
ዜና ሐተታ
ተወላጆቿ “የበረሃዋ ገነት” ይሏታል። “የፍቅር ከተማ” የሚሏትም ብዙዎች ናቸው። በዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ የከተሜነት ሥልጣኔ ቀድሞ ከፈነጠቀባቸው ከተሞች አንዷ መሆኗም ይነገራል። ድሬዳዋ ከተማ በብዙ ነገሮች ቀዳሚ ሆና ስትጠቀስ ብትኖርም ለበርካታ ዓመታት በእድገት ጎዳና ላይ መጓዝ አልቻለችም። ከእሷ በብዙ ዓመታት ዘግይተው የተቆረቆሩ ከተሞች በእድገት ጥለዋት ሲሄዱ እሷ እንደ ስሟ “የበረሃዋ ገነት” ሆና መቀጠል አልሆነላትም።
ጀምበር የማይጠልቅባት የምሥራቋ ፈርጥ እንዳስቆጠረችው እድሜና እንደተነሳችበት የሥልጣኔ ጉዞ ዘመኑን የዋጀች ከተማ ለመሆን አልታደለችም። በስም እንጂ በተግባር ለነዋሪዎቿም ይሁን በፍቅር ለምትቀበላቸው እንግዶቿ የምትመጥን አልሆነችም። መሠረተ ልማቷ የዘመነ፣ ምቹና ማራኪ ከመሆን ርቃ ቆይታለች። አሁን ግን የተወደሰችበትን “የበረሃዋ ገነት” ስሟን በተግባር የምትኖር ከተማ በምትሆንበት ጎዳና ላይ ትገኛለች።
የበርካታ የኢትዮጵያ ከተሞችን ገፅታ እየቀየረ ውብ፣ ምቹና ለነዋሪዎች ተስማሚ እንዲሆኑ እያደረገ ከሚገኘው የኮሪዶር ልማት ትሩፋት ድሬዳዋም ተቋዳሽ ሆናለች። ከአምስት ወር በፊት የተጀመረውና 11 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የከተማዋ የኮሪዶር ልማት የመጀመሪያ ዙር ሥራ የሞቃታማዋ ከተማን ውበትና ገጽታ ከመቀየር ባሻገር ያላትን ዕምቅ ፀጋና ታሪክ ገልጦ በሚያሳይ መልኩ እየገሠገሠ ይገኛል።
የከተማዋ የግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንድወሰን ጀምበሬ፣ ድሬዳዋ የመጀመሪያውን ዙር የኮሪዶር ልማት ተግባራዊ ለማድረግ ስትነሳ የከተማዋን ሰባት የሚሆኑ መስመሮች በመለየት እንደነበር ያስታውሳሉ።
እንደ አቶ ወንድወሰን ገለፃ፣ በድሬዳዋ ከተማ በአጠቃላይ በኮሪዶር መልማት አለበት ተብሎ በእቅድ የተያዘው 27 ኪሎ ሜትር ነው። ይህም በተለያየ ዙር በሂደት የሚለማ ነው። ከዚህ ውስጥ መሐል ከተማ ላይ በኮሪዶር የሚለማው አካባቢ 13 ኪሎ ሜትር ገደማ ይሸፍናል። በዚህ መሠረት በአንደኛው ዙር 11 ነጥብ 04 ኪሎ ሜትር መንገድ እየተሠራ ይገኛል። ከዚህ ውስጥ ከአንድ ኪሎ ሜትር በላይ ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል። ሌላው 5 ነጥብ 85 ኪሎ ሜትር ደግሞ 96 በመቶ ተጠናቋል። ይህን ሙሉ በሙሉ ለመጠናቀቅ የሚቀረው ዘመናዊ የመንገድ ዳር የመብራት ምሶሶ ማቆምና የብስክሌት መንገድ መዘርጋት ብቻ ነው። ቀሪው በመሠራት ላይ ይገኛል፡፡
ድሬዳዋ ከንግድ ጋር የተሳሰረች ከተማ በመሆኗ ከተማው ወጣ ብሎ ከሚገኘው ኢንዱስትሪ ዞን ጋር በኮሪዶር ልማት ለማስተሳሰር ወደ 14 ኪሎ ሜትር ገደማ በኮሪዶር ልማቱ ተካቷል። ከዚያ ውስጥ 2 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትሩ ደግሞ ከተማዋን ከአጎራባቹ ሺሚሊ ዞን ጋር የሚያገናኝ መንገድ ሲሆን በኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን እየተሠራም ይገኛል።
