ትርክት ያበላሸው የትዳር ክብር

ሰሞኑን ማኅበራዊ ገጾች ላይ አንድ ጽሑፍ ወደ ፎቶነት ተቀይሮ (ስክሪን ሻት ተደርጎ) ሲዘዋወር ተመለከትኩ። ጽሑፉ እንዲህ ይላል።

‹‹ከምታዘወትሪበት መናፈሻ አፈር ዘግኜ ቤቴ ወሰድኩ። ከረገጥሺው ባረገልኝ!››

ይህ ጽሑፍ ሲዘዋወር የነበረው በቀልድ ነበር። የቀልዶች ይዘት፤ ይህን የተናገረው ሰው ምን ያህል ውሸታም እንደሆነ፣ እንዴት ማጋነን እንደቻለበት፣ በተለይ ሴቶች ደግሞ፤ ወንዶች ምን ያህል ውሸታምና አስመሳይ እንደሆኑ በቀልድ መልክ ቢሆንም እየተገረሙ ሲገልጹት ነበር።

የጻፈው ሰውዬ የምሩን ይሁን እየቀለደ አይታወቅም፤ የማኅበራዊ ገጾች ባሕሪ መዝናኛ እና ጨዋታ ስለሚበዛበት ለጨዋታ ብሎ ሊሆንም ይችላል። ምናልባት ደግሞ የምሩንም ሊሆን ይችላል።

ለማንኛውም ይህ ጽሑፍ መነሻ ሃሳቤ እንጂ የትዝብቴ ዋና ጉዳይ እሱ አይደለም። ለጨዋታ እና ለቀልድ ሊሆን እንደሚችል ጠፍቶኝም አይደለም። ወይም ይቺ አንዲት ጽሑፍ ጠቅላላውን ትገልጻለች ብዬ አይደለም።

ልብ መባል ያለበት ነገር ግን፤ ፍቅር እና ትዳርን በተመለከተ የሚቀለዱ ቀልዶች ትርክት እያበላሹ ነው። የፍቅርን እና የትዳርን ክብር እያጠለሹ ነው። ሰዎች ትዳርን እንዲፈሩ እያደረጉ ነው። ‹‹በዚህ ዘመን ፍቅር የለም›› የሚል እውነት የሚመስል ሐሰተኛ ትርክት እየተገነባ ነው። ብዙ ሰዎች በዚህ ዘመን ፍቅር የለም እያሉ እያመኑ ነው፤ ብዙ ወጣቶች ትዳርን እንዲፈሩ እያደረገ ነው።

ብዙ ጊዜ ትዳር ላይ የሚቀለዱ ቀልዶችን ካያችሁ፤ ‹‹ከማግባት በፊት እና ከማግባት በኋላ…›› እየተባለ፤ ወንዱ ሲያገባ በጣም ተጎሳቁሎ፣ ከስቶ እና መንምኖ፤ ሴቷ ደግሞ በጣም ተመችቷት የሚመስሉ ቀልዶች ይቀለዳሉ። ይሄ ማለት ትዳር ለወንዶች ጎጂ፣ ጠቀሜታው ለሴቶች ብቻ እያስመሰለው ነው ማለት ነው። ልብ ብለን ካየነው ግን፤ እንዲያውም ወንድን ሰው የሚያደርገው ትዳር ነው። ሴት ልጅ ብቻዋን ሆናም ቢሆን ራሷን ትጠብቃለች። ወንድ ልጅ ግን ቤቱ እንኳን ሥነ ሥርዓት የሚኖረው ትዳር ሲኖረው ነው።

አሁንም ልብ በሉልኝ! ቀልዶች ቀልድ መሆናቸው ጠፍቶኝ አይደለም። ወይም ቀልድ አያስፈልግም እያልኩ አይደለም፤ ችግሩ ግን እውነት የሚመስል የተዛባ ትርክት እያሰረፁ መሆኑ ነው። ሰዎች የምርም እንደሚቀለደው እየመሰላቸው ነው።

‹‹በዚህ ዘመን ፍቅር የለም›› የሚባለው ነገር ለብዙዎች እውነት መስሎ እየታየ ነው። ፍቅር ዘመን የሚወስነው አይደለም፤ ፍቅር ዝግመተ ለውጥ የለውም። ፍቅር በሰው ልጅ ስሜት ውስጥ የሚኖር ነው። ዓይነቱና ሁኔታው ሊለያይ ይችላል እንጂ የሰው ልጅ ስሜት እስካለ ድረስ ፍቅር ይኖራል።

