ለምለም መንግሥቱ
እንደ ውሃ፣ ማዕድንና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ነገሮች ሁሉ የአየር ጠባይ ከፍተኛ የሆነ የተፈጥሮ ሀብት መሆኑን ስንቶቻችን እንገነዘብ ይሆን? ሀብቱን መሠረት አድርገን ከአረንጓዴ ልማት ጋር በማስተሳሰር ሃሳብ እንዲሰጡኝ የጠየኳቸው የብሄራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ክንፈ ኃይለማርያም እንደነገሩኝ የአየር ጠባይ ለአንድ ሀገር ዕድገት መሠረታዊ የተፈጥሮ ሀብት ሆኖ ጥቅም ላይ ይውላል። ወይም ያገለግላል። ሀብቱን በአግባቡ ተገንዝቦ ለግብርና ፣ለጤና ለትምህርትና ሌሎችም በማዋል ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን ማግኘት ይቻላል።
የአየር ጠባይ ጥቅም ላይ ሲውል በበቂ ዕውቀት መሆን ይኖርበታል። አሊያ አንዳንድ ጊዜ የአየር ጠባይ ዋልታ ረገጥ ሆኖ አደጋ ሊያደርስ ይችላል። ለአብነትም እንደ ጎርፍና ድርቅ የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ። በመሆኑም በሚደርሰው ጉዳት የሚፈጠረውን የህይወትም ሆነ የንብረት ቀውስ መታደግ እንዲቻል መሥራት ይጠበቃል። አሉታዊ ተጽዕኖ መቀነስ ከተቻለ ግን ጥቅሙ ከፍተኛ መሆኑን መገንዘብ ይገባል።
ከአረንጓዴ ልማት አኳያ ደግሞ የአየር ጠባይ ስላለው ግንኙነት አቶ ክንፈ እንዳብራሩት የአየር ጠባይ ከውሃ፣ ከአየር፣ ከዕፅዋት፣ ከበረዶና ከመሬት መስተጋብር የሚፈጠር በመሆኑ የዕፅዋት መጠን ሲጨምር አስተዋጽኦው ከፍተኛ ይሆናል። ተራሮች ሲራቆቱ ዝናብ እንዳይኖር ያደርጋል። መጠነኛ የሆነ ዝናብ ቢገኝ እንኳን ወደ መሬት እንዲሰርግ በማድረግም ተጽዕኖው ይገለጻል። በመሆኑም የአረንጓዴ ልማቱና የአየር ጠባይ አይነጣጠሉም።
ዘንድሮ በኢትዮጵያ ለ40ኛ፣ በዓለም ለ71ኛ ጊዜ ‹‹ውቅያኖስ የእኛ፣ የአየር ጠባይና የአየር ሁኔታ›› የተከበረው የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ቀን መሪ ቃሉ ከዚሁ ጋር ተያያዥነት አለው።
ስለ ዕለቱ መሪ ቃል አቶ ክንፈ እንዳስረዱት ውቅያኖስ ከፀሐይ ቀጥሎ የአየር ሁኔታና ጠባይን በመበየን ትልቅ አስተዋጽኦ አለው። ከባቢ አየር ኃይል የሚያገኘው ከፀሐይ ነው። ፀሐይ ደግሞ ያንን ኃይል ተቀብሎ ወደ የአየር ሁኔታና የአየር ጠባይ ሂደት ውስጥ ውቅያኖስ ካለው ስፋትና ብዙ ውሃ አምቆ ከመያዝ አቅም ጋር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው። ከዓለም ሶስት አራተኛው በውሃ የተሸፈነ ሲሆን፣ ሌላው ከመሬትና ከዕፅዋት አኳያም ውሃን ለማወቅ የሚያስፈልገው ሙቀት ወይንም ኃይል እንዲሁ ከፍተኛ ነው። በአጠቃላይ ውቅያኖስ ለአየር ሁኔታና ጠባይ አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነው።
ክረምት፣ በጋና በልግ ኤሊኖ በመባል በስፋት በሚታወቀው ተጽዕኖ ሥር ናቸው። ኤሊኖ ከኢትዮጵያ በጣም የራቀ ቢሆንም ከመካከለኛው ፓስፊክ የውሃ አካል መሞቅና መቀዝቀዝ መሆኑን አመላካች ነው። ለአብነትም የውሃ አካሉ ሲቀዘቅዝ ለክረምት ከሆነ ጥሩ ዝናብ ያመጣል። ሲሞቅ ደግሞ ለክረምት ከሆነ ደረቅ ያመጣል። በበጋው በተቃራኒው ማለት ነው።
