ብስለት
መጋቢት ወር 2012 ዓ.ም የመጀመሪያው የድንጋጤ ዜና የተነገረበት፤ ጥፍሩን ያሾለው፤ አይኑን ያፈጠጠው ጥርሱን ያገጠጠው ኮሮና መጣሁባችሁ ያለበት ወቅት ነበር። ያኔ አስፈሪ ጭራቅ እንዳዬ ህፃን ሁላችንም በየጓዳችን ተወሸቀን፤ ያልለመደብንን የፅዳት አርበኞች ነን ብለን የፅዳት እቃ ጦራችንን ታጠቅን፤ አዲስ አበባ ቆሻሻይቱን ከተማ የፅዳት አምባሳደር አድርገናትም ነበር። መገናኛ ብዙሀን ላይ የምናያቸው ሰዎች በሙሉ በፍርሀት ስለጭራቁ ሲናገሩ ይውሉ ነበር።
ታይቶና ተሰምቶ በማያውቅ ሁኔታ የሃይማኖት አባቶች በቴሌቪዥን መስኮቶቻችን እግዚኦ በማለት ሲያነቡ ተመለከትን። ቀድመን ከልክ በላይ ፈራነውና የፈራነውን ያህል ጉዳት አላደርስ ሲለን የት አባቱ ሊደርስ ነው በሚል ድፍረት ልባችን አበጠ። ወጣትነት ከበሽታ የሚያስጥል መድሃኒት የሆነ እስኪመስለን ድረስ ወጣቶቻችን የአፍ መሸፈኛውን ጭንብል ጣሉ። በየሰፈሩ ድግሱ ሰርጉ ማህበሩ ተጧጡፎ ቀጠለ።
ትልልቅ ጉባኤዎችና ዝግጅቶች በርካታ ህዝብ በተሰበሰበበት መከናወን ጀመሩ። ከሁሉም የሚገርመው ደግሞ በርካታ ህዝቦች ሊሰተናገዱበት የተዘጋጁት መርሃ ግብሮች ላይ ፍተሻው መጠናከሩ ነው። ኮቪድ- 19 በንክኪ ይተላለፋል እየተባለ ከእግር እስከ ራስ ድረስ አንዱ በተዳሰሰበት እጅ ሌላው የሚፈተሽበት ሁኔታዎችን መመልከት ጀመርን።
ትራንስፖርቶች ከልክ በላይ ሰው እየጫኑና እያጨቁ ባሉበት በአሁን ወቅት እንኳን ኮሮና ጉንፋን ያለም አይመስልⵆ በጣም ከመዳፈራችን የተነሳ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል የምናደርገው እንኳን በአስታዋሽ ሆኗል። በየመጠጥ ቤቱ߹ ሆቴልና የመዝናኛ ስፍራ እንዲሁም ድግስና ተስካሩ ሌላውም ሌላውም ላይ መገፋፋቱ ትርምሱ በረከተ። መዝናኛ ቦታዎችና ምግብ ቤቶች ከአፍ እስከ ገደፋቸው ጢም ብለው መሙላት ጀመሩ። የሞት ዜና ከየጉዳጉዱ እየወጣ በየቀኑ አስክሬን ለመሸኘት የቀብር ቦታዎች በሰዎች ሲሞሉ መመልከት የተለመደ ሆነ።
ለአገልገሎት ባንክ ቤት እንኳን ሲኬድ ያንንም ያንም ታጠቡ በሚሉበት አፋቸው ልፈትሻችሁ እያሉ ከዚኛው ወደ ዚያኛው ኮሮናን ማደል ልማድ ሆነ። አይተንና ሰምተን በማናቀው መልኩ ከስድስት መቶ በላይ የፅኑ ህሙማንን ቁጥር አስመዘገብን። በአንድ ቀንም 2057 ሰው በቫይረሱ የተያዘበት ሁኔታ አየን ከዛም በኋለ ባሉ ቀናትም ቢሆን 1ሺ 537 እና 1ሺ724 እያለ ነው ቁጥሩ እየሄደ ያለው ይህ ማለት ደግሞ ባለፈው አንድ ዓመት ከነበረው በቫይረሱ የመያዝ ምጣኔም እጅግ በጣም ከፍ ያለበት አስከፊ መከራ ከፊታቸን የተጋረጠበት ጊዜ ላይ መድረሳችንን ያመላክታል።
ሞት ጓደኞቻችንን፤ ዘመዶቻችንን፤ የቅርብ ሰዎቻችንን እያሳጣን ባለበት በዚህ ጊዜ ለምን ይሆን ስለጥንቃቄ እየተነገረን ጆሮ ዳባ ልበስ ያልነው? ብልጥ በሰው ሞኝ በራሱ ይማራል ይሉት ብሂል እንዳይደርስብን ሌሎች ሀገራት የከፈሉትን ያህል መስዋአትነት እንዳንከፍል ለማድረግ ለምን ይሆን የተሰላቸነው?
