ትምህርት-ተወዳዳሪነትን ተወዳድሮ ማሸነፍ

የኢትዮጵያ ትምህርት ስርዓት በተለያየ ምክንያት እየተፈተነ ያለ ዘርፍ ነው:: በተለይም ባለፉት ጥቂት አስርት ዓመታት ከጥራት አኳያ ብዙ ጥያቄዎች ሲቀርቡበት ቆይቷል:: ይህንን ክፍተት ለማሻሻል መንግስት ፖሊሲ ከማሻሻል አንስቶ የትምህርት ጥራትን የሚያረጋግጡ በርካታ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ሀገር አቀፍ ፈተናን የሚወስዱ ተማሪዎች የመውደቁ ምጣኔ ከፍተኛ መሆኑን ተከትሎ በርካታ ጥያቄዎች እየተነሱ ነው። ‹‹ለምን በዚህ መጠን ተማሪዎች ፈተናዎችን ማለፍ አቃታቸው?›› የሚሉ ሞጋቾችም ተበራክተዋል:: ከእነዚህ መካከልም የተወካዮች ምክር ቤት አንዱ ነው:: ምክር ቤቱ ‹‹ ለምን ይህንን ያህል ትምህርት ቤቶች ምንም ተማሪ ሳያሳልፉ ቀሩ፤ በምን ምክንያት ተማሪዎች በዚህ ልክ ወደቁ፤ ለምን የግል ትምህርት ቤቶች ከመንግስት ትምህርት ቤት ያነሰ ተማሪዎችን አሳለፉ …ወዘተ›› በማለት ተቋሙን ለሚመራው አካል ምላሽ የሚሹ ጥያቄዎችን ሰንዝረዋል:: በጥናት እንዲለይና ትክክለኛው ምክንያት እንዲያሳውቅ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል::

የተማሪዎች መውደቅ መንስኤ የተለያየ ምክንያት ቢኖረውም አንዱና ዋነኛው ተደርጎ የተወሰደው ግን ጥራትን ለማምጣት ሲባል ወደ ተግባር የተገባበት የአፈታተን ስርዓትን መቀየር እንደሆነ በብዙዎች ይታመናል:: በዚያው ልክም የፈተና ስርዓቱ የተማሪዎች አቅም እንደለየ የሚናገሩ አልጠፉም:: ለዚህም ማሳያው የ2016 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ውጤት ሲሆን፤ የግሉ ከመንግስቱ የተወዳደረበት፤ ውጤት እንደልብ ያልጋሸበበት እንደሆነ በውጤት ትንተናው ታይቷል:: ቀጣይነቱ ሲታይም ውጤቱ ከአምናው የተሻለ ተማሪ ያለፈበት ሆኖ ተገኝቷል:: እንዲያውም በወቅቱ በትምህርት ሚኒስቴር በተሰጠው መግለጫ እንደተባለው፤ የማለፊያ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች ቁጥር ከባለፈው ዓመት ሲነፃፀር በ9ሺህ 114 ተማሪዎች ብልጫ አሳይቷል።

ለሀገር አቀፍ ፈተናው ከተቀመጡ 674ሺህ 823 ተማሪዎች ውስጥ 36ሺህ 409 ወይም 5ነጥብ4 በመቶ የማለፊያው ውጤት ያመጡ ሲሆን፤ ይህም በተፈጥሮ ሳይንስ 28ሺህ 158 ወይም ዘጠኝ በመቶ ያለፉበትና በማህበራዊ ሳይንስ ደግሞ 8ሺህ 251 ወይም ሁለት በመቶ እንዲያልፉ የሆኑበትም ነው።

“በየዓመቱ ለሚኖረው ውጤት መሻሻል መሰረቱ የአፈታተን ስርዓቱ መቀየሩ ነው:: ይህ የፈተና አሰጣጥ አግባብ የሆነውን ተቋም አልያም ተማሪ ለይቷል፤ ብቁዎቹን አበረታትቶ የደከሙትን ደግሞ አቅማቸው ምን ድረስ እንደሆነ አሳይቷል:: ለተሻለ ሥራ እንዲነሱም እድል ሰጥቷል:: በተለይም ኩረጃን ተገን አድርገው የሚንቀሳቀሱ ተማሪዎችን አደብ ያስገዛ ነው::” ሲሉ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ የተናገሩትን ማስታወስ ተገቢ ነው።

“እንዲሁም” ይላሉ ሚኒስትሩ ተማሪዎች በራስ የመተማመን ባህልን እንዲያዳብሩም አድርጓቸዋል:: አቅሙ የሌላቸው ተማሪዎችም አማራጫቸውን እንዲያዩ አስችሏል:: በኩረጃ አልፋለሁ የሚለው አስተሳሰብ ቀርቶ ተማሪዎች አንችልም ብለው ከመቀመጥ ይልቅ ወደ ማንበቡና ለማለፍ ጥረት ወደ ማድረጉ እንዲገቡ መስመር አስይዟል:: ትምህርት ቤቶችም የአምና ውጤታቸው አስተምሯቸው ለተሻለ ነገር መስራት እንዲችሉም ሆነዋል::

