(ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ)
ሀገራዊው ምርጫ –
“እሳት ወይስ አበባ!?”
ያው መቼም እኔም እንደሰው፣
አንዳንዴ፣ አንዳንዴ ብቻ ሕሊናዬን እውነት
ሲያምረው፣
ሰብሰብ ብዬ የማስበው፤
“ቀድሞስ ቢሆን ለኔ ብጤ [ለሚዘራ የቀለም ዘር]፣
አዳሜ በኔ ላይ በቀር፣ ለእኔ መስክሮ አይናገር።”
ብዬ ከልቤ ስማከር፣ እኔው ከኔው ስከራከር፣
ተጨብጬ እማብላላው ያው መቼም እኔም
እንደሰው፣
የሐቅ ራብ ነፍሴን ሲያከው ልቤ ልቤን ሲሞግተው፣
“እውነትስ ምንትስ ማነው? [እያልኩ
እጠይቃለሁ።]
(“እሳት ወይ አበባ”፤ 1966 ዓ.ም፤ ማነው …ምንትስ)
የቅድመ ርዕስ መዘክር፤
ታላቁ የብዕር ዋርካችን ጋሽ ጸጋዬ ገብረ መድኅን በተወርዋሪ ኮከብ የሚመስል የሀገራችንና የሕዝቡ ብርቅዬ ልጅ ነበር። “ነበር አያኮራም” ብሂል በእርሱ ላይ አይሠራም። በአፀደ ሥጋ ቢለየንም ትቶልን ባለፈው ሥራዎቹ እስከ ምፅዓት ቀን ድረስ እኛ ቋሚዎቹ ብቻ ሳንሆን መፃኢው ትውልድም ሁሌም ሲዘክረው ይኖራል።
ከዚህ ታላቅ የጥበብ አምዳችን ጋር ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኘነው በሕይወቱ የመጨረሻ ዓመታት ግድም የሀገሩን አፈር በረገጠበት አንድ ዕለት በግዮን ሆቴል ውስጥ ነበር። በዚያ ዕለት ከባለቤቴ ጋር ወደ ሆቴሉ ጎራ ያልኩት አጭር የስብሰባ ቀጠሮ ስለነበረኝ ጉዳዬን ከውኜ እስከመጨረስ ድረስ እርሷ ቡና እየጠጣች እንድትጠብቀኝ በመመካከር ነበር።
ወደ እንግዳ መቀበያ ሳሎኑ ስናመራ ጋሽ ጸጋዬ ሶፋ ላይ ቁጭ ብሎ ከፊቱ የተቀመጠውን የቡና ስኒ በማንኪያ እያጫወተ ሲቆዝም ድንገት ዓይን ለዓይን ተገጣጠምን። “ጋሽ ጸጋዬ!” ብዬ ተንደርድሬ ለሰላምታ ስቀርበው ፊቱን ኮስተር አድርጎ “ተው! አንተ ሳትሆን እርሷ ትምጣ! እናንተ አእምሯችሁ ቆሽሿል። ቋንቋ ለቋንቋ የምንግባባው ከዚህች ርግብ አበባ ጋር ነው። እናንተማ ስትራቀቁ፣ የሕዝብን ቋንቋ የት ታውቃላችሁ? ከሕዝብ የራቃችሁ ባለሀገሮች…።” ንግግሩ እንዳስደነገጠኝ አልሸሽግም።
እውነትም ስብሰባዬን ጨርሼ ስመለስ “ዝምተኛዋ” ባለቤቴና ጋሽ ጸጋዬ የደራ ጨዋታ ይዘው ሁለቱም እየፈነደቁ ሲሳሳቁ አስተዋልኩ። እውነቱን ነበር፤ ከእኔ ጋር ቢሆን ኖሮ ፕሮቶኮሉ ስለሚከብድ እንደዚህ በተፈታ ስሜት ማውራታችንን እጠራጠራለሁ። ቁጣው በረድ ያለለት ስለመሰለኝም በድጋሚ ቀረብ ብዬ “ደህና መጣህ?” ብዬ ሰላም ስለው ፊቱን ፈካ አድርጎ “አየህ እናንተ ተማርን ባይ ነገር አርቃቂዎች፤ የምታወሩት የማትኖሩትን፤ የምትጽፉት የማታውቁትን ስለሆነ በጨዋታ አንግባባም። ይህቺ አበባ ግን ንፁህ ነች። ፖለቲካ አታውቅም። ሸር አይገባትም። ስምና ወርቅ አታመሳጥርም። ስለዚህ ቋንቋዬ ገብቷታል፤ ቋንቋዋም ገብቶኛል። “እናንተ ግን…!”
