ሰለሞን በየነ
ከ1960ዎቹ መጨረሻ በፊት በውጭ አገር የመማር ዕድል ገጥሟቸው ወደ አውሮፓና ሌሎችም አህጉሮችና አገሮች የሄዱ ምሁራን፣ የጦር መኮንኖችም ሆኑ የመንግሥት ሠራተኞች ትምህርታቸውን ሲጨርሱ የሚጣደፉት ወደ አገር ቤት ለመመለስ ነበር። ብዙዎች እንደሚስማሙበት ያቺ ዜጎች ሊሰበሰቡባት ይናፍቋት የነበረችን ምድር የደምና የጥላቻ ፖለቲካ የዘሩባት የ60ዎቹ የቀይና የነጭ ሽብር ተዋንያን መዘዝ ሁኔታውን ቀየረው። ኢትዮጵያ በስደት የተበላሸ ታሪክ ማስመዝገብ ጀመረች።
በወቅቱ ደርግ ወደ ሥልጣን የመጣው ሕዝባዊ አብዮትን ተንተርሶ እንደመሆኑ በንጉሣዊያኑ ጎራ፣ በኢሕአፓ፣ በመኢሶንም ሆነ በሌሎች የፖለቲካ ማዕቀፎች የተሠለፉ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች አገር ጥለው ተሰደዋል። ሞትና የአካል መጉደል የዕለት ተዕለት ክስተት በሆነበት ሁኔታ ስደት የተሻለው አማራጭ በመሆኑ በአብዛኛው በሕገወጥ መንገድ በባሌ፣ በሞያሌና በመተማ ብቻ ሳይሆን በጂቡቲና በአሰብ ወደቦች ሳይቀር የዚያ ትውልድ ክፋዮች በብዛት ተሰደዱ።
ዶክተር አብዱሰላም ሁሴንና ባለቤታቸው ወይዘሮ ነጅሃ አብዱል ሰመድ በደርግ ዘመን ይደርስ በነበረው ግፍና መከራ አገራቸውን ጥለው ባህር አቋርጠው ወደ አሜሪካ ከተሰደዱ ኢትዮጵያዊያን መካከል ናቸው። ተወልደው ያደጉት በምስራቋ ፀሀይ ድሬደዋ ከተማ ነው። ዶክተር አብዱሰላም በስደት ወደ አሜሪካ ካቀኑ በኋላ ከካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ቢ.ኤስ.ሲ ዲግሪያቸውንና ሜዲካል ዶክትሬታቸውን አግኝተዋል። እርሳቸውም እ.ኤ.አ. ከ1993 ጀምሮ በአሜሪካ በህክምና ሙያ ተቀጥረው እስካሁን ድረስ እያገለገሉ ይገኛሉ። እንዲሁም ባለቤታቸው ወይዘሮ ነጅሃ የላቦራቶሪ ክሊኒክላል ሳይንቲስት ሲሆኑ፤ በዛው በአሜሪካ እርሳቸውም በሙያቸው ተቀጥረው እያገለገሉ ቆይተዋል።
የአገራቸውን ፍቅር በልባቸው ይዘው በስደት ይኳትኑ የነበሩት እኚህ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በአካል ቢርቁም መንፈሳቸው ሁልጊዜም ኢትዮጵያ በመሆኑ፤ ከደርግ ውድቀት በኋላ አገራቸውን የመጎብኝት እድል አግኝተው ከዓመታት የስደት ኖሮ ወደ ትውልድ ቀያቸው የምስራቋ ጮራ ድሬደዋ ጎራ ይላሉ። በጉብኝታቸው ወቅት በአገሪቱ ብሎም በትውልድ ቀያቸው የተዘባ ጥራቱ የተጓደለ የጤና አገልግሎት በእጅጉ ልባቸውን ይነካዋል። በዚህም ምንም እንኳን በሚኖሩበት አሜሪካን አገር ሁለት ልጆች ወልደው ቅንጡ ኖሮን የሚኖሩ ቢሆንም፤ ሳይማር ያስተማራቸውን ማህበረሰብ በተማሩበት ሙያ ዝቅ ብለው ማገልገልና የአገሪቱን የጤና ዘርፍ ባላቸው እውቀት መደገፍ እንዳለባቸው ይወስናሉ።
በትውልድ ቀያቸው በምስሯቋ ጮራ ድሬደዋ ከተማ በተመጣጣኝ ዋጋ ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት የሚሰጥ ሆስፒታል ለመገንባት የኢንቨስትመንት ቦታ በተደጋጋሚ ቢጠይቁም ሰሚ ያጣሉ። በ1996 ዓ.ም የእናትና አባታቸውን መኖሪያ ቤት አፍርሰው 50 ተኝቶ መታከሚያ ክፍል ያለው ቢላል ሆስፒታልን በድሬደዋ ከተማ ልዩ ስሙ ኮኔል በተባለ ቦታ ገነቡ።
ጥር 1 ቀን 1996 ዓ.ም የወቅቱ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ወይዘሮ ኦሬሊያ ብራዜል በቦታው ተገኝተው አስመረቁት። ሆስፒታሉ ወደ ስራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ በተመጣጣኝ ዋጋ ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት በመስጠት ለምስራቁ የኢትዮጵያ ክፍል ብቻ ሳይሆን ለጎረቤት አገሮች ጅቡቲ እና ሶማሊያ እንደ ሪፈራል ሆስፒታል ሆኖ ማገልገል መጀመሩን ዶክተር አብዱሰላም ይናገራሉ።
እንደዶክተር አብዱሰላም ገለፃ፤ ሆስፒታሉ ከ140 በላይ ሰራተኞች ቋሚ የስራ ዕድል ከመፍጠሩ ባሻገር፤ ህብረተሰቡ ዓርብ ዓርብ 10 ብር ብቻ የካርድ ከፍሎ ሙሉ ምርመራ እንዲያገኝ በማድረግ በተመጣጠነ ዋጋና በነጻ በሚባል መልኩ ጥራት ያለው ህክምና እንዲያገኝ ማድረጉን ቀጠሉ። እንዲሁም ድርጅቱ ከ500 በላይ የኤች.አይ.ቪና የቲቢ ህሙማንን ከመንከባከብ ባሻገር ከ20 በላይ ወላጅ አልባ ህጻናትን ይዞ በማስተማር እስከ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ለመከታተል የበቁ ልጆችን አፍርቷል።