በዚህ የፈተና አሰጣጥ አንዱ የተገኘው ውጤት ‹‹ልጆቻችን የግል ትምህርት ቤት ስለተማሩ አይወድቁም፤ በጣም ጎበዞች ይሆናሉ›› የሚለው አስተሳሰብ መቀየሩ ነው የሚሉት ሚኒስትሩ፤ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ከግሎቹ አንጻር የተሻለ አቅማቸውን ያሳዩበት እንደነበርም አብራርተዋል::

በዚህ የፈተና አሰጣጥ ስርዓት ሁለት መልክ ያለው ውጤት እንደታየ የሚገልጹት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ የመጀመሪያው በ2016 የሀገር አቀፍ ፈተና 1ሺህ 363 ትምህርት ቤቶች ምንም ተማሪ እንዳላሳለፉ የታየበት ሲሆን፤ ሁለተኛው በፈተና ነጥረው የወጡ ተማሪዎች እንድናይ መሆናችን ነው ብለዋል:: በዚህም ምንም ላላለፉት ትምህርት ቤቶች ልዩ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ ሲሆን፤ ለተማሪዎቹ ደግሞ ማበረታቻ እንዲሰጥ ሆኗል:: ከተሰጡት ማበረታቻዎች መካከልም ተማሪዎቹ የውጪ የትምህርት እድል እንዲያገኙ፤ የሚፈልጉትን የትምህርት መስክ እንዲመርጡ፤ ትምህርት ቤታቸውም ለእነርሱ የሚመች እንዲሆን የማድረግ ሥራ ተከናውኗል:: ከዚያ ሻገር ሲልም በትምህርት ቁሳቁስና በገንዘብ ጭምር ማበረታቻዎችን እንደያገኙ ተደርጓል:: ይህ ደግሞ ሀገርን በትምህርቱ የማጽናት ሥራ ነውና ቀጣይነት ይኖረዋል ሲሉ አብራርተዋል::

አዎ ጎበዝ ተማሪዎች በብዙ መልኩ መደገፍ ይኖርባቸዋል:: ምክንያቱም ጉብዝና ዝም ብሎ የሚቸሩት አይደለም:: ከፍተኛ ድጋፍን፤ ጥረትንና ትጋትን ይፈልጋል:: በጥረታቸው አንዳንዶች ከክፍል ብቻ ሳይሆን ከትምህርት ቤት አንደኛ ለመውጣት ማበረታቻና ሙገሳን የሚያገኙት፤ ሌሎች ደግሞ ከተማን አልፈው እንደ ሀገር በደረጃ ተለይተው ከፍተኛውን ውጤት በመያዝ አጀብ የሚያሰኙት ከምንም ተነስተው አይደለም:: መምህራን የሚያስተምሯቸውን በአግባቡ ተቀብለው፤ የራሳቸውን የማጥናት ጥበብ ጨምረውበት በሚሰሩት ሥራ ነው::

መምህራን ለሁሉም ተማሪዎቻቸው እኩል ያስተምራሉ፤ እኩልም ይደግፋሉ:: ልዩነቱን የሚያመጣው የተማረው የመቀበል ችሎታና ጥረት ነው:: እናም ከእነዚህ መካከል ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሴቶችና ሕጻናት ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሸለማቸው ሴቶች ይገኙበታል:: እነዚህ ተማሪዎች ከመነሻቸው ጀምሮ ጊዜ ወርቅ ነው፤ የነገን እድል ይወስናል ብለው ሲታትሩ የቆዩ ናቸው:: እነዚህ ውስጥ በመጀመሪያ ያነጋገርናት ተማሪ ያስሚን ከድር አንዷ ስትሆን፤ በመንግስት ትምህርት ቤት የተማረችና ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበች ተማሪ ናት:: ትምህርት ቤቷም ቡልቡላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ይባላል::

