በኩረ ቃል፤
የጽሑፌን ዋና ርዕስ የተዋስኩት ከረጂም ዓመታት ወዳጄ ከመምህርና ደራሲ ስሜ ታደሰ የመጽሐፍ ርዕስ ነው። መምህር ስሜ ታደሰ በሚወደው የመምህርነት ሥራ ላይ እንደተጋና ሙያውን እንዳደነቀ እነሆ ድፍን አርባ ዓመትን አስቆጥሯል። ዛሬም ከዚሁ ተከባሪ ሙያው ላይ ሳይለይ ትውልድን በመቅረጽ ላይ ይገኛል።
መምህር ስሜ ታደሰ ከዋነኛው የማስተማሩ ሥራ ጎን ለጎን አሥር ያህል ዳጎስ ያሉ የጥናት፣ የምርምርና በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ መጻሕፍትን ለአንባቢያን በማድረስ ረገድም አንቱታን አትርፏል። ይህ ዕንቁ መምህር “ያልተዘመረላቸው” ከሚባሉ የአገር ባለውለታ ዜጎች ዝርዝር ውስጥ ቢካተት ተገቢም አግባብም እንደሆነ የዚህ ጸሐፊ እምነት ነው።
ይህ መምህርና ደራሲ ሁለት አሥርት ለሚጠጉ ዓመታት እያስተማረበት ባለው ኢንተርናሽናል ት/ቤት ውስጥ በተለየ ሁኔታ እያከናወነ ያለው የአርአያነት ተግባርና አግልግሎቱ ለሙያውና ለሕይወት ያለውን ጥርት ያለ ተልእኮና አክብሮት በሚገባ የሚያመለክት ነው። ካስተማራቸውና እያስተማራቸው ካሉት ተማሪዎቹ መካከል አንዳንዶቹ የቁንጮዎቹ የአገር መሪ ልጆች ሲሆኑ ብዙዎቹም የከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የታዋቂ ዜጎች፣ በተሰማሩበት የንግድ ሥራቸው ወይንም የተለያዩ የሙያ ዘርፎች አንቱታን የተጎናጸፉ ወላጆች ያፈሯው ልጆች ናቸው።
መምህሩ የሙያ ግዴታውን እየተወጣ ያለውም በክፍል ውስጥ ወስኖ ለሚያስተምራቸው ተማሪዎቹ ብቻ ሳይሆን ለወላጆቻቸው ጭምር የጻፋቸውን መጻሕፍት በአደራ እየላከ በየቤታቸው ከልጆቻቸው ጋር እንዲወያዩባቸውና እንዲሟገቱባቸው በማድረግ ረገድም ፈር ቀዳጅነቱን በሚገባ እያስመሰከረ መሆኑ ለየት ያደርገዋል።
ከጻፋቸው መጻሕፍት መካከልም በተለይም ይህ ጽሑፍ በርዕስነት የተዋሰው “ምን ሠርተን እንለፍ?”፣ “ተሳስቼ ነበር” በሚል ርዕስ በሁለት ተከታታይ ቅጾች፣ “የተከዳው እውነት” እና “ለእውነት እንቁም” የሚሉት አምስት መጻፍሕት በተለየ ሁኔታ በርዕሳቸውም ሆነ በይዘታቸው በሰፊ አንባቢያን ዘንድ በተማሪዎቹና በወላጆቻቸው መካከል ጥሩ የመወያያና የመከራከሪያ ርዕሰ ጉዳዮች እንደሆኑ ለማረጋገጥ ተችሏል።
መምህር ስሜ በአንድ ወቅት በማስተማር ተግባሩ ላይ እያለ በድንገተኛ ሕመም ተዝለፍልፎ በመውደቁ የትምህርት ቤቱ የሥራ መሪዎች ወደ ተለያዩ የሕክምና ተቋማት አስቸኳይ እርዳታ እንዲያገኝ ቢወስዱትም የጤና ባለሙያዎቹ “በተለይም በሁለቱ ተቋማት” የሰጡት መልስ “ልንረዳው አንችልም” የሚል ተስፋ አስቆራጭ ነበር።
