በለፈው ሳምንት የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን ቀኖች ነበሩ ማለት ይቻላል። ኢትዮጵያውያን ስለሀገራቸው ድምጽ የሆኑበት፣ የምዕራባውያንን ጠልቃ ገብነት የተቃወሙበት የአንድነት ቀን ነበር። “ለኢትዮጵያ እቆማለው፣ ድምጼን አሰማለው” በሚል መሪ ቃል በመላው ኢትዮጵያ የምዕራባውያንን ጣልቃ ገብነት በመቃወም በነቂስ ወጥተናል። መውጣት ብቻ አይደለም ሀያላን ሀገሮች በኢትዮጵያ ላይ ያላቸውን ያልተገባ አካሄድና እንቅስቃሴ እንዲያቆሙ ድምጽ አሰምተናል። ይሄ ብቻ አይደለም አንዲት ሉአላዊትና በድሞክራሲ መንገድ በተመረጠ መንግስት የምትመራን ሀገር ከአንድ አሸባሪ ቡድን ጋር አጣምሮ ማየት ተገቢ እንዳይደለ፣ ኢትዮጵያን ስለሀገራችን ማንኛውንም መስዋዕት ለመክፈል እንደተዘጋጀን ድምጻችንን አሰምተናል።
የተቃውሞ ሰልፉ የአንድና ሁለት ግለሰብ ወይም ደግሞ የጥቂት ሀገር ወዳድ ጥሪ ሳይሆን በውጪም በውስጥም ያሉ የሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ጥሪ ነበር። በዋናነት ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር አብሮ ኢትዮጵያን ለማዋረድና ለማፍረስ እየተንቀሳቀሰ ያለውን ሀገር በቀሉን አሸባሪ ቡድን በመቃወምና የምዕራባውያንን ከፍትህ ያፈነገጠ ጣልቃ ገብነት በመቃወም የተደረገ ነበር። በተቃውሞ ሰልፉ ላይ ብዙ ድምጾች ተሰምተዋል፣ ብዙ መፈክሮች ታይተዋል።
ከተሳታፊዎች ድምጽ ውስጥ የተወሰኑትን ብናነሳ እንኳን ” አሸባሪው ትህነግ ለሰሜኑ ጦርነትና ለትግራይ ህዝብ መከራና እንግልት ምክንያት ነው፤ ለሀገራችን አጠቃላይ ሰላም ሲባል ትጥቅ መፍታት አለበት” የሚሉ ድምጾች ተሰምተዋል። ከዚህ ባለፈም ” በአንዲት ሉአላዊት ሀገር ውስጥ መሳሪያ የታጠቀ ሁለት የጦር ሰራዊት የለም፣ አሸባሪው ትህነግ የኢትዮጵያ ጠላት ነው”፤ ” በሉአላዊነታችን አንደራደርም፣ በሰብዐዊ እርዳታ ስም ጣልቃ ገብነት ይቁም” የሚሉና ሌሎችም የቁጣ ድምጾች ከዚም ከዛም ተደምጠዋል።
ሲነኩን እንበዛለን የምንለው በምክንያት ነው። ቀናቶች ኢትዮጵያውያን ሲነኩን እንደምንበዛና ስለህልውናችን ቀልድ የማናውቅ መሆናችንን ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ያሳየንበት ነበር። የሰሜኑ ጦርነት እንዴት እንደተጀመረ ሁላችንም እናውቃለን። በራስ ወዳዱና እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል በሚል አስተሳሰብ ውስጥ ተወልዶ ባደገው አሸባሪው ትህነግ ነው። ሀገር ሲጠብቅና የትግራይን ህዝብ ሲያገለግል በኖረው የሰሜን እዝ ሰራዊት ላይ ጥቃት ፈጽሞ የጀመረው ነው።
