ታሪክን ለትምህርታችን፤
የሁለተኛው የዓለም ጦርነት በተጠናቀቀ ማግሥት የበርካታ ኮሚኒስት ሀገራት የፖለቲካ ፓርቲዎች “የዓለም የሰላም ካውንስል” (World Peace Council) በሚል ስያሜ የምክክር ተቋም ፈጥረው ነበር። ተቋሙ የተመሠረተበት ዋነኛ ዓላማ “ጉልበተኞቹና ጦረኞቹ የምዕራብ ሀገራት” ከጦር መሣሪያ እሽቅድምድ እንዲታቀቡ፣ በሉዓላዊ ሀገራት ውስጥ በቀጥታና በእጅ አዙር ቅኝ ገዢነት እንዳይሰለጥኑ ወይንም እንዳይሰየጥኑ፣ ጅምላ ጨራሽ የጦር መሣሪያዎቻቸውን ወደ ማረሻና የኢንዱስትሪ የማምረቻ ማሽኖች እንዲለውጡ ለመምከርና ለማስገደድ ታስቦ ነበር። “የራሷ እያረረባት…” የሚለውን ብሂል ያስታውሷል።
በአጭሩ “የሰላም ጉባዔው” ዋነኛ መሻት ኮሚኒስታዊው የምሥራቁ ርዕዮተ ዓለም በምዕራባዊው የኢምፔሪያሊዝም ቀኖና ላይ ጉልበት አግኝቶ በአሸናፊነት እንዲወጣ ታስቦ ነበር። አስተባባሪውና የበጀቱ ምንጭ ደግሞ የቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ኮሚኒስት ፓርቲ ነበር። በድጋሚ “አመድ በዱቄት ይስቃል” አባባልን ማስታወሱ ተገቢ ይሆናል።
እ.ኤ.አ በ1949 በፓሪስ ከተማ ሊካሄድ ለታቀደው ለዚህ “ዓለም አቀፍ የሰላም ጉባዔ” መሪ ዓርማ (Logo) ያስፈልግ ስለነበር የአዘጋጆቹ ሙሉ ድምጽ አግኝቶ የዓርማውን ንድፍ በ1948 ያዘጋጀው እስፓኛዊው ሠዓሊ ፓብሎ ፒካሶ (1881 – 1973) ነበር።
ይህ ታላቅ ዝነኛ የዓለማችን ሠዓሊ ጉባዔውን ይወክላል ብሎ የመረጠው ንድፍ “በአፏ የወይራ ቀንበጥ የያዘችን ርግብ” ነበር። የሰላም ተምሳሌቷ ርግብ ዓርማ ጸድቆ አገልግሎት ላይ በዋለ ማግሥት የምዕራብ ሀገራት ሠዓሊያን የዓርማውን ቅርጽና ይዘት በማብጠልጠል በሠዓሊው ላይ ለመሳለቅ ጊዜ አልወሰደባቸውም።
የምሥራቁን የዓለም ክፍል “በቅኝ ግዛትነት” እየተቆጣጠረ ያለው ኮሚኒስታዊው ርዕዮትና አመለካከት ራሱ በሽተኛና ታማሚ ስለሆነ፤ ለዓለም ሰላም መከበር ጠበቃ ሆኖ ሊከራከር የሞራልም ሆነ የሕግ ተቀባይነት ስለሌለው “የማታምኑበትን አታውጁ” የሚልና በተቃውሞ የታጀበ ንቅናቄ ዋነኛው የትችቱ ምክንያት ነበር።
“ስለዚህም…” አሉ ሠዓሊያኑ፤ “የሰላም ጉባዔው ሊወከል የሚገባው በቆሰለች የርግብ ንድፍ እንጂ የወይራ ቀንበጥ በአፏ ይዛ በምትከንፍ ርግብ መሆን አይገባውም” በማለት እጅግ በርካታ ሠዓሊያን የወይራ ቀንበጧ ከአፏ ላይ የወደቀና በደም የተጨማለቀች የርግብ ምስል በማዥጎድጎድ ተቃውሟቸውን አጠናክረው ቀጠሉ። ታሪኩ ብዙ የሚባልለት ስለሆነ እዚህ ላይ አቁመን ወደ ራሳችን ወቅታዊ ጉዳይ ተመልሰን ጓዳችንን እንፈትሽ።
ይህ አምደኛ ይህንን ታሪክ ባነበበት አንድ ወቅት “ኦ! ሰላም በስምሽ ስንት ግፍ ተሠራ!” የሚለው የዓለማችን ጩኸት ስሜቱን ነክቶት የሚከተለውን ባለ አራት ስንኝ ግጥም ያዋቀረው በሀገሩ ጉዳይ በእጅጉ እየቆዘመ ነበር።
“ቀንበጧን በመጣል የት ሄደች ለምን ግብር!?
የሰላምን ብሥራት አብሳሪዋ ርግብ።
እያልኩኝ ስጠይቅ የእኔም ተስፋ ወድቆ፣
ከደሟ ነጠብጣብ ጣለኝ እግሬ ወስዶ።”
ፓብሎ ፒካሶ ርግብን የሰላም ምሳሌ እንዲያደርግ ሃሳብ የፈነጠቀለት የቅዱስ መጽሐፉ የዘመነ ኖኅ የውሃ ጥፋት ታሪክ መሆኑ በሚገባ ይታወቃል። ታሪኩን በጥቂቱ እናስታውስ፡- “ከአርባ ቀናት በኋላ ኖኅ የሠራውን የመርከቧን መስኮት ከፍቶ ውሃው ከምድር ገጽ ጎድሎ እንደሆነ ለማወቅ ርግብን ላከ።…ርግቧም ወደ ማታ ተመለሰች። እነሆም የለመለመ የወይራ ቅጠል በአፏ ይዛ ነበር። ያን ጊዜ ኖኅ ውሃው ከምድር ላይ መጉደሉን አወቀ” (ዘፍጥረት ምዕ. 8)።
ከርግቧ በፊት የጥፋት ውሃ ከምድር ላይ መጉደሉን ተመልክቶ እንዲመጣ ኖኅ ልኮት የነበረው ቁራን ነበር። “እንዳለመታደል” ሆኖ ግን ቁራ በታማኝነት የተላከበትን ጉዳይ ከውኖ ከመመለስ ይልቅ በዚያው የውሃ ሽታ ሆኖ እንደጠፋ ታሪኩ ይነግረናል። በቋንቋችንም “የቁራ መልእክተኛ” በማለት ብሂል የፈጠርነው ልክ እንደ ሠዓሊው ፒካሶ ይህንኑ ብሉያዊ ታሪክ መነሻ በማድረግ መሆኑን ልብ ይሏል።
የእኛይቱ የሰላም ርግብ፤
ላለፉት እጅግ በርካታ ዓመታት የሀገራችንን አየር እየቀዘፈች የኖረችው በአፏ የወይራ ቀንበጥ ይዛ በነፃነት የምትበር የሰላም ርግብ ሳትሆን አካሏ ቆሳስሎ ደሟን እያዘራች የምታቃስት ታማሚ ርግብ ነበረች። ይህቺ የሰላም ተምሳሊቷ ርግብ ታክማ እንድትፈወስ በኢትዮጵያ ምድር ብዙ የመድኃኒት ፍለጋና የሕክምና ጥበብ ሲፈለግና ሲሞከር መኖሩ አይካድም።
“ያልታደልሽ እንዴት አደርሽ!” እንዲሉ ሆኖብን “የባሩድ ጭስና የደም ጠረን” ከማሽተት ያልተፈወሰው የሀገራችን ፖለቲካ ለዘመናት ሲዘወር የኖረው “ግደል ተጋደል” በሚል ቅስቀሳ ስለነበር እንጉርጉሯችን ብቻም ሳይሆን ኑሯችንም ጭምር ተሸምኖ የተከናነብነው ለጠብና ለጭቅጭቅ እንጂ ለሰላም ዋጋ ለመስጠት ጉልበታችን የፀና አልነበረም። ችግሮችን በሰላም ተነጋግሮ ከመፍታት ይልቅ በፖለቲከኞች እኩይ ቅስቀሳ እየተሟሟቅን መፋለምን እንደ ባህል ደርበነው እንደነበርም አይዘነጋም።
ከቀናት በፊት በደቡብ አፍሪካዋ ፕሪቶሪያና በናይሮቢ ከተሞች የተደረሰበት ሀገራዊው ስምምነት “ሰላም ርግባችንን እያቆሰለ” ፋታ የነሳት የጦር መሣሪያ ልሳኑ ተዘግቶ ሕዝባችን ሰላማዊ አየር እንዲተነፍስ ግድ ስለሆነ ነው። እንጂማ ስለ በደልና ስለ ቁርሾ፣ ስለ መጠቃት፣ ስለሞትና ውድመት፣ ስለ ሥነ ልቦና ቀውስና ስለ መፈናቀል ወዘተ. እያላዘንንና እርስ በእርስ እየተፋለምን እንኑር ብንል አሳማኝና በቂ ማስረጃና መረጃ መች ይጠፋ ነበር።
