አብርሃምተወልደ
የታክሲው ሰልፍ በጣም ረጅም ቢሆንም ከቤት አይቀርምና ተቀላቀልኩት። ብቅ የሚል ታክሲ ግን የለም፤ የትራፊክ መጨናነቅ አለ ማለት ነው ብዬ ራሴን አጽናናሁ። ሃሳብ ውስጥ ነኝ። ለራሴ ሳውጠነጥን ቆይቼ የሚመጣው ታክሲ ሁሉ በስርዓቱ ቢጭን እኮ ይደርሰናል አልኩ። ለሰው አልነበረም የተናገርኩት። ለካስ ጮክ ብዬ አስቤያለሁ ፤ ለብቻዬ አውርቻለሁ። አንዱ ተራ ጠባቂ ለካ ንግግሬን ሰምቷል። ‹‹ችግሩ ሰልፉ ብዙውን ጊዜ የሚፈርስ መሆኑ ላይ ነው። የፈረሰ ጊዜ ድብልቅልቁ ይወጣል ፤ አንደ አዲስ መጀመር ውስጥ ይገባል ፤ከእሱ ብቻ ያውጣን አለኝ።
ተሳፋሪውን አሰብኩት። ማለዳ ሥራዋን ብላ ልጆቿን ጥላ የወጣች እናት ተሯሩጣ ከሥራ መልስ የልጆቿን ዓይን ለማየት ልቧ መንጠልጠሉ ታሰበኝ፤ እራት ቁርስና ምሳም የምትሠራው እሷው ልትሆን ትችላለች። ሲለፋ ውሎ አንዳች ነገር በእጁ ይዞ ልጆቹ ሳይተኙ ቤቱ ለመግባት የቸኮለ አባትም ከመካከለችን እንደሚኖር ገመትኩ። ሁሉም ከያለበት ወደ ሰፈሩ ወደ ቤቱ ለማቅናት የክተት አዋጅ የተነገረ ያህል እንደሚጣደፍ ገባኝ።
ሁሉም ቤቱን ብሎ ትራንስፖርት ፍለጋ ቢሰለፍም ቢሮጥም ድካሙ ከንቱ ነው፤ምክንያቱም ፍላጎቱ የሚመለሰው እንደ ታክሲዎች ችርነት ነዋ! ተራ አስከባሪ ካለ ነገሮች በስርዓት የሚመሩበት ሁኔታ ስላለ ተራ ጠብቆ መሳፈር ይቻላል። እሱም ቢሆን ግን ከባለታክሲዎች አንዳንዴም ከተሳፋሪዎች ጋር መሞዳሞድ ነገር ስላለ ዓይን እያየ ሰው ያለተራው ይሳፈራል፤ መጣ ያሉት ታክሲ ተራውን ቀይሮ ይጭናል።
ተራችን ደረሰና ተሳፈርን፤ ጉዞ ተጀመረ፤ ረዳቱ ሂሳብ ሲል ጠየቀ። ገና ሂሳብ መቀበል ሲጀምር አለመግባባት ተከሰተ፤ አልከፍልም ምን ስለሆነ ነው ይህን ያህል የምሰጥህ? የሚል ተሳፋሪ ድምፅ ከፊት ወንበር አካባቢ ተሰማ። አነጋገሩ የሆነ በራስ መተማመን ያለበት ዓይነት ነው።
“ወንድም ካልተመቸህ መውረድ ትችላለህ፤ ስትገቡ ተናግሬያለው … ሲል ረዳቱ አስፈራራ። ጭቅጭቁ ጋለ፤ አልከፍልም ባዩ ተሳፋሪ ለራሱ የሚያንስ ባይሆንም ብዙ አጋዥ አያገኘም መጣ፤ “ አስር ብር የመደባችሁብን አንሶ አሁን ደግሞ ሌላ ትፈልጋላችሁ፤ ትክክለኛው ተመን እኮ ስድስት ብር ነው፤ አሁን ደግሞ አምስት ብር ትጨምራለህ ፤ኧረ ፈጣሪን ፍሩ›› ሲሉ አንድ አባት በምሬት ተናገሩ።
