አሁን ባለው የኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ በሽታና በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በገጠመው የጦርነት ችግር በሀገሪቱ ውስጥ አለመረጋጋቶች ቢኖሩም ‹‹ኑ ኢትዮጵያን እናልብስ›› በሚለው ሶስተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ከግለሰብ ግቢ ጀምሮ በተለያየ ምክንያት የተጎዱ ገላጣ ቦታዎችን፣የተመናመኑ ደኖችን፣የቱሪዝም መዳረሻዎችን በአረንጓዴ ለማልበስ ከ2013ዓም የክርምት ወር መግቢያ ጀምሮ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡በሶስተኛው ዙር የዛፍ ችግኝ ተከላ መርሃግብር ዕቅድ መሠረት በበጀት አመቱ አምስት ቢሊየን የዛፍ ችግኞች ናቸው የሚተከሉት፡፡ይሁን እንጂ በአካባቢ፣በቀበሌ፣በተለያዩ ተቋማት በጋራ እና በተናጠል ሁሉም በየአካባቢው ተጨማሪ ተግባራትን በማከናወን አሻራውን ለማሳረፍ እያሳየ ያለው ትጋት ክንውኑ ከዕቅድ በላይ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡
በዚህ በአረንጓዴ አሻራ የዛፍ ችግኝ ተከላ መርሃግብር በተለይም በወቅታዊው የሀገር ሁኔታ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን አለመረጋጋት ርቋቸውና በፀጥታ ስጋት ውስጥ ሆነው የአረንጓዴ አሻራ የዛፍ ችግኝ ተከላ መርሃግብርን በመተግበር አሻራቸውን ያሳረፉ አካባቢዎች በተለየ ሁኔታ ልዩ ግምት ይሰጣቸዋል፡፡በዚህ ረገድ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ይጠቀሳል፡፡ክልሉ አሁን አንፃራዊ ሰላም ውስጥ እንደሆነ ቢታወቅም ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ላይ አይደለም፡፡ክልሉ በዚህ ውስጥ ሆኖ መርሃግብሩን በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡ለመሆኑ በክልሉ የሁለት ዙር የአረንጓዴ አሻራ የዛፍ ችግኝ ተከላ መርሃግብ እንዴት አለፈ፣ምንስ ውጤት ተገኘ፣የአሁኑን የሶስተኛውን ዙር እንቅስቃሴና በአጠቃላይ የክልሉን የአካባቢ ጥበቃ ሥራ በተመለከተ ከሚመለከታቸው የክልሉ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ቆይታ አድርጌያለሁ፡፡
የቤንሻንጉልጉሙዝ ክልል ግብርና እና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ አቶ ባብከር ከሊፋ፤እንዳስረዱት በሶስተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ የዛፍ ችግኝ ተከላ መርሃግብር በዕቅድ የተያዘው 72 ሚሊየን የዛፍ ችግኞችን በማፍላት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች እንዲተከል ለማድረግ ነበር፡፡ይሁን እንጂ በክልሉ ተፈጥሮ በነበረው የፀጥታ ችግርና አለመረጋጋት ምክንያት በዕቅዱ መሰረት ማከናውን ባይቻልም፡፡40 ሚሊየን የተለያየ ዝርያ ያለው ችግኞችን በማፍላት ማዘጋጀት ተችሏል፡፡የችግኝ ተከላ መርሃግብሩ በክልሉ ከሚገኙ የፀጥታ ችግር ካለባቸው ከማሺና መተከል ዞኖች በተወሰኑ ወረዳዎች ካልሆነ በስተቀር በሁሉም አካባቢዎች ፈልቶ ከተዘጋጀው የዛፍ ችግኝ ወደ 38 ሚሊየን የዛፍ ችግኞች በተለያዩ አካባቢዎች ተተክሏል፡፡ቀሪው ችግኝም እንዲተከል እንቅስቃሴው ተጠናክሯል፡፡ምንም እንኳን የአካባቢው የፀጥታ ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ የተረጋጋ ባይሆንም በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በመጠቀም መርሃግብሩን ለመፈጸም ጥረት እየተደረገ ሲሆን፣በክልሉ ክረምቱ እስከ ጥቅምት ወር መጨረሻ ድረስ ስለሚቆይ በየችግኝ ጣቢያዎቹ የተዘጋጁት የዛፍ ችግኞች ሁሉ እንዲተከሉ ይደረጋል፡፡
በክልሉ በሁለት ዙሮች የተካሄዱ የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር የዛፍ ችግኝ ተከላ መርሃግብር ስለነበሩ እንቅስቃሴዎችና የተተከሉት የዛፍ ችግኞች የጽድቀት መጠንን በተመለከተም አቶ ባብከር እንዳስረዱት፤አምና በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ሰባትመቶሺ የዛፍ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን፣80 በመቶ የጽድቀት መጠን መመዝገቡን በተደረገ ዳሰሳ ተረጋግጧል፡፡ከዚያ በፊት በነበረው አመትም የመጀመሪያው ዙር በተመሳሳይ ውጤት ላይ ነው የሚገኘው፡፡የአረንጓዴ አሻራ የዛፍ ችግኝ ተከላ ከመጀመሩ በፊትም በክልሉ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ የተጠናከረ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ባብከር እንደገለጹት በክልሉ የሚስተዋለው እንደ አንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች የደን መመናመንና መራቆት ችግር ሳይሆን፣አካባቢው በተቃራኒው ነው የሚገለጸው፡፡ክልሉ በደን የተራቆተ አይደለም፡፡አረንጓዴ ልማቱ በእርሻ ከተሸፈነው መሬት በላይ ይበልጣል፡፡ክልሉ ካለው አምስት ሚሊየን ሄክታር መሬት ውስጥ እስካሁን በእርሻ የተሸፈነው ወይንም በሰብል የለማው መሬት አንድ ሚሊየን ሄክታር እንኳን የሚሆን አይደለም፡፡ክልሉ ከአረንጓዴ ልማቱ በላይ የሰብል ልማት የሚያስፈልገው በመሆኑ፣ደን ተመንጥሮ ለልማቱ ዝግጁ ሊሆን የሚችል ወደ ሶስት ሚሊየን ሄክታር መሬት ይገኛል፡፡ለማልማት የሚፈልግ ባለሀብት በቀላሉ ሊመቻችለት እንደሚችል እየተጠበቀ ነው፡፡ከዚህ ቀደም ደን ተመንጥሮ ወደ90ሺ ሄክታር መሬት ለባለሀብቶች ቢሰጥም ውጤት የሚያመጣ ልማት ግን አልተከናወነም፡፡አብዛኛው መሬት የተሰጠው ደግሞ መተከልና ካማሺ ዞኖች ውስጥ ነው፡፡በአካባቢዎቹ የተፈጠረው የፀጥታ ሁኔታ ደግሞ ልማቱን ስላስተጓጎለው የሚፈለገው ውጤት ሊመጣ አልቻለም፡፡በአሁኑ ጊዜም ለልማቱ ተመንጥሮ የተሰጠው ቦታ መልሶ ቀርከሃ በቅሎበታል፡፡