የዓለማችንንም ሆነ የሀገራችንን የሰላም ርግብ እየተኮሱና እያስተኮሱ ለማቁሰልና ከተቻለም ለመግደል የሚሽቀዳደሙ “የፀብ አዳኞች” መልካቸውም ሆነ ባህርያቸው ብዙና የተዥጎረጎረ ነው። በፖለቲካ ሤራ ራሳቸውን ለብጠው የሚያስተዋውቁትና የሚፎክሩት “ለሕዝባችን ጥቅምና ክብር ስንል ነው” በማለት ጠብመንጃቸውን እየወለወሉ ግፋ በለው በማለት እንደሆነ አይጠፋንም።
እነዚህን መሰል ፀረ ሰላም ኃይሎችን ደፈር ብለን በመገፍተር የዘጉትን የትምክህትና የእብሪት ኬላ በመክፈት ሕዝቡ እርስ በእርስ እንዲገናኝና ችግሩን እንደ ባህሉ በንግግርና በውይይት እንዲፈታ ቢደረግ ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ለመገመት አይከብደም። ሕዝብ ከሕዝብ ጋር ጠብም ሆነ ቁርሾ የለውም፤ ኖሮትም አያውቅም።
የየትኛውም አካባቢ ሕዝብ ከሌላው የሀገሩ ወገን ጋር የተዋሃደበት ታሪክ “የፀብ ሱሰኞቹ” እንደሚያወሩትና እንደሚያስወሩት በፕሮፓጋንዳ ወጀብ የሚናወጥ አይደለም። ተጋምዶው የፀናው በደም ትስስር ማህተም ነው። ጋብቻና መዋለድ፣ ኢኮኖሚውና ማኅበራዊ ትሥሥሩ አቆራኝቶታል። ሃይማኖትና እምነት እንዳይናወጥ መልሕቅ ሆኖታል። አንደኛው ወገን ከሌላኛው ጋር በደስታና በሀዘን፣ በመከራና በመልካም ግንኙነት ተፋቅሮና የሕይወቱ ዘይቤ አድርጎ መኖር የጀመረው ትናንት ወይንም ከትናንት በስተያ ተብሎ በሚገለጽ የዓመታት ቀመር አይደለም። ዱሮ ድሮ እየተባለም እንደ ተረት የሚወራለት አይደለም። ርዝመቱ ከዘለዓለም በፊት እና እስከ ዘለዓለም እንደሚባለው ነው።
የቅደመ ታሪክም ሆነ የድህረ ታሪክ እውነታ ይኼው ነው። ባህሉም ሆነ ወጉ፣ ልማዱም ሆነ ዘይቤው ከዚህ እውነታ የሚያፈነግጥ አይደለም። “አንተ ትብስ አንተ”ን በሚገባ ተለማምዶት ኖሯል። ወደፊትም ኑሮው ከዚህ እውነታ እንዲንሸራተት ሆኖ አልተሰራም። “ያንተ ጥንተ አመጣጥ ከዚህ ነው፣ ያንተኛው ከዚያ፣ የእነርሱ ታሪክ እንደዚያ ነው፣ የእነኛዎቹም እንደዚያ” እያሉ የመለያየት አውሎ ነፋስ እየዘሩ መከፋፈል የሚፈጥሩት እነማን እንደሆኑ ከትናንት ይልቅ የዛሬዋ ጀንበር ምስክርነቷን በግላጭ እየሰጠች ነው።
የጠብ እሳት የሚያጋግሉ፣ ሲያሻቸው ፍሙን የሚያዳፍኑ፣ በሉ ሲላቸው ደግሞ ያዳፈኑትን የጠብ ረመጥ አመዱን በመገላለጥ በሕዝቦች መካከል የእሳት ሰደድ የሚያቀጣጥሉት ጥቅምና ሥልጣን፣ ጊዜያዊ ዳረጎትና እንጎቻ የሚወረወርላቸውና ተሰፍሮ እየተሰጣቸው በሚጎነጩት የጠብ ጉሽ የሰከሩ ተቅበዝባዦችና ጥቂት “ሆድ አደሮች” ናቸው። ለዚህ እውነታ ማረጋገጫነት ሩቅ ማሰብና የታሪክ ሰነዶችን በማገላበጥ መድከም አያስፈልግም። ወቅታዊውን ሁኔታ ልብ ተቀልብ ሆኖ ማየቱ ብቻ በቂና ከበቂ በላይ ነው።