በተጨማሪ ሆስፒታሉ በ2009 ዓ.ም ኤሌክትሮኒክስ የጤና መረጃ አያያዝ ስርዓትን በድሬደዋ ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ በማድረግ ተሸላሚ ለመሆን የበቃ ሲሆን፤ በዚህም ሆስፒታሉ መንግስታዊና መንግስታዊ ላልሆኑ የጤና ተቋማት የተለያዩ የላቁ ተሞክሮዎችንና ቴክኖሎጂዎችን በማካፈል የአገሪቱ የጤናው ዘርፍ እንዲዘምን የበኩሉን አስተዋጽዖ እያበረከተ ይገኛል። እንዲሁም የድርጅቱ ባለቤቶች እንደ አንድ ተራ ተቀጣሪ ሰራተኛ ሆነው በካበተ ልምድና እውቀታቸው ህብረተሰቡን ወርደው ከማገልገል ባለፈ ከሚሰሩበት አሜሪካን አገር ነጻ የህክምና አገልግሎት የሚሰጡ ብቃት ያላቸውንና የበቁ ዶክተሮችን በማምጣት ህብረተሰቡ ጥራት ያለው ህክምና በነጻ እንዲያገኝ የማድረግ ስራ እየሰሩ መሆኑንም ይገለፃሉ።
በአጠቃላይ ሆስፒታሉ ባለፉት 17 ዓመታት የተለያዩ ፈተናዎችን በመጋፈጥ ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ ከመስጠት ጎን ለጎን የተለያዩ ማህበራዊ ኃላፊነቶችን ሲወጣ ቆይቷል። ነገር ግን አሁን ላይ የድርጅቱ ባለቤቶች የቆሙለትን ራዕይ ወደ ጎን በመተው ሆስፒታሉን ለመዝጋት የሚያስገድድ ችግር ስለደረሰ ሰራተኞቹን በመበተን ሆስፒታሉን እ.ኤ.አ እስከ መጋቢት 31/2020 ድረስ ለመዝጋት የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እየሰሩ እንደሚገኙ የሆስፒታሉ አስተዳደር አቶ ዘመድኩን አበበ ለዝግጅት ክፍላችን ገልጸዋል።
ውድ አንባቢዎቻችን እኛም ለዝግጅት ክፍላችን የቀረበውን ቅሬታ መነሻ በማድረግ ሆስፒታሉ ባለፉት 17 ዓመታት የደረሱበትን ችግርና አሁን ላይ ወደ መዘጋት ደረጃ ያደረሰው ምክንያት ምን ይሆን ስንል የሆስፒታሉን አቤቱታ፣ የግራና ቀኙን ሃሳብ እንዲሁም የሚመለከተውን አካል ምላሽና የጽሁፍ ማስረጃዎች ፈትሸን እንደሚከተለው ይዘንላችህ ቀርበናል።
የቢላል ሆስፒታል ባለቤቶች ድርጅቱን ለመዝጋት ውሳኔ ላይ ያደረሳቸው ምን ይሆን?
የቢላል ሆስፒታል አስተዳዳሪ አቶ ዘመድኩን አበበ በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት አሜሪካዊ በሆኑ ሁለት ባልና ሚስት (ዶክተር አብዱሰላም ሁሴንና ወይዘሮ ነጅሃ አብዱልሰመድ) ስም የተቋቋመ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሆስፒታል መሆኑን ይናገራሉ። ግለሰቦቹ ሆስፒታሉን ግንባታውን በ1993 ዓ.ም አስጀምረው ጎን ለጎን ደግሞ የተለያዩ የህክምና ቁሳቁሶችን ከውጭ አገር በማስገባት ግንባታውን በ1996 ዓ.ም አስጨርሰው ወደ ስራ ገብተዋል።
ሆስፒታሉም ወደ ስራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ባለፉት 17 ዓመታት የተለያዩ ፈተናዎችን በመጋፈጥ ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ ከመስጠት ጎን ለጎን የተለያዩ ማህበራዊ ኃላፊነቶችን እየተወጣ እንደሚገኝ አቶ ዘመድኩን ገልጸው፤ ከዚህ በተጨማሪ ሆስፒታሉ በዓመት ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ ግብር ለመንግስት እንደሚያስገባ ተናግረዋል።
እንዲሁም የሆስፒታሉ ባለቤቶችም ከ20 ዓመት በላይ በአሜሪካን አገር በህክምና ሙያ ላይ ተቀጥረው ባካበቱት ልምድና እውቀት ሳይማር ያስተማራቸውን ማህበረሰብ በራሳቸው ድርጅት ዝቅ ብለው ተቀጥሮ እንደሚሰራ አንድ ተራ ሰራተኛ በማገልገል ጥራት ያለው ህክምና በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ እያደረጉ ይገኛሉ። ዶክተር አብዱሰላም የውስጥ ደዌ እስፔሻሊስት ስለሆኑ ህሙማንን ያክማሉ።
ወይዘሮ ነጅሃ ደግሞ የላቦራቶሪ ባለሙያ ስለሆኑ የላቦራቶሪ ስራቸውን ያከናውናሉ። ከስራ ሰዓታቸው ካረፈዱ እንኳን እንደማንኛውም ሰራተኛ ከደመወዛቸው ይቆረጣል። በዚህ መልኩ በውጭ አገር የቀሰሙትን የካበት ልምድና እውቀት በአገር ውስጥ ለሚገኙ የጤና ባለሙያዎች በማካፈል ለአገሪቱ የጤና ዘርፍ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እያበረከቱ ይገኛሉ። እንዲሁም ጠንካራ የስራ ባህል ለህብረተሰቡ እያስተማሩ እንደሚገኙም ይናገራሉ።