በአጠቃላይ በአየር ጠባይ ለውጥ ምክንያት ውቅያኖሶች ባህሪያቸው እየተቀየረ ነው። ምክንያቱም ከፍተኛ ትነት ሲኖር ጨዋማነታቸው ይጨምራል። በሌላ በኩል ደግሞ በበረዶ መቅለጥ ምክንያት የባህር ወለል እየጨመረ መጥቷል። በመሆኑም የውሃ አካላት፣ የአየር ሁኔታና የአየር ጠባይ የተያያዙ ናቸው።
ኤጀንሲው የሀገሪቱን መልክዐምድርና አቀማመጥ የሚወክል ጣቢያ በሁሉም አካባቢዎች በማቋቋም የአየር ሁኔታና ጠባይ መረጃ በመሰብሰብ እየሰራ የሚገኝ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜም ከአንድ ሺ 500 በማያንሱ በሰውና በራሳቸው በሚሰሩ መሳሪያዎች መረጃዎችን በመሰብሰብ ለተለያየ አገልግሎት ተደራሽ ያደርጋል።
ስለመጪው የአየር ሁኔታም ትንበያ አገልግሎት ከመስጠት በተጨማሪ የሚያሰጋ ነገር ሲኖርም ቅድመ ማስጠንቀቂያ በመስጠትም ሊደርስ ከሚችል አደጋ ይታደጋል። ይሄ የሚቲዎሮሎጂ መረጃ አቅርቦት ትንበያና ቅድመ ማስጠንቂያ ሲሆን፣ በልማት ዳይሬክቶሬት ክፍሉ ደግሞ የግብርና፣ የጤና፣ የውሃ፣ የትምህርት ሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት በቋሚነት እንደ አስፈላጊነቱ በየሶስት ቀን፣ በአስር እና በወር የትንበያ አገልግሎት በመስጠት ከባለድርሻ አካላት ጋር ይሰራል።
የሚሰጠው መረጃ ተመሳሳይነት ቢኖረውም አጠቃቀሙ ግን ይለያል። ለአብነት ለውሃ የሚሰጠው ትንበያ ከዘነበው ዝናብና ከሚተነው የቀረው የግድቦች ውሃ የመያዝ አቅም ሲሆን፣ ለግብርና ደግሞ ለጤፍ፣ ለበቆሎና ለሌሎችም የአዝርዕት አይነቶች የሚያስፈልገው የውሃ መጠን፣ የትነቱና የአፈር አይነት፣ የዕፅዋቱ የዕድገት ደረጃ ይለያያል። ለጤና ከሆነ ደግሞ የአየሩ ሁኔታ ለወባ መራባት ምቹ ነው የሚለውን ያመላክታል። በዚህ መልኩ በተቋሙ የሚከናወነው ሥራ ዘርፍ ተኮር አገልግሎት ይባላል።
እንደ ሀገር በሁለት ክረምቶች በተካሄደውና ለሶስተኛ ዙር በተያዘው ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ኤጀንሲው መረጃ በመስጠት ስላለው ሚና አቶ ክንፈ ላቀረብኩላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ በዋናነት በማስተባበር ኃላፊነቱን እየተወጣ ያለው የተፋሰስ ልማት ባለሥልጣን ቢሆንም፣ ኤጀንሲው አብሮ እየሰራ ነው። ከግብርና፣ ከውሃ፣ ከኤሌክትሪክ ኃይልና ከአካባቢ ጋር የተያያዘ ሥራ የሚያከናውን ብሄራዊ የአየር ጠባይ ማዕቀፍ የሚባል ተቋቁሞ በጋራ ሥራዎች በመከናወን ላይ ናቸው።
ሌላው በተጨማሪ ሃሳባቸውን ያካፈሉን በኤጀንሲው የክልል ሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ማዕከላት ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሄኖክ ኃይሉ ናቸው። እንደርሳቸው ማብራሪያ ከውቅያኖሶች የሚገኘው መረጃ ለዘላቂ የአረንጓዴ ልማት በትንበያ መልክ ግብአት ሆኖ ያገለግላል።
ለአብነት ብለው ከጠቀሷቸው መካከልም የድርቅ ተጽዕኖ አንዱ ነው። ድርቅ ሊከሰት ይችላል ተብሎ ቀድሞ ሲተነበይ ወይንም ግምት ሲኖር ቀድሞ የሚታየው የውቅያኖስ ወለል የሙቀትና የቅዝቃዜ ሁኔታ ነው። ከዚህ በመነሳት የሚሰጠው ትንበያ ለአረንጓዴ ልማት ሥራው ግብአት ሆኖ ያገለግላል።
