‹‹ ሠራተኞች በመዋቅር ስም ከሥራቸው እንዲሰናበቱ ተደርጓል›› -ቅሬታ ያቀረቡ የሞሐ ለስላሳ መጠጦች ፋብሪካ ሠራተኞች

የዛሬው የፍረዱኝ አምድ ዝግጅታችን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሚገኘው የሞሐ ለስላሳ መጠጥ ፋብሪካ ንፋስ ስልክ ቅርንጫፍ ሰራተኞች እና አመራሮች መከካል የተፈጠረን አንድ ውዝግብ ያስመለክተናል።

‹‹የፋብሪካው አመራሮች መመሪያን እና አሰራርን ባልተከተለ አግባብ በቀጣይ ሶስት ዓመታት ካሉት የሚታሰብ የዓመት እረፍት በግዳጅ እንድንወጣ አድርገውናል። አዲስ መዋቀር ሰራን በሚል ሰበብ ከስራ ተባረናል። ከስራ መታገዳችን ሳያንስ የአገልግሎት ክፍያ ተከልክለናል። ከዚህ ቀደም የወጣችሁት የሶስት ዓመት ፈቃድ በአገልግሎት ክፍያ ተቀይሯል። በሚል ከፍተኛ በደል ተፈጽሞብናል። ህግ እና መንግስት ባለበት ሀገር እንዴት ይህን መሰል ግፍ ይፈጸምብናል? በፋብሪካው አመራሮች የተፈጸመብን ግፍ የኢትዮጵያ ህዝብ አይቶ ይፍረደን›› ሲሉ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል የመልካም አስተዳደር እና ምርመራ ቡድን አቤት ብለዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ግራ ቀኙን አይቶ መፍረድ ይችል ዘንድ የመልካም አስተዳደር እና ምርመራ ቡድኑ ከሰዎች እና ከሰነድ ያገኛቸውን ማስረጃዎች እንዲሁም መመሪያዎችን ዋቢ በማድረግ በምርመራው የደረሰባቸውን ጭብጦች በሚከተለው መልኩ አቅርቦታል።

አቤቱታው ከባለጉዳዮቹ አንደበት፦

አቤቱታ አቅራቢዎች በቁጥር ብዙ ናቸው። ነገር ግን ለደህንነታቸው ሲሉ ሁሉም አቤቱታ አቅራቢዎች ስማቸው በጋዜጣው እንዳይጠቀስ ጠይቀውናል። የአቤቱታ አቅራቢዎች ቅሬታ ተመሳሳይ በመሆኑ የሁሉም አስተያየት ባጭሩ እንዲህ ተዘጋጅቷል።

እንደ አቤቱታ አቅራቢዎች፤ የሞሐ ለስላሳ ፋብሪካ ንፋስ ስልክ ቅርንጫፍ ሰራተኞች ከአሰራር እና ከመመሪያ ውጪ በተደጋጋሚ እረፍት እንዲወጡ ተደርጓል። የ2015 ዓ.ም የዓመት እረፍት ተጠቅመው ቢጨርሱም ሰራተኞቹ ወደፊት በድርጅቱ መቆየት እና አለመቆየታቸው ሳይታወቅ የሚቀጥሉትን ሶስት ዓመታት (2017፣2018 እና 2019ዓ.ም) እረፍት እንዲወስዱ ተገደዋል።

ሰራተኛው እረፍት የሞላው በግዳጅ እና በድርጅቱ ችግር ሆኖ እያለ ሰራተኛው በራሱ ፈቃድ እረፍት እንደፈለገ ተደርጎ እንዲሞሉ ተደርጓል። በተጨማሪም ድርጅቱ በግዳጅ እንዲወጡ ማድረጉ ያልበቃው ድርጅቱ ሰራተኞቹን ከስራ አሰናበቷል። የተሰናበቱ ሰራተኞች የአገልግሎት ፈቃድ ቢጠይቁም የአገልግሎት ክፍያው ቀደም ሲል ተገደው በወጡት የሶስት ዓመት ፈቃድ የተካካሰ ስለመሆኑ ተነግሯቸዋል። ሰራተኞቹ ከስራ የተባረሩት ከአሰራር እና ከመርህ ውጭ መሆኑን ይናገራሉ።