“አቦ! እምትከፍሉ ከሆነ ክፈሉ ፤አለበለዚያ አንሄድም፤እንዳውም ከመኪናዬ ውረዱ ›› አለ ሹፌሩ። ከመጨረሻ ወንበር አካባቢ ያለ አንድ ተሳፋሪ “ ጎበዝ በቃ እንክፈል እና በሰላም በጊዜ ቤታችን እንግባ ›› ሲል ጭቅጭቁ ጨመረ። ሠርተን ነው የምንከፈለው ፤ሰርቀን አይደለም፤የተጠየቀውን የሚከፍል ሌባና አጭበርባሪ ነው አለ ሌላ ተሳፋሪ። ሌባ ሁሉ! አለ። ዱላ ቀረሽ በሉት።
አሽከርካሪው ከመኪናዬ ውረዱ ያላት ነገር አንድ ነገር አስታወሰችኝ። ቆይቷል፤ በአንድ ወቅት ከአንድ የክልል ከተማ ወደ አዲስ አበባ በአውቶቡስ እየመጣሁ ሳለ አለአግባብ ከፈሉ የተባሉ አንድ ተሳፋሪ ለምን ሲባል ማለታቸውን ተከትሎ ውዝግብ ይነሳል።
አሽከርካሪው ትልቅ ሰው ናቸው፤ ባለቤት ሳይሆኑም አይቀሩም። ልክ እንደዚህ የታክሲ ሾፌር መኪናውን አቁመው አልከፍልም የሚሉ ከሆነ ከመኪናዬ ይውረዱ ሲሉ ያሳስባሉ። ወረዱ የተባሉት ጎልማሳ ከዚህ በኋላ ማን ይቻላቻው። አልወርድም፤ መኪናውን የገዛኸው ህዝብ ለማገልገል ነው። ፈቃድ ያወጣኸው እየመረጥክ ልትጭን አይደለም ሲሉ መለሱለት።
ነገሩ ያላማራቸው አሽከርካሪ ረዳቱን እንዲገባ አርገው ጉዞ ተጀመረ። እኛም ለካስ እንዲህም አለ ብለን የሰውዬውን ምላሽ እያደነቅን መንገዳችንን መቀጠላችን ታወሰኝ። ከመኪናዬ ውረዱ ብዙ ጣጣ ሊያስከትል እንደምትችል በተለይ የታክሲ ሾፌሮች አያውቁም።
ይህ ሁሉ ሲሆን ታክሲው ዳር ይዞ ቆሟል። የአንዲት እናት ድምፅ ተሰማ። በእሳቸው ምክር እና ልመና ሹፌሩ ሃሳቡን ቀየረ። ረዳቱን “በቃ ግባ!” ብሎ አስር ብር ብቻ እንዲከፍሉ አርጎ ተንቀሳቀሰ። ማዘርን አመስግኑ አለ። መጀመሪያ ላይ አልከፍልም ያለውን ተሳፋሪ በጎሪጥ እያየ በዚህ ሰዓት እንዲህ ያለ ታሪፍ የለም፤ አቦ እንስራበት እንጂ ሲል በብስጭት ማሽከርከሩን ቀጠለ።
አንዳንዴ የትራንስፖርት ተቆጣጣሪዎች እንደ ተሳፋሪ ሆነው ሲጓዙ የታክሲ ሾፌሮች እንደፈለጉት መሆን ይቸገራሉ። ሾፌሩ እየቆየ እየቆየ ሰውየውን ጠርጥሮታል መሰለኝ እነሱ ደግሞ ተናግረው አይሳፈሩም እንዴ! ሲል ተናገረ። ተቆጣጣሪዎቹ ሌሎችን አያድኑም እንጂ ራሳቸውን ማዳን ያውቁበታል።
ያ ሁሉ ውዝግብ ቆሞ ዝምታ ሰፈነ። ከአጠገቤ የተሰነዘረ “እኔ የምለው!” የሚል ድምፅ ዝምታውን ሰበረው። በመስታወት ውጪ ውጪውን ሲያይ ቆይቶ ነው ይህን ያለው። ‹‹እኔ የምለው›› ሲል አሁንም ደገመው። ሰሚ ያገኘ ሲመስለው ነው መሰል ሰው ግን ገንዘብ ከየት እያመጣ ነው የሚገራርም መኪና የሚያሽከረው ሲል መኪናውን እያመለከተ ጠየቀ።