“እናንተ…” ያለው በእኔ አምሳያ እነማንን ወክሎ እንደሆነ ፍቺው ሳይገባኝና ትዝብቱ ሳይገለጥልኝ የዚያን ዕለት በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ተለያየን። ለምን “አበባን” ጠቀሰ? እኔና ዘመነ አቻዎቼን “እሳት ናችሁ!” ማለቱ ይሆንን? በማለት ስመራመር የኖርኩት እስከ ዛሬዋ እለት ድረስ ነው።
ከዚያ ገጠመኝ በኋላ ዳግም ሳንገናኝ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሞት እጁን ስለሰጠ የሙት ዓመቱ መታሰቢያ በኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበርና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋራ ዝግጅት በብሔራዊ ቴያትር ተከበረለት። አንጋፋው የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበርም ሳይውል ሳያድር ከሌሎች የሙያችን አርአያ ሰብ አንጋፎች ጋር የመታሰቢያ ቴምብር አሳትሞ ለትውልድ የሚተላለፍ ቅርስ አኖረለት።
“እሳት ወይ አበባ” የግጥም መድበል መጽሐፉ ትዝ ያለኝ የሀገሬ ወቅታዊ የምርጫ ሁኔታ “እሳት” ይሆን ወይንስ “አበባ” የሚል የስጋት ፍልስፍና ብጤ አእምሮዬን ወጋ ስላደረገው ነው። እናም ከመጻሕፍት ሼልፌ ላይ እጄን ዘርግቼ ለስንተኛ ጊዜ እንደሆነ እርግጠኛ ባልሆንም የብዕሩ ፍልስፍናና የነፍሱ ጩኸት ያስተጋባባቸውን ግጥሞች በጥሞና ውስጥ እንዳለሁ መጻኢውን ምርጫና ሀገሬን እያሰብኩ በለሆሳስ ማነብነቡን ተያያዝኩት።
“አበባ አንሆን ወይም እሳት፣
ተቅበዝብዘን በሃሳብ ምትሐት።
ለጽድቅ አልበቃን ለኃጢያት፣
ለነፍስ ወይ ለሥጋ ብፅዓት፣
ወድቀን በሕልም ዓለም ቅጣት፣
ፈርሰን በሰመመን መዓት።
ታዲያ ምን መናገሪያ አለን?
ዱዳው ልባችን ዋይ ይበል፣
ዕውር ነፍሳችን ይንበልበል፣
እስትንፋሳችን ይቃጠል።
እንጂ…እኛማ ተረግመን፣
መቼ መነጋገሪያ አለን?”
ይህ ሐቅ ሳይተናነቀን ብንውጠውና ቋንቋ ለቋንቋ ብንግባባ አንጋፋው ብዕረኛው እንዳለው በ“እሳት” ሳይሆን በ“አበባ” በተመሰልን ነበር። “በጥንብ አንሳ” አሞራ መልክ ሳይሆን “የሰላም ዘንባባን በአፏ በምታቀብልን ርግብ አምሳል” በተወከልን ነበር። ሩጫችን ለሥልጣን ወንበር ሳይሆን ያነቀፈውን ለማንሳትና የዛለውን ጉልበት ለመደገፍ ቅድሚያ በሰጠን ነበር። ቢሆንልንማ ኖሮ ሀገር “የተጎናጸፈችውን የሀዘን ከል” ተረባርበን በማውለቅ “ፀአዳ ልብስ” አልብሰን እምባዋን ባበስንላት እንጂ “በእበልጣለሁ የፖለቲካ እንቶ ፈንቶ” ጥዝጣዜዋን ባላከበድነው ነበር። “ነበር” እንጂ “ነው” ብርቃችን ስለሆነብንም ቁዘማና ግራ መጋባት የዕለት እንጀራችን ሆኗል። ስለዚህም ትውልዳችን “የእሳት ልጅ ረመጥ” ቢሆን ሊገርመን አይገባም።
የሥልጣን ህልመኛ ሯጮቻችን ማሊያ፤