የሞሐ ለስላሳ መጠጦች ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማህበር ሥራ አስኪያጅ ምላሽ ፦

አቶ አማኑኤል ሙሄ በሞሐ ለስላሳ መጠጦች ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው። እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፤ የባለሀብቱን ትእዛዝ ተከትሎ አሁን ላይ የሞሐ ለስላሳ ድርጅቶች ‹‹በሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ›› ስር እንዲጠቃለሉ ተደርጓል። ፋብሪካውንም ወደ ምርት ለማስገባት ጥረት እየተደረገ ነው።

ከሰራተኞች አቤቱታ ጋር በተገናኘ ምን አልባት ቅሬታው የቀረበው ከሶስት ወር በፊት ከሆነ ጉዳዩ የሚመለከተው ከሶስት ወር በፊት የነበረውን አመራር ነው። በአሁኑ አመራር ላይ ከሰራተኛ ቅነሳ ጋር በተያያዘ ቅሬታ ያቀረበ አንድም ሰው የለም። ቅሬታ የሚቀርብ ከሆነ ግን አሰራር እና መመሪያን ተከትለው አፋጣኝ ምላሽ እንደሚሰጡ ይናገራሉ።

ይሁን እንጂ አሁንም ሆነ በፊት በነበረው አመራር ያለአግባብ ከስራ የተቀነሱ ካሉ በጉዳዩ ላይ የማጥራት ስራ ይሰራል። ከዚህ በመነሳት በሰራተኛ አዋጁና በሰራተኛ ማህበሩ ሰነድ መሰረት አስፈላጊው እርምት ለመውሰድ ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

አዲሱ አመራር ድርጅቱን ከተረከበ በኋላ 540 የሚሆኑ ሰራተኞች ያለአግባብ ከስራ ተቀንሰዋል የሚል ቅሬታ ከሰራተኞች ይነሳልና እርስዎ በዚህ ላይ ያለዎት አስተያየት እንዴት ይመለከቱታል? ተብሎ ለተነሳላቸው ጥያቄ አቶ አማኑኤል በምላሻቸው፤ የበፊቱን በተመለከተ በህጉና በአዋጁ መሰረት መሆኑን ማረጋገጥ ነው። የአሁኑ ግን በአዋጁ እና ከሰራተኛ ማህበሩ ጋር በጋራ በመሆን የተሰራ ነው። ሰራተኛ ማህበሩ የማያውቀው አንድም ነገር አንሰራም።

አዲሱ አመራር እንደገና የመዋቅር (restructure) ስራ ሰርቷል። ይህም የተደረገው ድርጅቱን ከወድቀት ለማዳን ነው። በተደረገው መዋቅር መሰረትም የሰራተኛ ምደባ እየተደረገ ነው። በዚህ ውስጥ እያንዳንዱ የአመራሩ እንቅስቃሴ የሰራተኛ አዋጁን ያገናዘበ ነው። ከሰራተኛ አዋጁ ውጭ የተከናወነ ምንም አይነት ስራ የለም።

ድርጅቱ መዋቅር ሲሰራ መከተል የሚገባቸው ሂደቶች አሉ። ሰራተኛውም ማወቅ አለበት። ስለሆነም ህግንና አሰራርን ጠብቆ ከመስራት አንጻር ያለው ሂደት ምን ይመስላል? መዋቅር ስትሰሩ እና ድርጅቱን እንደገና ስታደራጁ በሀገሪቱ ከሚገኙ መመሪያ የትኛውን መሰረት አድርጋችሁ ሰራችሁ? የሚል ጥያቄ የተነሳላቸው አቶ አማኑኤል፤ መዋቅሩ የጸደቀው በሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ነው። ይሁን እንጂ እንደ ድርጅት መዋቅሩን ሲሰራ በነበረው ጥናት አመራሩ ተሳታፊ ነበር።

ከዚህ ባሻገር በመዋቅር መመሪያው ላይ ከድርጅቱ አመራሮች እና ከሰራተኛው የተውጣጡ የማህበሩ አባላት አመራሮችን ያካተተ የጋራ ውይይት ተደርጎበታል። ከዛ ውጭ ደግሞ መዋቅሩን የተመለከተውን መመሪያ ሰራተኛው እንዲያውቀው ለማድረግ በድርጅቱ የማስታወቂያ ሰሌዳዎች ላይ እንዲለጠፉ ተደርጓል።