አሸባሪው ትህነግ በዚህ ብቻ በአለም አቀፉ የወንጀል ህግ መጠየቅ ይችል ነበር። በነገራችን ላይ በአለም ታሪክ የገዛ ወንድሙን፣ የገዛ ወገኑን፣ ከወንድምነትና ከወገንነት ባለፈ በተለያየ ማህበራዊ ስራዎች ላይ እየተሳተፈ አጋርነቱን ያሳየን ሰራዊት አጥቅቶ ጦርነት የከፈተ ትህነግ ብቻ ነው። የሰሜን እዝ ለትግራይ ህዝብ ሁሉንም ነገር ነበር። የቡድኑ የክፋትና የጭካኔ ጥግ ከዚህ የሚጀምር ነው። ለኢትዮጵያ እቆማለው፣ ድምጼን አሰማለው ስንል የተነሳነው ይሄን ነውረኛ ቡድን ለመቃወም ነው።
ያለፉትን ሁለት አመታት ስለ አሸባሪው ትህነግ ያልጮህንበት ጊዜ የለም። በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ፊት የቡድኑን ነውርና ወንጀለኝነት ለመግለጥ በዚያም በዚህም ጮኽናል። በሀገር ውስጥ ያለንው እንደ ሰሞነኛው አደባባይ በመውጣት ድምጻችንን አሰምተናል። በውጪ ያሉት “ኖ ሞር” በሚል እንቅስቃሴ ስለነውረኛው ቡድን ተቃውሟቸውን በመግለጥ ላይ ናቸው። ጩኸታችን ፍሬ እስኪያፈራ ድረስ ገና እንጮሀለን። ስለ ክብራችን፣ ስለህልውናችን፣ ስለሉአላዊነታችን በሚሰሙንም ፊት ሆነ ሊሰሙን ባልፈለጉት ፊት እንጮሀለን።
ኢትዮጵያውያን በጋራ ቆመን፣ በጋራ ጮኸን ያላሸነፍንበት ጊዜ የለም። የአሁኑ መጮሀችንም ለማሸነፍ ነው። እውነታችንን አለም አቀፉ ማህበረሰብ እስኪረዳውና በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ መግባታቸውን እስኪያቆሙ ድረስ አደባባይ መውጣታችንን አናቆምም። በአንድነት ቆመን የጻፍናቸውን የትላንት ታሪኮቻችንን ለመድገም አሁን ትክክለኛው ጊዜ ነው። ኢትዮጵያን ለማዳንም ሆነ ወደ ከፍታዋ ለማውጣት ከዚህ የተሻለ ጊዜ የለንም። ስለ ነጻነታችን ለመጮህ፣ ስለክፉዎች ለመሟገት ትክክለኛው ጊዜ ላይ ነን። በዚህ ጊዜ ዝም የሚሉ የኢትዮጵያ ወዳጆች አይደሉም..በዚህ ጊዜ ዝም የሚሉ አሸባሪው ትህነግ ወዳጆች ናቸው።
እኛ ኢትዮጵያውያን ብዙ ነን..በታሪክ፣ በአንድነት፣ በጀግንነት ብዙ ነን። ለራሳችን አንሰን አናውቅም። ከትላንት እስከዛሬ የተራመድንባቸው ታሪኮቻችን የሚነግሩን ለራሳችን በቂዎች እንደሆንንና ከራሳችንም አልፈን ለሌሎች እንደተረፍን ነው። በሰላም መስከበር ተልእኮ ከአፍሪካ ተርፈን እስከ ኮሪያ ዘልቀናል። .ከትላንት የራቀ፣ ከአምና የሸሸ ኢትዮጵያዊነት የለንም። ዛሬም በትላንቱ መንፈስ ውስጥ ነን። ለነኩን እሳት፣ ላከበሩን ፍቅር ነን። ኢትዮጵያ ስለሀገራቸው በሚቆጡና፣ ስለክብራቸው በሚጮሁ የቁርጥ ቀን ልጆቿ መሀል ናት። አለም ያውቀናል..ማን እንደሆንንና ለምን በዚህ ልክ ከአሸባሪ ቡድን ጋር ወግነው እንደሚያስቸግሩን ግልጽ ነው። ክብራችንን እነሱ በሚፈልጉት መልኩ ስላልመነዘርንና፣ ለሀሳባቸውና ለምኞታቸው የተመቸ አቋም ስለሌለን ነው። ሲጠሩን አቤት፣ ሲልኩን ወዴት ስላላልን ነው።
የአሁኗ ኢትዮጵያና የአሸባሪው ትህነግ ዘመን የተለያዩ ናቸው። የአሸባሪው ትህነግ ዘመን ኢትዮጵያ በአሸባሪዎች ራስ ወዳድነት ለሌሎች ተላልፋ የተሰጠች..ኢትዮጵያዊነት ክብር ያጣችበት፣ ሉአላዊነቷ የተደፈረበት ነበር። በስልጣን ጥም በታወረ አእምሮ ያለባልደራስ የምትሰግር ፈረስ ነበረች። የብዙሀኑ ህዝብ መብትና ፍላጎት ተረግጦ የጥቂት ቡድኖች አላማና ፍላጎት የሚፈጸምባት ነበረች።
