ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የምታበረክተው አስተዋጽኦ ዝቅተኛ ቢሆንም የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ላለው ተፅዕኖ ግን በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ ናት። ጊዜ እየቆጠረ የሚከሰተው ድርቅ የሚያሳድረውን ጫናም ሆነ የአየር ንብረት ለውጡን መቋቋም የሚያስችል አቅም የላትም። የአየር ንብረትን ጠብቆ ለማቆየት የጎላ ሚና ያለው የደን ሀብት ለበርካታ ዓመታት ሲመናመን ቆይቷል።
ይሁንና ኢትዮጵያ ከቅርብ አመታት ወዲህ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ቀርፃ ተግባራዊ ማድረግ ጀምራለች። በስትራቴጂው የደን ጭፍጨፋና መመናመንን መቀልበስና ደኖች የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለመደገፍ እንዲውሉ ለማስቻል ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶታል። ኢትዮጵያ ካሏት እምቅ የተፈጥሮ ሀብቶችና የመልሚያ ዕድሎች አንዱ የደን ሀብት ነው። የደን ሀብቶችን መጠበቅ፣ ማልማትና በዕቅድ ጥቅም ላይ ማዋል ኢኮኖሚያዊ፣ ስርዓተ-ምህዳራዊና ማሕበራዊ ጠቀሜታው የጎላ ነው።
የተመናመነውን የደን ሀብቷን ከፍ ለማድረግም ዜጎቿን እያስተባበረች በየክረምቱ ችግኝ ትተክላለች። ከዚህ ቀደም ሕዝቡ በራሱና በየአካባቢው በሚኖሩ መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ የግብርና ተቋማት አማካይነት የክረምትን ወቅት መጠነኛ ችግኝ የመትከል ልማድ የነበረ ቢሆንም በተለይ ባለፉት ሶስት አመታት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አነሳሽነት አረንጓዴ አሻራ ማሳረፍ በሚል በተያዘው ፕሮጀክት በቢሊየኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን የመትከል እንቅስቃሴ እየተካሄደ ይገኛል።
ባለፉት ዓመታት በቢሊዬን የሚቆጠሩ ችግኞችን በአንድ ጀምበር በመትከል የራሷን አስተዋጽኦ ከማበርከቷም በተጨማሪ እንደ ሀገር ብቻ ሳይሆን ዓለምን ከካርቦን ልቀት ለመታደግ ለተያዘው ዓለም አቀፍ ጥረትም ጉልህ ፋይዳ አበርክታለች። ዘንድሮው በከፍተኛ ተነሳሽነት ህዝቦቿን በማስተባበር የዓለምን ችግር ለመፍታት የራሷን ድርሻ መወጣቷን አላቋረጠችም።
ይሁንና አሸባሪው የህወሓት ቡድን በኢትዮጵያ ህዝብ ትግል ከስልጣን መባረሩ በፈጠረበት ቁጭት ‹‹እኔ ከሞትኩ››በሚል ብሂል የአረንጋዴ አሻራ መርሃ ግብር ለማደናቀፍ ብዙ ጥረት አድርጓል ። የትግራይ ህዝብም በመርሃ ግብሩ ላይ ተሳታፊ እንዳይሆን ግልፅ ክልከላዎችን ሲፈጽም ቆይቷል። በዚህም ሳያበቃ በተለይ የክረምት ወቅቱን ጠብቆ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ትንኮሳዎችን አስፋፍቷል። የአረንጓዴ አሻራ ማሳረፊያ፣ የእርሻ ስራ ወቅቶችን ቆጥሮ የሀገራችንን ዕቅዶች ለማስተጓጎል በተለያዩ አካባቢዎች ትንኮሳ ማድረጉን አጠናክሮ ቀጥሏል። የተዘሩ ሰብሎችን ማበላሸች ፣ንብረት ማውደምና ማጥፋት የመሳሰሉትን የጥፋት እጆቹን በሁሉም አቅጣጫ ዘርግቷል።