ነገር ግን የሆስፒታሉ ባለቤቶች በቅንጦት ከሚኖሩበት አሜሪካን አገራቸውን በሙያቸው ለማገልገል ‹‹ሀ›› ብለው ሲመለሱ ፈተና እንደገጠማቸው የሚናገሩት አቶ ዘመድኩን፤ በተመጣጣኝ ዋጋ ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም በትውልድ ቦታቸው ለመገንባት የኢንቨስትመንት ቦታ ይሰጠን በሚል በተደጋጋሚ ለድሬዳዋ አስተዳደር ጥያቄ ቢያቀርቡም መልስ የሚሰጣቸው አካል ባለማግኘታቸው፤ የእናት እና የአባታቸውን ቤት አፍርሰው በቤተሰቦቻቸው ይዞታ ላይ ሆስፒታሉን መገንባታቸውን ይናገራሉ።
ሆስፒታሉም እየሰጠ ከሚገኘው ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት አንጻር ቢያንስ በቀን ከ250 እስከ 300 ታካሚ የሚያስተናግድ በመሆኑ ሆስፒታሉ ያሉት ተኝቶ መታከሚያ ክፍሎች በመጣበባቸው ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ የኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ቦታ ይሰጠን በሚል አመልክተዋል። ነገር ግን ከአምስት ጊዜ በላይ የኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ቦታ ይሰጣቸው ብሎ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ቢወስንም እስካሁን ድረስ ተፈጻሚነት ሳያገኝ 12 ዓመታት መቆጠሩን አስተዳዳሪው ተናግረዋል።
ከእነርሱ በኋላ ሌሎች ድርጅቶች የኢንቨስትመንት ቦታና ማስፋፊያ የጠየቁ እንደተሰጣቸው አቶ ዘመድኩን ገለጸው፤ ይሄም የሆስፒታሉን ባለቤቶች እንዳሳዘናቸው ይናገራሉ። አቶ ዘመድኩን አክለውም ሆስፒታሉ የፌዴራል ግብር ከፋይ ድርጅት በመሆኑ ሁሉም የፌዴራል ተቋማት መቀመጫቸው አዲስ አበባ ስለሆነ የተለያዩ አገልግሎቶችን ለማግኘት አዲስ አበባ መሄድ ግድ ይላል። ስለዚህ ትንሽም ሆነ ትልቅ የህክምና ቁሳቁስና መድሃኒት ሲያስገባ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የግድ አዲስ አበባ ተወስዶ በፌዴራሉ ጉምሩክ ባለስልጣንና የምግብና መድኃኒት ባለስልጣን መፈተሽና መቀረጥ ግዴታው ነው።
ሆስፒታሉ የሚያስገባቸውን እቃዎች ከወደብ በቀጥታ በከተማ አስተዳደሩ ጉምሩክ ባለስልጣንና የምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ተቀርጦና ተፈትሾ ማስገባት እየቻለ የግድ እቃው አዲስ አበባ ተወስዶ ከ10 እስከ 15 ቀን ፍተሻ ሲደረግ፤ ሆስፒታሉን ለእንግልትና ለወጭ ከመዳረጉ በላይ የህክምና ቁሳቁሶችና መድሃኒቶች ከጥቅም ውጭ ሲሆኑ ቆይተዋል። እቃዎቹም ከወደብ ወደ አዲስ አበባ እንዲሁም ከመዲናው ወደ ድሬዳዋ የሚመላለስበት የትራንስፖርት ወጪ አገርንና መንግስትን ለኪሳራ እየዳረገ እንደሚገኝ አስተዳዳሪው ይናገራሉ።
ያም ሆኖ በጥቅሉ ባለፉት 17 ዓመታት ሆስፒታሉ የተለያዩ ችግሮችን በመጋፈጥ ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት እያቀረበ የሚገኝ ቢሆንም፤ ግልጽነት በጎደለው መንገድ ዘጠኝ ሚሊዮን ብር ገደማ ባለቤቶቹ የግብር እዳ ውሳኔ ክፈሉ በመባላቸው ሆስፒታሉን ለመዝጋት መወሰናቸውን ይናገራሉ።
ሆስፒታሉ የተጣለበት የግብር እዳ ፍትሃዊም ተገቢም አለመሆኑን የሚናገሩት አቶ ዘመድኩን፤ ሆስፒታሉ ከ2009 እስከ 2011 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ጠቅላላ የትርፍ ግብር 4 ሚሊዮን እና የስራ ግብር 4 ሚሊዮን 627 ሺ 930 የሚከፍሉ ከ135 በላይ ሠራተኞችን ይዞ እንደነበር ይናገራሉ። ሆስፒታሉ በቋሚነት ቀጥሮ ከሚያሰራቸው የህክምና ባለሙያዎች በተጨማሪ የሆስፒታሉን አገልግሎት ጥራት ያለውና ሙሉ ለማድረግ ከፍተኛ ልምድና እውቀት ያላቸውን የህክምና ባለሙያዎችን በመንግስት ሆስፒታል ወይም ዩኒቨርሲቲ ቋሚ ሰራተኛ የሆኑ በትርፍ ጊዜያቸው በሆስፒታሉ እንዲሰሩ ውል በመዋዋል አገልግሎት እየሰጡና ተገቢውን ክፍያ በውሉ መሰረት እየተከፈላቸው መቆየቱን አስተዳዳሪው ያስታውሳሉ።
