ይበል ካሳ
አሁናዊ ሁኔታ
‹‹ ገንዘብ ገንዘብ የሚሆነው በባንክ ሲቀመጥ ሳይሆን ሲሰራበትና ሲገላበጥ ነው›› የሚሉት ወይዘሮ አለምነሽ ይልማ ለዓመታት እቁብ አሰባስበውና አጠራቅመው የያዙትን ገንዘብ አሮጌ ቤታቸውን አፍርሰው መስራትና ተጨማሪ ገቢ የሚያመጣ ክፍል አስፋፍተው ለመስራት የዘንድሮው እቅዳቸው ነበር። በእቅዳቸው መሰረትም የነበራቸውን ሶስት ክፍል ቤት አፍርሰውና በስድስት ክፍል አስፋፍተው ለማሰራት ስራ የጀመሩት ህዳር ወር ላይ መሆኑን ይናገራሉ። በህዳር ወር በ500 ብር ሲሚንቶ ገዝተው የጀመሩት የቤት ግንባታ ዛሬም ሳይጠናቀቅ የሲሚንቶ ዋጋ እስከ 750 ብር ለመግዛት አስገድዷቸዋል። ‹‹ ህዳር ላይ ሃያ ኩንታል ይበቃል ብዬ በ500 ብር ኩንታሉን ገዛሁ። ከዛ በኋላ ግን የሲሚንቶ ዋጋ በየጊዜው እየጨመረ ሄዶ እኔም የገዛሁት ሲሚንቶ ስላልበቃ በ560 ብር ከዛም በ610 ብር እያልኩ አሁን ለማጠናቀቂያ ስራ በ750 ብር ለመግዛት ተገድጇለሁ›› ሲሉ የሲሚንቶ ዋጋ መወደድና የምርት እጥረት መኖሩን በምሬት ይገልጻሉ።
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው የሲሚንቶና የግንባታ ብረት እጥረት በኮንስትራክሽን ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ መምጣቱ በተደጋጋሚ ሲጠቀስ ቆይቷል፡፡ አሁን ላይ ችግሩ እየተባባሰ መጥቶ በተለይም የሲሚንቶና የብረት እጥረት ከአቅም በላይ በመድረሱ በግንባታ ሥራዎች የተሰማሩ ሥራ ተቋራጮች ሰራተኞቻቸውን የመበተን ስጋት ውስጥ መግባታቸውን እያሳወቁ ናቸው። የኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማህበር መጋቢት 9 ቀን 2013 ዓ.ም በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ትኩረት ሰጥቶ ያስታወቀው ይሄንኑ ስጋቱን ነው፡፡
የማህበሩ ቦርድ ምክትል ሊቀመንበር ኢንጂነር የሱፍ መሐመድ እንደገለጹት፤ እየተባባሰ በመጣው የግንባታ አቅርቦት እጥረት የተነሳ ዘርፉ ችግር ላይ ወድቋል፡፡ በተለይም ለግንባታ ወሳኝ የሆኑ የሲሚንቶና ብረት አቅርቦት እጥረት እና የዋጋ ንረት ጎልቶ የሚታይ ችግር ሆኗል፡፡ ይሄም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባበሰ በመምጣቱ በዘርፉ ላይ የተሰማሩ ስራ ተቋራጮች ስራቸውን በአግባቡ ለመከወንና ለሰራተኞቻቸው ደመወዝ ለመክፈል እየተፈተኑ ናቸው። “በግብዓቶቹ እጥረት ሳቢያም ፕሮጀክቶችን ለማቋረጥ እየተገደድን ነው” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ እናም በዘርፉ የተሰማራው የሰው ኃይል እንዳይበተን መፍትሄ እንዲፈለግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባንኮች ለተቋራጮች ቅድሚያ ክፍያ እንዳይፈጽሙ የጣለው እገዳ አሉታዊ ጫና ማሳደሩንም ማህበሩ ገልጿል፡፡ “ተቋራጮች ውሉ ላይ በ290 ብር ሲሚንቶ ቢሞላም፤ እስከ 700 ብር ሲሚንቶ ገዝቶ ሥራው እንዳይቋረጥ እየሰራ ነው፡፡ ከዚህ በላይ ምን ማድረግ ነበረበት” ሲሉም በዘርፉ የተፈጠረውን ችግር በምሬት ይናገራሉ፡፡
የኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማህበር ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ግርማ ኃብተማሪያም በበኩላቸው “ዘርፉ ከገጠመው የግብዓቶች እጥረት ሌላ ከባንኮች የሚወጣው ገንዘብ ላይ የተጣለው ገደብ ችግር ላይ ጥሎናል” ብለዋል፡፡ ችግሩን ለማቃለል ሥራ ተቋራጮችና ግብዓት አምራቾች በቀጥታ የሚገናኙበት ሁኔታ እንዲመቻችም የማህበሩ ፕሬዚዳንት ጠይቀዋል፡፡
