የቴክኖሎጂ አብዮት

የዘመን ተፅዕኖን ማምለጥ አይቻልም። ቴክኖሎጂ እኛ ባንፈልገው እንኳን ዓለም ከፈለገው፣ አብዛኛው ሰው ከተጠቀመው፤ ተፅዕኖው የግድ ይነካናል።

የአንደኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ የማስታውሰው፤ በቤተሰባችን ያጋጠመ አንድ ገጠመኝ እንደ ምሳሌ ልጠቀም። ዘመኑ በ1990ዎቹ መጨረሻ አካባቢ ነው። በዚህ ወቅት በአካባቢያችን ስልክ ያለው ሰው አልነበረም። በአቅራቢያችን የምትገኝ አንዲት የገጠር ከተማ ውስጥ አንድ ለእናቱ የሆነ የመስመር ስልክ ነበር። ይህ ስልክ ከስድስት ቀበሌ በላይ የሆኑ ነዋሪዎች በክፍያ የሚጠቀሙበት ነው። ሩቅ ካለ ወዳጅ ዘመድ ጋር የሚገናኙበት ነው። አንገብጋቢ ጉዳይ ያለውም፤ አስማት የሚመስለውን ቴክኖሎጂ ለማየት የሚፈልገውም እኩል ይሰለፋሉ። ትንሽ ከተማ ቀመስ የሆኑት ደግሞ፤ ስልክ ተዓምር በሆነባቸው ነዋሪዎች ይገረማሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ አንድ የቤተሰብ አባል ለሕክምና ወደ አዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል መጣ። ሕመሙ ድንገተኛ ስላልሆነ ወረፋ መያዝ የግድ ነበር። አልጋ ለማግኘት በወራት የሚቆጠሩ ጊዜያት መጠበቅም የግድ ሆነ።

ከክፍለ ሀገር የሚመጡ ሰዎችን ለወራት ያህል አዲስ አበባ ውስጥ ሆናችሁ ወረፋ ጠብቁ ማለት ችግር ነው፤ ወጪውን አይችሉትም። ለዚህ ችግር የሆስፒታሉ መፍትሔ፤ ወረፋ ጠባቂዎች ስልክ ሰጥተው መሄድና ወረፋ ሲደርሳቸው እንዲደወልላቸው ማድረግ ሆነ። ‹‹ስልክ ስጡ›› ሲባል የእኛ ሰዎች ከየት ያምጡት? 1990ዎቹ መጨረሻ አካባቢ ደግሞ በብዙ የገጠር ከተሞች ጭምር የሞባይል ስልክ አገልግሎት የተጀመረበት ነው። እንዳለመታደል ሆኖ በወቅቱ የእኛ አካባቢ (ሌሎች የገጠር አካባቢዎችም ይኖራሉ) የሞባይል አገልግሎት ተጠቃሚ አልነበረም።

‹‹ኧረ ስልክ የለንም!›› የሚል አቤቱታ አቀረቡ። የሆስፒታሉ መልስ ግን፤ ለጊዜው አሠራሬ ይሄው ነው፤ ያላችሁ ሁለተኛ አማራጭ እዚሁ ሆኖ መጠበቅ ነው… የሚል ነበር።

እርግጥ ነው ይህ የሆስፒታሉ አሠራር የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ አይደለም። በዚያን ወቅት እንኳን ገበሬ የከተማ ነዋሪ የሚባለው ራሱ ሁሉም የሞባይል ተጠቃሚ ነው የሚባል አልነበረም። ዳሩ ግን ለጊዜው አማራጭ አልነበረውም። ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ‹‹ሪፈር›› ተብሎ የሚመጣውን ታካሚ ሁሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ የማስተናገድ አሠራር ካልዘረጋ በስተቀር በጊዜው በነበረው አቅም ማድረግ የሚችለው ያንን አሠራር ብቻ ነበር።

