ሀገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አነሳሽነት ከዛሬ ሶስት ዓመት በፊት ተጀምሯል።ባለፉት ሶስት ዓመታት ጊዜ ውስጥም በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች ተተክለዋል። በዚህም ተመናምኖ የቆየውን የሀገሪቱን አረንጓዴ ሽፋን በመጠኑም መመለስ ተችሏል። በቀጣይም የተተከሉ ችግኞች ሲያድጉ ለአረጓዴ ሽፋኑ ማደግ የማይናቅ አስተዋፅኦ እንደሚ ኖራቸው ተገምቷል።
በመጀመሪያው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ችግኞችን በሀገር አቀፍ ደረጃ መትከል ተችሏል። ከነዚህ ውስጥ 350 ሚሊዮኑ የሚሆኑት በአንድ ጀምበር ተተክለዋል።3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ለሚሆኑ ችግኞች ደግሞ በተለያዩ ጊዜያት እንክብካቤ ተደርጓል። 80 ከመቶ ያህሉ ችግኞች ደግሞ መፅደቅ ችለዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ በ2012 የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አምስት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል የታቀደ ሲሆን ከእቅዱ በላይ ማከናወን ተችሏል። በተመሳሳይም በ2013 ዓ.ም 6 ነጥብ 7 ቢሊዮን ችግኞችን መትከል መቻሉን የግብርና ሚኒስቴር ሰሞኑን አስታውቋል። ይህም በአረንጓዴ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በዓመቱ የሚተከሉ ችግኞች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መምጣቱን ይጠቁማል።
የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ‹‹ኢትዮጵያን እናልብሳት›› በሚል መርህ በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ሲከናወን ቆይቶ ባለፈው እሁድ በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ ተጠናቋል። ከአምናው በተሻለም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ችግኝ በሀገር አቀፍ ደረጃ መትከል መቻሉ ተነግሯል።
በዚሁ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ማጠናቀቂያ መርሐ ግብር ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ባለፉት ሶስት ዓመታት በክልሉ 9 ነጥብ 2 ቢሊዮን ችግኞች በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር መተከላቸውንና ከዚህ ውስጥ 84 ከመቶ ያህሉ መፅደቁን ገልፀዋል።በችግኝ ተከላ መርሐግብሩ የህብረተሰቡ ተሳትፎም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱንም ጠቁመዋል።