የግማሽ ምዕተ ዓመቱ ኢንዱስትሪ
የሃገሪቱ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪግ ኢንዱስትሪ ግማሽ ምዕት ዓመት ያስቆጠረ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ ዳሩ ግን ለበርካታ ዓመታት ለዘርፉ ትኩረት ሳይሰጠው ቆይቷል፡፡ በመሆኑም በዘርፉ የነበረው የልማት እንቅስቃሴ ደካማ የሚባልና ግማሽ ምዕተ ዓመታትን ቢያስቆጥርም ማደግ በሚገባው ደረጃ ያላደገና አሁንም ድረስ በጨቅላነት ደረጃ ላይ የሚገኝ ዘርፍ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ሀገሪቱም ከዘርፉ ልታገኝ የሚገባውን የኢኮኖሚና የቴክኖሎጂ
ልማት ሳታገኝ ቆይታለች፡፡ ሀገሪቱ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ለምታደርገው የትራንስፎርሜሽን ጉዞ የመጀመሪያውን አምስት ዓመታት ለሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን መደላድል ፈጥሮ አልፈዋል፡፡ በመሆኑም በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ኢንዱስትሪው መሪነቱን እየተረከበ እንዲሄድ ለማኑፋክቸሪግ ዘርፉ ትኩረት መሰጠቱ ይታወቃል፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተለይም ከሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን በኋላ ትኩረት ከተሰጣቸው የማኑፋክቸሪግ ዘርፍ አንዱ ደግሞ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪግ ንዑስ ዘርፍ ነው እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ለዚህም እንደ አንድ ምክንያት የሚጠቀሰው የኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂው የግል ባለሀብቱ የኢንዱስትሪው ሞተር መሆኑን በማመኑና ማንኛውም ባለሀብት በዘርፉ ለመሰማራት ቢፈልግ በሩን ክፍት በማድረጉ ነው፡፡
የብረታ ብረትና ኢንጂነሪግ ንዑስ ዘርፍ መሠረታዊ ብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ በመባል በሁለት የሚከፈል መሆኑን ከብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የተገኙ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ የመሠረታዊ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ የብረት ማዕድናትን፣ የውድቅዳቂ ብረቶችና የጠገራ ብረቶችን በመጠቀም ለኢንጂነሪንግ ንዑስ ዘርፍ ግብዓት የሚሆኑ የኢንዱስትሪ ውጤቶችን የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎችን የሚያካትት ሲሆን በኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ንዑስ ዘርፉ የሚካተቱት ደግሞ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ውጤቶችን በግብዓትነት በመጠቀም የተለያዩ የኢንጂነሪንግ ምርቶችን የሚፈበርኩ ናቸው፡፡
