
ኢትዮጵያ ከ40 በላይ የተለያዩ የከበሩ ማዕድናት አሏት። ከእነዚህ መካከል ሳፋየር፣ ኤምራልድ፣ ኦፓል፣ ጃስበር፣ ኦብሲዲያን፣ ጋርኔት፣ አሜቲስት እና ሲትሪን የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ። ኮረንድም እና ቤሪል ፋሚሊን በመባል የሚታወቁ እጅግ በጣም የከበሩ ማዕድናት በሀገሪቱ ይገኛሉ።
የከበሩ ማዕድናት በዓለም ሀገራት ኢኮኖሚ በሰፊው የሚያንቀሳቅሱ ናቸው። በከበሩ ማዕድናትና ጌጣጌጥ ዘርፍ በዓመት 250 እስከ 300 ቢሊዮን ዶላር እንደሚንቀሳቀስ ይታወቃል። ይህ መረጃ እንደሚያሳየው ዘርፉ ሰፊ ሀብት ማንቀሳቀስ የሚችል መሆኑን ነው። ሆኖም ኢትዮጵያ በርካታ የማዕድን ሀብት ቢኖራትም፤ ዘርፉ ገና ጅምር በሚባል ደረጃ ላይ የሚገኝ መሆኑን ተከትሎ፤ ከከበሩ ማዕድናት ማግኘት የሚገባት ጠቀሜታ እያገኘች አይደለም።
ማዕድናቱን ጥቅም ላይ በማዋል በተለያየ መልኩ ለዓለም ገበያ በማቅረብ ከፍተኛ ገቢ ለማግኘት ዘርፉን በደንብ ማወቅ እና መሥራት እንደሚገባ እየተገለፀ ይገኛል። በሌላ በኩል መንግሥት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ ማድረጉን ተከትሎ፤ በማዕድን ዘርፉ ላይ ለውጦችና መሻሻሎች እየመጡ መሆኑ እየተነገረ ነው። በከበሩ ማዕድናት ላይ ያሉ ለውጦችና መሻሻሎች ምንድናቸው? የዘርፉ የሥራ እንቅስቃሴ አሁናዊ ሁኔታ ምን ይመስላል? ስንል የዘርፉን ባለሙያ አነጋግረናል።
አቶ ቴዎድሮስ ስንታየሁ የኦርቢት ኢትዮጵያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅና የጀምስቶን ማኅበር ፕሬዚዳንት ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ከተደረገ በኋላ የከበሩ ማዕድን ዘርፍ አበረታች ለውጦች እያሳየ ውጤቶች እያስመዘገበ ይገኛል። በተለይ ወርቅ በከፍተኛ ደረጃ ወደ ብሔራዊ ባንክ በመግባቱ ከፍተኛ ለውጥ መጥቷል።
ሆኖም ከማዕድን ዘርፉ ከወርቅ ውጪ ሌሎች የከበሩ ማዕድናት የየራሳቸው ባህሪ ያላቸው በመሆኑ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው እምብዛም የተቀየሩ ነገሮች እንደሌሉ ይገልጻሉ። በእነዚህ ማዕድናት ዙሪያ በተለይ ሕገወጥነቱ የተስፋፋ መሆኑን ያስረዳሉ። ምክንያቱን ሲያብራሩ፤ ማዕድን ከማውጣት ጀምሮ ያለው ሂደት ግልጽነት በሰፈነበት ሁኔታ የተደራጀ አለመሆኑን እንደ አንድ መንስኤ ይጠቅሳሉ።
ማዕድናቱ ከወጡ በኋላ ወደ ውጭ የሚልኩ አካላት ጋር እስኪደርሱ በአብዛኛው የሚያዘዋወሩት በሕገወጥ እንቅስቃሴ ውስጥ ነው ሲሉም ይናገራሉ። ላኪዎቹም ገቢያቸው እንዳይታወቅ የሚፈልጉ በመሆኑ ፊት ለፊት አይወጡም። በሌላ በኩል መንግሥት ለወርቅ የሰጠውን ትኩረት ያህል ለሌሎች ማዕድናት ትኩረት ሰጥቷል ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል።