እኛ አባት በደንብ አዳምጠውት ኖሮ “ አጭበርብሮ ነዋ፤ ይሄኔ አጭበርባሪ ነጋዴ ወይም የባለስልጣን ልጅ ሊሆን ይችላል ፤ ሌላውማ እንኳን ይህን ዓይነት መኪና ሊገዛ በአግባቡም በልቶ ማደር አልቻለም፤ ሲሉ የሰጡት አስተያየት ተጨማሪ አስተያየቶች እንዲመጡ አደረገ። ከዚያ በኋላ ውይይት ሆነ። ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ትንተናዎች ተጀመሩ። የጉዞው መስመር ርቀት፣የትራፊክ መጨናነቁ እንደ ልብ ለማውራት አስቻሉ።
አንዱ ተሳፋሪ “ልክ ኖት! አባባ አንድ ነገር ግን ቢስተካከል ጥሩ መሰለኝ አለ። የባለስልጣን ልጆች ያሉት ትክክል ነው፤ ዓለምን የሚቀጩት እነሱ አይደሉ እንዴ፤ በየመዝናኛ ስፍራው የሚረጩትን ገንዘብ ለተመለከተ ይህ መኪና ያንሳቸዋል። ወጣት ያን ዓይነት መኪና ከየት ያመጣል? ነጋዴውም እንደዚያው ነው፤ ህዝብ በዋጋ ንረት ያለቅሳል፤ በዚያ ሰሞን ብቻ የዘረፉት ለብዙ ዓመት ያንቀባርራቸዋል ሲል አብራራ።
ኩዊንስ ሱፐር ማርኬት ስንደርስ ሳሳ ያለ ስልፍ ተመለከትን። አንደኛዋ ተሳፋሪ ምንድነው ስትል ወደ ሰልፉ በማመልከት ጠየቀች። አንድ ተሳፋሪ ስለ ሱፐር ማርኬቱ ለጠየቀቸው ግለሰብ ብቻ ሳይሆን ታክሲ ውስጥ ላለው ሰው በሙሉ በሚመስል መልኩ አስረዳ።
ለማስታወቂያው ስንት ይሆን የሚከፍሉት ያሉ አይጠፉም። ለማናቸውም ግን ስለሱፐር ማርኬቱ በመገናኛ ብዙሃን ብዙ ተብሏል። ነገሩን ሲያዳምጡ የነበሩ ግለሰብም ሁሉም እንዲህ ቅን ሆኖ በመጠኑ አትርፎ ቢሸጥ እንዴት መልካም ነበር አሉ።
እኔም ከተሳፋሪዎች ጋር ሃሳብ አልለዋወጥ እንጂ ያሉትን ሁሉ በሚገባ አዳምጫቸዋለሁ። “አንዳንድ ሰው ወር ቢያወራ አይሰለችም፤ አንዳንዱ ደግሞ ለሰከንድ አወሮቶ ይሰለቻል። ” የአባባን በሳል ትንታኔ አልጠገብኩትም። ሌሎች የሆዳቸውን መናገራቸውም ተመችቶኛል።
ሰዎች የሆዳቸውን ያወሩ የነበረበት ሁኔታ ሀገሬን በታክሲ ውስጥ እንዳያት አረገኝ። በእርግጥም በዚህች የታክሲ ጉዞዬ ውስጥ አገሬን አየኋት። ስለኑሮው የተነሳው ሃሳብ ፣የሃሳብ ልውውጥ የተደረገበት መንገድ ሁሉም ሀገርን መለስ ብሎ ያስመለክታል። ሀገሬን በታክሲ!!
አዲስ ዘመን መጋቢት 18/2013