ከምድር ወገብ በስተሰሜን ከሦስት ዲግሪ እስከ 18 ዲግሪ ላቲትዩድ እና በስተምሥራቅ ከ33 ዲግሪ እስከ 48 ዲግሪ ሎንግትዩድ የሆነው የኢትዮጵያ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ዓመቱን ሙሉ የፀሐይ ኃይል ማስገኘት እንደሚያስችል የመስኩ ምሁራንና የተለያዩ ጥናቶች ያመለክታሉ።እንደ ጥናቶቹም ሆነ ባለሙያዎቹ በየትኛውም የአገሪቱ ክልል ይህን ሀብት ለመጠቀም የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች አሉ።እንደነዚህ ጥናቶችና ባለሙያዎች ታዲያ ይህ ሁኔታ አገሪቱ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ሥልትን ተግባራዊ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ ይፈጥርላታል።በሀገራችን እጅና ጓንት የሆኑት የተፈጥሮ ሀብትና የአረንጓዴ ልማት ሥራዎችም ይሄን ተንተርሰው እየተከናወኑ ይገኛሉ።
የዘንድሮን የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ሥራን በውጤት ለማጠናቀቅ ከአሳለፍነው ጥር ወር ጀምሮ በየአካባቢው ከአንድ ወር በላይ ለዘለቀ ጊዜያት በትኩረት ሲሰራ ቆይቷል።ሥራው ከዘመቻ ሥራ ወጥቶ እንዲሠራም የአደረጃጀት ለውጥ መደረጉን ከዚህ ዓመት ጀምሮ ዓመቱን ሳይጠብቅ የዕለት ከዕለት ተግባር ሆኖ የሚቀጥል መሆኑን ሰምተናል።ሰኔ ግም ከማለቱም ይሄንኑ የተፈጥሮ ሀብት ሥራ የሚያጠናክር አምስት ቢሊዮን ችግኞችን በቤተሰብና በማህበረሰብ ደረጃ የመትከል ተግባር ተጧጡፎ የቀጠለበት ሁኔታ አለ።
ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ በአንድ ጀምበር 80 ሺህ ሄክታር መሬት የሚሸፍን ከ350 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል በሕንድ ተይዞ የነበረውን የዓለም ክብረ ወሰን መስበሯ አይዘነጋም። እነዚህን የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ያላቸው ተግባራት አቆራኝቶ መጓዝ የመሬት መራቆትን፣የደን መመናመንንና ከነዚሁ ጋር ተያይዞ የሚመጣ የአየር ጠባይ ለውጥ ችግርን ከመቅረፍ አንፃር የጎላ አስተዋጽኦ አለው። ይሄ አስተዋጽኦ ለግብርናው ዘርፍ ያለው ፋይዳ ከሌሎች ዘርፎች በእጅጉ የተለየና ከፍተኛ ነው።በመሆኑም በተለይ በአረንጓዴ አሻራ ልማቱ የግብርናው ማህበረሰብ ሰፊ ተሳትፎ ማድረግ አለበት።የመስኩ ምሁራን እንደሚሉት ቀዳሚው ዛፍ ተካይ ተቋም መሆን ያለበትም ግብርናውን የሚመራው የግብርናው ዘርፍ ነው።ዛፍ ሲጨፈጨፍም ሲቆረጥም ያገባኛል ማለት ይገባዋል።
የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን ስርዓቱ እንደ ሀገር በተጀመረበት መድረክ ሲናገሩ እንደተደመጡት ችግኝ ተከላውና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራው በተለይ ለግብርና ሥራው ውጤታማነት ዘላቂና አስተማማኝ መሰረት የሚጥል ነው።የአረንጓዴ አሻራ ተከላ እንደ ሀገር በአምስት ዓመታት 20 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል የተያዘውን መርሐ ግብር ለማሳካትና ለማስቀጠል ያለመ ከመሆኑ ጋር አርሶና አርብቶ አደሩ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጡት እንደሚገባም አሳስበዋል ።የዘንድሮ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ስነ ስርዓትን ለየት የሚያደርገው የጋዝ ልቀትን ከሚቆጣጠሩ ዛፎች አልፎ ለምግብነት በመዋል የምግብ ዋስትናችንን በሚያረጋግጡ ቋሚ አትክልትና ፍራፍሬዎች መመራቱ ነው። ቋሚ ተክሎቹና ፍራፍሬዎቹ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ የዋጋ ንረትና የአቅርቦት እጥረት ሰቅዞ የያዘው የሚመስለውን የፍራፍሬና አትክልት ገበያውን ከማረጋጋት አልፈው ሰፊ የሥራ ዕድል የመፍጠራቸው ዜና ከዕድገታቸው ቀድሞ እየተበሰረላቸው ይገኛል። ለዚህም ነው የግብርና ሚኒስትሩ በየመገናኛ ብዙኃኑ ደጋግመው በ2013 ችግኝ ተከላው አርሶ አደሩም ሆነ የግብርናው ዘርፍ ማህበረሰብ በስፋት እንዲሳተፍበት ጥሪ ሲያቀርቡ የተደመጠው።
ዕውነት ለመናገር አርሶ አደሩም አላሳፈራቸውም። የተከላ መርሐ ግብሩ እንደ ሀገር ‹‹አረንጓዴነት ለጋራ ልማት›› በሚል በይፋ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በሰፊው እየተሳተፈበት ይገኛል።ተሳትፎው በግሉ፣ በቤተሰብ ደረጃ እና እንደማህበረሰብም ነው።
አቶ አሸናፊ ሮባ በምሥራቅ ሸዋ ዞን ዱግዳ ወረዳ የሚገኘው የመቂ ባቱ አትክልትና ፍራፍሬ ሕብረት ሥራ ዩኒየን ምክትል ሥራ አስኪያጅ ናቸው። በዩኒየኑ ሥር 22 ማህበራት አሉ።በ22ቱ ማህበራት ሥር ደግሞ 12 ሺህ 990 አባላት አሉ። እሳቸው እንዳወጉን ታድያ እነዚህ አባላት በሙሉ ‹‹አረንጓዴነት ለጋራ ልማት›› በሚል እየተጠናቀቀ ባለው በ2013 ዓ.ም በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ሙሉ በሙሉ ተሳትፈዋል። በእርግጥ አባላቱ የራሳቸው መሬት ስለሌላቸው የተሳተፉት በራሳቸው መሬት አይደለም። ዱግዳ ወረዳ ለችግኝ ተከላው ባቀረበው ከ 2 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ ነው።በዚህ ቦታ ላይ ሐምሌ 6 ቀን 2013 ዓ.ም ከዱግዳ ወረዳ አመራር፣አርሶ አደሮችና ነዋሪዎች ጋር በጋራ በመሆን ከ2 ሺህ በላይ ቋሚ አትክልትና ፍራፍሬ ተክለዋል።
ለተከላ ያነሳሳቸው በፍራፍሬና አትክልቱ ዘርፍ እንደመሰማራታቸው ከሌላው ሕብረተሰብ ይልቅ እነሱ ስለ ፍራፍሬና አትክልት ጠቀሜታ የበለጠ ግንዛቤ ያላቸው በመሆናቸው ነው። አትክልትና ፍራፍሬ ሳይቆይ በቶሎ ለመበላሸት ተጋላጭ ቢሆንም ለምግብነት የሚሰጠው አገልግሎት ቀላል አይደለም። በዚህ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥና አሁን ያለውን የአትክልትና ፍራፍሬ የተጋነነ የዋጋ ንረት በማጣጣም ገበያን ማረጋጋት ይቻላል።በዚያ ላይ በገበያ ዳጎስ ያለ ገንዘብ ያስገኛልም ባይ ናቸው ጠቀሜታውን የሚያስረዱት ሥራ አስኪያጁ።