በሌላ አገላለጽ መሠረታዊ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪዎች ከብረት ማጣራት ጀምሮ የተለያዩ መጠን ያላቸውን የመጀመሪያ ደረጃ ምርቶችንና እነዚህን ምርቶች በግብአትነት በመጠቀም ዝርግና ጥቅል ልሙጥ ብረቶችን፣ የተለያዩ ቅርፅ ያላቸው ድፍንና ክፍት ረጃጅም የብረት ምርቶችን፣ ሽቦዎችን፣ የሽቦ ገመዶችን፣ ቆርቆሮዎችንና ምስማሮችን የማቅለጥ፣ የማሞቅና የመዳመጥ ቴክኖሎጂ በመጠቀም የሚያመርቱ ሲሆን ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪዎች የሚባሉት ደግሞ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ውጤትን በግብአትነት በመጠቀም የተለያዩ ቅርፅ ማውጫ ቴክኖሎጂዎችን በማቅለጥ ቅርፅ ማውጣት፣ በብየዳ፣ በመቀጥቀጥ መሳሪያዎችንና የተለያዩ መገልገያ ዕቃዎችን የሚያመርቱ ናቸው፡፡
የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ዘርፍ ለሌሎች የማኑፋክቸሪግ ዘርፎች በግብዓትነት በማገልገል ለኢንዱስትሪ መስፋፋት ከፍተኛ ሚና የሚጫወት ሲሆን ለሀገሪቱ የምጣኔ ሀብት ዕድገትም የላቀ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ዘርፍ ነው፡፡ ለዚህም ካለው ሀገራዊ ፋይዳ አኳያ ንዑስ ዘርፉን የሚደግፍ መንግሥታዊ ተቋም መቋቋም ነበረበትና የብረታብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ተቋቋሞ ወደ ሥራ ከገባ ሰነባብቷል፡፡
ሀገሪቱ በ2017 መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለመሠለፍ ከድህነት ጋር ከፍተኛ የሆነ ትግል እያደረገች ባለበት በዚህ ዘመን ከሁሉም ዘርፍ እምርታዊ ለውጥ እንደሚጠበቅ ይታመናል፡፡ ይህን መሠረት በማድረግም የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በ2017 በአፍሪካ ቀዳሚና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ ቀላል የብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ በመገንባት፣ ለከባድ ኢንዱስትሪዎች ልማት መሰረት ተጥሎ ማየት የሚል ራዕይ ሰንቆ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ ራዕዩን ዕውን ለማድረግ ታዲያ የብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ አቅምን ለማሳደግ የሚያስችል ምርምርና ጥናትን መሠረት ያደረገ የተቀናጀ የኢንቨስትመንት፣ የግብይትና ማኑፋክቸሪንግ ቴክኖሎጂ ድጋፍ ለልማታዊ ባለሀብቱ በመስጠት ተወዳዳሪ ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡
ለዚህም መንግሥት በብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍ ለተሰማሩ ኩባንያዎች ተመጣጣኝ የማበረታቻ ሥርዓቶችን ተግባራዊ በማድረግ ኢንቨስትመንቱ እንዲስፋፋም ጥረቱ ማድረጉን ጉዳዩን በበላይነት የሚመራው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት መረጃ ያመላክታል፡፡ በዚህ ረገድ በሁሉም ዘርፎች ማለትም በአርማታ፣ በስቲልና ፕሮፋይል፣በማሽነሪና ኢኩዩፕመንት፣ በአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ፣ በአሉሙኒየም ፕሮፋይል፣ በኤሌክትሮኒክስና ኤሌክትሪካል ኢንቨስትመንት ተሰማርተው የሚገኙ ኩባንያዎች ከ400 በላይ ሲሆኑ፣ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች 85 በመቶውን ሲሸፍኑ ቀሪው 15 በመቶ ደግሞ በውጭ ኩባንያዎችና በሽርክና የተያዙ ናቸው፡፡ በዚህም ለዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶ በተደረጉ ሥራዎች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ያለቀላቸው ጥሬ ዕቃዎችን በማስገባትና እሴት በመጨመር የግንባታ ዕቃዎች ለማምረት የተቋቋሙ ኢንዱስትሪዎች ዕድገት ማሳያታቸውን ኢንስቲትዩቱ ይገልጻል፡፡