ምንም ማድረግ የማይቻል ሆነና፤ ያንኑ አንድ ለእናቱ የሆነ የአካባቢያችንን የመስመር ስልክ ሰጥተው ተመለሱ። ያ ስልክ ደግሞ 24 ሰዓት የማይቦዝን ስለሆነ መስመሩን ማግኘት አይቻልም። ብዙ ጊዜ ለመደወል ብቻ እንጂ ለመቀበል አያገለግልም። ለመቀበል የሚጠቀሙበት በአካባቢው ተፅዕኖ ያላቸው (ፐብሊክ ሊደር የሚባሉት ዓይነት ማለት ነው) ሰዎች ናቸው። እነርሱ ግን ‹‹ሰው ይፈልጋችኋል›› ተብለው ይነገራሉ። በሌላ በኩል፤ እዚያው ከተማው ውስጥ ስለሆኑ ‹‹ስልክ ይፈልጋችኋል›› ብሎ ለመንገርም ቅርብ ናቸው። የእኛ ቤተሰቦች ግን ለዚህኛው ስልክ ራሱ ሩቅ ናቸው። ተሳክቶ እንኳን ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ቢደወል፤ ሊሰሙ የሚችሉት ቅዳሜ ቀን ለገበያ ሲሄዱ ነው።

ይህን እንደማሳያ የተጠቀምኩት የቴክኖሎጂን ተፅዕኖ ለመግለጽ ነው። ከተፅዕኖው ማምለጥ አይቻልም። ዓለም እና አብዛኛው አካባቢ ከተጠቀመው፣ ወደ መደበኛ የአሠራር ደንብ ይሄዳል። ስለዚህ የማይጠቀሙ ሰዎች ይጎዳሉ ማለት ነው። አዲስ አበባና ሌሎች የክልልና የዞን ከተሞች የሞባይል ተጠቃሚ መሆናቸው ሆስፒታሉ የአልጋ ወረፋ ለሚደርሳቸው ሰዎች ስልክ መደወልን አሠራር አደረገው ማለት ነው። የአሠራር ደንብ ከሆነ ደግሞ በግል ፍላጎትና በራስ ስሜት ብቻ መሄድ አይቻልም።

ለምሳሌ፤ አዳዲስ የማኅበራዊ ሚዲያ ዓይነቶች በመጡ ቁጥር ‹‹እኔ ይሄን አልወድም›› የሚሉ ሰዎች ይኖራሉ። ያ አልወደውም ያሉት ነገር ግን ከዓመታት በኋላ መደበኛ አሠራር ይሆናል። ከአሥር ዓመት በፊት ፌስቡክ ይወገዝ ነበር። አሁን ግን የሚዲያ ተቋማት ሳይቀር ወደ ዲጂታሉ ለመሄድ ተገደዋል። ትልልቅ ተቋማት ለማኅበራዊ ሚዲያ ራሱን የቻለ የሥራ መደብ አውጥተው ባለሙያ ይቀጥራሉ።

ኢሜል ገና አዲስ በነበረበት ዘመን ብዙ ሰዎች ከፖስታ እና ከደብዳቤ መላቀቅ ከብዷቸው ነበር። ኢሜል የጥቂት ሰዎች ብቻ ነበር፤ እየቆየ ሲሄድ መደበኛ አሠራር ሆነ። ማስታወቂያዎች ሲወጡ የኢሜል አድራሻ ማስቀመጥ የግድ ሆነ። መልዕክቶች በኢሜይል እንዲላኩ ተደረገ።

ቀጥሎ እንደ ቴሌግራም ያሉ አማራጮች ሲመጡ ብዙ ሰዎች (በተለይም ትልልቆች) አይጠቀሙትም ነበር። በለመዱት ኢሜል የመሄድ ፍላጎት ነበራቸው። እየቆየ ሲሄድ ግን እነሆ ቴሌግራም የብዙ ተቋማት የመልዕክት መቀበያ አማራጭ ሆኗል።

