ዳግም ከበደ
ምድራችን እጅግ የገዘፈች ከመሆኗ ባሻገር የብዝሃነት ጎተራ የተፈጥሮ ስብጥር ቋት ነች። በዚህች ምድር ላይ የሰው ልጆች ልክ እንደ ሌሎች የተፈጥሮ ኡደቶች ሁሉ የራሳቸው ባህል፣ የአኗኗር ዘይቤ የሚከተሉ የተለያየ ውብ ማንነት ያላቸው ናቸው።
ታዲያ በዚህ ምክንያት ቀን መሽቶ በነጋ ቁጥር ከአንዱ አጥናፍ ወደ ሌላኛው አጥናፍ አዳዲስ ጉዳይ፣ ያልተሰሙ ዜናዎች፣ የማይታወቁ ባህሎች፣ እፁብ ድንቅ የሚያሰኙ አዳዲስ ጉዳዮች ይደመጣሉ። ለዛሬ የዝግጅት ክፍላችን በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተሰሙ ግን ደግሞ ለሚሰማው ጆሯችንና ለሚመዝነው አእምሯችን እንግዳ የሆኑ ጉዳዮችን ወደናንተ ልናደርስ ወደድን። መልካም ቆይታ !
ጃፓን
ጃፓኖች በዓለማችን ላይ ካሉ አገራት ውስጥ ለባህል፣ ሥነ ሥርዓትና ለተፈጥሮ ያላቸው ትኩረት ጥብቅ እንደሆነ ይነገራል። በተለይ ማህበራዊ ስርዓትን የማክበርና በፍፁም የኃላፊነት ስሜት የመፈፀም ባህላቸው ከሌሎች አገራት አንፃር ሲታይ በእጅጉ የተሻለ መሆኑን ጥናቶችና መረጃዎች ይጠቁማሉ። ተፈጥሮን የመጠበቅና ሃይማኖታዊ ስርዓትን በጥብቅ ስነ ምግባር የመተግበር ኃላፊነትም እንደዚያው።
ለዛሬ በጃፓኖች ዘንድ የሚተገበር አንድ ሃይማኖታዊ ፌስቲቫል ምን እንደሚመስል ላጋራችሁ። ነገሩ ትንሽ ወጣ ያለ በመሆኑ በቤትዎ እንዳይሞክሩት ስንል ከወዲሁ እናስጠነቅቃለን። ነገሩ እንዲህ ነው የቡዲዝም እምነት ተከታይ የሆኑ ጃፓኖች በየዓመቱ ሃይማኖታዊ ስርዓትን ለመፈፀምና የመንፃት ስነስርዓት ለማድረግ በባዶ እግራቸው በጋለና በእሳት በተቀጣጠለ ረጅም የከሰል መንገድ ላይ ይሄዳሉ። ይሄ ስርዓት ሃይማኖታዊ ሲሆን በርከት ያሉ ጠቀሜታዎች እንዳሉት በመነኩሴዎችና በተከታዮቹ ዘንድ ይታመናል።
የእምነቱ ተከታዮች በተፈጥሯዊ ውበቱ በእጅጉ ተወዳጅ በሆነው በጃፓን ቶኪዮ በታኮሳን ተራራ ላይ በየዓመቱ በእሳት በተያያዘ ከሰል ላይ የመሄድ ስርዓትን ይፈፅማሉ። ባሳለፍነው ዓመት የኮሮና ወረርሽኝ በመኖሩ ምክንያት ለተሳታፊዎች ዝግ ሆኖ የነበረ ቢሆንም ዘንድሮ ግን አንድ ሺ ሰዎችን ብቻ አካትቶ ስርዓቱ ተፈፅሟል። ለመሆኑ ይህ ሃይማኖታዊ ክንውን ለምን ይፈፀማል?
ኮሾው ካሚሙራ የቡዲዝም ሃይማኖት መነኩሴ ናቸው። በእሳት ላይ በባዶ እግር የሚደረግ ስነስርዓት የሚፈፀመው እሳት ነብስን ሆነ ህሊናን ስለሚያነፃ እንደሆነ ይናገራሉ። ይህ ብቻ ሳይሆን ምእመናኑ ለአምላካቸው ቡድሃ የሚያደርጉት ፀሎት እንዲደርስ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።
አንድ አማኝ ልመናውና ፍላጎቱ ቡድሃ ዘንድ እንዲደርስ በዓመት አንድ ጊዜ በተራራው ላይ በሚደረገው ስነስርዓት ተካፍሎ ፍሙ በሚንቀለቀል በእሳት በተያያዘ ከሰል ላይ በባዶ እግሩ መሄድ እንዳለበት ይገልፃሉ። ታዲያ ያን ጊዜ ፍላጎቱና ፀሎቱ ከዓምላኩ ዘንድ ይደርሳል በሚል ይታመናል።
እኛ ግን ይህን ያበጡ እለት ሞት አይገኝም ነው የምንለው ፤ ምንም ይሁን ምን እሳትን በሩቁ እንላለን፡፡ በተለይ በእሳት መጫወት አይመከርምም ፤አይሞከርምም፡፡ ከእሳት ጋር መጫወት አደጋ እንደሚያስከትል ስለምናውቅም የማንትስን ጠባሳ ያየ በእሳት አይጫወትም እንላለን፡፡
ጀርመን
ስልጣኔ የሰውን ልጅ ግላዊ እያደረገው እንደሆነ በየጊዜው ወቀሳ ይቀርብበታል። በተለይ ከስልጣኔ ጋር ቀጥተኛ ተያያዥነት ያላቸው ቴክኖሎጂዎች ለማህበራዊ ግንኙነት መቃወስና ለግላዊነት መስፋፋት እንደ ዋንኛ ምክንያት ይቀመጣል።
“በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ አበው፤ ባሳለፍነውና በያዝነው የፈረንጆች ዓመት በዚህ ላይ የኮሮና ወረርሽኝ ተከስቶ እንዲሁም የተራራቀውን የዓለማችን ህዝብ ይበልጥ እንዲለያይና እንዲፈራራ አድርጎታል።
ታዲያ ይሄ ክስተት በሰው ልጆች ስነ ልቦና ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረም ይገኛል። በተለይ ብቸኝነት የሚሰማቸውና ለጥልቅ ድብርት የሚጋለጡ ሰዎች እየበዙ ነው። ይህን ስሜት ለመላቀቅ ታዲያ እራሳቸውን ለበሽታው አጋልጠው ማህበራዊ መቀራረብን የሚፈጥሩ ሰዎች ቀላል የሚባሉ አይደሉም።
ከወደ ሃቲገን ምእራብ ጀርመን ከሰሞኑ አንድ መልካም ወሬ ተሰምቷል። አንድ በግብርና ሥራ ላይ የተሰማራው ካምፓኒ ብቸኝነት የተሰማቸውና ከተፈጥሮ ጋር መቀራረብ ለናፈቃቸው ሰዎች አስደናቂ መላ ይፋ አድርጓል። “ነገርዬው ምን ይሆን” ላላችሁ ጉዳዩ ወዲህ ነው። ወደ ካምፓኒው ሜዳማ የእንስሳት ማርቢያ ስፍራ መጥተው ለዚሁ አላማ ከተዘጋጁ በጎች ጋር እንዲተቃቀፉና ብቸኝነቱን እንዲረሱ ነው ያመቻቸሎት።
በቅድሚያ ግን ሰው፣ ተፈጥሮና ማህበራዊ ግንኙነት እንደናፈቀዎትና ከበጎቹ ጋር ረዘም ላሉ ደቂቃዎች ለመተቃቀፍ ፍላጎት እንዳሎት ማሳወቅ ይኖርቦታል። ወረፋ ከያዙ በኋላ ያለምንም ክፍያ ያሻዎትን በጎች መርጠው ከስጋት ነፃ በሆነ መልኩ መተቃቀፍና ማህበራዊ ግንኙነቶን ማዳበር ይችላሉ።
ይህን ሲያደርጉ በአገልግሎቱ እርካታ ከተሰማዎት የግብርና ማእከሉን መደገፍ ይችላሉ እንጂ በጎቹ ጋር ተቃቅፈው ለምን መልካም ግንኙነት ፈጠሩ ተብሎ ክፍያ እንዲፈፅሙ አይገደዱም። እንዲያውም በተቃራኒው በጎቹን እንዲያቅፉና የተጠናወቶትን የብቸኝነት ስሜትና ድብርት እስከወዲያኛው እንዲሸኙ ይበረታታሉ እንጂ።
ታይላንድ
ይሄኛው አስገራሚ ትእይንት ደግሞ ወደ ታይላንድ ይዞን ይሄዳል። መቼም የኮሮና ወረርሽኝ ይዞት ያልመጣው መቅሰፍት ያልረበሸው የዓለም ክፍልና ዘርፍ የለም። ምድራችን በዚህ ቀውስ ውስጥ ዘርፈ ብዙ ችግር ውስጥ ወድቃለች። አገራት ኢኮኖሚያቸው ደቋል። ማህበራዊና፣ ፖለቲካዊ ትስስሮች ላሽቀዋል። በዋናነት ግን በቱሪዝም ዘርፍ ላይ ብርቱ ክርኑን አሳርፏል። በዚህም ጎብኚዎች ተወዳጅና ሊጎበኙ የሚችሉ ስፍራዎችን ደፍረው እንዳይጓዙባቸው የጣለው ተፅእኖ እጅጉን የበዛ ነው።
በዚህ ተፅእኖ ውስጥ እያለፉ ካሉ አገራት መካከል በቱሪስት መዳረሻነት የምትታወቀው ታይላንድ ትገኝበታለች። በወረርሽኙ ምክንያት ቱሪስቶች በአገሪቱ ካለመገኘታቸውም በላይ በዚህ ሥራ ውስጥ ተሰማርተው የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ተጎጂ ሆነዋል። ይህን ችግር ለመቅረፍ ታዲያ በቅርቡ አንድ መላ የዘየዱ ይመስላሉ።
ታይላንዳውያን ጎብኚዎች በቅርቡ እንዲመለሱ ትልቅ እገዛ ያደርግልናል ያሉትን የዝሆኖች ፌስቲቫል አካሂደዋል። በአገሬው ህዝብ ትልቅ ክብርና ጠቀሜታ ያለው ዝሆን ልዩ ቀኑ ሆኖ እንዲከበር ተወስኗል። ቱሪስቶች ፊታቸውን ወደ ታይላንድ እንዲያዞሩ ያደርጋል የሚል ተስፋም አሳድሯል። ታዲያ ዝሆኖቹ ከምንጊዜውም በተለየ መልኩ እረፍት አግኝተው ጣፋጭ አትክልቶችን ሲመገቡና ሲዝናኑ በፌስቲቫሉ ላይ ታይተዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 15/2013