በኢትዮጵያ 45 የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች የሚሳተፉበት ጉባኤ ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ በአፍሪካ 2ኛውን የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በማስመልከት 45 የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች የሚሳተፉበት ጉባኤ ሊካሄድ መሆኑን ፕላንና ልማት ሚኒስቴር ገለፀ፡፡ በጉባኤው ከ25 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች እንደሚገኙም ተገልጿል፡፡

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የሚካሄደውን የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ አስመልክተው በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ እኤአ ከመስከረም 8 እስከ 10 ቀን 2025 ድረስ የሚካሄደውን የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ታዘጋጃለች፡፡ ጉባኤው ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ኅብረት ጋር በመተባበር የምታዘጋጀው ሲሆን በአዲስ አበባ አዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል ይካሄዳል ብለዋል፡፡

ጉባኤው የአየር ንብረት ለውጥ ከመከላከል ባሻገር የፓን አፍሪካኒዝም ጥምረት ለማጠናከር ትልቅ አስተዋፅዖ ይኖረዋል ያሉት ሚኒስትሯ፤ አፍሪካውያን ዓለም አቀፍ ትስስር ለመፍጠር የሚያስችላቸውን የሲቪክ ማኅበራት፣ ወጣት ማኅበራት እና አጠቃላይ የግሉን ሴክተር የሚያሳትፍ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ጉባኤው በዋናነት የሚመራው የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር መሆኑን በመጠቆም፤ ዋና ጉዳዩ የአፍሪካ አረንጓዴ ልማት ለማስፋት የሚጠቅሙ ጥናታዊ ጽሑፎች እና በአየር ንብረት ለውጥ የተፈጠሩ ችግሮች ለመቅረፍ የሚያስችሉ መፍትሔዎች ለማስቀመጥ የሚያስችል እንደሚሆን አመልክተዋል፡፡

በተለይ ለአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመከላከል የፋይናንስ አቅርቦት እና ኢንቨስትመንት በግልፅ የሚያመላክት እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት ግብርና እና ገጠር ልማት ኮሚሽነር ሞሰስ ቪላካቲ በበኩላቸው፤ አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት እያስተናገደች ቢገኝም ለብክለቱ የምታደርገው አስተዋፅዖ ግን አነስተኛ ነው ብለዋል፡፡

በዚህም ሳቢያ በአሕጉሪቱ የንፁህ ውሃ አቅርቦት፣ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እንዲሁም የጤና እና የግብርና ለውጥ ለማምጣት አዳጋች ማድረጉን አመልክተው፤ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት እና መሠረታዊ ዕድገት ለማምጣት ጉባኤው ወሳኝ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በሔርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 10 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You