እኛ ላይ አልደረሰም ያልነው በሽታ ቤታችንን እያንኳኳ ባለበት በዚህ ወቅት ለምንድነው መደንገጥ የቃተን? ለምን አልፈራንም? ለምን ዜናውን እንደሰማን መግቢያ ቀደዳ ያሳጣን ሽብር በቀን ከሰላሳ ሰው በላይ እየሞተ እንደሆነ ሲነገረን ድንጋጤ ሽው ሊልብን ያልቻለው? ለምን ማለቅ መጥፋት ምርጫችን ሆነ? የጤና ባለሙያዎች የሚናገሩት ኮቪድ-19 በተለያዩ ሰዎች ላይ የሚስከትለው ውጤት የተለያየ ሊሆን ይችላል።
አብዛኞቹ በቫይረሱ የሚጠቁ ሰዎች ከዝቅተኛ እስከ መካከለኛ ህመም የሚገጥማቸው ሲሆን ወደ ሆስፒታል መግባት ሳይጠበቅባቸው ይድናሉ። የተቀሩት ደግሞ በከባድ ህመም የሚሰቃዩ ብሎም ህይወታቸውን የሚያጡ መሆናቸውን ነው። ከመሞት መሰንበት ምርጫችን ማድረግ ለምን ይሆን ያቃተን?
ሀገራችን በተራ በተራ እየተደራረበ ጫንቃዋን ያጎበጣት ችግርና መከራን ተሸክማ ባለችበት በዚህ ወቅት ለምን ይሆን በሀዘን እሳት እንድትለበለብ የፈረድንባት? ለምን ወገን መሞትን እጁን ዘርግቶ በፀጋ ለመቀበል ደፈረ?
ለምንድነው የጤና ተቋማት እንደሚሉት በሽታውን ለመከላከል እጅን በመደበኛነት በደንብ መታጠብ እጅግ ጠቃሚ መሆኑን ካወቅን በቀን መቶ ጊዜ መታጠብ ያቃተን? እስካሁን በሽታው እንዴት እንደሚተላለፍ በእርግጠኝነት የሚናገረ አንድም ጠቢብ የለም። ነገር ግን የኮሮና አይነት ቫይረሶች በበሽታው የተያዙ ሰዎች በሚያስሉበትና በሚያስነጥሱበት ወቅት በሚያወጧቸው ጥቃቅን ጠብታዎች አማካይነት ነው የሚባል መረጃ ብቻ እንሰማለን።
እነዚህን ጥቃቅን ጠብታዎች ወደ ሰው እንዳሄዱም ወደእኛ እንዳይመጡም መከልከል ስለምን ተሳነን? ስናስልና ስናስነጥስ አፍንጫና አፋችንን በሶፍት ወይም በክርናችን ለምን አንሸፍንም?፤ ፊታችንን እጃችንን ሳንታጠብ ከመነካካት ልማድ ለምን አንቆጠብም? የመሰባሰብ ልማዳችንን ቀኑ ደርሶ ከበሽታው ነፃ እስክንሆን ድረስ ለምን በትእግስት አናዘገየውም? ከሞት የማይሻል ነገር ይኖር ይሆን? ሞትስ በአንድ ፊቱ ግልግል ነው በሽታው የያዛቸው ሰዎች እንደሚሉት የህመም ስቃይ የስቃይ ዳርቻ መሆኑን ተረድተን ለምን ለጥቂት ጊዜ ማምለጫ ነው የተባልነውን ጥንቃቄ በሙሉ አናደርግም?