በአጋጣሚ ለሦስተኛ ጊዜ በተገኘበት የሕክምና ተቋም ውስጥ ታናሽ እህቱ በጤና ባለሙያነት ትሠራ ስለነበር ወደ ሞት እየተቃረበ የነበረው ወንድሟ ሳታስበው እጇ ላይ በመውደቁ ኡኡታዋን በማቅለጧ እንደ መባነን ብሎ ነፍስ የዘራው መምህር ወዲያው የታወሰው ህልፈተ ሕይወቱ ሳይሆን “ምን ሠርቼ ነው የማልፈው?” የሚለው መሠረታዊ ጥያቄ እንደነበር ደጋግሞ በመጻሕፍቱ ውስጥ ጠቅሶታል። ከበሽታው እንዳገገመም ሳይውል ሳያድር ይኼንኑ ሃሳብ የሚወክል ርዕስ የሰጠውን መጽሐፍ ለንባብ አብቅቷል።
ይህ ዐምደኛ የዚህን አርአያ ሰብ መምህርና ደራሲ ገጠመኝ ዘርዘር አድርጎ ለማስታወስ የገፈፋውና እረፍት
የነሳው የአገሩ ወቅታዊ ጉዳይ ነው። ብዙው “ነፍስ አወቅ” ኢትዮጵያዊ ዜጋ በየተግባሩና በየውሎ መስኩ ልክ እንደ ወዳጄ የመጽሐፍ ርዕስ “ምን ሠርቼ ልለፍ? ለእውነት እቆማለሁ እና ተሳስቼ ነበር!” ብሎ ቢጠይቅና መልሱን ለማግኘት ቢሞክር ኖሮ የአሳረኛዋን አገራችንን መልክ ያጠየመውና ያጎሳቆለው የዛሬው መከራችን አንድም ባልበረታብን አለያም ዕድሜው ባጠረ ነበር።
ይህ ምኞታችን ተግባራዊ ባይሆን እንኳን “ልጄ ሆይ እንደምትሞት ሆነህ ኑር፤ እንደምትኖር ሆነህ ሥራ” የሚለው የአዛውንቶች እድሜ ጠገብ ምክር የእያንዳንዱ ዜጋ የሕይወት መርህ ሆኖ ዕንቆቅልሻችንን እያወሳሰበ ካለው ግርግርና ቱማታ መስከንና መረጋጋት በቻልንም ነበር። በፈጣሪ እስትንፋስ ተፈጥሯል የሚባለውና የኅሊና ባለንብረት የሆነው የሰው ልጅ ያለ በቂ ምክንያት የንጹሐንን ደም አፍስሶ እንደምን የሰላም እንቅልፍ አግኝቶ ተኝቶ ያድራል? በዛሬዋ ጀንበር እያጋጠምን ያለው አንዱ የመከራችን ዕንቆቅልሻችን ይህ ነው።
አገርና ሕዝብን ከጥፋትና ከወድመት ከመታደግ ይልቅ የክፋት ዘዴዎችን ሲያውጠነጥኑ ማደርንስ በምን ቋንቋ መግለጽ ይቻላል? አየራችንን የበከሉት እኒህን መሰል ይዘት ያላቸው ዜናዎች እንዴት እየተስፋፉ “የባህል ያህል” ሥር ወደ መስደድ ደረጃ ሊደርሱ እንደቻሉ ቆም ብለንና ጨክነን ልንወያይባቸውና ልንመክርባቸው ይገባል።
የፖለቲካውን ጡዘት በሴራ አክርሮ ሕዝብ እንዳይረጋጋ ማድረግ፣ የኢኮኖሚውን አውታር በማናጋት ዜጎች ቀለባቸው እምባ እንዲሆን በስግብግብነት ተጠፍሮ በጭካኔ የዕለት እንጀራ ላይ መፍረድ፣ ፍትሕን ማጣመም፣ ተገልጋይን ማስለቀስ፣ በማንነት ፍረጃ ላይ እየተረባረቡ ከሰብእና ማነስ ወዘተ. ትሩፋቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ማሰቡ በራሱ ናላን ያዞራል። እነዚህን መሰል ማሕበራዊ ጉድፎች መቅረፍና ማስወገድ የሚቻለው ከከዳነው እውነትና ከኅሊናችን ጋር እርቅ ፈጥረን ለራሳችንና ለሌሎች የሰላም
መልእክተኛ ሆነን ስንገኝ ብቻ ነው።