በቅርቡ በተደረሰበት የሰላም ስምምነት ያሸነፈችው ኢትዮጵያ ነች። ያሸነፈችውም ያለ ምንም ልዩነት ለልጆቿ ሁሉ በእኩልነት በማሰብ ነው። ያሸነፈችው ይሄኛውን ወይንም ያኛውን ወገን ለመጥቀም ታሳቢ አድርጋ አይደለም። የአሸናፊነቷ መደላድል እውነትና እውነት ብቻ ነው። እርግጥ ነው ለሰላም ንግግሩ የተወከሉት “የባለ አደራ መልእክተኞች” ቁጥር ጥቂትና በጣት የሚቆጠር መሆኑ አይዘነጋም። ምናልባትም አምስት ወይንም ስድስት። የአሸናፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ግን በአሃዝ ይህን ያህል ተብሎ የሚቆጠር ሳይሆን “ሁሉም ዜጎች አሸንፈዋል!” ተብሎ የሚጨበጨብለት ነው።
ይህ ማለት ግን ከሕዝቡ መካከል ጥቂት ሰብዓዊ እንክርዳዶች ይጠፋሉ ማለት አይደለም። ይህ ሊሆን ግድ ነው። ከእነ ምሳሌውስ “ምንትስ ሁለት ወልዳ፤ አንዱ ለመጽሐፍ አንዱ ለወናፍ” ይባል የለ። እንኳን በሰው ልጆች መካከል ቀርቶ ምርጥ ዘር በዘራ የገበሬ ማሳ ውስጥም ቢሆን በሚያስጎመጀው አዝመራ መካከል ተመሳስለው የሚበቅሉ አረሞችና እንክርዳድ መኖሩ የተለመደና ተፈጥሯዊ ነው። የአረም ባህርይው ለምለም ሆኖ ከመታየት የዘለለ እዚህ ግባ የሚባል ጠቃሚ ፍሬ የለውም።
የደቡብ አፍሪካውንና የናይሮቢውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በተለያዩ የባዕድ ሀገራት የሚኖሩ “የጠብ ደቀመዛሙርት” ‹ምን ሲደረግ በኢትዮጵያ ምድር ሰላም ይሰፍናል› በማለት በየአውራ ጎዳናዎች፣ በየአደባባዮችና በየአውሮፕላን ማረፊያዎች ሳይቀር እየተጠራሩ የየሀገራቱን የሰላም አየር ሲበክሉ እየተስተዋለ ነው። “ይብላኝ ለቤትህ፤ መሳለቂያ አድርጎሃል ጎረቤትህ” እንዲሉ፤ እነዚህ ፀረ ሳለም ህሙማን “ከአሳዳሪዎቻቸው እየተቆነጠረ የሚሰጣቸው ዳረጎት የሚቀርባቸው መሆኑን ስለገባቸው መወራጨትን ስራዬ ብለው ተያይዘውታል። በእነርሱ ዘንድ “ምን ይሉኝ” ይሉኝታ ስለመፈጠሩም ያጠራጥራል።
ለእነዚህ ፀረ ሰላም ኃይሎች ሊነገራቸው የሚገባው አንድ ነገር ብቻ ነው። ነግ ተነገወዲያ ፖለቲካው የፈጠረው ኬላ ወለል ተደርጎ ሲከፈት ሕዝቡ ከየአካባቢው ፈንቅሎ እየወጣ ያለማንም ጎትጓች እየተቃቀፈ ሲላቀስና ሲተቃቀፍ፣ ይቅርታና ምህረት ሲቀባበል በዐይናቸው በብረቱ ያዩታል። ፖለቲከኞች የሰባበሩት የእርስ በእርስ ማሕበራዊ የመገናኛ ድልድይ ይጠገንና ምን ተዓምር እንደሚፈጥር በጠራራ ፀሐይ ይመለከቱታል። የሞቀ እየበሉ፣ የቀዘቀዘ እየተጎነጩ የሚያገሱትና የሚያቀረሹት የመንፈስና የሞራል መጻጉዕ የዲያስፖራዎቹ እነ እንቶኔ እውነቱን በግላጭ ሲያዩ ምን እንደሚሉ እንሰማለን፤ እናያለንም። ሰላም ይሁን።
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ህዳር 7/2015