ተማሪ ያስሚን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደረጃ ከፍተኛ ውጤት ካመጡት መካከል ስትመረጥ ያመጣችው ውጤት 570 በመሆኑ ነው:: ይህ ደግሞ ትልቅ የሚባለውን እድል አቀዳጅቷት፤ ራስ ገዝነትን በቅርቡ በተሰጠው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንድትገባ እድል አግኝታለች:: እንደሚታወቀው ራስ ገዙ ዩኒቨርሲቲ በሀገር አቀፍ በወጡ የትምህርት ምዘናዎች ብቻ የሚተዳደር አይደለም:: የራሱ የሆኑ የመመዘኛና የመምረጫ ፈተናዎች አሉት:: ከዚህ አንጻርም የራሱን ተማሪዎች ራሱ መርጦና ፈትኖ ያስገባል:: ከዚህ አንጻር እንደ ያስሚን አይነቶች ከፍተኛ ውጤት ያመጡና ያቀረበውን ፈተና ማለፍ የሚችሉ ተማሪዎች ናቸው በመመዘኛ መስፈርቱ መሰረት ዩኒቨርስቲውን መቀላቀል የሚችሉት:: ስለዚህም ያስሚን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅን ተቀላቅላ ትምህርት ጀምራለች::

ተማሪ ያስሚን እንደምትለው፤ ትምህርት በአንድ ጊዜ ጥረት ብቻ የሚሳካ አይደለም:: ሁልጊዜ ትጋትን እና ሥራን ይፈልጋል:: ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ ለትምህርት ትኩረት መስጠትንም ይጠይቃል:: ከዚህ አንጻርም ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ ውጤታማና የደረጃ ተማረ ነበርኩ:: ለዚህ ያበቃኝ ደግሞ በእቅድ መመራቴና ማጥናቴ ነው:: በተጨማረም የትምህርት ክትትሌ ጥሩ ነበር:: እናም ተማሪዎች ውጤታማ ለመሆን መጀመሪያ ማድረግ ያለባቸው በክፍል ውስጥ በአግባቡ ትምህርታቸውን መከታተል ነው:: ከዚያም የተማሩትን በፕሮግራም አቅደው ማጥናት ሲሆን፤ ይህንን ከቤተሰብ ድጋፍ ጋር አጣምረው መጠቀም መቻል ይኖርባቸዋል::

‹‹ጎበዝ ተማሪ ሆኖ መጀመር ቀላል ነው። ለብዙዎች ፈተና የሚሆነው የጀመሩትን የጉብዝና እርከን ቀጣይነት ባለው መልኩ ማስቀጠል ነው›› የምትለው ያስሚን፤ እሷን በዋናነት ለውጤት ያበቃት ግቧን ለማሳካት እስከ መጨረሻው ባላት ቁርጠኝነት መሥራት መቻሏ እንደሆነ ታስረዳለች:: የደረጃ ተማሪ መሆኗም ዛሬ የተጀመረ ሳይሆን ገና ከአንደኛ ክፍል የጀመረ እንደሆነ ትናገራለች::

ለተማሪ ትርፍ የሚባል ጊዜ እንደሌለና እያንዳንዱ ጊዜ ለትምህርት የሚውል እንደሆነ የምታስረዳው ተማሪ ያስሚን፤ ያልተቋረጠ የቤተሰብ ድጋፍና እንክብካቤ ማግኘት ለውጤታማነት እንደሚያበቃ ትናገራለች:: አክላም የቤተሰብ ድጋፍ ብቻ በቂ እንዳልሆነ ታነሳለች:: በተለይም ለሴቶች ሁሉም ደጋፊ መሆን እንዳለበት ትገልጻለች:: ምክንያቷ ደግሞ ሴቶች በትምህርት ቤት ብቻ ሳይሆን በማህበረሰቡ ጭምር ጫና የሚፈጠርባቸው መሆናቸው ነው:: እናም ማህበረሰቡ በአይነት ብቻ ሳይሆን በአስተሳብም ጭምር በርቱ ሊላቸው ይገባል ትላለች:: አቅም እንዳላቸው ዘወትር የሚነግራቸው ሰው ካገኙ ደግሞ የተሻለ ተማሪ መሆን እንደሚችሉም ራሷን አብነት አድርጋ ትናገራለች::

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶችን ሕጻናት ቢሮ ያደረገው ተግባር ለቀጣይ ስራቸው ብርታት እንደሚሰጣት የምትገልጸው ተማሪ ያስሚን፤ ድጋፉ የበለጠ እንድንሰራና ለሀገራችን ኩራት እንድንሆን ከማስቻሉም በላይ የቤት ስራ የተሰጠበት ነው ስትልም አብራርታለች:: በተለይ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ያደረገው እውቅናና ድጋፍ በመማር ማስተማሩ ሂደቱ ችግር እንኳን ቢገጥመን ከኋላችን ደጀን እንዳለ የሚያሳይ ነውና እንዲህ አይነት ድጋፎች ለሌሎችም የሚደረግበትና የሚጠናከሩበት ሁኔታ ቢመቻች መልካም እንደሆነ ጠቁማለች::