ለራስ የሚታወጅ “የክተት ጥሪ”፤
በዚህ ዕድሜ ጠገብ ጋዜጣ ላይ እጅግ በርካታ አገራዊ ህፀፆችን እየነቀስንና መልካሙን እያበረታታን ያለ መታከትና ያለ መቆጠብ መጻፍ ከጀመርን እነሆ ወደ አራት አስርት ዓመታት ልንጠጋ ጫፉ ላይ ደርሰናል። በመቶዎች ምናልባትም በሺህዎች ሊቆጠሩ የሚችሉት አብዛኞቹ ጽሑፎች በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩና ወደ ኅሊናችንና ወደ ቀልባችን ተመልሰን እንድንሰክን የሚያበረታቱ ናቸው።
በአንድ ወቅት ለንባብ የበቃን አንድ የምርምርና የጥናት ውጤት መነሻ በማድረግ ይሄው ጸሐፊ በአንድ አገራዊ መጽሔት ላይ ሃሳቡን ለማጋራት ሞክሯል። ጽሑፉ ለንባብ ከበቃ በኋላ በርካታ አስተያየቶች ደርሰውት እንደነበርም ያስታውሳል። ብዙ አንባቢያን በትንታኔው መደሰታቸውንና የተዘረዘረው እውነታ እንዳባነናቸው ቢገልጹም ጥቂት የማይባሉ አንባቢያን ግን በግኝቱ ላይ ልዩ ልዩ ጥያቄዎችን ማንሳታቸው አልቀረም ነበር።
ጥናቱ በተለያዩ አገራት ውስጥ የተሰራ ሲሆን መነሻ የተደረገውም በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ (መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ 90 ቁጥር 10) የተጠቀሰውና በብዙዎች ዘንድ እንደ ብሂል ተደጋግሞ የሚነገረውና የሰው የዕድሜ ጣሪያ የተወሰነበትን “የዘመኖቻችን ዕድሜ ሰባ ዓመት ቢበረታ ሰማንያ ዓመት ነው። ቢበዛ ግን ድካምና መከራ ነው” የሚለው ሃሳብ ነው። በጥናቱ ላይ የተሳፉት የተለያዩ የጥናት ዘርፍ ምሁራን በጋራ ተስማምተው የወሰኑትም “ሰባ ዓመት” የሚለውን ጣሪያ ሲሆን ይህቺን ቁራጭ አማካይ ዕድሜ በምንና ምን ጉዳዮች ላይ ሸንሽነን በማዋል ኖረን እንደምናልፍ በሚገባ በሰንጠረዥ አመላክተዋል።
ከእነ ጥያቄያችንም ቢሆን በአጥኚዎቹ የተዘጋጀውን የስታስቲክሱን መረጃ እንደ መነሻ በመውሰድ የራሳችንን አስተያየት እያከልንበት ማንነታችንን እንድንፈትሽበት ትንታኔውን እንደሚከተለው እናስታውሳለን።
ይህ የጥናት ግኝት ከአገር አገር፣ ከባህል ባህል፣ ከተሞክሮ ተሞክሮ ወዘተ. ሊለያይ እንደሚችል በሚገባ ይታወቃል። የእያንዳንዱ ሰው የሕይወት ተሞክሮና አኗኗርም በሽንሻኖ ከቀረበው ዜና መዋዕል ጋር በእጅጉ ሊጻረርም ሆነ ሊደጋገፍ እንደሚችል ለማናችንም አይጠፋንም። የቁጥሩና የመቶኛው ስሌት ይለያይ ካልሆነ በስተቀር ከእውነታው ነፃ መሆን ግን ከቶውንም እንደማይቻል ማሳወቁ አይከፋም።