የኢትዮጵያ ህዝብ ከልቡ አውጥቶና አንቅሮ የተፋውን አሸባሪውን የህወሓት ቡድን ከመደምሰስ ጎን ለጎን አረንጋዴ አሻራውን ከማሳረፍ አልተቆጠቡም። የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብሩን ከማሳካት አልቦዘነም። አሁንም የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያግዙ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያላቸውን ለአካባቢው ተስማሚ የሆኑ ተክሎችን በስፋት በመትከል ላይ ይገኛል። ወንድ ሴት ህጻን አዋቂ ሳይቀር ፣የመንግስት ሰራተኞች፣ አርሶና አርብቶ አደሩ ጭምር አረንጓዴ አሻራውን የማሳረፍ ተግባሩን አጠናክሮ ቀጥሏል።
የአየር ጠባይ ሚዛንን የሚጠብቁ የሀገር በቀል ዛፎች፣ ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ተክሎችን ከመትከል ባሻገር በኢኮኖሚ አበርክቶ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው የሚታመንባቸው እንደ ቀርከሃ ያሉትንም የመትከል እንቅስቃሴ አጠናክሮ ቀጥሏል።
ቀርከሃ ከጥንት ጊዜ ጀምሮ የሰው ልጆች ለምግብነት ለቤት ውስጥ ቁሳቁስ፣ለሙዚቃ መሳሪያ፣ለአልባሳት፣ ለመጓጓዣና ለቤት መስሪያ እንዲሁም ለባህላዊ የጦር መሳሪያ መስሪያ ሳይቀር ይጠቀሙበት እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ። ቀስ በቀስ ግን በበርካታ ሀገራት ከእጅ ስራ ተላቆ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ወደ ዘመናዊ አልባሳትና የቁሳቁስ ስራ ተሸጋግሯል።
አለም አቀፉ ደረጃ እኤአ በ2018 የቀርከሃ ገበያ 68 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር ስለማውጣቱና ይህ አሃዝም እኤአ 2025 የገበያ ድርሻው ወደ 98 ነጥብ ሶስት ቢሊየን ዶላር ከፍ እንደሚል የግራንድ ቪው የምርምር መረጃ ያመላክታል።
ኢንቨስትመንቱም የዚያኑ ያህል እንደሚስፋ የሚጠቁመው መረጃው፣ለምርቱ ያለው ግንዛቤ እየተሻሻለ መምጣትና ለመጠቀም ፍላጎት ማሳየት ለገበያውም ሆነ ለኢንቨስትመንቱ ድርሻ መጨመር ዋነኛ ምክንያት እንደሚሆን ያስረዳል።
በርካታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው ቀርከሃ በተለይ በኤሲያ በአፍሪካና በማእከላዊና በደቡብ አሜሪካ አገሮች በስፋት ይታወቃል።ቀርከሃ በስነ ምህዳር አገልግሎት ረገድ በብዝሃ ህይወት ጥበቃና በማህበራዊ ኢኮኖሚ እድገት እየጨመረ የመሄድ ሚና ያለው ነው።ካርቦን በመምጠጥ ጠቃሚና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያስችል እንደሆነም ይታመንበታል።
ቀርከሃ ለአፈርና ውሃ ጥበቃ ከፍተኛ የሆነ አካባቢያዊ ጠቀሜታ እንዳለው ይታወቃል። ከዚህም ሌላ ቀርከሃ ለብዙ የዱር አራዊት መኖሪያ፣ የምግብ ምንጭና የመሰደጃም ቦታ በመሆን የማይተካ ጠቀሜታ ያለው ነው። ቀርከሃ በቴክኖሎጂ በመታገዝ እጅግ በርካታ ዓይነት የምርት ውጤቶችን ለማምረት እድል የሚሰጥ ተክል ነው።