እንደሳቸው ገለፃ፤ ይሁንና ዘርፉ ገና በሙከራ ላይ እንደመሆኑ ሥርዓት ለማስያዝ በማዕድን ሚኒስቴር በኩል ብዙ ጥረቶች እየተደረጉ ናቸው። በተጨማሪ የማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስትቲዩት ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ጥናቶችን እያካሄደ ብዙ ሙከራዎችን እያደረጉ ይገኛሉ።
የግብይት ሥርዓቱን በማስተካከል ችግሮችን ለመቅረፍ የሚቻልበትን አካሄድ በተመለከተ ጥናቶች እየተካሄዱ ናቸው። ሆኖም ይህንን ወደ መሬት አውርዶ እንደገና የማዋቀር ሥራ እስካልተሠራ ድረስ፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ብቻ የሚያመጣው የሚታይ ለውጥ ላይኖር ይችላል ሲሉ አስረድተዋል።
በዚህም ወደ አንድ መስመር ሊያመጡ የሚችሉ ተስፋ ሰጪ ምልክቶች መታየት ጀምረዋል ሲሉ የተናገሩት አቶ ቴዎድሮስ፤ እየተገኙ ያሉ ለውጦችን በተመለከተ ቀደም ሲል በወጪ ንግድ ረገድ አንድ ሺ ዶላር የሚገመት የከበሩ ማዕድናት ለውጪ ገበያ በመላክ አምስት ሺ አምስት መቶ ብር የሚያገኝ ኪ፤ አሁን ባለው የምንዛሪ ለውጥ እጥፍ እያገኘ መሆኑን ይገልጻሉ። ከዚህ በዘለለ ዘርፉን በማሳደግና ለሀገር እንዲጠቅም በማድረግ ደረጃ ከወርቅ ውጪ ብዙ የመጣ ለውጥ አለመኖሩን ያመለክታሉ።
የአሠራር ክፍተት መኖሩን በመጠቆም፤ አሠራሩ ታች ወርዶ እሴት ለመጨመር የሚሞክሩትን ችግር የሚቀርፍ፣ የሚጠብቅና የሚያበረታታ አለመሆኑን ተናግረዋል። በዚህ የተነሳ በዘርፉ የተሰማሩ ሰዎች እሴት መጨመር ከመፈለግ ይልቅ፤ ለውጭ ሀገር ዜጎች በመደለል ኮሚሽን መሰብሰብ የሚችሉበት መንገድ መከተል ይመርጣሉ ብለዋል።
የከበሩ ማዕድናት ላይ እሴት በመጨመር ረገድ ብዙ ጥሩ ጅምሮች መኖራቸውን መካድ ባይቻልም፤ ይህንን የማበረታታት፣ የማበልጸግ፣ የማደራጀትና የማገዝ ሁኔታ ግን ገና ብዙ የሚቀረው ሥራ መሆኑን ያመለክታሉ። እሴት መጨመር ጥቅሙ የገባቸው ግለሰቦችና ድርጅቶች እንዳሉ ጠቅሰው፤ ይሁንና ከሙከራ ደረጃ ባለፈ ደረጃውን የጠበቀ ሥራ በመሥራት በኩል ክፍተት መኖሩን ያብራራሉ።
አቶ ቴዎድሮስ እንዳመላከቱት፤ ኦፓል ከሚመረተው ጥሬ እቃ አንጻር የተወሰነም ቢሆን ትርጉም ያለው መጠን ያህል እሴት የመጨመር ሥራ እየተሠራ ነው። ወደ ኋላ መለስ ብለን ስንመለከት፤ ወሎ ደላንታ አካባቢ ከአስር ዓመት በፊት አንድ ድንጋይ ቀራጭ አልነበረም። ዛሬ ከ120 በላይ የተመዘገቡ ግለሰብ ቀራጮች በቦታው ላይ እሴት እየጨመሩ ይገኛሉ።