ዛሬ ላይ አንድ ሰው ምንም ዓይነት የዲጂታል አማራጭ አልጠቀምም፤ መልዕክቴን ወይም ማመልከቻዬን በወረቀት ተቀበሉኝ ቢል ተቀባይነት ላያገኝ ይችላል። ምክንያቱም የዲጂታል አማራጮች የመደበኛ አሠራር አይነት ሆነዋል ማለት ነው። ከ30 እና 40 ዓመታት በፊት ደብዳቤ የሚያነብ ሰው ብርቅ ነበር። እነሆ በዚያን ጊዜ ትልቁ ቴክኖሎጂ፣ ትልቁ መሠልጠን፣ ትልቁ ቅልጥፍና… መልዕክት በደብዳቤ መለዋወጥ ነበር። ዛሬ ግን እንኳን ደብዳቤ ኢሜል ራሱ ልማዳዊ እየሆነ ነው።

በዚህ 10 ዓመት ባልሞላው ጊዜ ውስጥ እንደ ፌስቡክ ያሉ የጽሑፍ መልዕክት የሚነበብባቸው ፕላትፎርሞች ልማዳዊ እየሆኑ ነው፤ ባዶ ሊቀሩ ነው። አሁን ላይ ብዙ ወጣቶች ወደ ቲክቶክ እየሄዱ ነው።

ቲክቶክ ገና እንደተጀመረ ‹‹ቢዘጋ›› እስከማለት ድረስ ወቀሳዎች ነበሩ። ለዚህ ምክንያት የሆነው ደግሞ ብዙ የእብደት የሚመስሉ ነውር ነገሮች የሚታዩበት ስለሆነ ነው። ክፋቱ ደግሞ የሚታይ ነገር ስለሆነ የንባብ ልምድ እንኳን የሚጠይቅ አይደለም። ማንም ሰው ሊያየው የሚችል ነው።

ይሄ ሁሉ ሆኖ ግን አሁን አሁን እየተለመደ መጥቷል። እየተለመደ ከመምጣቱ የተነሳ ትልልቅ ሰዎች ሁሉ የሚጠቀሙት ሆነ። እንደ መዝናኛ ብቻ ሳይሆን እንደ አንድ የመረጃ አማራጭ መታየት ጀመረ።

አሁን ላይ ብዙ ባለሙያዎች በቲክቶክ ማብራሪያ እየሰጡ ነው። የሕክምና ባለሙያዎች፣ የሕግ ባለሙያዎች፣ የሥነ ልቦና ባለሙያዎች፣ የቋንቋ ባለሙያዎች… በቲክቶክ ሙያዊ ማብራሪያ ይሰጣሉ። ብዙ ወጣቶች የተለያዩ ቴክኒካል ነገሮችን አጠቃቀም ያሳያሉ። የተለያዩ ተሰጥዖዎቻቸውን ያሳያሉ። በጽሑፍ ይነበቡ የነበሩ የተለያዩ የአሠራር ቅደም ተከተሎችን (ማኑዋል) በማሳየት ማስተማር ተችሏል።

እነዚህ ባለሙያዎች ፌስቡክ ላይ ከመጻፍ ይልቅ በቲክቶክ ለመናገር የተገደዱት አብዛኛው ታዳሚ ያለው ቲክቶክ ላይ ነው በማለት ነው። ጽሑፍ እንኳን እየጻፉ ቲክቶኮች ላይ ማሳየት በተደጋጋሚ የምናየው ነው። የጽሑፍ የጽሑፍ እኮ ፌስቡክ ላይ መጻፍ ይቻል ነበር። እዚያ ብዙ ታዳሚ አያገኝም በሚል እሳቤ ነው። ወዲህ ደግሞ በተለይ ለቴክኒካል ነገሮች ማሳየት የሚያስችል መሆኑ ነው። ከዩትዩብም በተሻለ ለአጫጭር ነገሮች ምቹ ሆኖ ስለተገኘ ነው። ለንባብ ባሕል መዳከም ያለውን አሉታዊ ተፅዕኖ በሌላ ቀን እንመለስበታለን።

በአጠቃላይ የቴክኖሎጂ አብዮት ፈለግነውም አልፈለግነውም ተፅዕኖው ይደርሰናል።

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ህዳር 18/2017 ዓ.ም

 

 

 

Recommended For You