አዲሱ መዋቅር ሲሰራ ሰራተኛው እንዲወያይበት አልተደረገም ያሉት አቶ አማኑኤል፤ ለዚህም በህብረት ስምምምነት ሰነዱ ላይ ሰራተኛን ስለማወያየት የተባለ ነገር አለመኖሩን ይናገራሉ። ይህንን የተመለከተ ሀሳብ በሰራተኛ ማህበሩ ህግ አልተካተተም። መዋቅር ሲሰራም ሰራተኛው የተወከለው በሰራተኛ ማህበሩ ነው። አመራሩ የሚያደርገውን እያንዳንዱን እንቅስቃሴ በሰራተኛ ማህበሩ በኩል ለሰራተኞች ማሳወቃቸውን አመላክተዋል።

ድርጅቱ ከሰራተኛው ጋር ለመጨረሻ ጊዜ የህብረት ስምምነት ያደረገው መቼ ነው? አዲሱ አመራር ስራውን ከተረከበ ጊዜ በኋላ የተደረገ ስምምነት አለ? ተብለው የተጠየቁት አቶ አማኑኤል፤ ከሰራተኛው ጋር የህብረት ስምምነት መቼ እንደተደረገ እንደማያውቁ እና አዲሱ አመራር ድርጅቱን ከተረከበ በኋላም የተደረገ ምንም አይነት ስምምነት አለመኖሩን ጠቁመዋል። ሌላ ስምምነት እስከሚካሄድ ድረስ ከዚህ በፊት የነበረውን የህብረት ስምምነት ለስራ እንደሚጠቀሙት አመላክተዋል።

በሰራተኛውና በድርጅቱ የህብረት ሰነድ ተብሎ የወጣው ሰነድ በሀገር ደረጃ በማን እና በምን እውቅና አግኝቷል? ህብረት ስምምነቱ ሊገዛን አይችልም የሚል ሰራተኛ ቢኖር እንዴት ሊዳኝ ይችላል? የሚል ጥያቄ በዝግጅት ክፍሉ የተነሳላቸው አቶ አማኑኤል፤ የቀድሞው የድርጅቱ አመራር ከሰራተኛ ማህበሩ ጋር ተደራድሮ የተፈረመ የስምምነት ሰነድ በመሆኑ የህብረት ስምምነቱ እንደ መመሪያ የሚታይ ነው። በዚህም ሰራተኞች ይገዛሉ። ከዚህ በተጨማሪም ድርጅቱ በዋናነት የሰራተኛ እና አሰሪ አዋጁን እንደሚጠቀም ጠቁመዋል።

በህብረት ስምምነት ሰነድ ላይ የዓመት እረፍት አሰጣጥን በተመለከተ ሰራተኞች ቅሬታ ያቀርባሉ። ይህም ሰራተኛው ሳይፈልግ እና የዓመት ፈቃድ ሳይኖረው ከሚቀጥለው ዓመት ታሳቢ የሚደረግ እረፍት እንዲወጣ ይገደዳል። እረፍት ሲወጣም በድርጅቱ ችግር ሆኖ ሳለ በሰራተኛው ጉዳይ ተብሎ የአመታዊ እረፍት ‹‹ፎርም›› እንዲሞላ ይደረጋል። በዚህ አግባብ ሰራተኛው ወደፊት ከሚመጡ ዓመታት እረፍት እንዲወስዱ በማድረግ እና በአዲሱ መዋቅር ከስራ በተቀነሰ ጊዜ ተገዶ የወሰደው የዓመት እረፍት በአገልግሎት ክፍያ እንዲሸፈን አድርጋችኋል የሚሉ ቅሬታዎች በሰራተኛው ይነሳል።