አቶ ዘመድኩን በሆስፒታሉ በትርፍ ጊዜያቸው ተቀጥረው ለሚሰሩ ሰራተኞችም ክፍያው የሚፈጸምላቸው በቁጥር 3.0/487 መጋቢት 27 ቀን 2006 ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን በተላለፈ መመሪያ መሰረት በተ.ቁ 2 እንደተገለጸው ‹‹አንድ መስሪያ ቤት ወይም ድርጅት ተቀጣሪ የሆኑ ግለሰቦች በትርፍ ጊዜያቸው ለሌላ መስሪያ ቤት ወይም ድርጅት አገልግሎት ለመስጠት ውል ፈርመው በሚያገኙት ገቢ ላይ በመቀጠር የተገኘ ገቢ ነው ሊባል ስለማይቻል ቅድመ ግብር ከፋይ ቀንሰው እንዲያስቀሩ ኃላፊነት የተሰጣቸው አካላት አገልግሎቱን ያቀረቡ ባለሙያዎች የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር (TIN) ካላቸው ሁለት በመቶ ከሌላቸው 30 በመቶ ቀንሰው ለግብር ሰብሳቢ መስሪያ ቤት እንዲያስገቡ›› መመሪያው በሚያዘው መሰረት ሆስፒታሉ ሲፈጽም መቆየቱን ያስረዳሉ።
ሆስፒታሉም በትርፍ ጊዜያቸው ተቀጥረው ለሚሰሩ ሰራተኞች በዚህ መልኩ ክፍያ እየፈጸመ እያለ ከትርፍ ጊዜ ክፍያ ጋር ተያይዞ የተቋማት አሰራር ጉራማይሌ በመሆኑና አንዳንድ ግልጽ ያልሆኑ አሰራሮች በመኖራቸው፤ የትርፍ ጊዜ ክፍያን በተመለከተ ግልጽ የሆነ መመሪያ በጽሁፍ እንዲሰጣቸው ሆስፒታሉ በቁጥር BH/507/2019 በ4/4/2019 በተጻፈ ደብዳቤ በገቢዎች ሚኒስቴር የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤትን መጠየቁን አቶ ዘመድኩን ገልጸዋል።
እርሳቸው እንዳብራሩት፤ በደብዳቤ በቁጥር 3.0/487 መጋቢት 27 ቀን 2006 ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን በተላለፈ መመሪያ መሰረት በተ.ቁ 2 እንደተገለጸው በቋሚነት ተቀጥረው ከሚሰሩበት መስሪያ ቤት ውጭ በትርፍ ጊዜያቸው ለሰሩት ክፍያ ሲፈጸም ግብር ተቀንሶ የማስቀረት ኃላፊነት የአሠሪው አካል መሆኑን በመግለጽ የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር (TIN) ካለው 2 በመቶ ከሌለው 30 በመቶ ተቀንሶ ለታክስ ገቢ ሰብሳቢ መግባት አለበት ሲል፤ በሌላ በኩል የገንዘብ ሚኒስቴር ባወጣው ቅድመ ግብር ክፍያ ስርአት አፈጻጸም መመሪያ ላይ ደግሞ የሥራው ዓይነት ከቅጥር ጋር ግንኙነት የሌለው አገልግሎት ከሆነ የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር እና የንግድ ስራ ፈቃድ ሲያቀርብ ከክፍያው 2 በመቶ ቅድመ ግብር ተቀናሽ ሲደረግ ሁሉንም ማቅረብ ካልቻለ 30 በመቶ ቀንሶ መክፈል ያለበት መሆኑን ይገልጻል።
ከዚህ አንጻር በቋሚነት በዩኒቨርሲቲዎችና በመንግስት ሆስፒታሎች ተቀጥረው የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች በትርፍ ሰዓታቸው ከሆስፒታሉ ጋር ውል በመፈጸም የሚያገለግሉ ሲሆን፤ ከነዚህ ውስጥ የግብር መለያ ቁጥር እና የሙያ ምዝገባ ያላቸው ሲኖሩ የተወሰኑት ደግሞ የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር ብቻ ያላቸው አሉ።
ስለዚህ የግብር ህጉ የሚጠይቀውን ለመፈጸም ግራ ስለተጋቡ በሌሎች የመንግስትና የግል ሆስፒታሎች እንዲሁም ዩኒቨርሲቲዎች ተቀጥረው በማገልገል ላይ የሚገኙ የግብር ከፋይ መለያ ቁጥርና የሙያ ምዝገባ ፈቃድ ያላቸው በሌላ በኩል የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር ኖሯቸው የንግድ ምዝገባ ፈቃድ የሌላቸውን በትርፍ ጊዜያቸው በሆስፒታሉ ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞችን በምን መልኩ ማስተናገድ እንዳለባቸው ግልጽ የሆነ መመሪያ እንዲሰጣቸው በሚል ሆስፒታሉ በደብዳቤ መጠየቁን ይናገራሉ።
ነገር ግን ሆስፒታሉ በደብዳቤ ለጠየቀው ማብራሪያ ምንም አይነት ምላሽ ከጽህፈት ቤቱ እንዳልተሰጣቸው አቶ ዘመድኩን ገልጸው፤ የሆስፒታሉ ባለቤቶች ከ2009 እስከ 2011 ዓ.ም ድረስ ያለው ሂሳብ ኦዲት ይደረግልን ሲሉ በጠየቁት መሰረት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ በተያዘው በጀት ዓመት የሶስት ዓመት የሂሳብ ምርመራ ማድረጉን ይናገራሉ።
ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱም የሆስፒታሉን ሂሳብ ከ2009 ጀምሮ እስከ 2011 ዓ.ም ድረስ መርምሬ አገኘሁት ባለው የኦዲት ግኝት መሰረት በትርፍ ጊዜያቸው ተቀጥረው የሚሰሩ የህክምና ባለሙያዎች ላይ መቆረጥ የነበረበት የስራ ግብር 2 በመቶ ሳይሆን 30 በመቶ ስለነበር ለባለሙያዎች የተከፈለውን 28 በመቶ ሆስፒታሉ መክፈል አለበት በሚል 9 ሚሊዮን ብር ገደማ የግብር እዳ ውሳኔ ሆስፒታሉ ላይ እንደተጣለበት ይናገራሉ።
ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ በገቢ ግብር ማሳወቂያ ላይ እንዲከፍሉ የተጣለባቸው ውሳኔ ከፍተኛ እና የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/2008 እና የግብር ማስፈጸሚያ ደንብ ቁጥር 983/2008 ያላገናዘበ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ዘመድኩን፤ ከሰራተኞች የትርፍ ጊዜ ክፍያ ጋር በተያያዘ ግልጽ የሆነ መመሪያ በጽሁፍ እንዲሰጣቸው በቁጥር BH/507/2019 በ4/4/2019 በተጻፈ ደብዳቤ ጠይቀው መልስ ሳይሰጣቸው ከመቆየታቸውም በላይ የትርፍ ጊዜ የሰራተኞች የስራ ግብር 2 በመቶ ቅድመ ክፍያ ሆስፒታሉ ከሶስት ዓመት በላይ ሲያስገባ ገቢው ትክክል እንደሆነ ወስዶ ጽህፈት ቤቱ በየወሩ ሲቀበል ቆይቶ አሁን ላይ ‹‹ኦዲት አድርጉን›› ተብሎ ሲጠየቅ ለቅጣት መንደርደር ቀደም ብሎ ሆስፒታሉን ለመቅጣት የታሰበ ሴራ መኖሩን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ መሆኑን አቶ ዘመድኩን ተናግረዋል።
አቶ ዘመድኩን ሆስፒታሉም ታህሳስ 05/2012 ዓ.ም የተጣለበትን የግብር እዳ ውሳኔውን በመቃዎም ለታክስ ውሳኔ ቅሬታ አጣሪ ጽህፈት ቤት አቤቱታ ማቅረቡን ጠቅሰው፤ የታክስ ውሳኔ ቅሬታ አጣሪ ጽህፈት ቤቱም ሆስፒታሉ በተደጋጋሚ ማብራሪያ እንዲሰጠው ሲጠይቅ ማብራሪያ ካለመሰጠቱ ባሻገር እስካሁን 2 በመቶ ሲያስገባ ትክክል አለመሆኑ ሊገለጽ ይገባው ነበር።
ለተጠየቀውም ማብራሪያ መልስ ሊሰጠው ይገባ ነበር። ይሄ መደረግ ሲገባው ይሄንን በወቅቱ የነበሩ አመራሮች ባለማድረጋቸው መጠየቅ ባለባቸው ደረጃ የሚጠየቁ ይሆናል። ነገር ግን የገንዘብ ሚኒስቴር ባወጣው የቅድመ ግብር ክፍያ ስርጻት አፈጻጸም መመሪያ ቁጥር 2/20011 መሰረት ሁለት በመቶ ሳይሆን 30 በመቶ ቁረጡ ስለሚል ህጉ መጣስ ስለሌለበት ሆስፒታሉ የተጣለበትን የግብር ውሳኔ ሆስፒታሉ ሊከፍል ይገባል ሲል መወሰኑን ይናገራሉ።
አስተዳዳሪው የገንዘብ ሚኒስቴር በፌዴራል የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/2008 አንቀጽ 85(4)፣ አንቀጽ 99(2) እና በፌዴራል የገቢ ግብር ደንብ ቁጥር 410/2009 አንቀጽ 61 በተሰጠው ስልጣን መሰረት የቅድመ ግብር ክፍያ ስርጻት አፈጻጸም መመሪያ ቁጥር 2/20011 አንጻር በመመሪያ አንቀጽ 10 ቁጥር 4 ላይ፤ በአዋጅ ቁጥር 979/2008 አንቀጽ 92 (44) እና በደንቡ አንቀጽ 63 መሰረት ግብር ተቀናሽ የሚደረግበት ዕቃ ወይም አገልግሎት አቅራቢ የግብር ከፋይ መለያ ቁጥሩንና የጸና የንግድ ስራ ፈቃዱን ሁለቱንም ግብር ቀንሶ ለሚያስቀረው ገዥ ሊያቀርብ ካልቻለ ገዥ ለአቅራቢው ከሚፈጽመው ጠቅላላ ክፍያ ላይ 30 በመቶ ግብር ተቀናሽ ማድረግ አለበት ይላል።
በዚህ መሰረት በሆስፒታሉ በትርፍ ጊዜያቸው የሚሰሩ ባለሙያዎች አንዳንዶቹ የግብር ከፋይ መለያ ቁጥርና የጸና የንግድ ስራ ፈቃድ ሁለቱንም ባለማሟላታቸው 30 በመቶ መቆረጥ ነበረበት ከተባለ እንኳን ይህ መመሪያ ተግባራዊ የሚሆነው ከሚያዝያ 1 ቀን 2011 ጀምሮ ስለሚል በመመሪያው መሰረት ሆስፒታሉ ወደ ኋላ ያለውን ሊጠየቅ አይገባውም። ስለዚህ ሆስፒታሉ የሶስት ወር ቀሪ ግብር ብቻ ነው ሊጠየቅ የሚገባው የሚል ጥያቄ ሲነሳ የታክስ ውሳኔ ቅሬታ አጣሪ ጽህፈት ቤቱ ወደ ኋላ ሄዶ ነው መመሪያው ተግባራዊ የሚደረገው በሚል ውሳኔውን እንዳጸና ይናገራሉ።
የታክስ ውሳኔ ቅሬታ አጣሪ ጽህፈት ቤቱ ውሳኔ የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/2008 እና የግብር ማስፈጸሚያ ደንብ ቁጥር 983/2008 ያላገናዘበ ከመሆኑ ባሻገር ፍትሃዊ ያልሆነና አስተማሪ ያልሆነ ውሳኔ ነው ያሉት አስተዳደሩ፤ ድርጅቱ ቅሬታውን ለኢፌዴሪ ግብር ይግባኝ ኮሚሽን አቤት ማለቱን ተናግረዋል።