እንደ ያስሚን ሁሉ በአዲስ አበባ ሴቶችና ሕጻናት ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የተሸለመችውና የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናውን 533 ያመጣችው ሌላኛዋ ተማሪ ስም ረተመድህን ሲሳይ ትባላለች። ከፍተኛ ውጤት በማምጣቷ የተነሳ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅን ከተቀላቀሉት ጎራ ተመደባለች:: ትምህርት ቤቷ እንደ ያስሚን ሁሉ የመንግስት ሲሆን፤ ቡልቡላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው::

ስምረተመድህን ‹‹ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመግባቴ እጅግ ደስተኛ ነኝ:: ምክንያቱም አቅሜን የሚመጥን ትምህርት አገኛለሁ ብዬ አስባለሁ:: በተጨማሪም ለተሻለ ትምህርት እንኳን ልወዳደር ብል ሰፊ አማራጭን እንዳገኝ ይረዳኛል:: ከሁሉም በላይ ደግሞ የዩኒቨርሲቲ ትምህርት የራስን ጥረት የሚጠይቅ፤ ብዙ ማንበብን የሚፈልግና ቴክኖሎጂውን መጠቀም ግድ የሚል በመሆኑ መረጃ በቀላሉ እንዳገኝና የተሻለ ትምህርት እንድቀስም ያግዘኛል:: ስለሆነም ሌሎች ተማሪዎችም ይህንን እድል ለማግኘትና እንደእኛ ተመራጭ እንዲሆኑ በርትተው ማጥናት አለባቸው›› ትላለች::

አሁን ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ጉብዝና ብቻውን በቂ አይደለም:: ዘመኑን የሚመጥን መረጃ አነፍናፊ መሆን ይጠይቃል:: በተለይም እንደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን ቃል በቃል የሚያስተምሩበት ስላልሆነ ቀድሞ ማንበብ፤ ያልገባን መጠየቅና የተለያዩ አማራጮችን ተጠቅሞ እውቀትን ማጎልበት ይገባል:: ተወዳዳሪነትን ተወዳድሮ ማሸነፍ ካልተቻለ በቀላሉ ጉብዝናን ወይም ውጤታማነትን ማስቀጠል እንደማይቻልም ታስረዳለች::

ተማሪ ስምረተመድህን እንደምትለው፤ አሁን ላይ ዩኒቨርሲቲ ስንገባ በቀጥታ የፈለግነውን የትምህርት መስክ አንመርጥም:: ይህ ደግሞ ከ12ኛ ክፍሉ ባልተናነሰ መልኩ የቤት ስራ እንዳለብን የሚነግረን ነው:: ስለዚህም በርትቶ ማጥናትና የምንፈልገውን ትምህርት ክፍል ማግኘት ይኖርብናል:: ሁልጊዜ አንባቢና ለትምህርታችን ቅድሚያ የምንሰጥ መሆንን ይጠበቅብናል:: እኔም ስለገባሁ ብቻ ሳይሆን ከገባሁ በኋላም መስራት ስላለብኝ ነገን አቅጄ እየሰራሁ እገኛለሁ::

‹‹ተማሪዎች ውጤታማነታቸውን ለማስቀጠል እችላለሁ፤ አቅም አለኝን ለውስጣቸው መንገር ይኖርባቸዋል:: ተረጋግተው ፈተናዎችንም መስራት ይገባቸዋል:: ከዚህ አንጻር የእኔ እቅድ በተፈጥሮ ሳይንስ ስር ያሉ ሁለት የትምህርት መስኮችን ማግኘት ነው:: እነዚህም ኮምፒውተር ሳይንስ ወይም ሶፍት ዌር ኢንጅነሪንግ ናቸው:: ይህንን ደግሞ አሳካዋለሁ:: ምክንያቱም ትናንት ገና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እያለሁ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መግባትን እመኝ ነበር:: ሁኔታዎች እየጠበቡና የሚወድቀው ተማሪ እየሰፋ ቢመጣም ተስፋ ግን አልቆረጥኩም:: በዚህም ህልሜን አሳክቸዋለሁ:: አሁንም ይህንን አደርገዋለሁ:: ለዚህ ደግሞ ሌት ተቀን እሰራለሁ፤ እየሰራሁም ነው›› ትላለች::

ስምረተመድህን በመጨረሻም ስለተደረገላት ድጋፍ አመስግና በዩኒቨርሲቲ ትምህርቷ የተሻለ ውጤት ለማምጣት እንዳበረታታትና ነገ የእነርሱን ፈለግ የሚከተሉ ሴት ተማሪዎችን ጠንክረው እንዲሠሩ አስተማሪና የሚያበረታታ መሆኑን ጠቅሳ፤ ቀጣይነት ቢኖረው መልካም ነው ስትል አስተያየቷን ለግሳለች::

ከፍተኛ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት አምጥተው ማበረታቻ የተሸለሙ ተማሪዎች ፤

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You