ክልሉ የደን ሀብት ባለቤት ቢሆንም በተደጋጋሚ ለሳት ቃጠሎ እየተጋለጠ ጉዳት እየደረሰበት እንደሆነም ይነገራል፡፡አቶ ባብከርም እውነታውን አልሸሸጉም፡፡እርሳቸው እንዳሉት የቃጠሎ አደጋው በየአመቱ ያጋጥማል፡፡በክርምት ወቅት መልሶ የሚያገግም በመሆኑ እንጂ ጉዳቱ ከፍተኛ ይሆን ነበር፡፡ማስቆምም አልተቻለም፡፡መንስኤዎቹም ይታወቃሉ፡፡ለአካባቢው ማህበረሰብ በተለይም ለአርሶአደሩ ደንን መጠበቅና መንከባከብ እንደሚገባ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ይሰጣል፡፡ግን ተግባራዊ አፈፃፃሙ ደካማ በመሆኑ ደኑን ከቃጠሎ ማዳን ወይንም መታደግ አልተቻለም፡፡በተለይም በህዳርና ታህሳስ ወራቶች አሁን በክረምቱ ወራቶች ተራራውና ሸለቆው ወንዙ ሳይቀር እጅግ ውብ የሆነው አረንጓዴ በእሳት ይጠፋል፡፡ለቃጠሎው በምክንያትነት ከሚጠቀሱት መካከል አንዱ ክልሉ የመአድን ወርቅ መገኛ በመሆኑ በወርቅ ፍለጋ ላይ የተሰማሩ ወርቅ ለመፈለግ ሲሉ ደኑን ያቃጥላሉ፡፡ሌላው መንስኤ ለማገዶ የሚውል ከሰል በስፋት በማክሰል የመጠቀም ሁኔታ ነው፡፡በድንበር በኩልም ከሱዳን አካባቢ በተመሳሳይ እሳት ይነሳል፡፡በፀጥታ ምክንያት የሚፈጠር ችግርን ለመቋቋም ሲባልም አንዳንዴ የሚቃጠልበት ሁኔታ ይኖራል፡፡እንዲህ ያሉ መንስኤዎች እየተለመዱ መምጣታቸው በመከላከሉ ሥራ ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል፡፡ተግዳሮቱ የበዛ ቢሆንም የመከላከሉን ሥራ ለማጠናከር የሚደረገው ጥረት አይቋረጥም፡፡በክልሉ አሶሳ ዞን በሁለት ወረዳዎች ውስጥ መልካም ተሞክሮ ተጀምሯል፡፡የአካባቢው ሴቶችና ወጣቶች ተደራጅተው በአካባቢው የሚበቅለውን ሳቫና የተባለ የሳር ዝርያ ከአንድ ሄክታር እስከ 120 ኩንታል ሳር በማግኘት የተለያየ ግብአት ጨምረው ለከብት መኖ ገበያ ላይ በማቅረብ በመጠቀም ገቢ እያገኙ ነው፡፡ጥቅሙን ስለተገነዘቡም ሳሩ በእሳት ቃጠሎ እንዳይጎዳ እየጠበቁ ይገኛሉ፡፡አጭደው የተጠቀሙትንም መልሶ በማልማት በመተካት የእንክብካቤ ሥራም አጠናክረዋል፡፡በዚህ የተነሳም በአካባቢው ቃጠሎ ቀንሷል፡፡የእነርሱን ተሞክሮ ቀምሮ በሌሎችም አካባቢዎች በተደረገ እንቅስቃሴ ለውጦች በመታየት ላይ በመሆናቸው በዚህ መልኩ አረንጓዴ ልማቱን ከእሳት ቃጠሎ ለመታደግ ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡እስካሁንም በእንቅስቃሴው እስከ አራትሺ ሄክታር መሬት ለመሸፈን ተችሏል። ሌላው በደን ላይ የሚደርስ ቃጠሎን ለመከላከል የተሞከረው ሥራ ወጣቶች በክልሉ ካለው የእጣን ሀብት እንዲጠቀም በማድረግ ነው፡፡እስካሁን 