የሀገሪቱን የኤክስፖርት አቅም ለመጨመር ቡና ላይ በተሰራው ሥራ ባለፉት ሶስት ዓመታት በክልሉ 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን የተሻሻለ ችግኝ ቡና በክላስተር እንዲተከል መደረጉንም የክልሉ ፕሬዚዳንት ተናግረዋል። ይህንን ጨምሮ ባለፉት ሶስት ዓመታት በክልሉ 12 ቢሊዮን ችግኝ ስለመተከሉም ገልፀዋል።በዚህም በቆላም ሆነ በደጋ የክልሉ አካባቢዎች ላይ አየር ንብረትና የዝናብ ሁኔታ እየተሻሻለ ስለመምጣቱና ምርትም እየጨመረ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ለቀጣዩ ዓመት የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐግብርም ከወዲሁ አስፈላጊው ዝግጅት እየተከናወነ ስለመሆኑና 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል እቅድ መያዙን ጠቁመዋል።
የግብርና ሚኒስቴር አቶ ኡመር ሁሴን በበኩላቸው በ2013 ዓ.ም 6 ቢሊዮን ችግኞችን በሀገር ውስጥ እንዲሁም አንድ ቢሊዮን ችግኞችን በጎረቤት ሀገራት ለመትከል እቅድ ተይዞ በሀገር ውስጥ የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸውን 6 ነጥብ 8 ቢሊዮን ችግኞች መተከላቸውን ገልፀዋል። በጎረቤት ሀገራት የሚተከሉ ችግኞችንም በሚመለከት በታቀደለት መሰረት የሀገራቱን የአየር ሁኔታ ተከትሎ እየተፈፀመ እንደሚገኝ፤ ግማሾቹ ደግሞ ችግኝ እየቀረበላቸው እንደሚገኝና የተቀሩት ደግሞ በሂደት ላይ እንዳሉ ነው የተናገሩት ።
ሀገሪቱ በተለያዩ ችግሮች እየተፈተነች ባለችበት በዚህ ወቅት የህብረተሰቡ ተሳትፎ እየተጠናከረ መምጣቱንና የተተከሉ ችግኞችን መንከባከብና በተከላ፣ በመረጃ አያያዝና በቴክኖሎጂ የበለጠ መደገፍ በቀጣይ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑንም ገልፀዋል።
የኦሮሚያ ክልል ለአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐግብር ስኬት በተለያየ መልኩ በክልሉ በሚገኙ አደረጃጀቶችና መዋቅሮች በኩል የራሱን አስተዋፅኦ እያደረገ የሚገኝ ሲሆን የኦሮሚያ ደን ኢንተርፕራይዝም በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በርካታ ችግኞችን በመትከል ለአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ሽፋን መጨመር ቁልፍ ሚና ተጫውቷል ብለዋል ።
አቶ ዘውዴ ጉጂ በኦሮሚያ ደን ኢንተርፕራይዝ የደን ልማትና አጠቃቀም ዳይሬክተር ናቸው።እርሳቸው እንደሚሉት ባለፈው በጀት ዓመት ኢንተርፕራይዙ 14 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚጠጉ የተለያዩ የችግኝ አይነቶችን አፍልቶ ወደ 3 ሺ 600 ሄክታር የሚሸፍን ችግኝ ተክሏል። ለህብረተሰቡና ለተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ቦታ ውስደው እንዲተክሉ አድርጓል። አምና ከተተከለው ችግኝ ጋር ሲነፃፀርም የዘንድሮው አፈፃፀም ተቀራራቢ ነው።
ከካቻምናውና ከአምናው የአረንጓዴ የችግኝ ተከላ መርሐግብር ጋር ሲነፃፀርም የዘንድሮው ከፍተኛ ብልጫ አለው። ኢንተርፕራይዙ በመንግሥት በኩል የተሰጠውን የተከላ ቦታም እየሞላ ይገኛል። ከዚሁ ተከላ ቦታ ያረጀውን ዛፍ ግንድ ወደ ምርት በመቀየር ጥቅም ላይ እያዋለ ነው።