በቆጂ አካባቢ የሚገኘው የገለማ ዩኒየን ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ተሾመ ባልቻ የ2013 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር እንደ የክልሎቹ የአየር ጠባይ ሁኔታ ሲከናወን መቆየቱን በመጥቀስ ነው የግላቸውንና የማህበራቸውን አስተዋጽኦ ሊነግሩን የጀመሩት።እርሳቸው እንዳሉት ፤የማህበሩ አባላት አርሶ አደሮች ናቸው።በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ስነስርዓቱ የቅርቡ ይጠቀስ ከተባለ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በግላቸውም በማህበራቸውም ሲሳተፉ ቆይተዋል። በተለይ በ2011 እና 12 ዓ.ም የተተከሉትን ችግኞች በመንከባከቡም ቢሆን ሰርክ በግልም በጋራም እየተንከባከቡት በመገኘታቸውና አሁን ላይ ፀድቆ በጥሩ ሁኔታ ላይ በመሆኑ እሳቸውም ሆነ ማህበራቸው አይታሙም። ዘንድሮ በጋራም በግልም የተከሉት ደግሞ በብዛት ፍራፍሬ በመሆኑ ቶሎ ይደርሳል የሚል ዕምነት አላቸው።ፍራፍሬና አትክልት በአካባቢው ገበያ ተፈላጊ በመሆኑም ዳጎስ ያለ ገቢም ያስገኛል የሚል ዕምነት አላቸው።እስከ አሁን በማህበርና በግል በዘመቻ መልኩ ሲተክሏቸው የቆዩት ሀገር በቀልና የውጪ ዝርያ ያላቸው ችግኞች የሚፈለገውን ለውጥ እያመጡ መሆናቸውንም ያስረዳሉ።
ተራሮች ውሃ እንዲያመነጩ፣ታላቁን የህዳሴ ግድብ ጀምሮ በየደረጃው ያሉት ግድቦች በደለል እንዳይሞሉ የየራሳቸውን አስተዋጽኦ ያደረጉ መሆናቸውንም ይናገራሉ። እንደሳቸው የአፈር መሸርሸር በእጅጉ ቀንሷል።የወንዞች የውኃ መጠንም ቢሆን በእጅጉ የጨመረበት ሁኔታ እየተስተዋለ ይገኛል።ከአንዳንድ ጥናቶች እንደተገነዘቡትም ሆነ በተለምዶ የፊቱንና የአሁኑን ሁኔታ በመገምገም እንዳስተዋሉት የዛፍና የደን ሽፋን ዕድገት አሳይቷል።መስኖን የመጠቀም ሰፊ ዕድልም ተፈጥሯል። እየተከናወነ የሚገኘው የእርከን ሥራ አፈር እንዳይሸረሸር በማድረግ በወንዞች ላይ ሊደርሱ የሚችሉ ደለሎችን በመቀነስ እመርታ በማሳየት ላይ መሆኑን መካድ አይቻልም። በተለይ በአካባቢያቸው የእርሻ መሬት ላይ ውሃ እንዳይተኛ ከማድረግ አኳያ አስተዋጿቸው ጉልህ መሆኑንም ይጠቅሳሉ። ዘንድሮም በግልና በማህበር የተከሏቸው የቡናና የፍራፍሬ ችግኞች እንዲፀድቁ እንደ ማህበር፣ እንደ ህብረተሰብም ለኩትኳቶና ለእንክብካቤ በማነሳሳት የሚያደርጉትን አስተዋጾ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አጫውተውናል።
