
51ኛው የ‹‹ቡድን ሰባት›› (G7) አባል ሀገራት ጉባዔ በካናዳ፣ አልበርታ ግዛት ውስጥ በምትገኘው ካናናስኪስ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል። በጉባኤው የስብስቡ አባላት የሆኑት የአሜሪካ፣ ጃፓን፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ፣ ኢጣሊያ እና ካናዳ መሪዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ። የሜክሲኮ፣ የሕንድ፣ የደቡብ አፍሪካ፣ የሳዑዲ ዓረቢያ፣ የዩክሬን፣ የአውስትራሊያ፣ የብራዚል፣ የኢንዶኔዥያና የደቡብ ኮሪያ መሪዎችም ከካናዳ ግብዣ ቀርቦላቸዋል።
የዘንድሮው ጉባኤ ‹‹በመላው ዓለም ያሉ ማኅበረሰቦችን መጠበቅ፣ የኃይል መሠረተ ልማት ደኅንነትን ማረጋገጥና ዲጂታል ሽግግርን ማፋጠን እና የወደፊት ትብብሮችን መገንባትና ማጠናከር›› የሚሉ ዋና ዋና ተግባራትን ማዕከል አድርጎ እንደሚካሄድ ተገልጿል።
የዘንድሮው ጉባኤ፣ ከወቅታዊ ጂኦ ፖለቲካዊና የምጣኔ ሀብት ጉዳዮች አንፃር ጉባኤው በውጥረት የተሞላና የተራራቁ ሃሳቦች የሚንፀባረቁበት ስብሰባ ሊሆን እንደሚችል ሲነገር ነበር። ጉባኤው የመካከለኛው ምሥራቅ ባላንጣዎቹ እሥራኤልና ኢራን ውጊያ እያደረጉ ባለበት እና የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ወደ አሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ ከፍተኛ ታሪፍ በመጣላቸው አስቸጋሪ የንግድ ድርድሮች በሚደረጉበት ወቅት የሚካሄድ እንደሆነ ይታወቃል።
በጉባኤው ላይ የታደሙት ፕሬዚዳንት ትራምፕ የጉባዔውን አስተናጋጅ ካናዳን 51ኛዋ የአሜሪካ ግዛት መሆን አለባት እያሉ ሲናገሩ ከርመዋል። ምንም እንኳ ካናዳ ይህን የፕሬዚዳንቱን ሃሳብ ደጋግማ በአፅንዖት ብትኮንንም የትራምፕ አቋም ለወትሮው ሁነኛ ወዳጆችና ጎረቤቶች የነበሩትን አሜሪካንና ካናዳን ግንኙነታቸው ነፋስ እንዲገባበት ምክንያት ሳይሆን አልቀረም።
የትራምፕ የታሪፍ እርምጃ የሁሉንም የቡድን ሰባት አባላት ኪስ ዳብሷል። ሀገራቱ ከአሜሪካ ጋር የንግድ ስምምነቶችን ለመፈራረም እየተወያዩ ይገኛሉ። የውይይቶቹን ውጤት ለመጠበቅ ሲባል ጉባኤው ስለታሪፍ ጉዳይ ላይወያይ እንደሚችል ተገልጿል። እንግሊዝ ከአሜሪካ ጋር የንግድ ስምምነት ላይ መድረሷ ከአንድ ወር በፊት የተገለፀ ሲሆን፣ የአውሮፓ ኅብረትና ጃፓን የትራምፕ የ90 ቀናት ገደብ ከማለቁ በፊት ከአሜሪካ ጋር ስምምነት ላይ ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የሩሲያ-ዩክሬን እንዲሁም የእሥራኤል-ኢራን ጦርነት፣ የቻይና ተፅዕኖ እና ዓለም አቀፍ ንግድም በስብሰባው ትኩረት ሊያገኙ የሚችሉ ሌሎች ጉዳዮች እንደሚሆኑ ይጠበቃል። ቻይናም ስሟ ተደጋግሞ መነሳቱ አይቀርም። ከአባል ሀገራቱ የጋራ ውይይት በተጨማሪ የአሜሪካ-ደቡብ አፍሪካ፣ የአሜሪካ-አውሮፓ ኅብረት፣ የአሜሪካ-ካናዳ-ሜክሲኮ እና ሌሎች ውይይቶች ይደረጋሉ ተብሏል።
‹‹ቡድን ሰባት›› የሚባለው በኢኮኖሚያቸው የበለፀጉ ሀገራት ስብስብ የምጣኔ ሀብት አቅም ከዓለም አጠቃላይ ምርት 44 በመቶውን እንዲሁም ከዓለም ሕዝብ ደግሞ 10 በመቶውን ይሸፍናል። ከቡድኑ አባላት መካከል ትልቅ የምጣኔ ሀብት አቅም ያላት የዓለምን ኢኮኖሚ በበላይነት የምትመራው አሜሪካ ናት። አሜሪካ የቡድኑ ቁልፍ አባል ብትሆንም ፕሬዚዳንት ትራምፕ ግን ቡድኑን በተደጋጋሚ ሲተቹት ይደመጣሉ።
ቡድኑ ለዓለም ምን አበርክቶ እንዳለው ለትራምፕ ግልጽ አይደለም። ከሰባት ዓመታት በፊት በትራምፕ የመጀመሪያው የሥልጣን ዘመን የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪያቸው የነበሩት ጆን ቦልተን የቡድን ሰባት አባላትን ‹‹አሜሪካን እንደግል ባንካቸው የሚያስቡ ሀገራት›› ብለው አጣጥለዋቸዋል። ቦልተን በዚያው ወቀሳቸው ‹‹ፕሬዚዳንቱ በግልጽ ተናግረዋል፤ ከዚህ በኋላ ይህ አይቀጥልም›› ብለው ነበር።
ትራምፕ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው በ2018 በካናዳ አስተናጋጅነት በተካሄደው የቡድኑ ጉባኤ ላይ በጉባኤው የመጨረሻ ቀን የጋራ መግለጫ እንዳይወጣ አድርገው ነበር። የወቅቱን የካናዳ ጠቅላይ ሚነስትር ጀስቲን ትሩዶን ‹‹ውሸታምና ደካማ›› ሲሉ ወርፈዋቸውም ነበር።
በአንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 10 ቀን 2017 ዓ.ም