ለምሳሌ፤ መግቢያ ላይ የተጠቀምኩትን የልጁን አባባል እንየው። ‹‹ከምታዘወትሪበት መናፈሻ አፈር ዘግኜ ወሰድኩ›› የሚለውን ስናይ የተጋነነ ይመስላል። ወንድም ይሁን ሴት ሲያፈቅሩ ግን እንዲህ ነው። እንዳልኳችሁ ልጁ ምናልባትም ሲቀልድ ሊሆን ይችላል፤ እውነታው ግን እንደተባለው ነው። ወንድ ልጅ ሲወድ፤ የወደዳት ልጅ የረገጠችው አፈር ትርጉም ይሰጠዋል። የነካችው ግዑዝ ነገር ሁሉ ጣዕም አለው። እንኳን የተቃራኒ ፆታ ፍቅር ይቅርና፤ በሆነ ዝና የምናደንቀው ሰው ራሱ እንደዚህ ያደርጋል። ዝነኛ የእግር ኳስ ተጫዋቾች አፍንጫቸውን ያጸዱበት ሶፍት በጨረታ ተሸጧል። ከአፈር እና ከአፍንጫ ፅዳት የቱ ይከብድ ነበር? አፈር አይሻልም ወይ? ለዚያውም የተቃራኒ ፆታ ፍቅር ሲሆን ደግሞ አስቡት!

ምነው ባደረገኝ የደጅሽን አፈር

አንቺ ስትረግጪኝ እኔ እንድፈራፈር

የሚል የሕዝብ የቃል ግጥም አለ። ይህ ቃል ግጥም በታዋቂ ዘፋኞች ሳይቀር ተዘፍኗል። ይህን ዘፈን የሰማ ፍቅር ያልያዘው ሰው የተጋነነ ሊመስለው ይችላል። ይህን ግጥም የፈጠረው ሰውዬ ግን ይሄ ነገር ትዝ ያለው ስሜቱ ቢፈጠርበት ነው። ሌላ የሚያገኝባት ዕድል ሲያጣ፤ ‹‹ምነው አፈር በሆንኩና በረገጠችኝ›› ብሎ አስቦ ይሆናል።

ምነው ባደረገኝ የደጇን ገለባ

ልቅምቅም ልቅምቅም አርጋኝ እንድትገባ

የሚል የሕዝብ የሥነ ቃል ዘፈንም አለ። በገጠሩ የሀገራችን ክፍል (በተለይም በድሮው ጊዜ) ለማገዶነት የሚያገለግለው እንጨት እና ጭራሮ ነበር። ማታ ማታ የምድጃ ዳር የእሳት ማንደድ ምሽት ላይ እሳቱ ሊጠፋ ሲል፤ ወይም ሌሎች እንጨቶችን ማቀጣጠያ ገለባ ይለቀማል። ገለባ ለቅማ እንድታመጣ የምትታዘዘው ደግሞ ሴቷ ልጅ ናት። የሚወዳትን ልጅ ማግኘት የሚችልበት ዕድል ያጣ አፍቃሪ በእጆቿ ትነካካው ዘንድ ገለባ መሆን ያምረዋል ማለት ነው።

አብሬሽ አድሬ ሲነጋ ልሙት

ለሞት አይደለም ወይ የተፈጠርኩት!

የሚል በብዙዎች ዘንድ የሚታወቅ ሥነ ቃልም አለ። ብቻ በአጠቃላይ ሰው ለሚወደው ምንም ነገር ይሆናል። ነገርየው በጥበብ ሲሆን ምናልባት የተጋነነ መስሎ ሊሆን ይችላል እንጂ፤ አብዛኛው እኮ በተግባርም የታየ ነው። የሚወዱትን ለማግኘት የሕይወት መስዋዕትነት ይከፈላል።

ይህ ሁሉ ባለበት ግን፤ ‹‹በዚህ ዘመን ፍቅር የለም›› የሚለው ትርክት የፍቅርን እና የትዳርን ክብር እያወረደ ነው። የፍቅርን ኃይል እያኮሰሰ ነው። ሰዎች ተጠራጣሪ እንዲሆኑ እያደረገ ነው።

