ሙሉቀን ታደገ
በአዲስ አበባ የሚገኙ የግል ትምህርት ቤቶች የራሳቸውን መፅሐፍ በማተም ተማሪዎች ሊሸከሙት ከሚችለው በላይ እንዲጨነቁ እና ትምህርት እንዲጠሉ እያደረጉ ነው ሲሉ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የተማሪ ወላጆች ለአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ባደረሱት ቅሬታ መሰረት የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ያለውን አዲስ የአበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዳኘው ገብሩን አነጋግሮ የሚከተለውን ምላሽ ይዞ መጥቷል::
እንደ አቶ ዳኘው ገለጻ ትምህርት ቤቶች በይዞታ ጉዳይ ነው የግል ፣ የሚሲዮን ፣ የመንግሥት ወዘተ ብለን የምንጠራቸው እንጂ ሁሉም ትምህርት ቤቶች በሃገሪቱ ውስጥ የሚያስተምሩት ትምህርት ኢትዮጵያ ያወጣችውን ስርዓተ ትምህርት መሰረት ያደረገ ነው:: ይህንን ሁሉም ትምህርት ቤቶች ያውቃሉ:: ለማስተማር ፍቃድ ሲያወጡ ከመንግሥት የሚሳጣቸው ፈቃድ ይህንን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ያስገድዳቸዋል::
ነገር ግን የግል ትምህርት ቤቶች በተደጋጋሚ የሃገሪቱን ስርዓተ ትምህርት ሲጥሱ ይስተዋላል የሚሉት አቶ ዳኘው ፤ ስርዓተ ትምህርት ጥሰት የሚያከናውኑት በተለያየ መልኩ ነው ይላሉ:: ከእነዚህም መካከል አንደኛው ትምህርት ቤቶች የራሳቸውን መጽሐፍት አትመው ለትምህርት በማቅረብ ነው::
ይህ የግል ትምህርት ቤቶች በግላቸው የሚያትሙት መጽሐፍ ደግሞ የተማሪዎችን አቅም ያላገናዘበ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ተማሪዎች እድገት ላይ በእጅጉ ተፅዕኖ የሚፈጥር እንደሆነ ይናገራሉ:: የግል ትምህርት ቤቶች በራሳቸው የሚያትሙትን መጽሐፍ ለተማሪዎች መማሪያነት የሚያውሉት ለተማሪዎች አዝነው ሳይሆን ያተሙትን መፅሐፍ በውድ ዋጋ በመሸጥ ለማትረፍ
ከመፈለግ የመነጨ ነው:: በእርግጥ የግል ባለሀብቱ ወደዚህ ሥራ ሲገባ ትርፍ አገኛለሁ ብሎ ነው። ነገር ግን ትምህርትን ከትርፍ ጋር በማቆራኘት ተራ ሸቀጥ ማድረግ እንደማይቻል አቶ ዳኘው ይናገራሉ::
እንደ አቶ ዳኘው ገለጻ መጽሐፍ የማተም እና ስርዓተ ትምህርቱን የመቆጣጠር ብሎም የግል ትምህርት ቤቶች በዚያ ስርዓተ ትምህርት በትክክል ማስተማራቸውን የመከታተል ነገሮችን በተመለከተ ስልጣን የተሰጠው ለትምህርት ቢሮ ነው:: በመሆኑም ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ድረስ በትምህርት ቢሮ በሚተዳደሩ ትምህርት ቤቶች ሁሉ ሊያገለግል የሚችል የተማሪዎች መማሪያ መጽሐፍ አለ:: ይህ መፅሐፍ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ወስደው እንዲጠቀሙበት ይጠበቃል::
መፅሐፉ ከመታተሙ በፊት መርሐ ግብሩን አይቶ ስርዓተ ትምህርቱ የሚያዝዘውን ለማስተማር በሚያስችል ደረጃ ምሁራን መክረውበት ፤ ልጆች ወደፊት ከሚኖራቸው እድገት ጋር ተያይዞ ለዕድገታቸው እና ለዕድሜያቸው በሚመጥን መልኩ በተለያዩ ኤክስፐርቶች ተጠንቶ ነው ስርዓተ ትምህርቱ የተቀረጸው:: ይህንንም መሰረት አድርጎ ነው መጽሐፍት የሚታተሙት:: ስለሆነም ልጆች ዕድሜያቸውን መሰረት ተደርጎ ትምህርት እንዲያገኙ በመንግሥት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሆነ አቶ ዳኘው አመላክተዋል::
ከተማ አስተዳደሩ ተዘዋዋሪ ፈንድ በመመደብ ለግል ትምህርት ቤቶች የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የሚማሩባቸውን መጽሐፍት በተመጣጣኝ እና በጣም ትንሽ በሚባል ዋጋ ያቀርባል የሚሉት አቶ ዳኘው የግል ትምህርት ቤቶችም ከመንግሥት በትንሽ ዋጋ የሚሸጥላቸውን መፅሐፍ ለተማሪዎቻቸው እንዲሸጡ እና ተማሪዎቻቸው እንዲጠቀሙ የተቀመጠ አቅጣጫ አለ ይላሉ:: የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮም እያደረገ ያለው ይህንን ነው::