የሰራተኛውን መብት ሊያስጠብቅ የሚችል አንድም የህብረት ስምምነት አንቀጽ ተግባራዊ አይደረግም። ይልቁንም የህብረት ስምምነቱም ሰራተኛውን ለመቅጣት እና ለማሸማቀቅ እንደ ሽፋን እየተጠቀማችሁበት መሆኑን ቅሬታ ይነሳል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የእርስዎ ምላሽ ምንድን ነው? ተብለው የተጠየቁት አቶ አማኑኤል፤ አሁን ላይ ድርጅቱ ምርት ማምረት ስላቆመ ሰራተኛው ፋብሪካ መጥቶ የሚሰራው ስለሌለ እረፍት እንዲወስዱ ይደረጋል። ይህ ሲሆን ግን ሰራተኛው ተስማምቶ መሆን አለበት። ድርጅቱ እንዳይጎዳ እረፍት መውሰድ አለበት ሊባል አይችልም። በዚያውም ልክ የሚከናወኑ ስራዎች በመግባባት የተመሰረቱ ናቸው። በህጉ መሰረት የዓመት ፈቃድ እንኳን ወደ ገንዘብ ይቀየር የሚል አንቀጽ የለውም። አንድ ድርጅት ስራ የማይሰራ ከሆነ አንድ ሰራተኛ ድርጅቱ መጥተህ ቁጭ በል አይባልም።

ከዚህ በፊት የነበረ ሰው አመራር ድርጅቱ ስራ ባቆመ ጊዜ ሰራተኛውን እረፍት እንዲወጡ አድርጓል። ነገር ግን እረፍት በመውጣቱ የአገልግሎት ክፍያ ሊያጣ አይችልም። የበፊቱ አመራር አሰራር እና መመሪያ ጥሶ ከሆነም የአሁኑ አመራር ጉዳዩን እንደሚመለከተው ገልጸዋል።

በመዋቅሩ ከድርጅቱ ምን ያህል ሰራተኞች ተቀነሱ? ተብለው የተጠየቁት አቶ አማኑኤል፤ ከስራ የተቀነሱ ሰራተኞችን ቁጥር በትክክል እንደማያውቀት ተናግረዋል። ነገር ግን በተቻለ መጠን በመዋቅሩ አብዛኛው ሰራተኛ በስራ ገበታው ላይ እንዲቀጥሉ ለማካተት መስራታቸውን ጠቁመዋል።

ድርጅቱ ሰራተኛ ለመቀነስ መነሻችሁ ምክንያቱ ምንድን ነው? የሚል ጥያቄ የተነሳላቸው አቶ አማኑኤል፤ ሰራተኞች የተቀነሱበት አብይ ምክንያት የሞሐ የለስላሳ መጠጦች አክሲዮን ማህበር በኪሳራ ሊዘጋ ጫፍ ላይ በመድረሱ መሆኑን አመላክተዋል።

ከሰራተኛ ቅነሳ በተጨማሪ ድርጅቱ የአመራር ለውጥ ማድረጉን የሚገልጹት አቶ አማኑኤል፤ ለአመራር ለውጡም ምክንያትም ከዚህ በፊት በድርጅቱ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን ለመቅረፍ መሆኑን ገልጸዋል። ከዚህ በፊት የነበረው አደረጃጀት ትክክል አልነበረም። አንዱ ለድርጅቱ ውድቀት መንስኤ ትክክለኛ አደረጃጀት ስላልነበረው ነው። እያንዳንዱ ሰራተኛ ስራውን በአግባቡ እንዲሰራ የሚያስችል ግልጽ አሰራር አልነበረም። በእነዚህ እና መሰል ገፊ ችግሮች አዲስ መዋቅር መስራታቸውን ይናገራሉ።

የቀድሞው አመራር በተከተለው ደካማ የአሰራር ሂደት ድርጅቱን ለኪሳራ ዳርጓል። ድርጅቱን ለኪሳራ የዳረጉ አመራሮች ሳይጠየቁ ስራቸውን በአግባቡ ሲያከናውኑ የነበሩ ታታሪ እና ምስጉን ሰራተኞች በመዋቅር ስም ከስራቸው እንዲሰናበቱ ተደርጓል። ይህ ደግሞ ጉዳዩን “አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ” ያደርገዋል የሚል ቅሬታ ያስነሳል ተብለው የተጠየቁት አቶ አማኑኤል፤ ይህን በተመለከተ መጠየቅ የምትችሉት ሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕን ነው። እኛ አሁን ላይ እየሰራን ያለው ድርጅቱን በምን መልኩ ውጤታማ ይሆናል? በሚለው ነው። ከካሳ ክፍያ ጋር በተያያዘ ለተሰናባች ሰራተኞች በህጉ መሰረት (የሰራተኛ እና አሰሪ አዋጁ እንዲሁም በህብረት ስምምነቱ) ሁሉንም ነገር እንደሚደረግ ገልጸዋል።