ውቅያኖሶች ሙቀት አምቆ በመያዝ ሚናቸው ከፍተኛ በመሆኑ ዓለም ኃይል የሚያገኘው ከፀሐይ ነው። ውቅያኖሶች በጥልቀታቸውም የዓለምን 70 በመቶ ገጽታ ይሸፍናሉ። በመሆኑም ውቅያኖስ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ይሰጣል። በአሁኑ ጊዜም 90 በመቶ የሚሆነው የዓለም የንግድ እንቅስቃሴ በውሃ ላይ የተመሠረተ ነው። 40 በመቶ የሚሆነው የማህበረሰብ ክፍልም ኑሮው የተመሰረተው በውቅያኖስ ዳርቻ ላይ ነው።
በመሆኑም የማህበረሰቡ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች የተመሰረቱት በዚሁ ውቅያኖስ አካባቢ በመሆኑ ቁርኝቱ ከፍተኛ ነው። ከዚህ አንፃር ውቅያኖስ ለዘላቂ ልማት ቁልፍ መሆኑ ታምኖበታል። በተባበሩት መንግሥታት የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅትም ከመቸውም ጊዜ ልዩ ትኩረት ሰጥቶታል።
የዘንድሮው የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ቀን ሞቶ በውቅያኖስ ላይ ትኩረት ያደረገው ከዚሁ መነሻ ነው። ስለዚህ ውቅያኖሶችን መከታተል፣ ትንበያዎችን መሠረት አድርጎ መረጃዎች መስጠት ለዓለም ከፍተኛ የሆነ ጠቀሜታ እንዳለው አቶ ሄኖክ ያስረዳሉ።
ውቅያኖሶች ከአካባቢ የአየር ጠባይ ጋር በሚኖራቸው ጥምረት የአንድ አካባቢ የአየር ሁኔታና ጠባይ ላይ ተጽዕኖ የማድረግ አቅማቸው ከፍተኛ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ሄኖክ በውሃ ላይ ያለውን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር (ማኔጅ) ለማድረግ እንደ ማዕበል ያሉ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉትንና መርከቦች የሚሄዱበትን መሥመር ቅድመ ትንበያ በመስጠት ሊያደርሱ ከሚችሉት አደጋ ቀድሞ መጠበቅ እንደሚቻል ይገልጻሉ።
ሥራዎች በትብብር እንደሚሰሩና የትንበያ መረጃ ልውውጦችም በተባበሩት መንግሥታት የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት አስተባባሪነት የመረጃ ልውውጡ ተግባር እየተከናወነ መሆኑንም አመልክተዋል። ለውቅያኖሶች ባህሪ ጥሩ መረጃ አስፈላጊ እንደሆነም ጠቁመዋል።
እንደ አቶ ሄኖክ ፤ ከዚህ በፊት ጥቅም ላይ የዋሉ የመረጃ መሰብሰቢያ መሣሪያዎች ዛሬ ላይ ላይሰሩ ወይም ላያስፈልጉ ስለሚችሉ የዘመነ የመረጃ መሰብሰቢያ መሣሪያ ወሳኝ ነው። የመረጃ መሰብሰቢያ ቴክኖሎጂ በዓለም ላይ በየጊዜው ይቀያየራል። መሣሪያው ወቅቱ ከሚጠይቀው ጋር መራመድ ስላለበት መቀየሩ ግድ ነው።
በሰው የሚታገዝ የመረጃ መሰብሰቢያ ዘዴ በሰው አልባ ቴክኖሎጂ መተካት ከጀመረ ቆይቷል። ይሁን እንጂ የነበረውን አሰራር አስቀርቶ ወደ አዲሱ ለመሸጋገር የገንዘብ አቅም ወይንም ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ይጠይቃል። በመሆኑም በአሁኑ ጊዜ በዓለም ደረጃ ገና ሽግግር ላይ ወይም ትራንስፎርም እየተደረገ ነው።
