ኢትዮጵያ በረጅም የታሪክ ሂደቷ ውስጥ በርካታ ኩነቶችን ያለፈች አገር ናት፡፡ እስከ ዛሬዋ እለት ድረስም ቢሆን ጥላቶቿ እንዲሁም ወዳጅ መሰል ምቀኞቿ የተኙላት አገር አይደለችም፡፡ አልተሳካም እንጂ ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለመያዝ ያልተሞከረ ነገር ያልተወጣበት ዳገት የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ነገር ግን ብዙ ጊዜ ተሞክሮ ከሽፏል፡፡ እነዚህ በኢትዮጵያ የሚጎመዡ አገራት ሙከራቸውን የሚደርጉት ደግሞ ሁሌም የውስጥ ባንዳዎችን በመጠቀም ነው፡፡
“የእናት ሆድ ዥንጉርጉር” እንደሚባለው ይህች ታላቅ አገር እጅግ ጥቂት ማፈሪያ ባንዳ ልጆች ስላሏትም ያልተሳኩም ቢሆኑ ብዙ የእጅ አዙር ቅኝ ግዛቶች ሙከራ ተደርጎባታል፡፡ ነገር ግን ጥቂት ባንዳ ልጆች ቢኖሯትም መላው በሚባል ደረጃ ያለው ህዝብ ግን ይጠብቃታል፤ ይሞትላታልም፡፡ ሁሌም ህዝብ አሸናፊ በመሆኑ ኢትዮጵያ ከነ ክብሯ እዚህ ደርሳለች፡፡
በተመሳሳይ በውስጥ ጉዳዮቿ ሳይቀር የውጭ ጣልቃ ገብነቱ አንዴ ሞቅ ሌላ ጊዜ ቀዝቀዝ ሲል ይታያል፤ ይኸው ድርጊት አሁን ድረስ ቀጥሏል፡፡ ጣልቃ ገብነቱ ሁለት መልክ ያለው ሲሆን፤ የመጀመሪያው በቀጥታ የሚከናወን ነው፡፡ ለአብነትም የጣልያንን ወረራ ተከትሎ ምዕራባውያን አገራት በግልጽ ኢትዮጵያ ላይ ያደረጉት ጣልቃ ገብነት ተጠቃሽ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በተዘዋዋሪ መንገድ የሚደረግ ጣልቃ ገብነት ሲሆን እንደ የዓለም ገንዘብ ድርጅት፣ የዓለም ባንክ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ረድኤት ድርጅቶችንና ሚዲያዎችን የመሳሰሉ ተቋማትን በመጠቀም የሚደረገው ጣልቃ ገብነት ነው፡፡
በኢትዮጵያ አሁን ያለው ጣልቃ ገብነት ደግም ሁለቱንም አካሄዶች የተከተለ ነው፡፡ የአሜሪካ መንግስት ከዚህ ቀደም ለግብጽ በይፋ በመወገን ሁኔታ የኢትዮጵያን በአባይ ወንዝ የመጠቀም ፍትሃዊና ተፈጥሯዊ መብት ለመንፈግ ሞክሯል፡፡ “የአፍሪካን ችግሮች በአፍሪካውያን” የሚል መርህ ያለውንና በአፍሪካ አገራት ሙሉ ተሳትፎ የተቋቋመውን የአፍሪካ ህብረት ስልጣን ወደ ጎን በመተው ፍርደ ገምድል ውሳኔዎችንም ሲያሳልፍ አይተናል፡፡
ይህ አልሳካ ሲል ደግሞ አሸባሪነትን ለማጥፋት ቀዳሚ ነኝ የሚሉት ምዕራባውያን የራሱን አገር መከላከያ በክህደት ያጠቃውን አሸባሪውን የትህነግ ቡድን ወደ ስልጣን ለመመለስ የሚችሉትን ሁሉ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ለጦርነቱ ተጎጂዎች መሰጠት ያለበት ምግብና መድኃኒት ለሽብር ቡድኑ አባላት ሲያከፋፍልና ሲጠቀምበት ከማየት በላይ የሚያሳዝን ነገር ባይኖርም ይህንን እውነት ግን በአደባባይ ከማውገዝ ይልቅ አሸባሪን በመደገፍ እውነትን ለመደፍጠጥ ሲሞክሩ ነው የተስተዋለው፡፡
የዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች ጠበቃ ነን የሚሉት የውጭ ኃይሎች እነዚህን ምክንያቶቻቸውን ሰበብ አድርገው የገቡባቸው አገራት ሁሉ ወደ ፍርስራሽነት ሲቀየሩ ዓለም አይቷል፡፡ ኢራቅ፣ አፍጋኒስታን፣ ሶማሊያ፣ ሊቢያና የመሳሰሉት አገራት ዜጎች የሰላም አየር መተንፈስ ቅንጦት ሆኖባቸዋል፡፡
የቀውስ ፖለቲካ ነጋዴዎቹ እሳት ጭረው የመሳሪያ ገበያቸውን ያደራሉ፣ አዳዲስ የጦር መሳሪያዎቻቸውን ይሞክራሉ፣ የሃብት ምዝበራቸውንም ያጧጡፋሉ፡፡ ይህ በኢትዮጵያ ምድር ሊሳካ የሚችል ጉዳይ እንዳልሆነ ልጆቿ እያረጋገጡ ነው፡፡ ወደፊትም ያረጋግጣሉ፡፡
በእልቂት ደጋሾቹ ከጥንስሱ ጀምሮ የሚከናወነው ሴራ ከተቻለ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ካልተቻለ እንደ ትህነግ ያለ ተላላኪ መንግስት ኢትዮጵያ ላይ መመስረት የሚል ዓላማ እንዳለው የኢትዮጵያ ህዝብ ጠንቅቆ አውቋል፡፡ ለዚህም ነው የሚመጣውን የውጭ ጫና በአንድነት ሲመክት የቆየው፤ አሁንም እየመከተ የሚገኘው፡፡
ይህ አንድነቱ ዛሬም በሁሉም አቅጣጫ መጠናከሩ ለኛ እጅግ የሚያስደስት ለጠላት ደግሞ ሴራው እየከሸፈ መሆኑን የሚያሳይ መሆኑን ደግሞ በኢትዮጵያ ላይ ቀጥተኛና የእጅ አዙር ጫና እያሳደሩ ያሉ ምዕራባውያን ሁሉ ሊረዱት ወደቀልባቸው ተመልሰውም የአገሬን እውነት ሊያውቁና ሊቀበሉ ብሎም በዛው ልክ ቆመንለታል ለሚሉት ዴሞክራሲና ፍትህ ታማኝ ሊሆኑ ይገባል፡፡
ኢትዮጵያ ረጅም የመንግስትነት ታሪክ ያላት አገር ከመሆኗም በላይ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምስረታና በአፍሪካ ህብረት መመስረት ላይ ከተቀሩት የአፍሪካ አገራት በተሻለ መልኩ የላቀ ሚናዋን የተወጣች አገር መሆኗን የሚስተው አለ ብዬ አላምንም፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ በተለይም ሰላምና ፍትህ ለራቃቸው አገራት ቀድማ የምትደርስ አቅሟን ተጠቅማም ድምጽ የምትሆን አገር መሆኗም የሚካድ አይደለም፤ አሁንም በገሀድ የሚታይ ሀቅ በመሆኑ ፡፡