የህብረት ስምምነቱን አይተውት ያውቃሉ? ተብለው ለተጠየቁት በደንብ! የሚል ምላሽ የሰጡት አቶ አማኑኤል፤ ከሀገሪቱ ካሉ ህጎች ጋር ምን ያህል ተጣጥሞ የሚሄድ ነው? ምን ያህልስ የሀገሪቱን ህግ ያከበረ ነው? ብለው ያምናሉ ለሚለው ጥያቄ የህብረት ስምምነቱ ሲወጣ የሀገሪቱን ህጎች መነሻ አድርጎ ነው። በተለይም የሰራተኛ እና አሰሪ ህጉን ያከበረ መሆኑን ገልጸዋል።

ምላሻቸውን ተከትሎ ዝግጅት ክፍሉ ለአብነት ያህል የህብረት ስምምነቱ ላይ እንደተመላከተው ፋብሪካው ዓመታዊ ጥገና በሚያደርግበት እና በድርጅቱ ስራ በማይኖርበት ወቅት ሰራተኞች ፈቃድ እንዲወጡ የህብረት ስምምነቱ ያስገድዳል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የዓመት እረፍት ፈቃድ የሌለው ሰው በታሳቢ ፈቃድ እንዲወጣ ሊደረግ ይችላል። ብዙዎቹ የህብረት ስምምነቱ ህጎች ደግሞ አሻሚ ናቸው። ከአሻሚነቱ ባሻገር ድርጅቱ ሰራተኞችን በፈለገው ልክ ማሽከርከር እንዲችል የሚያደርግ ነው። ይህ ደግሞ እርስዎ ከጠቀሱት ከሰራተኛ እና አሰሪ አዋጁ ጋር የሚጣረስ ነው። የሰራተኛውንም መብት የሚጨፈልቅም ነው። ታዲያ! የህብረት ስምምነቱ ምኑ ላይ ነው ከሰራተኛ እና አሰሪ አዋጁ ጋር ተጣጥሞ የሚሄደው? የማህበሩ ህጎች ከሀገሪቱ ህጎች ጋር የማይጣረሱ መሆናቸውን ማረጋገጫሁ ምንድን ነው? የሰራተኛ ተወካዮች በትክክል ሰራተኞችን የማይወክሉ፤ ለአመራሩ እና ለድርጅቱ ባለሀብት ያደሩ ናቸው ተብሎ በሰራተኛው ዘንድ ቅሬታ ይነሳባቸዋል ለሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት አቶ አማኑኤል፤ የሰራተኛው ማህበር ተወካዮች ሰራተኛውን ይወክላሉ አይወክሉም የሚለው ላይ እኛን ባታስገቡን ደስ ይለኛል። ምክንያቱም ሰራተኛው መርጦ የወከለው አመራር አለ ብዬ አምናለሁ።

ከህጉ ጋር በተያያዘ 2014 ዓ.ም ላይ ከጸደቀው የህብረት ስምምነት በኋላ የሚገቡ ሰራተኞችም በዚሁ ህግ ነው የሚመሩት። የህብረት ስምምነቱ ከሰራተኛ እና አሰሪ አዋጁ በታች ነው። የህብረት ስምምነቱ አዋጁ የሰጠውን መብት ሊከለክል አይችልም። ስለሆነም ሰራተኛውም በአዋጁ መሰረት መብቱን መጠየቅ ይችላል። ሁሉም የድርጅቱ ሰራተኛ ደግሞ ማህበር አባል አይደለም። ስለሆነም ሁሉም ሰራተኛ የግድ በህብረት ስምምነቱ ይገዛል ማለት አይደለም። ተገዥ የሚሆነው በሰራተኛ እና አሰሪ አዋጁ ነው። በሰራተኛ አሰሪ አዋጁ የተጣሰ ህግ ካለ ግን ቁጭ ብለን ማየት እንችላለን።