የብረት ማዕድናትን በማልማት ለአገር ውስጥ ምርት መጠቀም ቁመና ላይ ያልተደረሰ ቢሆንም ያለውን ውስን የውድቅዳቂ ብረታ ብረቶችን ተጠቅሞ የአርማታ ብረት፣ የአሉሚኒየም፣ የኮፐር፣ የኤሌክትሪክና የቴሌኮም ኬብሎችን የሚያመርቱና የአገሪቱን ፍላጎት ማሟላት የሚችሉ ኢንዱስትሪዎች በመፈጠራቸው በግብአት ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን መቀረፋቸውን በ2009 ዓ.ም የወጣው መረጃ ያመላክታል፡፡
ለዘርፉ የህልውና ፈተና
ባለፉት ዓመታት በሀገሪቱ በነበረው የሰላም መደፍረስና ከዛም በቀጥሎ በመጣው ሀገራዊ ለውጥ ጋር ተያይዞ በሃገሪቱ ውስጥ በነበረው የኢኮኖሚ አለመረጋገትና የኢኮኖሚ ሻጥር ምክንያት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ተፈጥሯል። ከነጋዴዎችና ከደላሎች ጋር ተያይዞም የብረትና የሲሚንቶ እጥረት እና የዋጋ ንረት ተከስቷል። ለኮንስትራክሽን የሚያስፈልጉት ግብዓቶች በአብዛኛው ከውጭ የሚገቡና በውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ላይ የተመሰረቱ በመሆናቸው ጥሩ መነቃቃት ውስጥ የነበረው የግንባታ ዘርፍም ችግር ውስጥ ገብቷል፡፡ በተለይም ለዘርፉ በዋና ግብዓትነት የሚያገለግሉት ብረታ ብረትና ሲሚንቶ ምርቶች ላይ ከፍተኛ የአቅርቦት እጥረት በመፈጠሩ ለዘርፉ ትልቅ ፈተና ሆኖበት ይገኛል፡፡
የመፍትሔ እርምጃዎች
ችግሩን በተመለከተ የሲሚንቶ አከፋፋዮችና ቸርቻሪዎች የንግድ ሕጉ በሚፈቅደው አግባብ ሀገርንና ህዝብን የማገልገል ግዴታቸውን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የማይወጡ ከሆነ የህብረተሰቡን የኑሮ ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል መንግስት አዋጭ ያለውን እና የዘርፉን ችግር ሊፈታ የሚችል ውሳኔ የሚወስን መሆኑን የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መግለጹን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል፡፡ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማህበር መግለጫ ከማውጣቱ አስቀድሞ እንደዘገበው ሚኒስቴሩ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት፣ ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከክልልና ከተማ አስተዳደር ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊዎች፣ ከሲሚንቶ አምራቾች፣ አከፋፋዮችና ቸርቻሪዎች ጋር በሲሚንቶ ምርት አቅርቦትና ስርጭት ዙሪያ ውይይት ማካሄዱም ተገልጿል ፡፡ በዚህም አከፋፋዮችና ቸርቻሪዎቹ በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ ወደ ትክክለኛው የንግድ መስመር የማይገቡ ከሆነ መንግሥት ጣልቃ ገብቶ የኮንስትራክሽን ዘርፉ በሲሚንቶ እጥረት ምክንያት የተደቀነበትን ችግር በመፍታት ምርቱ በቀጥታ ለተጠቃሚው እንዲደርስ ለማድረግ እንደሚሰራ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል አስጠንቅቀዋል፡፡ መንግስት አጥንቶ ካልፈቀደ በስተቀር በሲሚንቶ ምርት የመሸጫ ዋጋ ላይ ምንም ዓይነት ጭማሪ ማድረግ በሕግ እንደሚያስጠይቅ አስገንዝበዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 14/2013