እንደ አቶ ዳኘው ገለጻ በግል ትምህርት ቤቶች የሚስተዋለው ሌላኛው ችግር ደግሞ በተለያዩ ቋንቋዎች ትምህርት መስጠት ነው። በመጀመሪያ ደረጃ አንድ ሕፃን በአፍ መፍቻ ቋንቋው የመማር ዴሞክራሲያዊ መብቱ ሳይሆን ሰብዓዊ መብቱ ነው። ሰብዓዊ መብት ደግሞ ማንም የማይገረስሰው መብት ነው::
ሰው በእናት ቋንቋው የመናገር እና የማሰብ መብት አለው:: ይሁን እንጂ የሃገሪቱን ስርዓተ ትምህርት በመጣስ ብዙ ቋንቋዎችን የሚያስተምሩ የግል ትምህርት ቤቶች አሉ:: በዚህ ደረጃ ሕፃናትን ብዙ ቋንቋ እንዲማሩ ማድረግ ፈፅሞ ስህተት ነው:: ነገር ግን ልጆች ከፍ እያሉ ሲሄዱ ለተጨማሪ መግባቢያቸው እና ለተጨማሪ እውቀታቸው ሌሎች ቋንቋዎችን ቢማሩ ጥሩ ነው::
ነገር ግን በዚህ ጉዳይ ላይ ለበርካታ ጊዜ ከወላጆች ጋር ስምምነት ላይ መድረስ አልተቻለም:: ወላጆች የሚያዩት ልጆቻቸው የውጭ ቋንቋ መሸምደዳቸውን ነው:: በዚህም ልጆቻቸው ያወቁ መስሎ ይታያቸዋል:: እውነት ነው ቋንቋ መሳሪያ ነው፤ ነገር ግን ቋንቋን በመሸምደድ አይደለም የልጆች እውቀት ሊገነባ የሚችለው::
ልጆች ያላቸውን ኃይል አዚሁ ላይ ጨርሰው ይሄዳሉ:: በዚህ የተነሳ ልጆች በቀጣይ ትምህርት ለመማር ይከብዳቸዋል:: ይሰላቻሉ:: ይህ ደግሞ በአስተሳሰባቸው እና በዕድገታቸው ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል:: ይሁን እንጂ አንዳንድ ወላጆች ይህንን አምኖ ለመቀበል እንደሚቸገሩ አቶ ዳኘው ይናገራሉ::
ከላይ የተጠቀሱት እና ሌሎች በግል ትምህርት ቤቶች የሚስተዋሉ ችግሮች እንዲቀረፉ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ሲሠራ ነበር፤ አሁንም እየሠራ ይገኛል የሚሉት አቶ ዳኘው፤በዚህም ብዙ ትምህርት ቤቶችን አሽገንም ቀጥተንም እናውቃለን ይላሉ::
ከአሠራር ስርዓት ውጪ በመንቀሳቀስ ከስህተታቸው አልመለስ ያሉ ትምህርት ቤቶችን ከስርዓቱ ውጪ እንዲሆኑ ተደርገዋል:: ነገር ግን አሁንም ችግሩን መቶ በመቶ ማጥፋት ግን አልተቻለም:: ለዚህም እንደዋና ምክንትነት የተጠቀሰው በትምህርት ቢሮ በኩል አልፎ አልፎ የሚታዩ ጉድለቶች ናቸው::
ነገር ግን የሃገሪቱን ስርዓተ ትምህርት አካሄድ ጥሰው ትምህርት ቤቶችን ትምህርት ቢሮው በሚቀጣ ጊዜ ለምንድነው የሚቀጡት የሚል ወላጅም አለ:: ይህ ተገቢ አይደለም:: አንዳንዴ ወላጆች ለልጆቻቸው ከሚሰጠው ትምህርት ይልቅ ክፍያ ያሳስባቸዋል:: ክፍያው አቅም ይጠይቃል እንጂ በልጆች እድገት ላይ የሚያመጣው ነገር የለም::
ነገር ግን የግል ትምህርት ቤቶች ከልጆች አቅም ውጪ የሚሰጡት ትምህርት ነው ሊያሳስባቸው የሚገባው:: ምክንያቱም የትምህርቱ ክብደት እና ቅለት በልጆች እድገት ላይ ከፍተኛ የሆነ ተፅዕኖ ስላለው::
እንደ አቶ ዳኘው ገለፃ፤ ሁላችንም በልጆች አስተዳደግ ላይ የጋራ አስተሳሰብ መያዝ ያስፈልጋል:: በዚህም ሰብዓዊ ሀብቱ መሰላት አለበት:: ሰብዓዊ ሀብቱን ደግሞ የሚያሰላው ትምህርቱ ነው::
ትምህርት ሰብዓዊ ሀብቱን ሊያሰላ የሚችለው ደግሞ ከልጆች እስተዳድግ አኳያ በባለሙያዎች ተጠንቶ የሚሰጥ ስርዓተ ትምህርት እና እሱን ተከትለው የሚወጡ መጽሐፍትን መጠቀም ስንችል ነው:: ነገር ግን ከሕፃንነት ዕድሜ በላይ የሚሰጠው ትምህርት ዜጎችን የሚያቀጭጭ እና ለነገም ዜጎች ተስፋ እንዳኖራቸው የሚያደርግ ስለሆነ በዚህ ጉዳይ ላይ ህብረተሰቡ እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል::
አዲስ ዘመን መጋቢት 17/2013