃሚነት ማረጋገጥ አንዱ መንገድ ነው:: አርሶ አደሩ ያመረተውን ምርት ለገበያ አቅርቦ ተገቢውን ዋጋ የሚያገኝ ከሆነ ለምርቱ ብዛትም ሆነ ጥራት በማሰብ በጥንቃቄ መስራቱ አይቀርም። በዞኑም የበርበሬ ምርታማነትን ለማሳደግ ሲታሰብ፤ የተቀመጠው አንዱ የትኩረት አቅጣጫ የገበያ ጉዳይ ነው።

ገበያን በተመለከተ ዋናው ሥራ በመካከል ጣልቃ የሚገባውን ደላላ ማስወገድ ነው። በዞን ደረጃ በዚህ ረገድ በላፉት ጥቂት ዓመታት በቁጥጥርና በመረጃ ቅብብሎሽ የተሠሩ ሥራዎች የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያስቻሉ ሆነዋል። በአሁኑ ወቅት በዚህም በአንድ የምርት ወቅት አስከ አንድ ሚሊየን ብር ገቢ ያገኙ አርሶ አዳሮችን መፍጠር ተችሏል ይላሉ።

ዛሬ በበርበሬ ምርት ቤተሰብ ከማስተዳደር ልጅ ከማስተማር አልፈው ብዙዎች ሞተርና የተለያዩ መኪናዎችን ለመግዛት በቅተዋል:: ከተማ ቦታ ገዝተው ቤት መሥራት የቻሉ በርካቶች መሆናቸውንም አመላክተዋል። በሕብረት የእርሻ ትራክተር ለመግዛት የደረሱ መኖራቸውንም ይገልፃሉ።

አቶ ሁሴን እንዳመላከቱት፤ ሀገር ባለው አበርክቶ የበርበሬ ምርት የውጪ ምንዛሬ ለማስገኘት የበቃ ነው። በዚህ ረገድ በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለውጪ ገበያ ቀርበው የውጪ ምንዛሬ ከሚያስገኙ ምርቶች መካከል ቀዳሚዎቹ ሮዝመሪና በርበሬ ናቸው። ከክልሉ ከፍተኛ በርበሬ የሚያቀርበው ደግሞ ሀላባ ዞን ነው።

በዚህ ዓመት ብቻ ከሮዝመሪና ከበርበሬ 12 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል:: ከዚህ ወስጥ አብዛኛውን ድርሻ የሚወስደው በርበሬ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን፤ በስፋት እየተጀመረ ያለው ለሥራ እድል ፈጠራም ተመራጭ እየሆነ የመጣው፤ በርበሬን አዘጋጅቶ መላክ ነው:: ይህ በቀጣይም በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል ይላሉ።

በርበሬ የራሱ ባሕሪ ያለው በመሆኑ ሊቀመጥ የሚገባው ለብቻው ከሌሎች ሰብሎች ጋር ሳይነካካ ነው። በማድረቅ ሂደትም መቀመጥ የሚኖርበት በሲምንቶ አልያም በእንጨት በተዘጋጀ አልጋ ላይ ብቻ መሆን አለበት። በአፈርና ከከብቶች አዛባ በተዘጋጁ መደቦች ላይ ከተቀመጠ እና ለኪሎ መጨመር ተብሎ ውሃ ከተርከፈከፈበት አፍላ ቶክሲን የመፍጠር እድል አለው ይላሉ።

አንዳንድ አርሶ አደሮች የበርበሬ ምርትን ለገበያ ሲያቀርቡ ኪሎ እንዲጨምር ውሃ እስከ መጨመር የሚደርሱ ነበሩ። ይህንን የሚያደርጉት ደላሎች በገበያው መሀል እየገቡ ዋጋ በማራከስ ተገቢውን ክፍያ እንዳያገኙ ስለሚያደርጓቸው ነበር። የሚሉት አቶ ሁሴን፤ ይሁንና በአሁኑ ወቅት ባለሙያዎች ቁጥጥር ከማድረግ ባለፈ፤ ተገቢውን የምክርና የድጋፍ አገልግሎት እያደረጉ ናቸው። ባለፉት ዓመታት በዘመቻ መልክ በስፋት ግንዛቤ ለመፍጠር የተከናወኑ ሥራዎች ችግሩን ሙሉ ለሙሉ መቅረፍ ባይቻልም በጣም ለመቀነስ አስችሏል ይላሉ።