34 የወጣት ማህበራት ተደራጅተዋል፡፡ወጣቶቹ ከእጣን ሽያጭ ገቢ ስለሚያገኙና ሀብትም ስለሚያፈሩበት እጣን የሚያመርተው ዛፍ በቃጠሎ እንዳይወድም ይከላከላሉ፡፡እጣን የሚያመርት ችግኝም በመትከል የእንክብካቤ ሥራ ይሰራሉ፡፡ጅምሩም አበረታች በመሆኑ ውጤት እንደሚያስገኝ ተስፋ አሳድሯል፡፡በከማሺና አሶሳ ላይ ያጋጠመው የፀጥታ መደፍረስ እንቅስቃሴውን ቢያቀዛቅዘውም ጥቅሙ ከፍተኛ እንደሆነ ግንዛቤ ተይዟል፡፡ዋንዛና ሌሎች ሀገር በቀል ዝርያ ያላቸውን ዛፎች ለግንባታና ለተለያየ ለኢንደስትሪ ግብአት በማዋል አርሶ አደሩ እንዲጠቀም የተጀመረው ሥራም በተጨማሪ የመከላከሉን ሥራ እያገዘ ይገኛል፡፡በዚህ መልኩ በባለሙያ የታገዘ ስልጠና በመስጠትና ግንዛቤም በመፍጠር የአካባቢውን ማህበረሰብ የኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያሳደጉ መሄድ ካልተቻለ እስካሁን በተኬደበት መንገድ መኖሪያቤት ይቃጠላል፡፡ሰውና እንስሳ ይጎዳል.እህል ይጠፋል በሚል የመከላከሉን ሥራ ውጤታማ መሆን እንደማይቻል ወይንም ውጤት እንደማያስገኝ ከተደረጉት ጥረቶች መረዳት ተችሏል፡፡
አካባቢው ላይ ስለደን ልማት ሳይሆን፣ስለሰብል ልማት ቢነሳ የተሻለ እንደሆነ ከአቶ ባብከር ለመረዳት ችያለሁ፡፡ይህም ሆኖ አረንጓዴ ልማቱ አልተቋረጠም፡፡ቀደም ሲልም ሆነ አሁንም በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር የተለያዩ የዛፍ ችግኞች በመተከል ላይ ናቸው፡፡አረንጓዴ ልማቱ አትክልትና ፍርፍሬ ልማትንም ባካተተ ቢከናወን ኢኮኖሚያዊ ጥቅምን ስለሚያስገኝ በዚህ ረገድ ስላለው እንቅስቃሴ፣እንዲሁም አካባቢን መሠረት ያደረገ የዛፍ ችግኝ ተከላ መርሃግብርን በማከናወን ረገድም የተደረገውን ጥረት እንዲገልጹልኝ ላቀረብኩት ጥያቄ አቶ ባብከር በሰጡት ምላሽ፤ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያላቸውን ቡናን ጨምሮ እንደ ማንጎ አቡካዶ ያሉ ለምግብነት የሚውሉ ፍራፍሬዎች ልማት እንዲከናወን ጥረት እየተደረገ ነው ማህበረሰቡም በአረንጓዴ የዛፍ ችግኝ ተከላ መርሃግብር ላይ ሲሳተፍ በዚህ መልኩ እንዲንቀሳቀስ ነው እየተደረገ ያለው። ከ60 እስከ 70ሺ የሚሆኑ የሱዳን ስደተኛ ዜጎች በሰፈሩበት በአሶሳ ዞን ውስጥ ባኦከሞን ጨምሮ በአምስት አካባቢዎች የልማት ሥራ በማከናወን መሸፈን ተችሏል፡፡ከከልሉ አካባቢዎች በስደተኞቹ መኖሪያ አካባቢ የተራቆተ በመሆኑ የፍራፍሬ ልማትን ማዕከል ያደረገ አረንጓዴ ልማት መከናወኑ ስደተኞቹ የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አግዟል፡፡ክልሉ በማንጎ ልማት በስፋት የሚታወቅ በመሆኑ በኩታ ገጠም ልማት ጭምር የትኩረት አቅጣጫው ማንጎ ላይ ቢሆንም ቡና በሚለማባቸው አካባቢዎችም የቡና ችግኝ ተተክሏል፡፡አካባቢን መሰረት ያደረገ የዛፍ ችግኝ ተከላን በተመለከተም በምላሻቸው በክልሉ ወይናደጋ፣ቆላማ፣እንዲሁም በሱዳን ድንበር አካባቢም ከአዋሳኝ ሀገሩ ጋር የሚመሳሰል የአየርፀባይን ባገናዘበ ነው የዛፍ ችግኞች ተከላ መርሃግብሩ በመከናወን ላይ የሚገኘው፡፡ከተክል አይነቶችም ቀርከሃ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ይስማማዋል፡፡ከፍራፍሬ ደግሞ ማንጎ ይጠቀሳል፡፡