‹‹እሴት አጨማመራቸው ደረጃው ያልጠበቀ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ከፍተኛ እድገት ያመጣ ነው። ›› ያሉት አቶ ቴዎድሮስ፤ እነዚህ የማገዝ፣ የማብቃት፣ አቅም የመገንባትና ደረጃውን የጠበቀ ሥራ እንዲሠሩና ቀጣዮቹም ወደ ሕጋዊ መስመር እንዲመጡ የማድረግ ሥራዎች ይቀራሉ ሲሉ ገልጸዋል።
በአንድ ወረዳ ይህንን ሁሉ ቁጥር ማድረስ ቀላል አይደለም፤ ትልቅ ውጤት ነው። ይህንን ትልቅ ውጤት ወደሚፈለገው መስመር ለማምጣት ሥራ ያስፈልጋል የሚሉት አቶ ቴዎድሮስ፤ በዚህም በሕገወጥ መንገድ እንዳይሸጡና ሕጋዊ መስመር እንዲከተሉ ደረጃውን የጠበቀ ሥራ እንዲሠሩ አቅማቸውን ለመገንባት ሥራዎችን መሥራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
በጣም በጥቂት ሰው ወደ ውጭ የሚልከው እሴት ተጨምሮ የተሠራውን መሆኑን አስታውሰው፤ ይሁንና በብዙኀኑ የሚላከው ከዚያም ከዚህም የተለቃቀመው ተጨማምሮ ነው። ይህንን ለማስተካከል እሴት መጨመርን በተመለከተ በደንብ ተደራጅቶ በእውቀት የተመራ ሥራ ሊሠራ ይገባል ይላሉ።
ሕገወጥ ግብይቱን ብዙ ሰው ፈልጎ ባይገባበትም፤ አሁን ያለው አሠራር ግን የሚያስገድድ መሆኑን ያስረዳሉ። ችግሩን መቅረፍ የሚቻለው የእሴት ጨማሪዎችን ችግራቸውን በመመልከት፤ ሥራው ላይ ያሉ አካላትን በማሳተፍ ሥራዎች ሲሠሩ መሆኑን ያመለክታሉ።
‹‹በአጭር ጊዜ የከበሩ ማዕድናትን በተመለከተ በወርቅ ላይ የመጣውን ከፍተኛ ዓይነት ለውጥ ማምጣት የሚቻለው እሴት በመጨመር ነው። በዚህ በኩል ጅምሩ ጥሩ መሰረት እየተጣለ ነው፤ ›› የሚሉት አቶ ቴዎድሮስ፤ የእሴት መጨመር ጥቅምን በተመለከተም አስረድተዋል። በጥሬው አንድ ብር የሚሸጠው ማዕድን ሲቀረጽ 10 ብር ይሸጣል። በጥሬ እቃው ላይ እሴት ሲጨመር ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ይኖረዋል። እንዲሁም የሥራ እድል ይፈጥራል። ሲሉ እሴት መጨመር ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም እንደሚያሳድግ አስረድተዋል።
አቶ ቴዎድሮስ እንዳብራሩት፤ በሌላ በኩል ሕገወጥነት በመቅረፍ ከማዕድን የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ ማዕድን የማውጣት ሥራ ላይ ከተሰማሩ አካላት ጀምሮ መሥራት ያስፈልጋል። በዋናነት ማኅበራት ሲደራጁ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው አሠራር እንዲሠሩ ማድረግ ይጠበቃል።
በማኅበራት ተደራጅተው የሚሠሩ አምራቾች ከሮያሊቲ ክፍያ ውጭ የገቢ ግብር ክፍያ አይከፍሉም። የግንዛቤ እጥረት ስላለባቸው ደረሰኝ አይሰጡም፤ ተደብቀው ይሸጣሉ። ይህንን እንዳያደርጉ ግንዛቤን ማስፋት፣ ማሳደግና ማስተማር ያስፈልጋል። የግድ ግብይቱን ሥርዓት በማስያዝ ብዙ ተጎዳኝ ነገሮችን መፈታት አለባቸው። የማዕድን ሚኒስቴርም ግብይቱ ላይ ሥራ ቢሠራ ለውጥ ማምጣት እንደሚችል አምኖ እየሠራበት ነው። ይህን አጠናክሮ ማስቀጠል ይጠበቅበታል ይላሉ።