ስምምነቱ ሰራተኛን ይበድላል ከተባለ ስምምነቱን ማስተካከል ያለበት ራሱ ሰራተኛው ነው ያሉት አቶ አማኑኤል፤ ነገር ግን አሁን ያለው የሰራተኞች የህብረት ስምምነት የሰራተኛውን መብት የሚያስጠብቅ ነው ብለው እንደሚያምኑ ይናገራሉ። አንዳንዶቹ የህብረት ስምምነቱ አመራሮች እንደሀገር ባሉት የሰራተኛ ማህበራት ኮንፌደሬሽን ውስጥ የስራ ኃላፊነት ያላቸው ናቸው። በመሆኑም በእነሱ የተዘጋጀው የሞሐ የህብረት ስምምነት ህግ የሀገሪቱን ህግ የዘነጋ ነው ብለው እንደማያምኑ ያስረዳሉ።

ቅሬታ ያቀረቡ የድርጅቱ ሰራተኞች እንደሚናገሩት፤ የሰራተኛ ማህበሩ የድርጅቱን ጥቅም እንጂ የሰራተኛውን መብት የሚያስከብር አይደለም። የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ለማየት እንደሞከረው አንዳንድ የህብረት ስምምነቱ አንቀጾች ለድርጅቱ ቋሚ ጠበቃ የሆኑ እስኪመስሉ የተጻፉ ናቸው።

ለምሳሌ ሰራተኞች በህይወት ይኑሩ ወይም አይኑሩ በማይታወቅበት ሁኔታ ለሚቀጥሉት ሶስት አመታት ከሚኖራቸው የዓመት እረፍ ታስቦ ዛሬ ላይ የአመት እረፍት እንዲወጡ ተደርጓል። እንደነዚህ አይነቱ አሰራር ደግሞ ሰራተኞች አስቸኳይ እና አስቸጋሪ የግል ጉዳይ ቢገጥማቸው እረፍት እንዳያገኙ የሚያደርግ ነው። መንግሥት ለሰራተኞች የዓመት እረፍትን ታሳቢ አድርጎ መመሪያ ያወጣው ሰራተኞች በፈለጉበት ጊዜ ከመስሪያ ቤቱ ጋር በመስማማት እንዲያርፉ አይደለም? ሰራተኞች ገና በታሳቢነት እስከ ሶስት ወራት በእረፍት ስም ከስራ አስወጥታችሁ ከዚህ በኋላ ያለረፍት እንዴት ነው የሚሰሩት? ታዲያ ! ይሄ አይነቱ አሰራር ተገቢ ነው? ይህ አሰራር ሰራተኞችን መበደል አይደለም ? በዚህ ጉዳይ ምን ይላሉ? ተብለው በዝግጅት ክፍሉ ጥያቄ የተነሳላቸው አቶ አማኑኤል፤ እንደዚህ አይነት አሰራር በድርጅቱ ይኖራል ብለው እንደማያስቡ እና ነገር ግን ይህን መሰል አሰራር በተጨባጭ በድርጅቱ ካለ ፍተሻ እንደሚያደርጉ አስረድተዋል። ይህን አይነት አሰራር በድርጅቱ ካለ የበፊቱ አመራር ይህን ለምን አደረገ የሚለውን ምክንያት አጣርተው ለሰራተኛው እና ለሚመለከታቸው እንደሚያሳውቁ ተናግረዋል።

በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞች ጎተራ ጊቢ በሚገኘው የድርጅቱ የማስታወቂያ ቦርድ ላይ በአስገዳጅ በሆነ መልኩ ስማቸው ተለጥፎ ይገኛል። ይህ በሆነበት አግባብ እንዴት ስለኩነቱ አላውቅም ይላሉ? ተብለው የተጠየቁት አቶ አማኑኤል፤ ሰራተኞች እረፍት እንዲወጡ መለጠፉን እንደሚያውቁ ገልጸው፤ ለሶስት ዓመት የሚደርስ መሆኑን ግን እንደማያውቁ ያስረዳሉ።