አቶ ባብከር በአጠቃላይ በክልሉ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ በጠንካራና በክፍተተት ካነሷቸው መካከልም የአካባቢው ማህበረሰብ የዛፍ ችግኝ ተከላ መርሃግብሩ ላይ የሚያደርገውን ተሳትፎ በእንክብካቤው ላይም በተመሳሳይ እንዲፈጽም ተከታታይ የሆነ ግንዛብ መፍጠር፣ችግኝ በማፍላት ላይም ያልደረሱ ችግኞችን ለተከላ ማቅረብ፣ችግኝ በማፍላት ሥራ ላይ ለተሰማሩ በቂ የሆነ በጀት በመመደብ የሚጠናከሩበት ሁኔታ በመፈጠር ላይ ያሉ ቀሪ የቤት ሥራዎች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
የክልሉ የአካባቢ የአረንጓዴ ልማት ከእሳት ሰደድና ከተለያየ ጉዳት እንዲጠበቅ የክትትልና ቁጥጥር ሥራ የሚያከናውን የአካባቢ ደን ሀብት ጥበቃና የአየርንብረት ለውጥ ክፍል ቢኖርም አደረጃጀቱ ከክልሉ የገጠር መሬትና ኢንቨስትመንት ሥር መሆኑ የቁጥጥርና ክትትል ሥራውን በአግባቡ ለመወጣት አላስቻለውም። በመሆኑም ካለፈው አንድ አመት ጀምሮ እራሱን ችሎ ባለሥልጣን መስሪያቤት ሆኖ ተደራጅቷል፡፡በአደረጃጀት ምክንያት ሳይንቀሳቀስ የቆየው ይህ ክፍል ባለሥልጣን ከሆነ ወዲህስ ከተቋቋመለት ዓላማ አኳያ ምን ተግባራትን አከናወነ? የባለሥልጣኑን ኃላፊ አቶ አብዱልከሪም ሙሳመሐመድን ጠይቄያቸው በሰጡት ምላሽ፤አብዛኛው ሥራ ለቀጣይ የሥራ የክትትልና ቁጥጥር ሥራ በሚያግዙ የአሰራር አቅጣጫዎች ላይ በጥናት የተደገፈ እንቅስቃሴ ላይ ነው ትኩረት የተደረገው። የጥናት መዋቅሩም የአካባቢ፣የደን፣የአየርንብረት ለውጥ ዘርፎችን መለየት፣እንዲሁም እያንዳንዱ ዘርፍ የሚያከናውናቸው ዝርዝር ተግባራት፣ለአብነትም በደን ዘርፍ የደን ጥበቃ፣ክትትልና ቁጥጥር፣የደን ውጤቶች ክትትልና ዝግጅት፣በአካባቢ ዘርፍ ደግሞ የአካባቢና ማህበራዊ ተጽዕኖ ግምገማ ይጠቀሳል፡፡ወደ ሥራ ከተገባ በኃላም የክትትልና ቁጥጥር ሥራው በምን መልኩ መፈጸም እንዳለበት፣በሥራ የተገኘ ለውጥ በተለይም ማህበረሰብ ላይ ያስገኘውን በጎ ነገር በጥናቱ ተካትቷል፡፡ጥናቱ በጀትንም ያካተተ ሲሆን፣ጥናቱ የማህበረሰብ ተጠቃሚነትንም ማዕከል ያደረገ በመሆኑ በአስፈላጊነቱ ላይ ለማህበረሰብ ውይይት ቀርቧል፡፡በክፍሉ በኩል የተደረገው የሥራ የመዋቅር ጥናትም ጸድቆ እንዲተገበር ለክልሉ ሲቪልሰርቪስ ቀርቦ ምላሽ እየተጠበቀ ነው፡፡በ2014 በጀት አመት ሙሉ ለሙሉ ወደተግባራዊ ሥራዎች በመግባት ጥናቱን መሠረት ያደረገ ሥራዎች ለመሥራት በባለሥልጣኑ በኩል ዝግጅት ተደርጓል፡፡
ለምለም መንግሥቱ