ነገር ግን ከዚህ ቀደም ለትራንስፖርት አበል ሆስፒታሉ ካወጣው ወጪ ጋር በተያያዘ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ በወጪነት አልይዝም ሲል ሆስፒታሉ ለፌዴራሉ ግብር ይግባኝ ኮሚሽን አቤት ብሎ ለትራንስፖርት ከከፈሉት ወጪ ላይ የሚጠበቅባቸውን ግብር ከፍለው በወጪነት መያዝ አለበት በሚል ውሳኔ ቢሰጥም ከሶስት ዓመት በላይ ተፈጻሚ ሳያደርግ እንደቆየ አቶ ዘመድኩን ጠቁመው፤ ‹‹የዘገየ ፍትህ እንደተከለከለ ይቆጠራል››፤ ከባለፈው የቅሬታ አፈታት ስርዓት አንጻር አሁን ላይ ይግባኝ ያሉት ጉዳይ ቅሬታው ታይቶ ውሳኔ እስኪሰጥበት ከሶስት ዓመት በላይ ሊፈጅ ከመቻሉ ባሻገር ቢወሰንላቸው እንኳን ተፈጻሚነቱ ላይ የሆስፒታሉ ባለቤቶች ጥርጣሬ እንዳደረባቸው ተናግረዋል።
በመሆኑም ባለሃብቶቹ ሳይማር ያስተማራቸውን ወገናቸውን በሙያቸው ለማገልገል መጥተው በተመጣጠነ ዋጋ ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት እየሰጡ ባለበት ጊዜ ግልጽ አሰራር ባለመኖሩ ምክንያት ቅጣት የሚጣልበት ሁኔታ ከተፈጠረ ድርጅቱን ዘግተው ወደ መጡበት አገር ለመመለስ ድርጅቱን እ.ኤ.አ እስከ መጋቢት 31/2020 ለመዝጋት የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ከወዲሁ እየሰሩ እንደሚገኝ እና ለሁሉም ሰራተኞች ቅድመ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን አቶ ዘመድኩን ተናግረዋል።
ባለሃብቶቹ እዚህ ውሳኔ ላይ መድረሳቸውን ለድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ለከንቲባ ፅህፈት ቤት፣ ለከተማዋ ገቢዎች፣ ጤና፣ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮዎች እንዲሁም ለድሬደዋ ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤትና ዲያስፖራ ጽህፈት ቤት ማሳወቃቸውን ገልጸው፤ የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በኮሚቴ ደረጃ ተዋቅረው ሆስፒታሉ ድረስ በመሄድ ስለጉዳዩ ጠይቀው ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ከመረዳታቸው ውጪ፤ ጉዳዩ እንዲያውቁት ከተደረጉ ሌሎች አካላት እስካሁን ምንም አይነት ምላሽ እንዳልተሰጠ ይገልፃሉ።
በአጠቃላይ ቢላል ሆስፒታል ለድሬደዋና አጎራባች ክልል ነዋሪዎች ተገቢውን የሕክምና አገልግሎት በመስጠት በአገሪቱ የሚታየውን የጤና ተቋማት እጥረት ለመቅረፍ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ የሚናገሩት አስተዳደሩ፤ በዚህ ችግር ምክንያት ሆስፒታሉ ለህብረተሰቡ እየሰጠ ያለውን አገልግሎት መዝጋት የለበትም። ባለሃብቶቹ ድርጅቱን ዘግተው መሄዳቸው ህዝብና መንግስትን የሚጎዳ በመሆኑ የሚመለከተው አካል ሁሉ ለችግሩ ‹‹ጆሮ ዳባ ልበስ›› ሳይል ችግሩን በቶሎ ፈትሾ መሃል ላይ ገብቶ ለችግሩ መፍትሄ በመስጠት ስምምነት የሚፈጠርበትን መንገድ ማመቻቸት ይገባል ይላሉ። ከአገር ውስጥ አልፎ ለጎረቤት አገራት እንደሪፈራል ሆስፒታል ሆኖ እያገለገለ ያለውን ተቋም ከመዘጋት መታደግ የመንግስት ኃላፊነት እንደሆነ ይናገራሉ።
በገቢዎች ሚኒስቴር የድሬደዋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት
በጽህፈት ቤቱ የታክስ ህግ ተገዥነት ስራ ሂደት አቶ መስፍን በቀለ እንደገለጹት፤ አንድ ግብር ከፋይ የግብር ህጉን አውቆ ከሚሰራው ስራ ላይ የሚጠበቅበትን የግብር ኃላፊነት እራሱ አውቆ መክፈል የግብር ከፋዩ ወይም የድርጅቱ ኃላፊነት ነው። በመሆኑም በተለይ ከፍተኛ ግብር ከፋይ ድርጅቶች የሚጠበቅባቸውን የግብር ኃላፊነት በአግባቡ ተወጥተዋል ወይስ አልተወጡም በሚል ኦዲት የሚደረግ ሲሆን፤ በዚህ አግባብ ጽህፈት ቤቱ ቢላል ሆስፒታልን ከ2009 እስከ 2011 ዓ.ም ድረስ ያለውን ሂሳብ ኦዲት ተደርጓል።
ሆስፒታሉም ኦዲት ሲደረግ ከመንግስት ሆስፒታልና ከዩኒቨርሲቲ በቋሚነት ተቀጥረው የሚሰሩ የህክምና ባለሙያዎች በሆስፒታሉ በትርፍ ጊዜያቸው የሚሰሩ ሲሆን፤ ድርጅቱም በትርፍ ጊዜያቸው ተቀጥረው ከሚሰሩ ባለሙያዎች የስራ ግብር እረዘም ላለ ጊዜ 2 በመቶ ብቻ እየቆረጠ ለመንግስት ገቢ ሲያደርግ እንደነበር አቶ መስፍን ያስረዳሉ።