ታዲያ እነዚህ ምዕራባውያን በራሳቸው ጥቅም ላይ ማንም እንዲመጣ እንደማይፈልጉት ሁሉ ለምን በሌሎች ጥቅም ላይ ይረማመዳሉ የሚለው የሁልጊዜም ጥያቄዬ ነው፤ ይህን ጥያቄ መመለስ ደግሞ እጅግ በጣም አስፈላጊም ይመስለኛል፡፡ በተለይም የዴሞክራሲ አባት እናት ነን፤ የሽብርተኞች መድኃኒት ነን ብለው በሚያወሩት ምዕራባውያን ዘንድ፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብም አገሩን ከጠላት ለመጠበቅ ዘብ ቆሟል፡፡ የህዝቡ ግልጽ መልዕክትም በምዕራባውያን ሴራ ኢትዮጵያ መቼም አትፈርስም! ሁሌም ሁላችንም ከአገራችን እውነት ጎን እንቆማለን የሚል ሊሆን ይገባል፡፡
ሁሉም ወገን በውጭም በውስጥም ያለው ኢትዮጵያዊ አገሩ ከያዘችው እውነት ጎን መሰለፍ አሁን ላይ የውዴታ ግዴታው መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ በዓለም አደባባይ ብሎም በአገራችን ዜጎች ከያሉበት ተሰባስበው ድምጻቸውን ለዓለም ማህበረሰብ ለማሰማት እውነታችንን ለማስረዳት የጀመሩት መንገድ እጅግ ጥሩ ከመሆኑም በላይ ኢትዮጵያ ሁሌም በልጆቿ ታፍራና ተከብራ እንዲሁም ድል አድርጋ እንደምትኖር ማሳያ ይመስለኛል፡፡ ሁላችንም በአንድነት ከአገራችን እውነት ጎን የምንቆምበት ጊዜው ደግሞ አሁን ነው፡፡
‘ለኢትዮጵያ እቆማለሁ ድምጼን አሰማለሁ’ በሚል መሪ ሃሳብ ሊካሄድ የታቀደው ሰላማዊ ሰልፍ ላይም በመሳተፍ ኢትዮጵያ ከያዘችው እውነት ጎን በመቆም ከአሸባሪው የትህነግ ቡድን ጋር በመወገን ኢትዮጵያ ላይ ተጽእኖ ለማሳደር የሚጥሩ አካላትን ማሳፈር በመሆኑ እንደ ዜጋ የሚጠበቅብንን ለማድረግ መዘጋጀት ይገባል። መንግስት የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት ለማስጠበቅና ሉአላዊነቷን ለማረጋገጥ የሄደበትን ርቀት ማድነቅ እንዲሁም መደገፍ ኢትዮጵያን መደገፍ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልገናል።
የትህነግ የሽብር ቡድን ህልውናውን ለማቆየት ሲል የትግራይ ሕዝብን ለከፋ ችግር እየዳረገ በመሆኑም ይህ ግፍና መከራ በግልጽ እንዲታወቅ፤ ግፍና መከራውን ወደ ጎን በመተው ኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ጫና የሚፈጥሩ አካላት በቃችሁ ለማለትም ከዚህ የተሻለ ጊዜ ይኖራል ብዬ አላስብም። ከዚህ ባለፈ የውጭ ኃይሎችን ጣልቃ ገብነት ማውገዝ እና ከኢትዮጵያ ጎን የቆሙ አገራትን ማመስገን ኢትዮጵያዊ ባህላችን ያስተማረን ጨዋው የእኛ ስነ ምግባር ነው።
ኢትዮጵያውያን ይህንን በሉዓላዊነት ላይ የተጋረጠ መልከ ብዙ ጫና በጋራ ቆመን መመከት ካልቻልን በተመሳሳይ የኢትዮጵያን የግዛት አንድነትን ለማስጠበቅ መንግስት እያደረገ ያለውን ጥረት መደገፍ ከተሳነን እውነት የአባቶቻችንን አደራ በሊታ ሆነን በታሪክ መዝገብ የምንሰፍር ትውልዶች እንሆናለን። አበቃሁ፡፡
በእምነት
አዲስ ዘመን ጥቅምት 14/2015