የኮሪዶር ልማቱ “የበረሃዋን ገነት” ከማዘመንና ከማስዋብ ባሻገር የከተማዋንና የአካባቢውን የሥራ ባህል እንደቀየረ አቶ ወንድወሰን ያስረዳሉ። ለዚህም ከፍተኛ አመራሩ በየቀኑ የኮሪዶር ልማቱ በሚከናወንባቸው ቦታዎች ላይ ተገኝቶ በመከታተልና በመቆጣጠር ሌት ተቀን መትጋቱ፣ ሠራተኛውም ሌትና ቀን በፈረቃ የሚሠራበት ሁኔታ መፈጠሩን ማሳያ አድርገው ይጠቅሳሉ።
አቶ ወንድወሰን ሲያብራሩም፣ የከተማዋ የኮሪዶር ልማት ሥራ ሲጀመር ሰፊ የሰው ጉልበት እንደማስፈለጉ ከ1 ሺህ 500 በላይ ለሚሆን ሰው የሥራ ዕድል መፈጠሩን ይናገራሉ። በማኅበር የተደራጁ በርካታ የጉልበት ሠራተኞች፤ ስድስት የሚሆኑ የግንባታ ተቋራጮችም የሥራ ዕድሉ ተቋዳሽ ናቸው። በተዘዋዋሪ በየመንገዱ ኮሪዶር ሥራ ላይ ለሚገኙ ሠራተኞች ምግብና መጠጥ የመሳሰሉትን በማቅረብ ብዙ ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ሆኗል። ይህ ከሥራ ዕድል ፈጠራ አኳያ ሲታይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከፍተኛ ነው በማለትም ያብራራሉ።
እንደ ኃላፊው ገለፃ፣ የኮሪዶር ልማቱ ሲጠናቀቅ ከተማዋን ምቹና ውብ ከማድረግ ባሻገር ከመሠረተ ልማት አኳያ ብዙ ጥያቄዎችን ይመልሳል ተብሎ ይጠበቃል። ብዙዎቹ የኢትዮጵያ ከተሞች እንዳሉባቸው ችግሮች ሁሉ ድሬዳዋም የተሟላ የእግረኛ መንገድ የላትም፣ የብስክሌት መንገድም አልነበራትም ማለት ይቻላል። “ይሄ በሌለበት ሁኔታ ነው የምንቀሳቀሰው፣ ትራንስፖርት ወይም ተሽከርካሪ ተኮር ብቻ መሠረተ ልማት ነው የነበረን። በኮሪዶር ልማቱ ይህን መቀየር ተችሏል ነው ያሉት በኮሪዶር ልማቱ ደኅንነቱን የጠበቀ የእግረኛና የብስክሌት መንገድ እንዲሁም የመዝናኛ ቦታዎች ይኖረናል።” የሚሉት አቶ ወንድወሰን፣ ይህም ትራንስፖርት ወይም ተሽከርካሪ ተኮር የነበረውን የማኅበረሰቡን እንቅስቃሴ ጤና ተኮር ወደ ሆነ በእግርና በብስክሌት የመንቀሳቀስ ልምድ ለማምጣት ዕድል ይፈጥራል። በዚህም ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ ትራንስፖርት የግድ አይሆንም ማለት ነው፣ ይህ ደግሞ “ትልቅ ስኬት ነው” ይላሉ።
“ማኅበረሰቡን ወደዚህ እንዲመጣ ስታደርገው መንገዱ አሰልቺ እንዳይሆን በየቦታው የሚያርፍበትና የሚዝናናበት ስፍራ ያስፈልገዋል። ለዚህም የተለያዩ አረንጓዴ ስፍራዎችን ማዘጋጀት ያስፈልጋል። ይህም በኮሪዶር ልማቱ በበርካታ ስፍራዎች ተግባራዊ ሆኗል።” ሲሉም መሠረተ ልማቱን መሥራት ብቻም ሳይሆን በአግባቡ ለመጠቀም ሁኔታዎችን ምቹ ለማድረግ ከተማ አስተዳደሩ የሚያደርገውን ጥረት ይገልፁታል።