መልሶ ችግኞችን የመተካትና በክፍት ቦታዎች ላይ ችግኞችን የመትከል ሥራውንም ያከናውናል። ከዚህ ውጪም ኢንተርፕራይዙ ሞዴል ገበሬዎችን በመምረጥ ምዝገባ አካሂዶ ችግኞችን እንዲተክሉ ያደርጋል። ህብረተሰቡም ችግኞችን ወስደው እንዲተክሉ ሁኔታዎችን ያመቻቻል። ለምግብነት የሚውሉ ችግኞችንም ምርት መስጠት ሲጀምሩ የምርት ዋጋ ገበሬዎችን በማስከፈል ለህብ ረተሰቡ እንዲሸጥ ይደረጋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብሩ ከተጀመረ የዘንድሮው ሶስተኛ ሲሆን ኢንተርፕራይዙ በሶስት ዓመታት ውስጥ በየዓመቱ ከሶስት ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በችግኝ እንዲሸፈን አድርጓል።የተከላ ቦታዎቹም በተለያዩ የኦሮሚያ ዞኖች ሲሆን ጅማ፣ ኢሊባቡር፣ ወለጋ፣ ቦረናንና አርሲን ጨምሮ ሁሉንም የኦሮሚያ ዞኖችን ያጠቃልላል። የኦሮሚያ ልዩ ዞንም በዚሁ ውስጥ ታቅፏል።
የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ እንደ ኦሮሚያ ክልል የአረንጓዴ ሽፋንን ከማሳደግና የአየር ንብረት ለውጥን ከማሻሻል አኳያ ትልቅ ውጤት እያመጣ ይገኛል።ከዚህ በፊት በክልሉ ወደ 3 ከመቶ ወርዶ የነበረውን የደን ሽፋንም ወደ 26 ከመቶ አሳድጓል።እንደሀገርም ዘንድሮ ያለው የደን ሽፋን ወደ 16 ከመቶ ከፍ እንዲል አስተዋፅኦ አድርጓል።
ከችግኝ እንክብካቤ ጋር በተያያዘም በኢንተርፕ ራይዙ በዚሁ ጉዳይ የሚሰሩ የቴክኒክ ሰዎች በመኖራቸው የችግኝ እንክብካቤው ትኩረት ተሰጥቶበት የሚሰራበት ነው።ችግኞች ገና ከመተከላቸው በፊትም አስፈላጊው የቦታ ዝግጅት ይደረጋል።ችግኞች ተተክለው በጎርፍ ምክንያት አልያም ከተተከሉ በኋላ በሰዎችና በእንስሳ ተረጋግጠው ሲጠፉ በአንድ ወር ውስጥ በምትካቸው ሌላ ችግኝ እንዲተከል ይደረጋል።የአረምና የኩትኳቱ ሥራም ይካሄዳል።የችግኝ ጥበቃ ሥራም ይከናወናል። ይህም ለአራትና አምስት ተከታታይ ዓመታት ይሰራል።
በዚህም ኢንተርፕራይዙ ባከናወናቸው የችግኝ እንክብካቤ ሥራዎች የመፅደቅ ምጣኔው በጥሩ አፈፃፀም ደረጃ ላይ ይገኛል፤ ተጨባጭ የሆነ ለውጥም መጥቷል።ባለፈው ዓመት የበጋው ወቅት ረዘም ያለ የነበረ በመሆኑ የችግኞች የመፅደቅ ምጣኔ ወደ 84 ከመቶ ያህል ነበር። ይሁንና በአብዛኛው የመፅደቅ አማካኝ ምጣኔው 88 ከመቶና ከዚያ በላይ ነው። የመፅደቅ ምጣኔው ግን ከቦታ ቦታ ይለያያል።ለአብነትም ክፍት የግጦሽ መሬት በሀገሪቱ የተለመደ እንደመሆኑ በነዚህ አካባቢዎች ላይ የችግኞች የመፅደቅ ምጣኔ ዝቅ እንደሚልና እስከ 67 ከመቶ የሚደርስበት ሁኔታ አለ። በአጠቃላይ ግን በሶስት ዓመቱ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር የመፅደቅ ምጣኔው 88 ከመቶ ደርሷል።
ከዚሁ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ጋር በተያያዘ ኢንተርፕራይዙ በቀጣዩ መንግሥት ችግኞችን እንዲተክልባቸው በሰጠው ቦታዎች ላይ ክፍተት እንዳይኖርና ሙሉ በሙሉ እነዚህን ቦታዎች በችግኝ የመሸፈን እቅድ ይዟል።
በሌላ በኩል ደግሞ ከመንግሥት የሚሰጡ የተራቆቱ መሬቶችን ተቀብሎ ለማልማት ዝግጅቱን አጠናቋል። ገበሬውም በነፍስ ወከፍ የራሱ ደን በመንገድ ዳርና በማሳ ውስጥ እንዲኖረውና በተለያየ የአግሮ ፎረስቲ ስርዓት ውስጥ ተሳታፊ ሆኖ በተለይ ችግኞችን ከኢንተርፕራይዙ በመውሰድ የደን ሽፋኑን ቢያንስ በሚቀጥሉት ዓመታት ውስጥ ከ30 ከመቶና ከዛ በላይ ለማድረግ አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 4/2013