የአሁኗ ኢትዮጵያ ግን ሌላ ናት..ሌላ ስለሆነች እኮ ነው የተነሱብን። የአሁኗ ኢትዮጵያ ያን የውጪ ጣልቃ ገብነትን የተቃወመች፣ ለራሴ በቂና ከበቂ በላይ ነኝ ብላ የምታምን ናት። የአሁኗ ኢትዮጵያ እኔ ከአለም በፊት ነበርኩ፣ አሜሪካና ሀያል ነን የሚሉ ሀገራት እንደሀገር ከመመስረታቸው በፊት፣ እንደ መንግስት ከመቆማቸው በፊት እኔ ሀገርና መንግስት ነበርኩ ብላ የምታምን ናት። የአሁኗ ለአለም ጥቁሮች ነጻነትን ፋናጊ ነኝ፣ ማንም በኔ የውስጥ ጉዳይ ሊያቦካና ሊጋግር አይችልም ብላ በጽናት የቆመች ናት።
ምዕራባውያን ይቺኛዋን ኢትዮጵያ አይፈልጓትም። አዳወዷጽም፡፡ለእነሱ የሚሆን ምንም ስለሌላት ይጠሏታል። እኔና እናንተ ግን ይቺኛዋን ኢትዮጵያ ከመውደድ አልፈን እናፈቅራታለን። ምክንያቱም ለእኛ የሚሆን ብዙ ነገር አላት። አንዳንድ ምዕራባውያን ይቺኛዋን ኢትዮጵያ ቢፈልጓት ኖሮ ከአሸባሪ ጋር አብረው በዚህ ልክ አይፈታተኗትም ነበር። ይቺኛዋን ኢትዮጵያ ቢፈልጓት ኖሮ አሁን ላይ ከሕወሓት ሸር ይልቅ ከእኛ እውነት ጋር ይቧደኑ ነበር።
እየጮህን ያለንው፣ “ኖ ሞር” እያልን ያለነው፣ በመፈክርና በቁጣ አደባባይ እየወጣን ያለነው ለዚችኛዋ ኢትዮጵያ ነው። አሁን ላይ እየሞትንና እየተጎሳቆልን ያለንው ለዚችኛዋ ኢትዮጵያ ነው። በእውነትና በፍትህ ለእኔም ለእናተም ሀገር ልትሆን፣ ክብር ልትሆን፣ ታሪክ ልትሆን የምትችል ሀገር ታስፈልገናለች። እየታገልን ያለነው ሀገር ለመፍጠር ነው..ከ አሸባሪው ትህነግ እና ከአስተሳሰቡ የጸዳች፣ ዘረኝነትና ብሄርተኝነት የማይቀነቀንባትን ጦብያ ለመፍጠር ነው። የየትኛውም ሀገር የበላይነት የማይንጸባረቅባት፣ ለልጆቿ ምቹና ተስማሚ የሆነችን ምድር ለመፍጠር ነው።
የትኛውም ሀገር እንደኢትዮጵያ አይነት የአንድነት ታሪክ የለውም። ታሪኮቻችን ሁሉ በአንድነት ተጀምረው በአንድነት ያበቁ ናቸው። ዛሬም አንድነት ብቻ ነው የሚያስፈልገን። አንድ ከሆንን ሁልጊዜም አሸናፊዎች ነን። አንድ ከሆንን ሁሌም ባለታሪኮች ነን። አሸባሪው ትህነግ እና ጃሌዎቹን በአንድነት ካልሆነ አናሸንፋቸውም። በህዳሴ ግድባችን ላይ ያሳየነውን የአንድነት መንፈስ በችግሮቻችን ላይ መድገም አለብን።
ኢትዮጵያዊነት ከአንድነት የላቀ ሌላ ደማቅ ስም የለውም። ኢትዮጵያዊነት ሲነሳ አብሮ የሚነሳ አንድ ነገር ህብረታችን ነው። ጠላቶቻችን የተበታተኑት፣ ከእግራችን ስር የወደቁት በአንድነት ክንዳችን ነው። አሁን ላይ ላሰብን ማናቸውም ችግር መፍትሄ የሚሆነው በአንድነት መቆም፣ በአንድነት ድምጽ ማሰማት ነው። በአንድነት ከተነሳን የሚችለን ሀገርና ህዝብ የለም። ኢትዮጵያን ከአውሬዎች ታድገን የራሳችን ብቻ የምናደርጋት የአንድነት ድምጽ ሲኖረን ነው።