የህክምና ባለሙያዎች እንደሚሉት የፊት መሸፈኛ ጭንብሎች ብቻቸውን የሚፈለገውን ያህል በሽታውን ለመከላከል አያስችሉም። ሁሉንም የጥንቃቄ መንገዶቸ ባለመሰላቸት መከናወን ይኖርብናል። መኖር ሊያውም ያለሰቃይ መኖር በነፃ የተሰጠን የተፈጥሮ ፀጋ ነው። ይህን የተፈጥሮ ፀጋችንን ሊነጥቁን የተነሱ ገጠመኞች ሲከሰቱ ደግሞ በመረጋጋት መፍትሄውን ማጤን ይኖርብናል።
የዓለም ጤና ድርጅት ከ56 ህሙማን ላይ በሰበሰበው መረጃ መሰረት በኮሮና ቫይረስ ከተያዙ አምስት ሰዎች መካከል አራቱ ቀለል ያሉ የበሽታውን ምልክቶች ብቻ ያሳያሉ። በዚህም መሰረት 80 በመቶው ቀለል ያሉ ምልክቶችን የሚያሳዩ ሲሆን 14 በመቶው ከባድ ምልክቶችን 6 በመቶዎቹ ደግሞ ክፉኛ ይታመማሉ በዚህም እስከሞት ይደርሳሉ። ከነዚህ ከባድ ህመምን ከሚያሰተናግዱት መካከል ላለመሆናችን ምን ዋስትና ይኖረናል?
ሀብታም የተማረ የሀገር ሽማገሌ ትልቅ ለምድር ለሰማይ የከበዱ አባቶች ገና የህይወትን ዳገት መውጣት ያልጀመሩት አፍላ ወጣቶች ምኑ ከምኑ ይጠቀሳሉ ሁሉም በያለበት ከባድ ስቃይን እያሰተናገደ ብሎም የሞት ፅዋን እየጨለጠ ባለበት በአሁን ወቅት መዘናጋት አይገባም።
ሰው ያለ ጉዳይ ከቤቱ አይውጣ እግሩን ይሰብስብ፤ እስከቻለው ድረስ እጁን ይታጠብ አፉንና አፍንጫውን ይሸፍን፤ መኖር ብቻ ሳይሆን ለመኖራችን ዋና ማገር የሆነው ማህበረሰብ በጋራ በተቀናጀ ክንድ ተጋገዘን የዘመናችን ጠላት የሆነው ኮሮና ቫይረስ ላይ እንደ ጀግኖች አባቶቻችን ድል ይነሳ።
የዛሬ አንድ ዓመት የዚህ አስፈሪ ነጣቂ ጭራቅ ወሬ በተሰማበት ወቅት የታጠቅነውን ትጥቅ ስንላመድ የጣልነውን የፅዳት እቃ እናንሳ፤ ዳግም በኮሮና ማለቅ በኮሮና መሞት ይብቃ እንበልና ስለደህንነት አስበን በጋራ ለመትረፍ እንረባረብ፤ ሁሌም አዲስ ቀን ያጓጓልና የምታጓጓው የህይወት ፀሃይ እንዳትጠለቅብን ልብ ያለው ልብ ይበል ብዬ አበቃሁ።
በጤና ያሰንብተን።
አዲስ ዘመን መጋቢት 15/2013