በተለይም ለቤት ውስጥ እቃዎች፣ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች፣ ለሀይል ምንጭ፣ ለምግብነት፣ ለልብስ፣ ለግንባታ፣ ለወረቀት ውጤቶችና ለልዩ ልዩ ምርቶች የጥሬ እቃ ምንጭ በመሆን ያገለግላል። ለበርካቶች በተለይ የገጠሩ ህዝብ የስራ እድል በመፍጠር ኑሮውን ለማሻሻልና ከድህነት ለመውጣት አቅም እየፈጠረ ይገኛል።
በአፍሪካ በተለይ ኢትዮጵያ፣ ኬንያና ኡጋንዳ፣ በርካታ የቀርከሃ ሀብት እንዳላቸው ይታወቃል።ኢትዮጵያ በቀርከሃ ምርታቸው ከሚታወቁ የአፍሪቃ ሀገሮች ውስጥ አንዷ ነች። በአገሪቱ እስከ አንድ ነጥብ አርባ ሰባት ሚሊዮን ሔክታር መሬት የሚሸፍን ቀርከሃ አለ ተብሎ ይታመናል።
ይህም ከአፍሪካ 60 በመቶው ድርሻ የሚወስድ ነው።ይሁንና ኢትዮጵያ የቀርከሃን ምርት በአግባቡ አልተጠቀመችበትም። የቀርከሃ ምርትን ግብዓት በማድረግ በዘመናዊ ኢንዱስትሪ የተለያዩ ምርቶችን ለማምረት አልተቻለም። ይህ ሀብት ከጥቂት ባህል ቀመስ ቤተ መብሎች ወንበርና ጠረጴዛነት ባሻገር ወደ ሰፊ እንጀራ ሲለወጥ ብዙም አይታይም።
አሁን ያለው የቀርከሃ ሀብት ልማት አያያዝና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ያልታገዘ ነው። በዚህ ምክንያት የቀርከሃ ደኖች እየተመነጠሩ የእርሻ መሬት ማስፋፊያ ከመሆናቸውም በላይ ባለው የቴክኖሎጂ ውስንነትና የግንዛቤ እጥረት እንዲሁም ትኩረት ተነፍጎት በመቆየቱ ሳቢያ የቀርከሀ ምርት በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ያለው ድርሻ በደኑ አካባቢ ላለው ህብረተሰብ ከሚሰጠው አነስተኛ ግልጋሎት ውጪ እዚህ ግባ በማይባል ደረጃ ላይ እንዲገኝ አድርጎታል።
በአለም አቀፍ ደረጃ የቀርከሃን ምርት በከፍተኛ መጠን ኤክስፖርት የሚያደርጉት የእስያ አገራት ናቸው። ኢትዮጵያ በአንፃሩ በአለም ገበያው ውስጥ አለችበት ለማለት አስደፍርም። ድርሻዋም ከአንድ በመቶ በታች ፣በመጠንም ዜሮ ነጥብ 2 በመቶ ነው። ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ ጠቀሜታውን በተረዱ ባለሀብቶች፣ ግለሰቦች የተለያየ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ እየሰሩ ይገኛል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህም በመንግስት ተቋማት ደረጃ ትኩረት በማግኘት ላይ ይገኛል።
እኤአ በ2018 ተሻሽሎ በወጣው የደን አዋጅ ውስጥ ከቀርከሃ እንደ ደን ተቆጥሮ በፖሊሲ እንዲደገፍ ተደርጓል። ቀርከሃ ካለው የማልማት ባሕሪና ከሚሠጠው ጥቅም አንጻር እንደ ጥጥና ሌሎችም የግብርና ሰብሎች እስትራቴጂ ተቀርጾለት ወደ ስራ ተገብቷል። ይህ እስትራቴጂም ለአስር አመት የሚያገለግል ነው። ሲያገለግልም በሁለት አምስት አመታት ቁጥጥር እንዲደረግበት ተወስናል።