በባለሙያ ረገድ እንደ ዞን ከተማን ጨምሮ አራት መዋቅሮች አሉ:: በሶስቱ ወረዳዎች በበቂ ሁኔታ በዘርፉ የተማሩ ባለሙያዎች አሉ። እነዚህ ባለሙያዎች ከአርሶ አደሩ ጋር ከመሬት መረጣ ጀምሮ በሁሉም ሥራዎች አብረው በመንቀሳቀስ በየወቅቱ የድጋፍና ክትትል ሥራዎችን ያከናውናሉ። ከእነዚህ በተጨማሪ በቀበሌ ደረጃ ደግሞ እንደየሁኔታው ከአራት እስከ ስድስት የልማት ጣቢያ ባለሙያዎች የሚመደቡ ሲሆን፤ ከአርሶ አደሩ ጋር በቅርበት የሚሠሩ ይሆናል።

የዞኑ ባለሙያዎችም ስልጠና ከመስጠት ባለፈ እርሻው ድረስ በመሄድ አርሶ አደሩን የማማከር የገጠሙትን ችግሮች በመለየት የመፍትሄ መንገዶችን የማመላከት ሥራ ያለ ሟቋረጥ ያከናውናሉ። በከተማ ግን በርበሬ በስፋት እየተመረተ ቢሆንም፤ በዚህ ረገድ የራሱ የሆነ መዋቅር የለውም። በቋሚነት የተመደበ ባለሙያ ባይኖርም፤ እነዚህ ከላይ ከቀበሌ እስከ ዞን በመደበኛነት የሚሠሩ ባለሙያዎች በከተሞችም አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ መሆናቸውን ይናገራሉ።

አቶ ሁሴን የቀጣይ እቅዳቸውን አስመልክተው እንደተናገሩት፤ ከለውጡ በኋላ የምርት ወቅትን ለማሳደግ የተጀመሩ ሥራዎች አሉ። ከዛ በፊት የምርት ወቅቶች የመኧርና የበልግ ብቻ ነበሩ። በአሁኑ ውቅት ግን ከእነዚህ በተጨማሪ ቅድመ በልግ፤ በተለይ አንድ ወረዳ ሙሉ ለሙሉ በቆሎ፣ ድንች እና ቦሎቄ እንዲዘራ እየተደረገ ይገኛል። ሁለተኛው ወቅት በጸደይ ሽምብራና ጎመን እንዲመረት እየተደረገ ነው። የመስኖ ወቅት ተብሎም እንደየአካባቢው የተለያ ምርቶችን በማምረት አምስት የምርት ወቅት ለመፍጠር ተችሏል።

በ2017/18 የምርት ዘመን ከአስር ሺ በላይ ሄክታር መሬት ላይ አምስት ጊዜ ለማልማት እንቅስቃሴ ተጀምሯል። ለዚህ ደግሞ ሁለቱንም ወቅቶች በአግባቡ መጠቀም የሚገባ ሲሆን፤ በግብአት አቅርቦትና ክትትልና ድጋፍ ላይ ብዙ መሥራት ይጠይቃል ይላሉ።

ሌላው እንደ ተግዳሮት የተለየውን የዘር አቅርቦት ችግር ለመፍታት ሆሪሲንካ ከሚባል ዩኒየን ጋር በስፋትና በጥራት ለማዘጋጀት ይሠራል ያሉት አቶ ሁሴን፤ በሽታን በመከላከል ረገድ እስካሁን እንደ ተቋም በርካታ የምርምር ሥራዎች የተከናወኑ ቢሆንም የሚጠበቀውን ውጤት ለማስመዝገብ አልቻሉም። በመሆኑም ካሉት የምርምር ማእከላት ጋር በጥምረት ለመሥራት ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

በተጨማሪ በዞኑ ያለው መሬት ከ95 በመቶ በላይ ለሜካናይዜሽን እርሻ ምቹ መሆኑን በማስታወስ፤ በአሁኑ ወቅት በበጋ አስከ 80 በመቶ በትራክተር ለማረስ ተችሏል። በመሆኑም ባለፈው ዓመት በአስር ቀበሌዎች የነበረውን መካናይዜሽን እርሻ በቀጣይ በሁሉም አካባቢዎች ለማዳረስ ይሠራል ብለዋል።

ራስወርቅ ሙሉጌታ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You