በኦሮሚያ ክልል ሎሚ አዳማ የገበሬዎች ህብረት ሥራ ዩኒየን 63 ሺህ አምራች አባላት አሉት። እንደ ዩኒየን በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ልማት ላይ በየዓመቱ ይሳተፋሉ።በየዓመቱም በግማሽ ሄክታር መሬት የተከላ መርሐ ግብሩን ስነ ስርዓት ያከናውናል።ዘንድሮም እንደዚሁ በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ የተሻሻሉ ቋሚ የአትክልትና ፍራፍሬ ተክሎችን ተከላ መርሐ ግብር ያከናወነበት ሁኔታ እንዳለ የዩኒየኑ ሥራ አስኪያጅ አቶ ታደለ አብዲ ነግረውናል።
እንደ አቶ ታደለ ገለጻ፤ ዘንድሮ እንደ ዩኒየን በአባላቱ ከተተከሉት ፍራፍሬና ቋሚ ተክሎች ውስጥ አቡካዶ፣ማንጎ፣ ፓፓያ እንዲሁም ከቋሚ ተክል ቡና ይገኝበታል። በተለይ አቡካዶው፣ማንጎውና ፓፓያው በሦስትና በሁለት ዓመት አጭር ጊዜ ውስጥ የሚደርሱ ናቸው።በሁለት ዓመት የሚደርሱም አሉ።ከዚህ ቀደም ግን የነበሩት ዝርያዎች ከአምስት እስከ ሰባት ዓመት የሚፈጁ ነበሩ።ቀደም ሲል የተተከለው ፓፓያ ዘንድሮ ደርሶ ለገበያ የቀረበበትና በአካባቢያቸው በየመንገዱ የሞላበት ሁኔታ አለ። ይሄ እንደ ዩኒየን ፣እንደ ሀገርና እንደ አካባቢው ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።ነገር ግን አስተዋጽኦ ዕውን የሚሆነው ችግኝ በተከላው ወቅት ሊደረጉ የሚገቡ ጥንቃቄዎችን በአሟላ ሁኔታ ሲካሄድ ነውም ባይ ናቸው አቶ ታደለ ። የእሳቸው ዩኒየን ይሄን ተከትሎ ተከላውን የሚያካሂድ በመሆኑ የተከለው በተገቢው መንገድ ለመጽደቅ የሚበቃበት ሁኔታ መኖሩን ይጠቅሳሉ። በችግኝ ተከላ ወቅት መደረግ ካለባቸው በርካታ ጥንቃቄዎች አንዱ ጉድጓድ ቆፍሮ ማዘጋጀት ነው ይላሉ። ዩኒየኑ ይሄን ጉድጓድ የሚያዘጋጀው ከተከላው ከሁለት ሳምንት በፊት ቀደም ብሎ መሆኑንም ይጠቁማሉ። አተካከሉም ላይ ችግኙን ከነላስቲኩ አለመትከልና የችግኞቹ ሥራቸው አለመታጠፉን እርግጠኛ መሆን እንደሚገባም ያላቸውን ተሞክሮ ጠቅሰው ምክር ይለግሳሉ። የቦታ መረጣው የሚወሰነው በሚተከለው ችግኝ አይነት መሆኑንም ይጠቁማሉ።
በተለይ እንደ ቡና፣ፓፓያ፣አቡካዶና ማንጎ ያሉ ቋሚ ተክሎች የሚተከሉበትን ቦታ ቀድሞ መወሰን ተገቢና አስፈላጊም ነው ባይ ናቸው። በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እኛም ሆን ገፀ-ምድራችን ተጠቃሚነታችን የጎላ ነው። ከመሬታችን ብንነሳ የሁሉም ነገር መሠረት የሆነውን አፈር በብርቱ መጠበቅ አንዱ ፋይዳው ነው::
በሁለተኛ ደረጃ የዝናብ ሥርጭቱ የተዛባ በመሆኑ የሚገኘውን የዝናብ መጠን በመሬት ውስጥ መሰነቅ የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች አሉት። ዘንድሮ ደግሞ እንደ ፍራፍሬና ቡና ያሉ ቋሚ ተክሎችን መሰረት አድርገን ስነስርዓቱን በማካሄድ በብዙ መንገድ ተጠቃሚ መሆን የምንችልበትን መንገድ ሊያስቀይሰን ችሏልና በጋራም በግልም የአረንጓዴ አሻራ ልማት ላይ በመሳተፍ አሻራችንን እያሳረፍን ጥቅማችንን እናስከብር እንላለን።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 20/2013