ቀርከሃን በመጠቀም ብቻ የደን ጭፍጨፋን ማስቀረት ይቻላል። የካርበን ልቀት በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ አቅም አለው። ፈጣን እድገት ስላለው ቀርከሃን የሚፈለገውን ግብ ለማሳካት እጅጉን ወሳኝ ነው። የአየርና የውሃ ብክለት እንዲሁም በወንዞች ዳር አካባቢ፣ በሃይቆች ዙሪያ በመትከል የአፈር መሸርሸር ለመከላከል በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ በማድረግ እጅግ ከፍተኛ የሆነ አስተዋፅኦ እንዳለው በመረጋገጡ ትኩረት ሰጥቶ እየተሰራበት ይገኛል።
በስትራቴጂው አገሪቱን ቀርከሃ ሃብት ሽፋን ወደ 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር ለማሳደግ ታቅዳል። ልማቱን በሰፊውና በሁሉም መስክ የማሳደግ ተግባራም ልዩ ትኩረት ተሰጥታል።በዘንድሮው አመት በከፍተኛ ሁኔታ በሁሉም ክልሎች ቀርከሃን የማልማት ስራ እየተሰራ ይገኛል። በእስትራቴጂ በአምስት አመቱ ወደ 54 ሺ ሄክታር አዲስ የቀርከሃ ተከላ ለማልማት ታቅዳል። በአስር አመት ውስጥ 124 ሺ ሄክታር ነው።
የአካባቢ ደን እና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽንም የቀርከሃ ሃብትን በማልማት ሂደት በዘንድሮ አመት 20 ሺ ሄክታር በሁሉም ክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች ለመትከል አዘጋጅቶ 56 ሚሊየን ችግኝ ከአረንጋዴ አሻራ መርሀ ግብር ጋር በማጣመር ቀርከሃ እንዲለማ አድርጓል። በመንግስት በጀት መሬት ተለይቶ አስፈላጊው መደላድል ተፈጥሮለት ቀርከሃ ልማቱ በስፋት እየተካሄደ ይገኛል።
በቀርከሃ ምርት እሴት ሰንሰለት ላይ ግንኙነት በጣም ዝቅተኛ ነው። ምርቱ የት አለ፣ምን ምን አምርቷል፣ ኢንዱስትሪም ምን ይፈልጋል የሚለውን ማስተሳሰር ብሎም በእውቀትና በቴክኖሎጂ የተደረገ የቀርከሃ ልማት ተግባራዊ ማድረግ ረገድ በርካታ ስራዎች ይጠይቃል። ቀርከሃ ሃብትን በቴክኖሎጂ በማገዝ ለውጭ እና ለአገር ውስጥ ገበያ ተደራሽ በማድረግ ረገድ ብዙ ስራዎች መስራት ያስፈልጋል። በዘርፉ ላይ መስራት ቢቻል በርካታ ኢንዱስትሪዎችን ፋብሪካዎች መቀላቀልና ለበርካቶች የስራ እድሎችን መፍጠር ይቻላል።
በብዛት ብዙ ኢንቨስተሮች ወደ ሴክተሩ እንዲገቡ ማድረግ እና ያሉትንም ማበረታታት የግድ ይላል። በዚህ ረገድም ኮሚሽን መስሪያ ቤቱ የተለያዩ ጥረቶችን እያከናወነ ይገኛል።የእሴት ሰንሰለቱን ማስፋት ወይንም ማሳደግ እንዲሁም ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ ደረጃ የሚሳተፉ እና ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸውን ኢንቨስተሮች ይበልጥ መደገፍና ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል።
ያለውን የቀርከሃ ሀብት በተሻለ አያያዘ ጥቅም ላይ የማዋል፣በተጨማሪ ቦታ ላይ ቀርከሃን ለማልማት፣ በምርምርና በቴክኖሎጂ መታገዝ፣የቀርከሃ ምርት የገበያ ትስስርና የእሴት ሰንሰለት ላይ መስራት፣ በዘርፉ ትምህርትና ስልጠና ላይ ትኩረት መስጠት፣ የቀርከሃ ኢንዱስትሪዎችንና ባለሀብቶችን መደገፍ ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት የግድ ይላል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ነሐሴ 27/2013