ኢትዮጵያም በሽግግር ሂደት ውስጥ ትገኛለች። ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ስትራተጅክ ዕቅድ ቀርጾ እየሰራ ሲሆን እስካሁንም ኤጀንሲው ከሶስት መቶ በላይ በሚሆኑ ሰው አልባ ዘመናዊ የአየር ትንበያ መስጫ ጣቢያዎች ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል። ጎን ለጎንም በሰው ታግዞ የሚሰራ ስራ መኖሩን ጠቅሰዋል።
በትራንስፖርት ዘርፉም በአራት ዓለም አቀፍና በ18 የሀገር ውስጥ የአውሮፕላን ማረፊያዎች ውስጥ በዘመናዊ የትንበያ መሣሪያ የታገዘ ሥራ በመከናወን ላይ እንደሆነ ነው የገለጹት። ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለመጠቀም የሚያስችለው ሽግግር በሰፊ ዕቅድ በምዕራፍ እየተከፋፈለ የሚከናወን እንጂ በአንድ ጊዜ የሚፈለገው ደረጃ ላይ የሚያደርስ እንዳልሆነ አቶ ሄኖክ ያስረዳሉ።
በጥቅሉ ኢትዮጵያ በትንበያ መረጃ አሰጣጥ በምን ደረጃ ላይ እንደምትገኝ አቶ ሄኖክ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ መረጃ የመስጠቱ ሂደት ከትንበያ፣ የሀገሪቱ መልክዐ ምድር ሸፍኖ መረጃ መሰብሰብንና ከተለያየ አቅጣጫ ነው የሚቃኘው። ከዚህ በመነሳት አሁን ባለው የትንበያ መረጃ እስከ 80 በመቶ ያህል ትንበያ እየተሰጠ ይገኛል። መረጃ መሰብሰቢያዎች ሽፋን ላይ ግን ክፍተቶች መኖራቸውን ያነሳሉ። ችግሩ ከመሰረተ ልማት አለመሟላት ጋር ይያያዛል።
መሠረተ ልማት አለመሟላቱ የመረጃ ትንበያ መሰብሰቢያ ጣቢያዎች ለማቋቋም እንቅፋት ፈጥሮ ነበር። የትንበያ መረጃ የጣቢያ ማስተር ፕላን በማዘጋጀት ችግሩን ለመፍታት ጥረት በመደረግ ላይ ሲሆን፣ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ጊዜ ውስጥ ሀገሪቱን ወካይ የሆኑ የትንበያ መረጃ መሰብሰቢያ ጣቢያዎች እንደሚተከሉም ተናግረዋል።
የሚቲዎሮሎጂ ትንበያ ለሁሉም ዘርፍ እጅግ ጠቃሚ እንደሆነ የሚታመን ቢሆንም ግብርናቸው በዝናብ ላይ የተመሰረተ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገሮች የአየር ሁኔታና ጠባይ ከመከታተል አንፃር የግብርና ሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ለግብርና ምርትና ምርታማነት ዕድገት ቁልፍ ሚና አለው።
የግብርና ምርትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ግብአቶች ለመጠቀም፣ ዕለታዊ፣ ሳምንታዊ ፣ ወርሃዊና ወቅታዊ የሰብሎች ዝናብ መጠን ፍላጎትና ስርጭትን እንዲሁም የሰብል ዕድገት ደረጃ ትንበያ፣ ግምገማና የሰብሎች ውሃ ፍላጎት እርካታ ለማረጋገጥ ከማገዙ በተጨማሪ ለከብቶች የሳር ግጦሽ እና ለአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደሮች የውሃ ሽፋን ከፍ እንዲል የግብርና ሚቲዎሮሎጂ መረጃ አገልግሎት ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
የሚቲዎሮሎጂ ትንበያና ቅድሚያ ማስጠንቀቂያ አገልግሎት የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ የአየር ሁኔታና ጠባይ ትንበያና ቅድሚያ ማስጠንቀቂያዎችን እስከማሰራጨት ያሉትን የአገልግሎት ዘርፎች እንደ ሚያካትት ከኤጀንሲው ያተገኘው መረጃ ያመለክታል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 16/2013