ሌላው የግብይት ሥርዓቱ በምን መልኩ ይሆን የሚለውን ሁሉንም አካላት በማሳተፍ ለሁሉም አመቺ የሆነ የግብይት ሥርዓት መፍጠር ግድ ይላል። የሚሉት አቶ ቴዎድሮስ፤ ከዚህ ባሻገር ለውጥ የሚያመጣው እሴት የሚጨምሩት እሴት እንዲጨምሩ በማበረታታት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
እሴት በመጨመር ረገድ የገንዘብ አቅርቦት፣ የደረሰኝና የማሽን ችግር መኖሩን አስታውሰው፤ እንዲሁም የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት መኖሩንም ጠቁመዋል። በቀላሉ ችግሩን ለመፍታት የገንዘብ ብድር በማመቻቸት፣ ማሽኖችን ሊያስገቡ የሚችሉባቸውን መንገዶች መፍጠርና ከደረሰኝ ጋር የተያያዙ እና የመሳሳሉት ማነቆዎችን በመፍታት የማስተካከል ሥራዎች ቢሠሩ እሴት ጨማሪዎች ማበረታት ይቻላል ሲሉ አስረድተዋል።
በሕገወጥ የሚገዙት ተፎካክረው ጥሬ እቃውን ገዝተው እሴት ጨምረው መሸጥ የሚጀምሩት፤ እሴት የሚጨምሩትን ማበረታታና አቅም መፍጠር ሲቻል ነው። ለዚህም የመንግሥት ድጋፍ፣ እገዛ እና እውቅና ካለ በራሱ ጊዜ ሕገወጥነቱ እንደሚጠፋ እና ይህ ዋነኛው መከላከያ ዘዴ ነው የሚል እምነት እንዳላቸውም ያመላክታሉ። ጨምረውም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር አስፈላጊውን ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ የሚያስፈልግ መሆኑም ሊዘነጋ እንደማይገባ ያስታውሳሉ።
እንዲሁም ሕገወጥነት እንዳለ በመንግሥትም የሚታወቅ ጉዳይ ቢሆንም፤ ብዙ ጊዜ በኮንትሮባንድ ውስጥ የሚሳተፉ ሰዎች እርምጃ ሲወሰድባቸውና ተጠያቂ ሲደረጉ አይስተዋልም። እዚህ ላይ ትኩረት ተደርጎ ቢሠራ ለውጦችን ማምጣት ይቻላል ብለዋል።
በሌላ በኩል በከበሩ ማዕድናት ዙሪያ ሰዎች በከፍተኛ ደረጃ እውቀት አላቸው የሚሉት አቶ ቴዎድሮስ፤ ሥራውን በመሥራት የሚወሰድ ትምህርት እንዳለ ሆኖ ብዙ ሰው ራሱን እያስተማረ የተለያዩ ሥልጠናዎች በራሱ ጥረት ለመውሰድ ይሞክራል። ይህን ተከትሎ በማዕድናቱ ዙሪያ ብዙ የእውቀት ችግር የለም።
ይሁንና አንዳንድ ጊዜ ተገኝተው ምንነታቸው የማይታወቁ ሌላ ሀገራት ያልተገኙ ማዕድናት ሲገኙ፤ ያንን የመለየት ችግር ያጋጥማል። እስከ አሁን በሌላው ዓለም ተገኝተው የታወቁና ኢትዮጵያ የሚገኙ ማዕድኖች ለመለየትና ደረጃ ለማውጣት ብዙ ሰው ሲቸገር አይስተዋልም ያሉት አቶ ቴዎድሮስ፤ እንደክፍተት መነሳት ያለበት ማዕድናቱን የማወቅ ጉዳይ ሳይሆን በዓለም ላይ ከፍተኛ ገበያ ያላቸው በኢትዮጵያ በብዛት ማምረት የሚቻሉ ማዕድናት በዝቅተኛ ዋጋ መሸጣቸው ነው ሲሉ ጠቁመዋል።