እርሶ ስለዚህ ነገር እንደማያውቁ ተናግረዋል። ነገር ግን እንደዚህ አይነቱ ነገር ተፈጽሞ ከሆነ ልክ ነው ወይስ አይደለም ብለው ያምናሉ? የሚል ጥያቄ በዝግጅት ክፍሉ የቀረበላቸው አቶ አማኑኤል፤ በድርጅቱ እንደዚህ ተደርጎ ከሆነ ልክ አይደለም። የሶስት ዓመት እረፍት አስቀድሞ መውጣት ተገቢነት የለውም። የሰራተኛ አዋጁም ነገሮች ከሰራተኛ አቅም በላይ ካልሆኑ በስተቀር የዓመት እረፍት በገንዘብ እንኳን ተለውጦ እንዲሰጥ እንደማያበረታታ አመላክተዋል። አሁን በድርጅቱ ተፈጠረ የተባለው ነገር በተጨባጭ ሆኖ ከተገኘ የማስተካከያ እርምጃዎችን እንደሚወስዱ ጠቁመዋል።

ከሰራተኞቻችሁ የደህንነት ጋር ተያይዞ ጥያቄ የተነሳላቸው አቶ አማኑኤል፤ አንድ ፋብሪካ የሰራተኞችን ደህንነት የሚያስጠብቅ መሳሪያ ማሟላት ግዴታ አለበት። እሱን ህግ ሞሐ አይጥስም። ምርት ማምረት ስንጀምር ደግሞ ለምርት የሚያስፈልጉ የደህንነት ቁሳቁሶችን እናሟላለን። ድርጅቱ ኪሳራ ውስጥ በነበረበት እና ደመወዝ መክፈል በማይችልበት ወቅት የደህንነት መጠበቂያ መሳሪያዎች አልነበሩም። አሁን ግን በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ስር ከገባ ወዲህ በወጥነት ደመወዝ እየከፈልን ነው። እንደ መርህ እና ኢንተርናሽል ካምፓኒ ከሆነው ከፔፕሲ ኮላ ጋር ስለምንሰራ ደረጃውን የጠበቀ ስራ መስራት አለብን። ከዚያ አኳያ በስራ ጊዜ በሰራተኞች ላይ የሚደርስን አደጋ ለመቀነስ የሰራተኞችን ደህንነት መጠበቂያ ቁሳቁስ እንዲያሟሉ ህጉም እንደሚያስገድድ ገልጸዋል።

በየጊዜው ከፋብሪካው የሚወጣ በካይ ጭስ ወደ ጎተራ ኮንዶሚኒም ይለቀቃል። በዚህም የጎተራ ኮንዶሚኒም ነዋሪዎች በጤናቸው ላይ ጉዳት ማድረሱን ይናገራሉ። ይህን እንዴት ይመለከቱታል? ይሄ ጭስ ምን ያህል ሰዎችን እንደማይጎዳ አረጋግጣችሁ ነው ወደ ጋራ መኖሪያ ቤቱ የምትለቁት? ስለተባለው ነገር መረጃው እንደሌላቸው እና ስለጉዳዩ የሚያውቁት አለመኖሩን ተናግረዋል። ይሁን እንጂ እንዴት ነው የሚወጣው? ከየት ነው የሚወጣው? የሚወጣውስ ጭስ በሰዎች ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ምንድን ነው? የሚለውን አጣርተው ምላሽ እንደሚሰጡ ተናግረዋል።

የአካባቢ ጥበቃ ፋብሪካዎቻቸውን ጎብኝቶ በሚሰጣቸው ግበረ መልስ መሰረት ማስተካከያ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ አማኑኤል፤ ወደፊትም በጎተራ ኮንዶሚኒም የሚሰጣቸውን ግብረ መልስ ተመልክተው የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወስዱ ተናግረዋል። ነገር ግን እስካሁን ተፈጠረ የተባለውን ችግር እንደማያውቁት አመላክተዋል።

ውድ የአምዳችን ተከታታዮች በቀጣይ ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት አነጋግረን ምላሻቸውን ይዘን የምንቀርብ ይሆናል። ቸር ቆዩ።

ሙሉቀን ታደገ ፣ ሞገስ ተስፋ እና መክሊት ወንድወሰን

 

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You