በሀገራችን የፖለቲካ ምርጫ ታሪክ እንዳሁኑ የባለ ዲግሪ ምሁራን ወረራ የበረታበት ውድድር ተስተውሎ ስለመሆኑ እርግጠኛ አይደለሁም። ከፖለቲካ ውድድር ይልቅ ለአንድ ከፍተኛ የተከበረ ታላቅ ዩኒቨርሲቲ (Prestigious University) ለአስተማሪነት ቅጥር ለመወዳደር የሚረባረቡበት ግፊያ እስኪመስል ድረስ “ምሁራኖቻችን” ሥልጣን ወይም ሞት በማለት የጨከኑ ይመስላል። እጩ ተመራጮቹ የተመለመሉት በፖለቲካ ብስለታቸው ይሁን ወይንም በአካዳሚያ ጉልበታቸው እርግጠኛ ለመሆን የክርክራቸውን የአቅም ምስክርነት ታግሶ መጠበቁ ይሻል ይመስለኛል።
መቼም አገር ለመምራት የትምህርት ሥልጠና አስፈላጊነት ምን ያህል ወሳኝ እንደሆነ ማነጻጸሪያውን የምናሳያው ያለፉትን የፓርላማ ተብዬ ውሏችንን በመጠቆም ይሆናል። “ያለፈው በደሌን ተወው፤ ጌታ ሆይ አደራ አታስታውሰው” ብሎ እንዳዜመው የሀገራችን የአንድ ወቅት ዝነኛ ዘማሪ ትንታኔውን “በሆድ ይፍጀው” ትዝብት በማለፍ በዛሬው ጉዳያችን ላይ ማተኮሩ ይበልጥ አዋጭ ይመስለኛል።
ሀገሬን የሞረሞራት “የከበሩ የምሁራን ፖለቲኞች” ርሃብ ሳይሆን ለሀገር ኖረው ለሀገር የሚሞቱ ጸኑዓንን ዜጎችን ነው። በሕይወት ዘመናቸው መደበኛ እንጀራቸውንና ከፍታቸውን ከመንከባከብ ውጭ አደባባይ ወጥተው በሀገራቸው የጋራ ጉዳይ ድምጻቸውን ወይንም ብዕራቸውን ያላሰሙ “ጎምቱዎች” ዛሬ እጣ ወጥቶላቸው ለመጻኢው ሀገራዊ ተስፋ አለንላችሁ ቢሉ ትርፉ ትዝብትም ንቀትም ከመሆን አማራጭ አይኖረውም። በክፉ ጊዜ ተሸሽገው “በደጉ” ጊዜ አለንላችሁ ቢሉን የሀገራችን ጠላ ጠማቂ እህትን መሰል ትዝብት ከማትረፍ ውጭ ፋይዳ አይኖረውም። “ለጌሾ ወቀጣ ማንም ሰው አልመጣ፤ ለመጠጡ ጊዜ ከየጎሬው ወጣ” እንዳለችው መሆኑ ነው።
የምርጫው ሩጫ ፍጻሜ በህልማቸው ከጎመጁለት የተትረፈረፈ የጥቅማ ጥቅም ማዕድ ላይ ለመጉረስ አስበው ከሆነ ለጊዜው ሕጉን ትተን “በኢትዮጵያ አምላክ” እዚያው “በጠበላችሁ” እንላቸዋለን። የግል አታካች ሙያቸው አሰልችቷቸው ወይንም የምርምር አቅማቸው ቀበቶ ላልቶና የዕለት እንጀራቸውን ማግኘት ከብዶባቸው ነገር አልሳካላቸው ብሎ የተሻለ ለውጥ ፍለጋ ከሆነም “በሕዝብ አምላክ” እያልን በመማጸን ገና ቀኑ ስላልመሸ ወደ ህሊናቸው እንዲመለሱ እንማጠናለን።
ግራ በመጋባት ወጀብ ውስጥ እየተላጋች ያለችውን ሀገሬን ዛሬ የሚያስፈልጋት “በነፍሳቸው ተወራርደው” የሚታደጓትን ብርቱዎች እንጂ “ነፍሳቸውን ለማዳን” የፖለቲካ ጥጋጥግ የሚፈለጉትን ድንጎጦች አይደለም። ህሊናቸው የሚመራቸውን እንጂ ህሊናቸውን ቀብረው “ነፃነታቸውን የሚያውጁትንም” አይደለም። ዘብ ከቆሙለት የፖለቲካ ሥርዓት ይልቅ “የሕዝብ ደጀን” ለመሆን የጨከኑ እንዲሆኑም ምኞታችን ነው።