በዚህም ሆስፒታሉ ከመቀጠር የሚገኘውን የስራ ግብር ማስገባት ባለበት መልኩ ለመንግስት ገቢ ሲያደርግ እንዳልነበር አቶ መስፍን ጠቁመው፤ በኢትዮጵያ የታክስ ህግ መሰረት የትርፍ ሰዓት ክፍያ የስራ ግብር ሁለት በመቶ ሳይሆን ሰራተኛው በቋሚነት ተቀጥሮ ከሚሰራው መስሪያ ቤት ከሚያገኘው ደመወዝ ላይ በትርፍ ጊዜ የሚያገኘው ገቢ ተደምሮ ታክሱ ከተሰላ በኋላ የሚመጣውን ቀሪ ሂሳብ መክፈል አለበት። ስለዚህ ሰራተኞቹ በሚኖራቸው የገቢ ደረጃ መሰረት የትርፍ ሰዓት ክፍያ የስራ ግብር ከ10 በመቶ እስከ 35 በመቶ የሚቆረጥ ነው። ገቢያቸው እያደገ ሲሄድ አብሮ የሚቆረጠው ታክስ እያደገ እንደሚሄድ ባለሙያው ያስረዳሉ።
ስለዚህ በሆስፒታሉ በትርፍ ጊዜያቸው ተቀጥረው የሚሰሩ የጤና ባለሙያዎች ሌላ ቦታ ላይ በመደበኛነት ወይም በቋሚነት ተቀጥረው የሚሰሩ በመሆናቸው የሰራተኞችን የስራ ግብር በቋሚነት ከሚሰሩበት ተቋም የሚያገኙትን ደመወዝ እና በትርፍ ጊዜ የስራ ስዓት የሚያገኙትን ገቢ ደምሮ ታክሱ ከተሰላ በኋላ ቀሪ ሂሳቡን ማስከፈል ሲገባ፤ ነገር ግን ሆስፒታሉ በትርፍ ጊዜያቸው ተቀጥረው ከሚሰሩ ባለሙያዎች ከሚከፍላቸው ጠቅላላ ክፍያ ላይ ሁለት በመቶ ብቻ እየቀነሰ ግብር ሲያስገባ እንደነበር ባለሙያው ያስረዳሉ።
ስለዚህ ሆስፒታሉ በትርፍ ሰዓታቸው ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞችን እንደንግድ ግብር ከፋይ ታሳቢ በማድረግ ሁለት በመቶ ብቻ ግብር እየቆረጠ ለመንግስት ገቢ ሲያደርግ እንደነበር አቶ መስፍን ጠቁመው፤ ሆስፒታሉ ሁለት በመቶ ግብር ሲያስገባ የነበረው ከንግድ ትርፍ ከሚከፍሉ ሰዎች እንደተቀነሰ አድርጎ ሲያስገባ እንደነበር ተናግረዋል።
ነገር ግን በአዋጅ ቁጥር 979/2008 አንቀጽ 92 ንዑስ አንቀጽ 1 መሰረት ከሚፈጽሙት ጠቅላላ ክፍያ ላይ ሁለት በመቶ ግብር ቀንሶ የማስቀረት ግዴታ የተጣለባቸው ሰዎች በአገሪቱ ውስጥ ወይም በአንድ የዕቃ አቅርቦት ውል ከብር 10 ሺህ በላይ ለሆነ የዕቃ አቅርቦት ለሚፈጸም ክፍያ አሊያም በአገሪቱ ውስጥ በአንድ የአገልግሎት ውል ከሦስት ሺህ ብር በላይ ለሚፈጸም ክፍያ ሁለት በመቶውን ቀንሰው ያስቀሩ ለመንግስት ገቢ ያደርጋሉ። ስለዚህ ግብር ከፋዩ የተቀነሰለትን ሁለት በመቶ በአመቱ መጨረሻ ፌዴራል ላይም ይሁን ክልል ወይም ከተማ መስተዳድር ላይ የንግድ ትርፉን ሊከፍል ሲሄድ በዚህ መልክ የከፈላቸውን ደረሰኞቹን ይዞ ከሚከፍለው ግብር ላይ አቀናንሶ ገቢ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
ስለዚህ በገቢ ግብር አዋጁም ሆነ በመመሪያው ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው ከመቀጠር ገቢ ላይ የሚገኝ ገቢ ግብሩ ተሰልቶ ለሚመለከተው አካል ገቢ መደረግ ያለበት በመቀጠር ገቢ ታክስ ህግ መሰረት ነው። በመሆኑም ሆስፒታሉ ኦዲት ሲደረግ ከመቀጠር ገቢ ላይ የሚገኝ ገቢ በመቀጠር ገቢ ታክስ ህግ መሰረት ግብሩ ተሰልቶ ለመንግስት ገቢ መደረግ ሲገባው፤ ነገር ግን እነዚህ ሰዎች የንግድ ስራ ለመስራት ፈቃድ ያወጡ አይደሉም። በሙያቸው ተቀጥረው የሚሰሩ ናቸው። ስለዚህ ሆስፒታሉ ከነዚህ ሰዎች ላይ ሁለት በመቶ ሲቆርጥ የነበረው እንደ ንግድ ግብር ከፋይ አድርጎ መሆኑን ባለሙያው ይናገራሉ።
በዚህ መሰረት ሆስፒታሉ ከ2009 እስከ 2011 ዓ.ም ያለውን ሂሳብ ኦዲት ሲደረግ በደርጅቱ በትርፍ ሰዓታቸው ተቀጥረው ለሚሰሩ ሰራተኞች ሁለት በመቶ ብቻ ለመንግስት የስራ ግብር ቆርጦ 13 ሚሊዮን 231 ሺ 782 ብር ለሰራተኞቹ የከፈለውን በወጪነት እንዲያዝለት ጠይቋል። ነገር ግን በገቢ ግብር አዋጅ 979/2008 መሰረት በትርፍ ሰዓት ተቀጥረው የሚሰሩበት ገቢያቸውና ሰራተኞች በቋሚነት ተቀጥረው የሚያገኙት ደመወዛቸው ተደምሮ ከ10ሺ 500 በላይ ገቢ የሚያገኙ ከሆነ ተቀናሽ መደረግ ያለበት የስራ ግብር 35 በመቶ ነው።
ስለዚህ በሆስፒታሉ በትርፍ ጊዜያቸው ተቀጥረው የሚሰሩ ዶክተሮች ወርሃዊ ገቢያቸው ቢያንስ ከ10 ሺህ 500 በላይ በመሆኑ ሆስፒታሉ ለባለሙያዎች ከከፈለው 13 ሚሊዮን 231 ሺህ 782 ብር ላይ 30 በመቶ ለመንግስት ታክስ ገቢ ማድረግ ሲገባው ሁለት በመቶ ብቻ ታክስ በማድረጉ 28 በመቶውን እንዲከፍል መወሰኑን አቶ መስፍን ተናግረዋል።