ምርቱ በብዛት እየወጣ በአነስተኛ ዋጋ የሚሸጡበት ሁኔታ መኖሩ፤ የጎንዮሽ ጉዳት ያለው መሆኑን ገልጸው፤ እሴት ለሚጨምሩ ኩባንያዎች ተወዳዳሪ ለመሆን እንዳይችሉ ያደርጋል ይላሉ።
አቶ ቴዎድሮስ፤ አብነት ጠቅሰው ሲያስረዱ፤ ከጋሞ አካባቢ የሚመጣ አጌት የሚባል የከበረ ማዕድን አለ። በኮንቴነር እየተሞላ በማይረባ ገንዘብ እንዲወጣ እየተደረገ ነው። የእሳቸው ኩባንያም ይህንን ማዕድን እሴት ጨምሮበት ለውጭ ገበያ እንደሚልክ በመጠቆም፤ የማዕድኑ ከፍተኛ ምርት በማይረባ ዋጋ እንዲወጣ ሲደረግ ሀገር ውስጥ ያለውን እሴት የመጨመር ጅምር ተስፋ የሚያጨልም መሆኑን ያመላክታሉ።
ተወዳዳሪነት እንዳይኖርና ተስፋ መቁረጥ እንዲኖር የሚያደርግ በመሆኑ፤ በመንግሥት ግንዛቤው ኖሮ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አስገንዘበዋል። ‹‹ድንጋዮቹ የኢንዱስትሪ መሰረት የሚባሉ ናቸው። ውድ እንደሚባሉ ድንጋዮች ተፈልገው የሚገኙ አይደሉም። ሁልጊዜ በቀላሉ የሚገኙ በመሆናቸው ብዙ የሥራ እድል ይፈጥራሉ። ›› የሚሉት አቶ ቴዎድሮስ፤ እነዚህም በማይረባ ገንዘብ ወደ ወጪ ሀገር እንዲወጡ የሚደረግበት ሁኔታ መኖሩን ገልጸዋል። ይህንን በጥልቀት መገንዘብና ሌሎች ሀገራት በዚህ ኢንዱስትሪ የደረሱበትን ደረጃ መመልከት እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል።
አቶ ቴዎድሮስ እንዳብራሩት፤ የከበሩ ማዕድናት ኢንዱስትሪ አዲስ ቢሆንም በቀላሉ በሀገር አቅም ሊሠራ የሚችል ነው። የሚያስፈልጉት መሠረታዊ ግብዓቶች የሰለጠነ የሰው ኃይልና ጥሬ እቃ ነው። እነዚህም በከፍተኛ ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ ይገኛል። እንዲሁም በየጊዜው አዳዲስ ማዕድናት ቁጥር እየጨመረ ነው። ኢትዮጵያ በዚያ ደረጃ በቂ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅባታል።
የከበሩ ማዕድናትን ማግኘትና እሴት መጨመር ረጅም ዓመታት የማይወስድ፣ ውስብስብ ቴክኖሎጂን የማይጠይቅ፣ የውጭ ባለሙያና ኢንቨስትመንት የማይፈልግ በመሆኑ በሀገር ውስጥ አቅም በአጭር ጊዜ ለኢኮኖሚው ጠቃሚ በሆነ መልኩ መዋል ይችላል። አላቂ የተፈጥሮ ሀብት ቢሆንም የሥራ እድል የሚፈጥር እና ሀገርን በአግባብ ለመጠቀም የሚያስችል በመሆኑ፤ ያለውን መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም የሁሉም ርብርብ ያስፈልጋል ሲሉ አስገንዘበዋል።
በወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 6 ቀን 2017 ዓ.ም