በዚህ ጸሐፊ “ጨዋ ግምገማ” እስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስ ከገዢውም ይሁን ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ያልሰማነውና ልንሰማው የምንፈልገውን እውነት አንዳቸውም ትንፍሽ ሲሉ ያለማድመጣችን የፖለቲካችን ግትር ባህርያት ምን ያህል ከብረት የጠነከረና የማይተጣጠፍ እንደሆነ በሚገባ ማረጋገጥ ይቻላል። አንዱን መሠረታዊ ማሳያ ብቻ እናመላክት። ለመሆኑ የትኛው ፓርቲ ነው “እኔ ካሸነፍኩ ከዚህኛው ፓርቲ ይህንን ሃሳቡን ሙሉ ለሙሉ ተቀብዬ አብሬ እሰራለሁ። ከዚያኛው ፓርቲ ደግሞ ይሄኛውን ስትራቴጂ የጋራ መርህ በማድረግ አብሬ ለማስፈጸም እተጋለሁ። ከወዲያኛው ፓርቲ ደግሞ ያኛውን እቅዱን አብረን ለመፈጸም እምላለሁ ወዘተ.” ሲባል የሰማ ካለ መልሶ ቢያሰማን ለመተራረም ጥሩ አብነት ይሆናል። በግሌ ግን አልገጠመኝም።
የሚሻለውና የሚበጀው በአንድ ፓርቲ ጥላ ሥር የተሰባሰቡት “የምሁራን ሸንጎ አባላት” ደፈር ብለው በአካዳሚው ክበብ ውስጥ እንደተለማመዱት “የለም አንድ ምርምር ሲደረግ የተለያዩ ሃሳቦች ስለሚመሳከሩ ለፖለቲካ ሥርዓታችን ሊበጅ ስለሚችል ከሌሎች ፓርቲዎችም መልካሙን ሃሳብ እንጋራ፣ በጋራ በሚያግባቡን ስትራቴጂዎች ላይም አብረን ለመምከር ልበ ሰፊ እንሁን” ብለው ሊመካከሩም ሆነ አለቆቻቸውን ሊመክሩ ይገባል።
ያለበለዚያ ቀንቀሎ ስልቻ፣ ስልቻውም ቀንቀሎ መሆኑ እየታወቀ የራስን “ማኒፌስቶ” ቅዱስ፣ የሌላውን “ስትራቴጅክ ዕቅድ” እርኩስ አድርጎ መከራከር ለሀገርና ለሕዝብ ቀርቶ ለራስ “ነፍስም” አይበጅም። እንኳን አላፊ ጠፊ የፖለቲካ ሥርዓት ቀርቶ የአንድ ግለሰብ የማንነት ውቅር እንኳን የተገነባው በብዙ ባለድርሻ አካላት አስተዋጽኦ ነው። ከቤተሰብ፣ ከማሕበረሰብ፣ ከትምህርት ተቋማት፣ ከሃይማኖት፣ ከአርአያ ሰብ ግለሰቦች፣ ከሰፊው ኅብረተሰብ ወዘተ. እያልን በመዘርዘር ብዙ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል።
ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ሀገሬ የተራበችው ተስፋ እንጂ ጠብና ጠበኞችን አይደለም። እኛነትን እንጂ እኔና እኔነትንም አይደለም። እቅፍ አበባ ይዞ የነገ ቀኗን ብሩህ የሚያደርግላትን ተስፈኛና ተስፋ እንጂ በራሱ የርእዮተ ዓለም ገል እሳት እየጫረ “ና ደሞ ገለል” በማለት የሚያቅራራ ጀብደኛ ቡድንና ቡድንተኞችንም አይደለም። ጋሽ ጸጋዬ በግጥሙ ውስጥ ትዝብቱን እንደገለጸው ምርጫውና ውጤቱ በእጃንም በደጃችንም ነው።
አበባ አንሆን ወይ እሳት፣
ተጠምደን በምኞት ቅጣት፣
ሰመመን ባጫረው መዓት፣
ዕድሜያችንን እንዳማጥናት፣
እሳት አንሆን ወይ አበባ፣
በሐቅ እንቅ ስንባባ፣
ባከነች ልጅነታችን እየቃተትን ስናነባ።
ሳንፈጠር በሞትንባት፣
ሳናብብ በረገፍንባት፣
ሳንጠና ባረጀንባት፣
አበባ ወይንም እሳት፣ መሆኑን ብቻ አጣንባት።
ይህ መቃተት የደራሲው ምጥ ብቻም ሳይሆን የኢትዮጵያና የሕዝቧም ጭምር ነው። ሰላም ይሁን።
አዲስ ዘመን መጋቢት 15/2013