ይመስለኛል እንዲህ ዓይነት የተስፋ መቁረጥ ስሜቶች የተፈጠሩት የሚወዱትን ካለማግኘት ነው። ፍቅር ማለት ደግሞ የግድ የሚወዱትን ማግኘት ብቻ ላይሆን ይችላል። የምትወደውን ወንድ ያጣች፣ ወይም የሚወዳትን ሴት ያጣ፤ ‹‹ምን ፍቅር አለና ነው!›› ሊሉ ይችላሉ። ልብ ማለት ያለብሽ ግን፤ አንቺ ነበርሽ እንጂ የምትወጂው እሱ አልነበረም የሚወድሽ! አንተ ነበርክ እንጂ የምትወዳት እሷ አልነበረችም የምትወድህ! የወደደሽ መስሎ አታለለሽ ማለት ይወድሽ ነበር ማለት አይደለም፤ የሚወድ አያታልልም። የወደደችህ መስላ አታለለችህ ማለት ትወድህ ነበር ማለት አይደለም።

ብዙ ጊዜ የምንሸወደው ነገር፤ የምንወደው ሰው ላይ ያለው የማታለል እና የማጭበርበር ባሕሪ አይታየንም። የምንወደውን ሰው ስንከተል፤ የሚወደንን ሰው ልብ አንለውም። እንዲያውም ይህንን ሃሳብ የሚገልጽና ጥቅስ መሆን የሚችል አንድ ገላጭ ጽሑፍ እዚያው ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አይቻለሁ።

‹‹በእኔና ባንቺ መካከል ያለው ልዩነት፤ እኔ ለአንቺ ብዬ ሌሎችን እተዋለሁ፤ አንቺ ደግሞ ለሌሎች ብለሽ እኔን ተውሽኝ›› የሚል ነው።

በነገራችን ላይ ማኅበራዊ ሚዲያ ማለት ሕዝብ ማለት ነው። ለምሳሌ፤ ሥነ ቃሎች ግለሰባዊ ባለቤት የላቸውም። ‹‹የሕዝብ›› ተብለው ነው የሚገለጹት። አንድ ታዋቂ ዘፋኝ ሲዘፍነው ምናልባትም የእሱ ሊመስል ይችላል፤ ያ የቃል ግጥም ግን ቴፕ እና ካሴት የሚባል ነገር የማያውቅ ገበሬ የሚያንጎራጉረው ነው። ሥነ ቃል ‹‹የሕዝብ›› የሚባልበት ምክንያት የማን እንደሆነ ስለማይታወቅ ነው። መቼም ሁሉም ሕዝብ አንድ ላይ ሆኖ አይፈጥረውም፤ ዞሮ ዞሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ግጥሙን የሚገጥመው አንድ ሰው ነው። ዳሩ ግን የእገሌ ተብሎ ስለማይሰነድ እና ሁሉም እየተቀባበለ ስሜቱን ስለሚገልጽበት ‹‹የሕዝብ›› ይባላል።

ማኅበራዊ ሚዲያም ልክ እንደዚህ ነው። ምንም እንኳን ማኅበራዊ ሚዲያ ምንጭ ለመጥቀስ ምቹ ቢሆንም፤ ዳሩ ግን ሰዎች እየተቀባበሉ ስሜታቸውን ይገልጹበታል። አንድ ጥበበኛ ሰው የተናገረው ነገር፤ ልክ እንደ ጥቅስ ሆኖ ይዘዋወራል፤ መጨረሻ ላይ የማን እንደነበር ባለቤቱ ይጠፋል። ይህን በተመለከተ ሳምንት በዝርዝር እንመለስበታለን።

ወደ ዋናው ጉዳያችን ስመለስ፤ ፍቅር እና ትዳር ላይ የሚደረገው የማጣጣል ዘመቻ ሐሰተኛ ትርክት እየገነባ ነው። ፍቅር ዘመን የሚሽረው አይደለም፤ እንደ ባሕል ዕቃዎች ‹‹ድሮ ቀረ›› የሚባል አይደለም። ፍቅር ከሰው ልጅ ሕይወት ጋር የሚቀጥል ነው። እናንተ ያፈቀራችሁትን ስላላገኛችሁ፤ ዘመኑ ፍቅር የለውም ማለት አይደለም፤ አንተ ወይም አንቺ ስለተከዳችሁ ሁሉም ከሃዲ እና አጭበርባሪ ነው ማለት አይደለም።

ይባስ ብሎ ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዋናዎቹ ሚዲያዎች ሳይቀር መፋታትን እንደ ኖርማል (መደረግ ያለበት ነገር) የሚያስመስሉ፣ አርዓያ መሆን ሲገባቸው ፍቺን የሚያስተዋውቁ ታዋቂ ሰዎችም እየታዩ ነው።

ፍቅር አለ! ትዳርም ክቡር ነውና የማጠልሸት ትርክት እንዳይገነባ እንጠንቀቅ!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ህዳር 14/2017 ዓ.ም

Recommended For You