ቀደም ሲል በተዝረከረከ መልኩ የተዘረጉ የመብራት፣ ውሃና የስልክ መሠረተ ልማቶች በኮሪዶር ልማቱ በመሬት ውስጥ እንዲሆኑና መልክ እንዲይዙ ተደርጓል። በኮሪደር ልማቱ እንዲሠሩ ከተመረጡ መንገዶች መካከል ቀደም ሲል መሸት ሲል ለመጓዝ አስቸጋሪ የነበሩ አካባቢዎች ይገኙበታል። ነምበር ዋን አካባቢ የኮሪዶር ልማት አንዱ ሲሆን፣ ከምሽት 12:00 ሰዓት በኋላ ለመጓዝ አስቸጋሪ እንደነበር ኃላፊው ያስታውሳሉ። አሁን በመንገድ መብራቶች፣ በተዋቡ አረንጓዴ ስፍራና መዝናኛዎች የተለየ ገፅታን ተላብሶ ለትኛውም ሰው በማንኛውም ሰዓት ለመንቀሳቀስ ምቹ ሆኗል። የተዘጋጁት አርባ ያህል ሱቆችም ከንግድና አገልግሎት እንቅስቃሴ በተጨማሪ ለአካባቢው ነፍስ የዘሩ ሆነዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሁሉም ከተሞች እየተንደረደሩ ያሉት በነዳጅ የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎችን በመቀነስ በኤሌክትሪክ ኃይል ወደሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ለመቀየር ነው። ድሬም እዚህ ላይ ትኩረት አድርጋ እየሠራች ነው። ከወዲሁ መሠረተ ልማት በማዘጋጀት ረገድ እየተሰናዳች መሆኗን የሚያረጋግጠውም 12 መኪኖችን በአንድ ጊዜ ቻርጅ ማድረግ የሚያስችል ጣቢያ የተገነባ ነው፣ ወረፋ በሚኖርበት ጊዜ ተሽከርካሪዎች ተራ የሚጠብቁበት በቂ ፓርኪንግ/መቆሚያን ያካተተም ነው። ይህ ከጤና፣ ኢኮኖሚና አካባቢ ጥበቃ አኳያ ብዙ ፋይዳ አለው ይላሉ አቶ ወንድወሰን።
ቀጥለው ሲናገሩም “አካባቢው ከፍተኛ ሙቀት ያለበት እንደመሆኑ ማኅበረሰቡ ፀሐዩን ፍራቻ የእግረኛና የብስክሌት መንገዱን በፈለገው ሰዓት ላይጠቀም ይችላል። ጥላ ሊያገኝ ይገባል።” በማለት፣ ስለዚህም የሚገነቡት መንገዶች ዳርቻ ውበት ያላቸው ዛፎችን መትከል ግድ እንደሚል ነው የተናገሩት።
በዚህ ረገድ ቀደም ሲል የነበሩ ዛፎች ዲዛይን ጠብቀው አዲስ የሚተከሉት እስኪደርሱ እንዲቆዩ ተደርጓል። በኮሪደር ልማቱ ሥራ ወቅት ቀድሞ የነበሩ ዛፎች ላይም ብዙ ጉዳት አልደረሰም፣ ትንሽ አስቸጋሪ የነበረው ትልቁ የከዚራ መስመር ምድር ባቡር አካባቢ ነው። እዚያ አካባቢ 1ነጥብ 1 ኪሎ ሜትር ያህል ርዝመት ያለው መንገድ 10 ሜትር ስፋት የነበረውን መንገድ ወደ 33 ሜትር ማስፋት እንደተቻለ ኃላፊው ያስረዳሉ። ይህም በአካባቢው የነበሩ ዛፎችና አረንጓዴ ስፍራ እንዲነሳ አስገድዷል። በተሻለ አረንጓዴ ስፍራና በአዳዲስ ዛፎች ግን እንዲተካ ተደርጓል። ከዚራ የምትታወቀው በጥላዋ ስለሆነ ያረጁ ዛፎችና አረንጓዴ ስፍራዎች በተሻለ እንዲተኩም ተደርጓል ብለዋል።
የታሪካዊቷ ድሬዳዋ የኮሪዶር ልማት የነዋሪዎችን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያረጋገጠ እንደሚገኝ እግር ጥሎት ምሥራቃዊቷ ገነት የተገኘ አለመመስከር አይችልም። የኮሪደር ልማት ሥራው ለነዋሪዎች ምቹና ውብ ገጽታ በመፍጠር የከተማዋን ዕድገት የሚያሳልጥ የመስሕብ ስፍራ እየፈጠረ እንደሚገኝ ገና ሳይጠናቀቅ ከወዲሁ እየታየ ነው። ነዋሪዎችም በዚህ ደስተኛና አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙ ከንቲባው ከድር ጁሀር በቅርቡ መግለፃቸው ይታወሳል።
በቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 10 ቀን 2017 ዓ.ም