በዚህም ሆስፒታሉ ከ13 ሚሊዮን 231 ሺህ 782 ብር ላይ 30 በመቶ የስራ ግብር ቆርጦ በጠቅላለው 5 ሚሊዮን 937ሺህ 940 ብር ግብር ለመንግስት ማስገባት ይጠበቅበት ስለነበር፤ ሁለት በመቶውን ቀድሞ ያስገባው ተቀናንሶ 3 ሚሊዮን 996 ሺ 324 ብር ፍሬ ግብር እንዲከፍል ውሳኔ ተሰጥቷል። እንዲሁም በታክስ ህጉ መሰረት ፍሬ ግብሩን በወቅቱ ባለመክፈል 1 ሚሊዮን 840ሺህ 11 ብር፣ ግብር በማዘግየት 2 ሚሊዮን 42 ሺህ 243 ብር እና ግብር አሳንሶ በማሳወቅ 1 ሚሊዮን 113ሺህ 420 ብር ቅጣት፤ በጥቅሉ ፍሬ ግብሩና ቅጣቱ ሲደመር እንዲከፍሉ ውሳኔ የደረሳቸው 8 ሚሊዮን 992ሺ ብር መሆኑን ባለሙያው ተናግረዋል።
አቶ መስፍን እንደሚገልፁት፤ የኦዲት ግኝት ማግኘት ብቻ ሳይሆን ግብር ከፋዩ የህግ ተገዥነቱን በሚፈጽምበት ወቅት ያሉትን ክፍተቶች አይቶ እንዲያስተካክል እድል የመስጪያና የመማሪያ መድረክ በመሆኑ፤ ሆስፒታሉ ባለሙያዎች በህጉ መሰረት መክፈል የነበረባቸውን የትርፍ ሰዓት የስራ ግብር ክፍያ ሁለት በመቶ ሳይሆን 30 በመቶ መሆኑን አሳውቆ በኦዲት ግኝቱ የተወሰነውን ገንዘብ መክፈል እንዳለባቸው በግልጽ ማስረዳት ይችላል።
በሌላ በኩል መንግስት ባለፈው ዓመት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ የተቀዛቀዘውን የንግድ እንቅስቃሴ ለማነቃቃትና ለዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር ሲባል መመሪያ 64ን አውጥቷል። በመመሪያውም አንድ ግብር ከፋይ የተወሰነበትን ውሳኔ ከ2008 እስከ 2009 ዓ.ም ድረስ ካለምንም ቅሬታ ፍሬ ግብሩን የሚከፍል ከሆነ ወለድና ቅጣቱ እንደሚነሳለት፤ እንዲሁም ፍሬ ግብሩን በአንድ ጊዜ የሚከፍል ከሆነ ደግሞ ከፍሬ ግብሩ 10 በመቶ ቅናሽ እንደሚደረግለትና ይሄንን ማድረግ የማይችል ከሆነ ደግሞ የፍሬ ግብሩን 25 በመቶ በአንድ ወር ውስጥ ከፍሎ ቀሪውን በአንድ ዓመት ውስጥ መክፈል የሚችል እድል ማመቻቸቱን ተናግረዋል።
ስለዚህ ግብር ከፋዮቹ በዚህ መንግስት ባመቻቸላቸው እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማስረዳትና የማግባባት ስራ መሰራቱን ገልጸው፤ በመመሪያ 64 መሰረት ሆስፒታሉ የተወሰነበትን የግብር ውሳኔ ቢከፍል ከ8 ሚሊየን 992ሺህ ብር ውስጥ ቅጣቱና ወለዱ ተነስቶለት 3 ሚሊየን 996 ሺህ 324 ብር ፍሬ ግብሩን ብቻ በመክፈል ከፍተኛ የግብር እዳ እንደሚቃለልለት ተናግረዋል።
የሆስፒታሉ ባለቤቶች ለህብረተሰቡ አገልገሎት የሚሰጥ በመሆኑ እነዚህን እድሎች እንዲጠቀምበት ያላሰለሰ የግንዛቤ ፈጠራ ስራ ቢሰራም ውሳኔውን አሻፈረኝ በማለት ለታክስ ውሳኔ ቅሬታ አጣሪ ጽህፈት ቤት አቤቱታ ማቅረባቸውን አቶ መስፍን ጠቁመው፤ ጽህፈት ቤቱም የግብር ውሳኔው ተገቢ ነው ሲል ውሳኔውን ማጽናቱ እንዲሁም የጽህፈት ቤቱን ውሳኔ አሻፈረኝ በሚል ለፌዴራሉ ግብር ይግባኝ ኮሚሽን አመልክተው ጉዳዩን ኮሚሽኑ እየመረመረው ሲሆን፤ ኮሚሽኑ ስለጉዳዩ ጽህፈት ቤቱን በጠየቀው መሰረት ያለውን ሂደት በአግባቡ በደብዳቤ መገለጹን ተናግረዋል።
በአጠቃላይ በታክስ ህጉ መሰረት መክፈል ያለባቸውን ግብር ባለመክፈላቸው ድርጅቱን እንዘጋለን ወደሚል ውሳኔ ውስጥ መግባታቸው ህጋዊም ፍትሃዊም አይደለም። ይሄ ድርጅት ወደ እዚህ ስራ ሲገባ የአገሪቱን ህግ አምኖ በዚህ ህግ አማካኝነት ለህብረተሰቡ የሚጠበቅበትን አገልግሎት ለመስጠት ለመንግስትም የሚጠበቅበትን ግብር ለመክፈል ነው። ስለዚህ በህጉ መሰረት መክፈል ያለበትን ግብር እንዲከፍል ሲጠየቅ ደርጅቱን እዘጋለሁ ማለት ተገቢ አለመሆኑን ባለሙያው ተናግረዋል።
አቶ መስፍን አክለውም ከትርፍ ጊዜ የስራ ሰዓት ጋር ተያይዞ እስካሁን በአገሪቱ ያለው ህግ ይሄው ነው። የተቀየረም አዲስ የወጣም ህግ የለም። ከአሁን በፊት ያለው አሰራር ይሄው ነው። እንደነርሱ ለፌዴራል ግብር የሚከፍሉ የጤና ተቋማት የትርፍ ሰዓት የስራ ግብር እየከፈሉ የግብር ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ያሉት በዚሁ ተመሳሳይ ህግ ነው። አዲስ ነገር የለም። ለእነርሱ የተለየ ነገር አልተጠየቀም። በተጨማሪም በጽህፈት ቤቱ በኩል ግብር ከፋዮች የአገሪቷን የግብር ህግ አውቀው የሚጠበቅባቸውን ግብር በአግባቡ እንዲወጡ እንጂ ሌላ ተልዕኮ እንደሌለ ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 15/2013