ሌሎችን ዝርዝር ጉዳዮች ለጊዜው እናቆይና እያንዳንዱ አቅሙ ለሥራና ለኃላፊነት፤ ጤንነቱም አስተማማኝ የሆነ ግለሰብ በዕድሜ ቆይታ ዘመኑ በተግባሩ ላይ የሚያሳልፋቸው አሥራ ስድስት ዓመታት (22.8%) እንዳሉ ሆነው፤ ስሌቱ ሊበዛም ሆነ ሊያንስ እንደሚችል ልብ ይሏል፤ ጥያቄው መሆን የሚገባው “ስንት ዓመት በሥራ ላይ ተጠምጄ ኖርኩ?” ማለት ብቻም ሳይሆን “የማልፈው ምን ቋሚ ሐውልት አቁሜ ነው?” የሚለው ሊሆን ይገባል።
ከአሁን ቀደም በዚሁ ጋዜጣ ላይ Todd Henry የተባሉ እንግሊዛዊ ደራሲ “Die Empty” በሚል ርዕስ የጻፉትን እጅግ ተወዳጅና ተነባቢ መጽሐፍ አስመልክቼ ዘርዘር ያሉ ሃሳቦችን ማካፈሌ አይዘነጋም። የመጽሐፉ ዋነኛ የጭብጥ አስኳል፤ “በተሠጠህ የሕይወት ዘመን ያለኽን እውቀት፣ ሀብት፣ ብቃትና በጎነት፣ ያለ ስስት ለሰው ልጆች ሁሉ የጋራ በረከት እንዲሆን አንጠፍጥፈህ እለፍ እንጂ ለአፈር ቀለብ እንዲሆን በክፋትና በስግብግብነት ተገንዘህ ዓለምን አትሰናበት” የሚል እንደነበር የጋዜጣው ቤተሰቦች ያስታውሱ ይመስለናል።
የመምህርና ደራሲ ስሜ ታደሰን “ምን ሠርተን እንለፍ?” የመጽሐፍ ርዕስም ለመዋስ ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያት ይኸው ነው። ርዕሱ ይኽንን መሰል ሞጋች እውነታ በሚገባ ማጉላት ብቻም ሳይሆን ለዛሬው ዕለተ ረቡዕ የቀረበውን የመልእክታችንን አንኳር ሃሳብ የመሸከም አቅሙም ከፍ ያለ መሆኑን በማስታወስ ጭምር።
በየትኛውም አገርና ባህል ወይንም ዐውድ ውስጥ የተፈጠረ የሰው ልጅ በሙሉ (ሰባም ይሁን ሰማንያ ወይንም መቶ ከምናምን) የተቆረጠለት ዕድሜው አብቅቶ ግባ መሬቱ እንደሚፈጸም ይዘነጋ ካልሆነ በስተቀር ሊረሳ የሚችል አይደለም። ትኩረት ሊሰጥበት የሚገባው ዋነኛው ሃሳብ የአሟሟታችን ዓይነትና የሞታችን ጉዳይ ብቻ ሳይሆን “ምን ሠርተን እንለፍ?” የሚለው ሞጋች ጥያቄ ቀዳሚ ትኩረታችን ሊሆን ይገባል። ይህንን የማንፈጽም ከሆነ ግን “ሞት ሲደርስ ቄስ፤ ጦር ሲደርስ ፈረስ” ይሆንና በፀፀት እየተቀጣን ወደ መቃብራችን ለማዝገም እንገደዳለን።
እያንዳንዱ ነፍስ አወቅ ዜጋ ይህንኑ እውነታ ተረድቶ የበጎነቱን አሻራ ዘር ያለንፍገት በመዝራት የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት መልክና የአኗኗራችን ውበት እንዲደመቅ የራሱን ጠጠር አኑሮ ቢያልፍ አገራችንና ሕዝባችን እንደምን ከፍ ወዳለ ደረጃ መመንደግ እንደሚችሉ ለመገመት አይከብድም።
“ምን ሠርቼ ልለፍ፤ የጧት ገድ ይሁን፣
ማምሻ ላይ ትካዜ፤ መርዶ እንዳይሆንብን።
አለች ይባላል ሙሾ አሙሺዋ አስረጋጅ። ይኼው ነው። ሰላም ይሁን።
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ኅዳር 21/ 2015 ዓ.ም