የሚያሸንፉን ሲከፋፍሉንና በአሉባልታ ወሬ ሲያናውጡን ብቻ እንደሆነ ነው ። የሚያሸንፉን እንደ አሸባሪው ትህነግ ካሉ የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ሲያብሩ ብቻ እንደሆነ ነው ። እኛም ልናሸንፋቸው የምንችለው በአንድነት ስንቆም ብቻ እንደሆነ ልንረዳ ይገባል። አሁን ከሆነውና እየሆነው ካለው የሀገር ስሜት በላይ ስለሀገራችን ድምጽ ማሰማት ይኖርብናል።
አሸባሪው ትህነግ ት ፍጻሜ እየተቃረበ ነው..በዚህ ግብዐተ መሬት ላይ ከወዳጆቹ በኩል የሚመጡ አንዳንድ አሉባልታዎችና ጣልቃ ገቦች መኖራቸው አይቀርምና እንደሰሞነኛው ስለሀገራችን አደባባይ መውጣታችን መቀጠል አለበት። እውነታችን እስኪገባቸው ድረስ፣ እየጮህን ያለነው ለምን እንደሆነ እስኪረዱ ድረስ አደባባይ መውጣታችንና መናገራችን ይቀጥላል።
አሸባሪው ትህነግ ኢትዮጵያን ለመገዳደር አቅም ኖሮት ሳይሆን በኢትዮጵያ ጠላቶች እየተደገፈ ስለመጣ ነው ህልውናውን ያቆየው። ቡድኑ ሲያጠቃ ዝም እያሉ ኢትዮጵያ ስታጠቃ ቺሀታቸው ይበረታል ። የመግለጫ ጋጋታ የሚያወጡ፣ የማዕቀብ መዐት የሚያወርዱ..እነሱ ናቸው ጠላቶቻችን። እነዚህ ጠላቶቻችን አንድ የሚፈሩት ነገር አለን..እርሱም አንድነታችንን ነው።
ለራሳችን በቂዎች እንደሆንን በድምጻችን ልናሳውቃቸው ይገባል። ኢትዮጵያዊነት አሁን እነሱ እንደሚሉት በሌሎች ድጋፍና እገዛ የቆመ አይደለም። ራሳቸውን ችለው በቆሙ እግሮች፣ ራሳቸውን ችለው በሚያስቡ ጭንቅላቶች የቆመ ነው። ከአሸባሪው ትህነግ ጋር የሚያረግዱት እንደፈለጉ ሊሆኑብን መግቢያ ቀዳዳ ፍለጋ ነው። ክብራችንን አሳልፎ ለሚወስድ ምንም አይነት የማርያም መንገድ የለንም ። በማስፈራራት ፣ በእርዳታና በእርቅ ስም የማርያም መንገድ እየፈለጉ ያሉ ወደፊትም አይሳካላቸውም። ለዚህ የሚሆን የስነ ልቦና ውቅር የለንም ።
ኢትዮጵያ ጣፍጦን የምንጠራው ስም ነው። በዚህ በጣፈጠ ስማችን ውስጥ መራራዎችን የሚታገስ ሞራል የለንም። ስለ ኢትዮጵያ ሰልፍ መውጣታችን ሁሌም ይቀጥላል። በዚህ የሚያበቃ ምንም የለንም። የጀመርናቸው ነገሮች ሁሉ ኢትዮጵያን ከፊት አድርገን የምንቀጥላቸው ናቸው። ስለኢትዮጵያ ገና እንጮሀለን። እንደ እያሪኮ በጩሀት የክፉዎችን ሀሳብ እንደረምሳለን። ኢትዮጵያ ዝቅ ለማድረግ የክፋት ግንብ የሚገነቡ ባብሎናውያንን ቋንቋቸውን እንደባልቃለን።
ለራሳችን በቂዎች እንደሆንን፣ ችግሮቻችንን ለመፍታት የመፍትሄ ሀሳብ እንዳለን አለም እንዲያውቅና እንዲረዳ ገና እንጮሀለን። እኛ ከአለም በፊት ሀገርና ህዝቦች ነበርን። የሌሎችን ጣልቃ ገብነት የሚፈቅድ ታሪክም ማንነትም የለንም። ከራሳችን አልፈን ለመላው ጥቁር ህዝብ የቀና ማለት ምክንያት ሆነን ኖረናል። አፍሪካን የወለደ ማህጸን የሌሎችን ጣልቃ ገብነት የሚፈቅድ ሞራል የለውም። ሀገራት የአሸባሪው ትህነግን እኩይ ተግባር ከመደገፍ እንዲቆጠቡና ሩቅ ሊያስኬድ ከማይችል ተግባራቸው እንዲሰበሰቡ ድምጻችንን እናሰማለን።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ጥቅምት 19/2015